ከምናባዊ ተጠያቂነት ወደ ተጨባጭነት ያሻገረ ሕግ

17

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 29 ‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው›› ይላል። ሆኖም የሰዎችን ደህንነት፣ ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል በእነዚህ መብቶች ላይ ሕጋዊ ገደቦች ሊደነገጉ እንደሚችሉም በህገ- መንግስቱ ሰፍሯል። ሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን የሚገስሱ፣ የሌሎችን ደህንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ለማስቻል በአሁኑ ወቅት የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ረቂቅ ህግ አዘጋጅቷል።

የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የተዘጋጀው ይህ ረቂቅ ህግ «ሐሳብን በነጻ ከመግለጽ መብት ጋር ይቃረናል፤ እንዲሁም የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ይነፍጋል» ብለው የሚሞግቱ ሲኖሩ፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ረቂቅ ህጉ ተገቢነት ይገልፃሉ። በመሆኑም ረቂቅ ህጉ የዜጎችን የመናገር ነጻነት ይገድባል ወይንስ አይገድብም? ረቂቅ ህጉ እውን ለአገሪቱ አስፈላጊ ነውን?

እንደ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ትንታኔ በአገራችን የሚስተዋለው የፖለቲካ ባህላችን ኋላቀር እና ብዙም ያልጠነከረ ነው። የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ያላቸው አገሮች ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የጥላቻ ንግግር ትልቅ ተግዳሮትና አሳሳቢ ችግር እየሆነ በመምጣቱ አንዳንድ አገሮች አዳዲስ ህጎችን እያወጡ ይገኛሉ።

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ የጥላቻ ንግግርንና ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከል የሚያስችል ህግ መውጣቱ አስፈላጊ ነው። ህጉም ጠንከር ሊል ይገባል። ነገርግን ህጉ ሲወጣ የአገርን፣ የህብረተሰቡንና የግለሰብን ደህንነት ለማስጠበቅ መሆን አለበት እንጂ የሀሳብ ነጻነትን ለመንቀፍ፣ ለመጋፋት፣ ለማፈን፣ ወይም ደግሞ የፖለቲካ ስርዓቱን ጥቅም ለማስጠበቅ መሆን የለበትም።

በተጨማሪም የፍትሐብሄርና የወንጀለኛ መቅጫ ህጎቻችን ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ቢይዙም እነዚህ ህጎች በወጡበት ወቅት ማህበራዊ ሚዲያው በወቅቱ ባለመኖሩ፤ በቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ህጎች ወይም ፍትሐብሄር ህጎች በማህበራዊ ሚዲያው በአንድ ጊዜ ለሚሊዮኖች የሚሰራጨውን የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን ለመቆጣጠር ስለማይቻል ለየት ያለ ባህሪ ያለውን ይህን የመገናኛ ብዙሃን ለየት ያለ ህግ በማውጣት መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ።

የአቶ ልደቱን ሀሳብ የሚጋሩት የህግ ባለሙያ፣ አማካሪ እንዲሁም ጠበቃ አቶ ደበበ ሐይለገብርኤል «እንደእኛ አገር በብሄር፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ በተከፋፈለ አገር ውስጥ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በጥንቃቄ መምራት ካልተቻለ አደጋው የከፋ ይሆናል። አሳሳቢነቱን በማመዛዘን መንግሥት ይህንን ረቂቅ አዋጅ ሊያረቅቅ ችሏል። ህጉ በብሄር፣ በኃይማኖትና በግለሰቦች ላይ ሊመጣ የሚችለውን ተጽዕኖ ከመከላከል አኳያ መታየት ይኖርበታል፤ ህጉ ለአገሪቱ እጅግ አስፈላጊም ነው» ሲሉ ተናግረዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ፍሰሃ፤ በኢትዮጵያ የወጣውን የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ረቂቅ አዋጅ ለማየት እንደቻሉ ጠቁመው፤ ችግሮችን ለመቆጣጠር ያደጉ አገራት መሰል ህጎችን ማውጣታቸውን፤ ነገርግን በኢትዮጵያ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ጥላቻ ምንድን ነው? የሚል ግልጽ አቋም እንደሌለው፤ ህግ በማርቀቅ ስርዓት ላይ አንዱ ትልቁ የህግ የበላይነት የሚታይበት ግልጸኝነት ሲሰፍን በመሆኑ ይህ ህግ ግልፀኝነትን እንደማያሟላ ይናገራሉ ።

« የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን አንድ ላይ አብሮ ለማስኬድ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ሀሰተኛ መረጃ የግል አመለካከት ስለሆነ ሊገደብ አይችልም። በመሆኑም መንግሥት ሀሰተኛ መረጃን ሊያጣራበት የሚችልባቸውን አሰራርና አቅም ያላቸው ተቋማትን ሳይገነባ ለመቆጣጠር አይችልም። ስለዚህ ይህን ህግ የሚያስፈጽመው ማነው ብንል መልስ የለውም። ምክንያቱም አንድ ፍርድ ቤት አንድን መረጃ ሀሰተኛ ነው ብሎ የሚያረጋግጥበት አቅም የለውም። በአጠቃላይ ችግሩ በማህበራዊ ሚዲያ በሚተላለፉ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ብቻ ስላልሆነ አዋጁ መፍትሄ ሊሆን አይችልም» ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ።

በማህበራዊ ሚዲያው የግለሰቦች ስም የሚጠፋበት፣ ያለአግባብ የሚወነጀሉበትና የሚወቀሱበት በዚህም ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የሚገቡበት እንዲሁም የአገርና የህዝብ ሰላም የሚታወክበት ሁኔታ መኖሩን የሚገልፁት አቶ ልደቱ፤ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጉዳይ የአገራት የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያም የራስዋ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ስለሚኖራት እንደዚህ አይነት ህግ መውጣቱ ከመሰረታዊ ህጉ ወይም ከህገ መንግስቱ ጋር ይጻረራል ብለው እንደማያምኑ ያስረዳሉ።

እንደ አቶ ልደቱ ገለፃ ህገመንግስቱ በአንድ በኩል የሀሳብ ነጻነትን ሲያስቀምጥ በሌላ በኩል ዜጎች የአገር ደህንነትንና የዜጎችን መብት መጣስ እንደሌለባቸው ያስቀምጣል። ያማለት በህገመንግስቱ አንድ መብት ምንጊዜም ሲሰጥ አብሮ ኃላፊነት የሚሰጥ በመሆኑ፤ ያለኃላፊነት የሚሰጥ መብት የለም። ስለዚህ ይህ ህግ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ይገድባል የሚል እምነት የላቸውም ።

በተመሳሳይ የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ፤ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ፍጹማዊ መብት አይደለም ሊገደብ ይችላል። ስለዚህ ኢትዮጵያ የተለየ አዋጅ አላወጣችም። የአዋጁ መውጣት ዋና አላማው መንግሥት ማህበረሰቡን እንደ ማህበረሰብ አገርን እንደ አገር ለማስቀጠል ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ሀሳቡን በነጻነት በሚገልጽበት ወቅት በተመሳሳይ የሌሎችን መብት ለማስጠበቅ የወጣ ህግ ነው። አሁን ላይ እየረቀቀ ያለው የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ አዋጅ በየትኛውም መመዘኛ በህገመንግስቱ ከተቀመጡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶች ጋር የሚቃረን እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

እንድ ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ማብራሪያ የጥላቻ ንግግርን የሚገድብ ህግ አስፈላጊ ነው። ነገርግን የወጣው ህግ አንድን ሰው በዘፈቀደ የጥላቻ ንግግር ተናግሯል በሚል ወደ እስር ቤት እንዲገባ የሚያደርግ ነው። እንዲሁም በህገመንግስቱ አንቀጽ 29 ላይ የተቀመጠውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጻረር ነው። የተለየ አቋም ይዞ መንግስትን የሚተችና የሚናገር ሰው ካለ ይህ ሀሰተኛ መረጃነው በማለት በማሸማቀቅ ሰው ፈርቶ ሀሳቡን ሳይናገር እንዲኖር የሚያደርግ ነው። አዋጁ አሁን ላይ በአገሪቱ ላለው ወቅታዊ ችግር አይነተኛ መፍትሄ ያመጣል ብዬ አላምንም። በአጠቃላይ አዋጁን መሬት ላይ ለማውረድ አዳጋችና የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት፣ ዴሞክራሲንና ሰብዓዊ መብትን የሚነፍግ፣ዜጎች በመንግስት ላይ ተቃውሞ እንዳያሰሙ የሚያደርግ ሲሆን፤ በአንጻሩ መንግስት እንደፈለገ እንዲሆን ሽፋን የሚሰጥ አፋኝ ህግ ነው ።

«ህግ ስለወጣ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይፈታል ማለት አይቻልም፤ ስለዚህ ህጉ ሰላምን ለማስፈን አንድ መሳሪያ ሲሆን፤ ችግሩ ደግሞ በዘላቂነት የሚፈታው ከዴሞክራሲያዊ ባህል መስፋፋትና ማደግ ጋር ተያይዞ ነው» ሲሉ፤የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ በበኩላቸው « ህጉ የጥላቻ ንግግርንና የሀሰት መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ያስችላል የሚል እምነት አለኝ። ነገርግን አፈፃፀሙ በጣም መጥበቅ የለበትም። በጣም ጠብቆ ሌላኛውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አደጋ ላይ መጣል የለበትም። አንድ ህግ ጥሩ ወይም መጥፎም ሊሆን ይችላል። ነገርግን ህጉን ጥሩና መጥፎ የሚያደርገው አተገባበሩ ነው። ስለዚህ መንግሥት በአግባቡ እንዲተገበር የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ይገባል» ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ሀሰተኛ መረጃዎችን መከላከል የሚቻለው ህግ ስለረቀቀ ሳይሆን በበቂ ሁኔታ ግልጽና ወቅታዊ መረጃዎችን በስፋት ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ፤ለማህበረሰቡ የስነምግባር ትምህርቶችን በመስጠት፣ መልካም እሴቶቻችንንና ባህሎቻችንን በማስፋትና በማዳበር የጥላቻ ንግግርንና ሀሰተኛ መረጃን መቆጣጠር እንደሚቻል ይጠቁማሉ።

እርሳቸው አክለውም በለውጡ ማግስት የተሻረው የጸረ ሽብር ህጉ ሽብርን ለመከላከል አስፈላጊ ቢሆንም፤ በግልጽ መሰረታዊ የሚባል ችግር እንደነበረበት። አሁን ላይ አንጻራዊ ለውጥ መጥቷል በሚባልበት ወቅት ይህንን ረቂቅ አዋጅ ማውጣት የፀረ ሽብር ህጉን በሌላ መንገድ እንደመተካት እንደሚቆጠር፣ የወጣው ህግ በተመሳሳይ እንደ ጸረ ሽብር ህጉ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት፣ እንዲሁም ህግ በራሱ አፋኝ ላይሆን ይችላል ነገርግን ሲተገብር የማይተገበር ከሆነ አፋኝ እንደሚሆን፣ ህጉን በተፈለገው መንገድ በመተርጎም ዜጎችን ለማፈን የወጣ ህግ እንደሆነና ቀደም ሲል የነበረው የፀረ ሽብር ህግ ለእንደዚህ አይነት ችግር ተጋላጭ ነው ተብሎ መንግሥት ሲወቀስ እንደነበረው ሁሉ አሁን ላይ ዳግም የዜጎችን ነጻነት የሚያሳጣ ህግ መውጣቱን ይገልፃሉ ።

አቶ ልደቱ በበኩላቸው « አሁን የወጣውን ህግ ከጸረሽብር ህጉ ጋር እያያያዙ መጥፎ አድርጎ ማየት አስፈላጊ አይደለም። ከአሁን በፊት የነበረው የሽብር ህጉ በቂ ውይይት ሳይካሄድበት አንድ የፖለቲካ ድርጅት የራሱን ፍላጎት ወይም ተጽዕኖ ለመፍጠር ብሎ ተግባር ላይ ያዋለው ህግ ነው። ስለዚህ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴንና የፖለቲካ ተቃውሞ እንቅስቃሴን ያልለየ ህግ ሲሆን፤ በጅምላ ሁሉንም ሽብርተኛ አድርጎ የሚፈርጅ ህግ ነበር። ሆኖም ያ ህግ ስህተት ስለነበረበት ይህኛውም ህግ ስህተት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ስለዚህ ያ ህግ በአሰራር፣ በአወቃቀርና በይዘት ደረጃ የነበሩበት ችግሮች አሁን እንዳይደገም ጥንቃቄ ሊደረግና ልንማርበት ይገባል ብለዋል።

« አዲሱ ህግ ለመንግስትና ለፖለቲካ ኃይሎች ሲባል ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ደህንነት በሚጣጣም መልኩ መቀረጽ አለበት። ህጉ ላይ ተገቢነት የላቸውም የሚባሉ ነጥቦች ካሉ ነቅሰን እያወጣን በመተቸት እንዲሻሻሉ ማድረግ ይኖርብናል እንጂ በጥቅሉ ህግ አያስፈልግም የሚለው አካሄድ አዋጪ አይደለም። ይሄም የአገሪቱን ተጨባጭ ወቅታዊ ሁኔታን በአግባቡ ካለመረዳትና ካለማገናዘብ የመጣ ችግር ይመስለኛል » ሲሉ አቶ ልደቱ አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ።

በተመሳሳይ የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ « ህጉ ሲታይ ያንያህል ዜጎችን የሚያሳቅቅ አይደለም። ለአብነት ከአሁን በፊት የነበረው የጸረሽብር አዋጁ ያልተገለጸና ተግባር ላይ ያልዋለ ሀሳብን አስበሀል በሚል ዜጎችን ለእስርና ለእንግልት የዳረገ ነበር። በእኔ እምነት ይህ አዋጅ ከዚህ ቀደም ከነበረው የጸረ ሽብር አዋጅ ጋር የሚወዳደር አዋጅ አይደለም። አሁን ላይ የወጣው ህግ የአገርንና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ህግ ነው ብዬ አስባለሁ» ሲሉ ያስረዳሉ።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር መኮነን እምነት አዋጁ ከጸደቀ በዜጎች ላይ ትልቅ ስጋት ይፈጥራል። ለውጡን አይደግፉም ተብለው የተፈረጁና ለውጡ ህጋዊ አይደለም ብለው ቅሬታ የሚያነሱ ማህበረሰቦችን መንግሥት እንደፈለገ የሚያፍንበት፣ የዜጎችን ነጻነት የሚነፍግበት፣ ሰብዓዊ መብቶች የሚጣሱበት፣ ያለአግባብ ሰዎች እንዲታሰሩና እንዲንገላቱም ያደርጋል። በአጠቃላይ አዋጁ ዴሞክራሲን የሚያጠብብና የሚያቀጭጭ ሲሆን፤ ዜጎች በአገራቸው ነጻነት ተሰምቷቸው እንዳይኖሩ የሚያደርግ በመሆኑ በመንግሥት ላይ ቅሬታና ተቃውሞ የሚያስነሳ አዋጅ ነው ።

እንደ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱና የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ላለ በጣም ኋላቀርና ያልዳበረ የፖለቲካ ባህል ላላት አገር ቀርቶ ዓለም ላይ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል ላላቸው አገሮች ይህ አይነት አዋጅ አስፈላጊ ነው። በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግርና የሀሰት መረጃ ትልቅ የብሄራዊ ደህንነት ስጋት እየሆነ መጥቶባቸዋል።

ማህበራዊ ሚዲያው አገርን እስከማጥፋት መንግሥትን እስከመገልበጥ የሚደርስ ኃይል እንዳለው በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች እንዲሁም በጎረቤት አገሮች አይተናል። የችግሩን አደገኝነትና ከባድነት ተረድተን የመፍትሄ አቅጣጫውንም አብረን ማስቀመጥ የማንችል ከሆነ ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የብሄራዊ ደህንነት አደጋን ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህ ችግሩ ልጓም ካልተበጀለት አገሪቱም መሰል ችግሮች ውስጥ ልትገባ ትችላለች ።

አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2011

 ሶሎሞን በየነ