በወንጀል ተግባር የተሳተፉ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

35

አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ፖሊስ እና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በሁሉም ችግር በተፈጠረባቸው ክልሎችና አካባቢዎች የምርመራ እና የዓቃቤ ህግ ቡድን በማደራጀት የምርመራ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አሳወቀ።

በፌዴራል ዓቃቤ ህግ የህግ ጥናት ማርቀቅ እና ማፅደቅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አለመረጋጋት እንዳይኖር ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች እየታሰሩ ተጠያቂ እየሆኑ ነው። ሰሜን ሸዋ ላይ በከሚሴ ጦርነት የሚመስል ተግባር የፈፀሙ እየታሰሩ ናቸው። በየቀኑ ቁጥራቸው የሚጨምር በመሆኑ ለመግለፅ ቢያዳግትም ከሃምሳ ያላነሱ ሰዎች ታስረዋል። የምርመራ ቡድን እዛው ሆኖ መጠየቅ ያለበትን እየተጠየቀ ነው።

በከሚሴ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም የምርመራ ቡድን እየተዋቀረ ተጠርጣሪ አጥፊዎች እየተያዙ መሆኑን ጠቁመዋል።

‹‹መንግሥት ተዳክሟል፤ ህግ ማስከበር አይችልም የሚል ሃሳብ ካለ ስህተት ነው።›› ያሉት አቶ በላይሁን፤ መንግሥት የታጠቀ ሃይል ነው። ህግ ሊያስከብር የሚችልበት የተደራጀ መዋቅር አለው። ከመንግሥት ዓቅም እና ቁጥጥር ውጪ የሚሆን ምንም ነገር የለም። የመንግሥትን ታጋሽነት እና ሆደ ሰፊነት ባልሆነ መልኩ መጠቀም ግን ለድርጊት ፈፃሚው ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ተናግረዋል።

‹‹ህዝቡ በአግባቡ የዴሞክራሲ ሥርኣቱን እንዲለማመድ ለማድረግ ዕድሉን ለመስጠት እንጂ እንዲያውም የህግ የበላይነትን ከማስፈፀም አንፃር ያለበትን ደረጃ የምናውቀው ውስጡ ያለነው እኛው ነን።›› ያሉት አቶ በላይሁን፤ ማንም ቢሆን ይጠየቃል። ዋናው መነሻ የሚሆነው የተሰራው ጥፋት እና መረጃው መገኘት መቻሉ ብቻ ነው ብለዋል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2011

ምህረት ሞገስ