የአንጋፋው የሚዲያ ተቋም ችግኝ ተከላ

71

ተማሪ ሕይወት አላምረው የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን በመርሐ ግብሩ ላይ ተሳታፊ ነበረች። እርሷ በአበቦች ውበትና ፍካት ትደሰታለች። ታዲያ ነገን ለማየት ለምትጓጓው ውበት ዛሬ ተጨንቃ ችግኝ ተክላለች። በትምህርቷም የነገ ህይወቷ እንደ አበባ የፈካ ይሆን ዘንድ በትጋት እንደምታጠና ነው የምትናገረው። ህይወት ለዕጽዋት ያላት ክብር ትልቅ ነው። በእድሜ ትልቅ የሆኑ ሰዎች ዛፍ ሲተክሉ ስታይ ደግሞ ደስታዋ ወደር የለውም፤ ለዚህም ነበር ካለማንም ጉትጎታ በችግኝ ተከላው ላይ ስትሳተፍ የነበረው።

አቶ ሱልጣን መሐመድ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ላለፉት 26 ዓመታት አገልግለዋል። እስካሁን ድረስም አገራዊ ዘመቻ በታወጀ ጊዜ ሁሉ በችግኝ ተከላ ተሳትፈዋል። ቢሾፍቱ ድረስ ሄደው ችግኝ ተክለዋል። በዚህ ዓመት ግን በተቋማቸው አቅራቢያ አራት ኪሎ በሚገኘው ዳግማዊ ምንሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግኝ ተክለዋል፡፡

እንደ አቶ ሱልጣን አስተሳሰብ በትምህርት ቤቱ የተካሄደው የችግኝ ተከላ ትርጉሙ ዘርፈ ብዙ ነው። ችግኞች ሲተከሉ ተማሪዎች ይመለከቱ ነበር። ይህ ደግሞ በቀጣይ አገር ተረካቢ የሆኑ ሕፃናት በአዕምሯቸው ላይ መልካም ዘር እንደመዝራት ይቆጠራል። የእውቀት ችግኝ በሚተከልበት ቦታ የዛፍ ችግኝ መትከላችን ትርጉሙ እጥፍ ድርብ ነው ይላሉ። ተቋሙም በቀጣይ መሰል ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመጠቆም፤ ችግኝ መትከል በአንድ አገር ላይ የሚኖረው ጥቅምና ዓለም አቀፋዊ አንድምታው የላቀ ስለመሆኑ ያብራራሉ።

ወጣት አንተነህ ሞገስ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ሥራ ከጀመረ ወዲህ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ ተሳትፏል። በእርሱ እይታ ዛሬ ላይ የምንተክለው ችግኝ መጪውን ትውልድ ንጹህ አየር እንዲተነፍስና ጤናማ ምህዳር ላይ እንዲኖሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ስለሆነ ይህ ሊበረታታ ይገባል ባይ ነው።

እንደ ወጣት አንተነህ ገለፃ፤ የአትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በርካታ ጋዜጠኞችን የያዘ ተቋም ሲሆን ህዝብን በማነቃቃትና ማህበራዊ ኃላፊነትን እንዲወጡ በማድረግ ረገድ የሚያስመሰግኑ ሥራዎችን ማከናወኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኅብረተሰቡን ማነቃቃት ብቻ ሳይሆን በራሳቸው የአገራዊ ጥሪ አካል ሆነው በችግኝ ተከላ መሳተፋቸው ዓርአያ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው ይላል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ውበትና መናፈሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ነፃነት ደረጄ፤ አንጋፋው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአንጋፋው ዳግማዊ ምንሊክ ትምህርት ቤት ችግኝ መትከሉ ያስመሰግነዋል፤ አገራዊ ጥሪውን በአግባቡ የተወጣ ተቋም ብለውታል፡፡ እንደ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሁሉ ሌሎች ተቋማትም በችግኝ ተከላው ላይ አሻራቸውን እንዲያስቀምጡና አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ያሳስባሉ፡፡

የአትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድም ተክሉ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት 78 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ህዝብና መንግሥትን በሰፊው ሲያገለግል የቆየ ነው። በአሁኑ ወቅትም የምስረታውን 78ተኛ ዓመት በማስመልከት ለሁለት ወራት የሚቆይ ሁነት ቀርፆ የተለያዩ ተግባራትን በመከወን ላይ ነው።

ትናንት በዳግማዊ ምንሊክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም የዚሁ አንዱ አካልና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ ምላሽ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። በቀጣይም ተቋሙ ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን በስፋት የሚወጣ ታማኝና ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ሕዝብና መንግሥትን የሚያገለግል ተቋም እንዲሆን ዘርፈ ብዙ የለውጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011

ክፍለዮሐንስ አንበርብር