የታመመው እግር ኳሳችን ፍቱን መድሃኒትን ይፈልጋል!

14

ገና ከጠዋት ጽንሰ ሃሳቡ እውን ሲሆን መርሆዎቹ ሰላም፣ አንድነት፣ መቻቻልና መከባበር ናቸው። ዘረኝነት፣ ጸብ ግጭትና መናቆር ከቆመበት ዓላማ ጋር በፍጹም የማይሄዱና የሚጸየፋቸው ነገሮች ናቸው። በግጭት እና አለመግባባቶች ተለያይተው የነበሩ ህዝቦች ስፖርት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በወንድማማችነት የተቃቀፉበት ሁኔታ በርካታ እንደሆነም የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በአጠቃላይ ስፖርት ማለት ወንድማማችነት፣ ሰላምና ፍቅር ነው።

ይሁንና ይህ ቅዱስ ዓላማን ያነገበ ነገር ከዓላማዎቹ ተቃራኒ በመውሰድ ለግጭት፣ ለጦርነትና ለህዝቦች እልቂት የዳረጉትም አልጠፉም። በዚህም ሰላምንና ወንድማማችነትን ማስፈንን ዓላማ አድርጎ የተነሳው ስፖርት ለብዙዎች ስቃይና እንባ ምንጭ ሊሆን የቻለበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ብዙዎችን አሳዝኗል። ለማንም ግልጽ እንደሆነው ስፖርት የተፎካካሪነትንና የተወዳዳሪነትን መንፈስ የተላበሰና ማሸነፍና መሸነፍን በጸጋ መቀበልን የሚጠይቅ ነው። በስፖርቱ መበሳጨቱም ሆነ መፈንደቁ የሚያምረው ግን በሰላማዊ አውድ ሲከወንና ሲከወን ብቻ ነው።

ዛሬ ዛሬ አገራችንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም አገራት በስፖርቱ መድረክ እየታዩ ያሉት የዘረኝነት፣ የግጭትና የብጥብጥ ተግባራት ከሰላማዊው የስፖርት መንፈስ የራቁና የብዙዎችን ስሜት እየጎዱ ያሉ ናቸው። ከእነዚህ አጓጉል ተግባራት የተነሳም ብዙዎች በስፖርቱ ከመታደም ከመራቃቸውም በላይ የስፖርቱ ተወዳጅነትም በእጅጉ እየተጎዳ ይገኛል። መደሰቻ መሆን የሚገባቸው የስፖርት ውድድሮች የፍራቻና ሰቆቃ መንስዔም እየሆኑ ነው።

በተለይም በአገራችን የስፖርታዊ ውድድሮች መርህ የሆነው ስፖርታዊ ጨዋነት በእጅጉ እየተጣሰ ውድድሮቸ ባሉ ቀን ግጭቶችና ዝርፊያዎች እየተስተዋሉ ነው። የአንድ ስፖርት ክለብ ደጋፊ ወደሌላው ለመሄድ እየፈራና እየተከለከለ ያለበትም ሁኔታ በመከሰት ላይ ነው። አሸናፊውም ተሸናፊውም ክለብ ኢትዮጵያውያን ሆነው ሳለ ይህ ሁሉ ግጭትና ጉዳት መከሰቱ እጅጉን የሚያሳዝን ነው።

ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው የአገራችን ስፖርቶች በተለይም እግር ኳሱ ያለበት ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ደረጃችን ከጊዜ ወደጊዜ እየወረደ መሄዱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በስታዲየሞች በሚደረጉ ውድድሮችም የሚስተዋለው እጅግ አሰልቺ የሆነ ጨዋታ ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታና በሌላ እግር ኳስ የደጋፊው እንደጠላት ጎራ ለይቶ ዜጋን ማጥቃትና ንብረት ማውደም ከምን የመነጨ ነው ያስብላል። ቢያድለን ኖሮ የስፖርቱ መድረክ ወንድማማችነትን ለማጠናከርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጉላት ሚናው እጅግ ትልቅ ነበር።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወድድሮችን በክልሎች ለመመልከት በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ከከተማ ከተማ ይንቀሳቀሳሉ። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለእንግዶች አቀባበል ቢደረግ ወንድማማችነትንና አንድነትን በእጅጉ ለማጠናከር ያግዛል። ደጋፊው ሆቴል፣ ትራንስፖርትና መዝናኛን ጨምሮ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በስፋት ስለሚጠቀም ቀደም ብሎ በመዘጋጀት ከዚሁ ገበያ ለመጠቀም መስራትም ብልህነት ነው። ከዚህ በተቃራኒው ተሂዶ ወደ አካባቢ የመጣ እንግዳን ማጥቃትና ይህን ተከተሎ ረብሻና ዝርፊያን ማስፋፋቱ የኢትዮጵያውያን ባህል ካለመሆኑም በላይ ማንንም ተጠቃሚ አያደርግም።

በእግር ኳሱ መድረክ እየታዩ ያሉት እነዚህ አጓጉል ተግባራት በደንብ ሊጠኑና መንስዔያቸው ታውቆም በፍጥነት መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል። የክለቦችን አደረጃጀት መፈተሽና በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮቸን አዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መምከርም ቅድሚያ ሊሠጠው እንደሚገባ ይታመናል። የጉዳዩ ባለቤት የሆኑትን ክለቦችና ደጋፊዎችን የመፍትሄው አካል ማድረግም ግድ ይላል።

የተለያዩ ከተሞችን ክልሎችንም ሆነ ቡድኖችን ውክለው የሚወዳደሩ ክለቦች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው። በሌላ አነጋገር አሸናፊውም ተሸናፊውም ኢትዮጵያዊ ክለብ ነው። በተለያየ ስያሜና አደረጃት ስር ሆነው ይወዳደሩ እንጂ ዋነኛ ዓላማቸው በዓለም አቀፍ መድረክ የአገራችንን ኢትዮጵያን ስም ከፍ ማድረግ ነው። ስለሆነም ደጋፊዎችም ሆኑ የክለብ አመራሮች ይህን ትልቅ ሥዕል ታሳቢ አድርገው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል።

በአጠቃላይ ዘረኝነት፣ ነውጥ፣ ረብሻና ጥላቻ ከሰላማዊው ስፖርት መርሆ ጋር በፍጹም የማይሄዱና ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌላቸው ሁሉም ተረድቶ በአሁኑ ወቅት በጽኑ የታመመውን የአገራችንን እግር ኳስ ስፖርት እንፈውሰው መልዕክታችን ይሆናል!

 አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011