‹‹ጥበብ የጎደለው ውሳኔ የወደፊት ሕይወትን ያበላሻል›› – መምህር አሸናፊ ከበደ

24

«ወጣትነት ውበት ነው፤ ወጣት ኃይል ነው፡፡ ትኩስ ጉልበት፣ንቁ አዕምሮና ፈጣን እንቅስቃሴ ያለበት። የደሙ ሙቀትና የጡንቻው ንዝረቱ በገፅታው ላይ የሚነበብበት፤ አፍላ ስሜት የሚፈታተንበት፣ ለወደደው ሕይወት የሚሰጥበት…» ይላል ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ፤ የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን መምህር አሸናፊ ከበደ በዚህ ባህሪ ውስጥ ያለ ወጣት ነው።በጨዋታችን እነዚህን ሁሉ ስሜቶች አነብበን፤ተረዳን።

መምህር አሸናፊ፤ አዲስ ነገር በማለም ፤አዲስ ነገር በማየትና በመነሳሳት የሚተጋ ነው። ለማጎብደድ ወገቡ፣ ለመንበርከክ ጉልበቱ፣ ለማጎንበስም አንገቱ የማይፊቅድለትና ሙሉ ፍቅር ሰጥቶ ሙሉ ፍቅር መቀበል የሚችል፣ አዕምሮውን የማያስመታ ቀጥታ ለእውነት የቆመም ነው። እናም በተለያዩ የህይወት ተሞክሮዎቹን በማንሳት ያጫወተንን ለእናንተ አንባብያን እንዲህ አቋደስናችሁ።

ስዩምን አሸናፊ አሸነፈው

ወጣቱን መምህር አሸናፊን መጀመሪያ ቤተሰቦቹ ስዩም እያሉ ነበር የሚጠሩት። ሆኖም የአንድ ቀን የአያቱ ገጠመኝ ይህንን መጠሪያውን ቀይሮታል። በእርግጥ ይህ ስም ለእርሱ ተመችቶታል። ከባህሪው ጋርም የሚሄድ ነው። ገጠመኙ የተከሰተው አያት ከወላይታ ወደ መተሃራ በሚጓዙበት ጊዜ ነበር።

እናም ይዟቸው የሚሄደው ሹፌር ለአዛውንቶች የሚሰጠው ክብር፣ ልጆችን ወጣቶችንም የሚያስተናግድበት መንገድ ልዩ ነበር። ሁሉንም በአንድ መንገድ ማስተናገድ ቢከብድም ለእርሱ ግን ሁሉን የተቻለው ነበርና መንፈሳዊ ቅናት ተሰማቸው። ከዚያም አያት «ለመሆኑ ስምህ ማን ይባላል» ሲሉ ጥያቄ አነሱ። እርሱም አሸናፊ እንደሚባል ተናገረ። በዚህ ስም አወጣጥ የተገረሙት አያትም ይህ ለልጅ ልጄ የተሻለ ስም ነው ሲሉ ህጻኑን ስዩምን አሸናፊ ሲሉ ስሙን ቀየሩት።

ወጣቱን መምህር አሸናፊን መጀመሪያ ቤተሰቦቹ ስዩም እያሉ ነበር የሚጠሩት። ሆኖም የአንድ ቀን የአያቱ ገጠመኝ ይህንን መጠሪያውን ቀይሮታል። በእርግጥ ይህ ስም ለእርሱ ተመችቶታል። ከባህሪው ጋርም የሚሄድ ነው። ገጠመኙ የተከሰተው አያት ከወላይታ ወደ መተሃራ በሚጓዙበት ጊዜ ነበር። እናም ይዟቸው የሚሄደው ሹፌር ለአዛውንቶች የሚሰጠው ክብር፣ ልጆችን ወጣቶችንም የሚያስተናግድበት መንገድ ልዩ ነበር።

ሁሉንም በአንድ መንገድ ማስተናገድ ቢከብድም ለእርሱ ግን ሁሉን የተቻለው ነበርና መንፈሳዊ ቅናት ተሰማቸው። ከዚያም አያት «ለመሆኑ ስምህ ማን ይባላል» ሲሉ ጥያቄ አነሱ። እርሱም አሸናፊ እንደሚባል ተናገረ። በዚህ ስም አወጣጥ የተገረሙት አያትም ይህ ለልጅ ልጄ የተሻለ ስም ነው ሲሉ ህጻኑን ስዩምን አሸናፊ ሲሉ ስሙን ቀየሩት።

የትናንቱ ህጻን የዛሬው ወጣትና መምህር አሸናፊ፤ የተወለደው መተሃራ ከተማ ነው። የመተሃራ ልጆች መለያ የሆነውን ባህሪ የተላበሰ እንደሆነ የተለያዩ መገለጫዎቹ ያሳያሉ። ለአብነት የመጀመሪያው ተግባቢነታቸው ሲሆን፤ ሌላው በጨው ምክንያት ጥርሳቸው ቢጫ ቀለም መያዙ ነው። እንደውም አሸናፊ ከዚህ ከቢጫ ጥርሱ ጋር በተያያዘ ሌላ ቅጽል ስምም እንዳለው ይናገራል። ይህ ስም የወጣለት በተከላካይነት ቦታ እየገባ ሲጫወት ለመለየት ያስችላቸው ዘንድ የሚጠቀሙበት ነው። ቅጽል ስሙም «ቢጫው» ነበር።

እንግዳችን፤ በመተሃራ እስከስምንት ዓመቱ ብቻ ነበር የቆየው። ምክንያቱም አባትና እናቱ መለያየታቸውን ተከትሎ ሁለቱንም ላለማስቀየም ሲል ከዚያ ቦታ ለቆ እድገቱን ወላይታ ሶዶ አጎቱ ጋር እንዲያደርግ ተገዷል። እንደውም የአባቱ መጠሪያ ሳይቀር በአጎቱ እንዲሆን አድርጓል። «አጎቴ የልጅነት መምህሬ ነው። እርሱን መሆን እንድችል አድርጎኛል» ይላልም ስለ አሳደጉት አጎቱ ሲናገር። ፈጣንና ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ ያይ እንደነበር የሚናገረው የትናንቱ ህጻን የዛሬው ወጣት መምህር አሸናፊ፤ ያየውን ነገር ከመናገር ወደኋላ የማይልና ሁሉ ነገር እውነታው እንዲወጣ የሚፈልግ የመሆኑ ምስጢር አጎቱ እንደነበር ይናገራል።

«መምህርነት የሚያኮራ ሙያ መሆኑን ከአጎቴ ተረድቻለሁ። እኔም በልጅነቴ መሆን የምፈልገው መምህር ነበር» የሚለው ወጣት አሸናፊ፤ የመምህር ልጆች ወደቀለሙ የሚቀርቡና የሚሰጣቸው ክብር በጣም ከፍ ያለ እንደነበር፤ መጽሀፍትን ከሌላው ተማሪ በተሻለ መልኩ የማግኘት እድሉም እንደነበራቸው ይናገራል። ይህ ደግሞ በትምህርታቸው በጣም ጎበዞች እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም ነው ያጫወተን።

መምህር አሸናፊ ሌላም ቅጽል ስም አለው፤ ጥሩ ነገሮችን መርጦ በማድረጉና መጥፎ ነገሮች ሲከሰቱ በፍጥነት መፍትሄ እንዲያገኙ በማድረጉ «ንቧ» እያሉ ይጠሩታል። አሸናፊ በልጅነት ጊዜው እጅግ ጨዋታ ወዳድ እንደነበር ያስታውሳል። በተለይ እግር ኳስ ላይ በጣም ጎበዝ ተጨዋች መሆኑን ይገልጻል። ውፍረቱ ግን ብዙም የማያጫውተው ፈተና ቢሆንበትም በፍቅሩ እንደገታው ይናገራል። በዚህም የመተሃራን አካባቢ በመወከል ብዙ ቦታዎች ላይ ተጫውቷል።

ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው አሸናፊ፤ ቤተሰብን በማገዝ በኩልም አይታማም። እንደውም ከቤተሰቡ በርካታ ሥራዎችን ከሚሰሩት መካከል የመጀመሪያው ነው። በተለይም ልጆችን ማስጠናትና ትምህርት ቤት የመውሰድ ግዴታ የእርሱ ነበር።

ልጅነትን ሀያል አድርጎ እንዲመለከተው ያስቻለውን ሲያነሳ ደግሞ እንዲህ ይላል። «በልጅነቴ ለሰፈርም ሆነ ከሰፈር ውጪ ላለ ሰው የምሰጠው ፍቅር፣ የምኖርበት ሰፈር ጓደኞቼ ብቻ ሳይሆኑ የሚናፍቁኝ ከሌላ አካባቢም ጭምር መጥተው አብረው የሚያሳልፉት መሆናቸው የልጅነት ዘመኔ ለዘላለም ቢኖር ያሰኘኛል። ደግሞ ደጋግሞ ቢመጣም እላለሁ። የጉብዝና መለኪያ በሰፈር የሚመጣ ውጤትም መሆኑ የዛሬን መቀናናት ስለሚያስረሳኝ ልጅነት ወሰን የሌለውና ንጹህ ፍቅር ብቻ ያለበት እንደሆነ ይሰማኛል» ይላል።

የትምህርት ሀሁ

ወላይታ ሶዶ ቦዲቲ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን ሲያስታውስ «ቀለሜነቴን የጀመርኩባት ቤቴ ናት“ ይላታል። እናም በዚህች ቤት ብዙ ነገር ቀስሜባታለሁና እናቴ፤ መምህሬ ሳልላት ማለፍ አልፈልግም» የሚለው ባለታሪኩ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እስከ አስራ አንደኛ ክፍል በዚህችው ቦዲቲ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። 12ኛ ክፍልን ደግሞ ሶዶ ኮንፕሬንሲፍ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማሩን ይናገራል። ቀጣዩን ክፍል ለመማር ደግሞ ወደ አምቦ በመጓዝ አምቦ ኮምፒውተር ሳይንስ ኮሌጅ በመግባት የኮምፒውተር ትምህርትን አጥንቷል።

«አምቦ ህይወትን የተማርኩበት ትምህርት ቤት ነው። ከቋንቋ ጀምሮ የህይወት ልምዶችን ቀስሜበታለሁ። ፤ለእኔ አምቦና ጎንደርን የጀግና ምድር ናቸው እላቸዋለሁ። ምክንያቱም ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር በይፋ የሚናገሩበትና የሚያገኙበት ነው። ለእኔም ፊት ለፊት መናገርን ያስተማረኝ ይህ ቦታ ነበር። ያልመሰለኝን እንዳል ቀበል አድርጎኛል» ይላል።

ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ በትምህርቱ የደረጃ ተማሪ እንደነበር የሚናገረው ባለታሪኩ፤ በዩኒቨርሲቲም ቢሆን ይህንኑ ጉብዝናውን ይዞ ቀጥሏል፤ የማዕረግ ተመራቂ ለመሆን በቅቷል። ይህ ደግሞ በቀጥታ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን በመምህርነት እንዲቀላቀልዕድልከፍቶለታል። በዩኒቨርሲቲ መስራቱ ደግሞ ሌላ የእድል በር ከፈተ፤ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመጡ አጫጭር ስልጠናዎችን በቀላሉ እንዲያገኝ ረዳው።

በዚህ ብቻ የትምህርት ጥማቱን ያላረካው መምህር አሸናፊ፤ በዝውውር ምክንያት ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሄዶም በዘርፉ የሚመጡትን የውጪ አጫጭር ስልጠናዎች ተከታትሏል። ሁለተኛ ዲግሪውንም ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሳለ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ገብቶ ተመርቋል። በቀጣይም ሦስተኛ ዲግሪውን ለመማር የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሆነም አጫውቶናል።

ወጣትነት በመምህር አይን

ወጣትነት በትኩስ ኃይል የምንሞላበትና “የእሳትነት ባህሪ” የሚገለጽበት እንደመሆኑ መጠን እንደእሳት ሁሉንም ማቃጠል ሳይሆን የሚጠቅመውን መርጦ ለለውጥ መነሳትን የሚጠይቅ እንደሆነ ይናገራል መምህር አሸናፊ። ለዚህም ምክንያት አለው። የምንፈልገውን ነገር ለማድረግ ፍጥነትን መቀነስ ይገባናል። ይህ ደግሞ ስሜትን ይገላል፤ ለውጤታማነት ያበቃል። ራስን ገሎ ለስኬት መብቃት ደግሞ ሰው ባያውቅልህም ታሪክ እንዲዘክርህና እንዲኖርህ ትሆናለህ ባይ ነው።

ወጣትነት ለፈለጉት ነገር መሞትንም የሚጠይቅ የዕድሜ ክልል እንደሆነ የሚናገረው መምህር አሸናፊ፤ በወጣትነት መምህር መሆን ሁለት አይነት ጫፍ አለው። የመጀመሪያው ከእድሜ ይልቅ ብስለት የሚጎላበት ሲሆን፤ አንድ ላይ መሄድ ይችላሉ ያስብላቸዋል። ከአስተሳሰብ ሙያ ይቀዳል። ወጣት ሲኮን ደግሞ ብዙ ፍላጎት ያለበት፤ ወጣት የሆነውን ምቹነት በመጠቀም ለመለወጥ መነሳትን ያነገበ ነው። እናም በዚህ ጊዜ ህይወት ከበስተጀርባ ያለች መሆንን ለተረዳ ወጣት መምህርነት እውነትም መምህር መሆን የሚቻልበት መሆኑን ይገልጻል።አርባና ሀምሳ ዓመት የመስሪያ ጊዜ የሚሆነው የቀጣይን የኑሮ ደረጃ ሲታይበት ነው። እናም የብዙ ሥራና የነቃ ተሳትፎ ጊዜ ይህ በመሆኑ እነዚህን ሁሉ ማየት ይገባልም ይላል።

ሁለተኛው ጫፍ ነው ብሎ ያነሳው ደግሞ ወጣት መምህር መሆን አስቸጋሪ ሁነቶች የሚያጋጥሙበት መሆኑን ነው። ትዕግስት ማጣት፣ ነገሮች ቶሎ እንዲሆኑና እንዲተገበሩ መፈለጉ ከእድሜ ባለጸጎቹ እንደሚለየው ይናገራል። ትምህርቱ በዘመነበት ሁኔታ በደንብ ያልዘመነ መሆንም አንዱ ክፍተት መሆኑን ያነሳል።

ለመምህር የሚሰጠው ክብር በሚሰጠው ልክ አልሆነም። መምህርነት እውቀት ማበልጸጊያ፣ ያለን መስጪያ፣ ሰዎችን መቅረጫ ነው። ነገር ግን ወጣቱ በዚያ ልክ ሰውን ቀርጾ እያወጣ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም። ስለዚህ ውህደቱ ጥቂት ነው የሚል ምልከታ አለው። ባለፉት ልክ የዛሬ ወጣት እያስተማረ ነው ማለት የማያስችሉ ምክንያቶች በራሴ ስለካው አሉ። ግን ጥረት የሚያደርጉም እንዳሉ መካድ አይቻልም ይላል።

«እንደኔ በአዕምሮዬ ውስጥ ያሉ መምህራንን ለመምሰል ሁልጊዜ እጥራለሁ። እየሆንኩትም ነኝ ብዬ የማስባቸው በርካታ መገለጫዎች አሉኝ። ለአብነት አባት የመሆን ተግባሩ፤ አርአያዬ የነበሩት መምህራን እውቀታቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉት ጥረት ማድረጌ፤ የእውቀት አቅማቸው፣ እውቀ ታቸውን ለተማሪ የሚያስተላልፉበት መንገድ እና ለሰው የሚሰጡት ክብር በትክክልም አስተምሮኝ እየኖርኩት ነው ብዬ አምናለሁ። ለዚህ ደግሞ ምስክሮቼ ተማሪዎቼ ናቸው» ይላል በወጣትነቱ መምህርነትን አንዴት እየተወጣው መሆኑን ሲናገር።

ሥራ

አካባቢም ሆነ የትምህርት ሁኔታን በየጊዜው የመቀየር ፍላጎት እንደነበረው የሚናገረው መምህር አሸናፊ፤ የመማር እድገቴ የሚመጣው ያለውን ምቹ ሁኔታ በመመልከት ልምድ የማገኝበትን ሁኔታ ስፈጥር ነው ብሎ ያምናል። እናም ከአንዱ ቦታ አንዱ የተለየ አቅምና ልምድ ይኖረዋልና በአንድ ቦታ መርጋትን አይፈልግም። ምክንያቱ ደግሞ በአንድ አይነት አሰራር መቀጠል አለመፈለጉ ነው። ለዚህም ይመስላል መጀመሪያ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተማረ፤ ቀጣዩን ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ላይ ያደረገው። በእርግጥ ከሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውጪ አላስተማረም። ነገር ግን ከማስተማሩ ባሻገር ሌሎች ሥራዎች ላይ ይሳተፍ ስለነበር «ቦታ ባልቀይርም የተለያየ የአሰራር ሂደቶችን መመልከት ችያለሁ» ይላል። በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተመረቀበት ሙያ ሁለት ዓመት አስተምሯል። በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ዛሬ ድረስ እያስተማረ ይገኛል። በዩኒቨርሲቲው ከማስተማሩ ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያገለገለ ሲሆን፤ ለአብነት ከ2004 እስከ 2007 ዓ.ም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ነበር። በኋላ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ስኩል ኦፍ ኢንፎርማቲቭ ዲን ሆኗል። አሁንም እያስተማረ በዲንነቱ እያገለገለ ነው።

በኔዘርላንድ የሚኖረውን «ኢንተርና ሽናል ስፖርት ፎር ኢዲኩዬሽን» የሚል መጠሪያ ያለውን የአጎቱን ድርጅት በማስተዳደርም ዛሬ ለብዙዎች መድረስ እየቻለ ነው። የወላይታ ወጣቶች ለጋ ቡድንን ያቋቋመና አሁን በፕሬዚዳንትነት የሚመራም ነው። በስፖርቱ ዘርፍም የወላይታ ዲቻን ክለብ በወጣቱ አማካኝነት እንዲታገዝ የማድረግ ሥራ ይሰራል።

ማህበራዊ ሀላፊነት

አሸናፊ በዩኒቨርሲቲ ብቻ አይደለም የሚያስተምረው ማህበ ረሰቡን በማገልገም ይማራል፤ ያስተምራል። በተለይም ወጣቱን ለአገሩ የሚሰራ ከማድረግ አንጻር ጥሩ አርአያ የሚሆን ወጣት እንደሆነ ይነገራል። ለዚህም በዋናነት የሚነሳው ከወላይታ ልማት ማህበር ጋር በመሆን የሰራቸው ሥራዎች ናቸው። የተለያዩ የውጪ አገር እርዳታዎችን በመጻጻፍ ያመጣል።

በኔዘርላንድ የሚኖረውን የአጎቱን ድርጅት በማስተዳደር ዛሬ ለብዙዎች እየደረሰ ያለው እንግዳችን፤ የድርጅቱ ዋና ሥራ የሆነውን የትምህርት ዘርፉን የማገዝ ሥራ በአግባቡ እያከናወነ ነው። መጽሀፍት ኮምፒውተሮችና ሌሎች መማሪያ ቁሳቁሶችን ለትምህርት ቤቶች በድርጅቱ አማካኝነት ያደርሳል። ከዚህ ባሻገር ከአሜሪካ ከሚገኙ የቀድሞ የሰላም በጎ አድራጊዎች ጋር በመሆንም ቴክኖሎጂን በትምህርት ዘርፉ ለማስፋት የቻለ ነው። ትውልዱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኝ ከማስቻል አንጻር ከፍተኛ ሥራ እየሰራም ይገኛል።

በወላይታ ውስጥ ለ11 ትምህርት ቤቶች 31 ላፕቶፕ ኮምፒውተር፣ አንድ ሰርቨርና 30 ሄድ ሴት ያለው ቴክኖሎጂ እንዲመጣ ማድረጉን ይናገራል። ወላይታን ተሻግሮ ከአማራ ክልል ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመቀናጀት ለአማራ ክልል አምስት ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ ቴክኖሎጂና ትምህርት እንዲኖርም አስችሏል። በዚህ ያላቆመው ወጣቱ መምህር፤ ወደ ሲዳማም ተሻግሮ ለመሰናዶ ትምህርት ቤት ይህንኑ ሥራ ሰርቷል።

ትግራይም እንዲሁ አክሱም የህዝብ ቤተ መጽሀፍት ላይ ይህንኑ ቴክኖሎጂ የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻችቷል። መስራት ልምዱ የሆነው መምህር አሸናፊ፤ የውሃ፣ የሴቶች እኩልነት ላይም እንዲሁ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ ነግሮናል። «ፌሌክ» ከሚባል ወረቀት አምራችና ህትመት ከሚሰራ ድርጅት ጋር በመጻጻፍም እንዲሁ ለአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሁለት ዙር የሚሆን ለ1ሺ200ተማሪዎች ሙሉ የጽህፈት መሳሪያ እንዲሰጥ አድርጓል። በዚህም በትምህርት ቤቱ የነበረውን የተማሪዎች የማቋረጥና የመውደቅ ምጣኔ መቀነስ እንደተቻለ አጫውቶኛል።

እንግዳችን፤ ወጣቱ ላይ የሰራሁት ሥራ ጥሩ ውጤት ያመጣ ይመስለኛል ይላል። ምልክቱ ደግሞ ለውጡን ተከትሎ ወጣቱ ብዙ ያልገባውና መከተል ያለበትን ያሳወቀበት በተለይ ብሔር ተኮር እንቅስቃሴዎች እንዲከሽፉና ወጣቶች ከዚህ ግለኝነት እንዲወጡ በማድረጉ ዙሪያ ጎላ ብዬ ታይቻለሁም ይላል።

ተግባራቱን የምከውነው በንግግርና በማስ ተባበር ብቻ ሳይሆን በብዕሬም ጭምር ነው የሚለው ባለታሪኩ፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩን የሚያደናቅፉ አካላትን በማህበራዊ ድህረገጽ በመጻፍና ወጣቱንም በማስተባበር እንደታገላቸው ይናገራል። በሐዋሳ በነበረው የወላይታ ልጆች ጥቃት ዙሪያም የማረጋጋትና ተቃውሞው በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ማድረግ ላይ መሳተፉንም ያነሳል። በዚህም እስከ እስር እንደ ደረሰ ይናገራል።

አሸናፊ ዴሞክራሲ ለወላይታ የሚመኝና የሚሰራ ወጣት ሲሆን፤ ለእስር የዳረገው ማህበረሰቡ የእርስ በእርስ ትስስሩን እንዲያጠናክር በማድረጉ ዙሪያ በሰራው በርካታ ሥራዎች መሆኑን ይናገራል።ይሁንና ዛሬም ቢሆን በዚህ ተስፋ እንደማይቆርጥና የለጋ ቡድኑን በልማትና በፖለቲካው እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ የተለያዩ ተግባራትን እንዲያከናውን ማድረጉን አላቆመም፤ ማቆምም እንደማይፈልግ ይናገራል።

ገጠመኝ

ኔዘርላንዱ ሀምስተርዳም ከተማ ውስጥ ነው ይሄ የሆነው። ከተማዋን ለማየት እየተዘዋወረም ነበር። እናም ለጥቁር ስደተኞች ሰብአዊ መብት መከበር አንዲት ሴት ትጮሃለች። እርሷ ምኗም አይነካም። ምክንያቱም ነጭ ነች። ሆኖም ሙግቷ ግን የጥቁሮች ነው። ለብዙ ነጮች መሰብሰብና ከንቲባው በር ላይ የመደርደራቸው ምስጢርም ይህቺው ሴት ናት። በኋላ ለመሆኑ ማን ትሆን ሲል ይጠይቃል።

ነጭ ጋዜጠኛ ነች። «ጥቁሮች ምግብ፣ ውሃና መጠለያ ያስፈልጋቸዋል። አገራችን እስከገቡ ድረስ የእኛ ዜጎች ናቸው፤ የሰው ልጆችም ናቸው» ነበር በንግግሯ የምታሰማው። ይህ ንግግሯ የሳባቸውና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ያሳሰባቸው ሰዎችም መኪናቸውን እያቆሙ ይቀላቀሏት ጀመር። እናም እዚያ ላይ ሆኜ አገሬን አሰብኩ ይላል ባለታሪኩ። ሰብዓዊነት አይደለም ብሔር በዘር ደረጃ ነጭና ጥቁር የሚለውን መለየት እንደማይችል በነጭ አገር ተማርኩ። ስለዚህም አገሬ ላይ ይህ ሲሆን ላለመፍቀድ ነው አሁንም እየታገልኩ ያለሁት ባይ ነው።

ቀጣዩ ውጥን

አንድነት፣ ፍቅር፣ ፍትህና ማንበብ ለእኔ የደስታ ምንጮቼ ናቸው የሚለው መምህር አሸናፊ፤ ሰዎች መሆን የሚፈልጉትን ነገር በትክክል አውጥተው ሲሆኑት ማየት ለእኔ ትልቅ ደስታን ይሰጠኛል። ይህ እንዲሆኑ ደግሞ በማነባቸው ውስጥ ያሉትን ሁሉ ለማጋራት እሞክራለሁ ። ስለዚህም አሁን ማድረግ የምፈልገውም በምሰራበት መስክ ማለትም በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ራስን በትምህርት ማበልጸግ ነው። አገሬንም በዚህ ከፍ ማድረግ እፈልጋለሁ ብሎናል።

ከተቻለ የፈጠራ ሥራዎች ላይ መስራት ካልተቻለ ደግሞ የተፈጠሩትን በማሻሻል አዲስ ለማድረግ መጣር ላይ እንደሚሰማራም ነግሮናል። ወጣቶችም በቴክኖሎጂው ዘርፍ እኔን በልጠው እንዲጓዙ ማድረግ ላይ መስራት እፈልጋለሁ ብሏል። ከዚያ በዘለለ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግም ነው ያጫወተን።

እኔ ለሁሉም አርአያ ነኝ ብዬ አላስብም፤ ከእኔ የሚልቁ ብዙዎች አሉ። ይሁንና ትንሽ ፈንጥቄአለሁ የምለው ነገር ግን በመኖሩ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን አውቀው ለእውነት እንዲቆሙ ማድረግመቻሌ ነው። በተመሳሳይ ያልታዩ ወጣቶች እንዲወጡና እንዲታዩም የተቻለኝን አደርጋለሁ። በዚያው ልክ መሪዎች እንዳይነኩ የሚፈልጉትን በመንካት ለእውነት እንዲቆሙ ማድረግ ላይ ተሟግቻለሁ፤ እሟገታለሁም። ትውልዱ ፍትህ ሲጓደል ዝም እንዳይልም የማነቃቃት ሥራ መስራቴን እቀጥላለሁ።

የሰው ልጅ አቅሙን ብቻ ሳይሆን ጉድለቱንም መረዳትና ጎዶሎውን ለመሙላት መጣር እንዳለ በትም አስተምራለሁ። የስርዓት መተካካቱ ቀጣይነት ይኖረዋል። ስለሆነም ወጣቱ ኢትዮጵያን መጠበቅና ለእርሷ መኖር እንዳለበትም በምችለው ሁሉ ለማስተማር ጥረት አድርጌያለሁ። በቀጣይም ይህንን ከማድረግ አልቦዝንም ይላል።

ቤተሰብ

«ከእኔ ጋር ለምትኖር ለትዳር አጋሬ መጠንቀቅ እፈልጋለሁ። አሁን ያለሁበት ሁኔታ ደግሞ ለዚህ የሚጋብዝ አይደለም። ስለዚህ ስረጋጋ ብቻ ነው ማግባት የምፈልገው።» ይላል ስለቤተሰቡ እንዲያጫውተን ስንጠይቀው፤ ቀጥሎም ቤተሰብ በትዳር ውስጥ ብቻ አይደለም ያለው። እናት አባት፣ ያስተማረን አካል ሁሉ ቤተሰባችን ነው። ስለዚህም እነዚህን ሁሉ ባለኝ ነገር እደግፋለሁ። ብዙዎች እየተለወጡና ለቁም ነገር እየበቁ በመምጣታቸውም ደስተኛ ነኝ።

ምክረ አሸናፊ

አንድ ሰው በወጣትነት ዕድሜው በርካታ ምርጫዎች ከፊቱ ይደቀናሉ፤ አንዳንዶቹም በሕይወቱ ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። በአሁኑ ጊዜ የሚደረጉ አንዳንድ ምርጫዎች የወደፊት ሕይወትንም ይነካሉ። እናም ጥበብ የተሞላባቸው ምርጫዎች አስደሳችና የተሳካ ሕይወት ያስገኛሉና ወጣቶች ይህንን ሊያደርጉ ይገባል ። ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎች የወደፊት ሕይወትን ሊያበላሹ ይችላሉና መጠንቀቅ ይገባል።

“ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጉዳትያገኘዋል” ይላል መጽሀፍ ቅዱስ። ስለዚህም አብረናቸው የምን ውላቸውንሰዎች መምረጥ ወይ ጠቢብ አሊያም ተላላ ያደርገናልና ምርጫችንን ማስተ ካከል የዛሬ ወጣቶች ሥራ መሆን አለበት ።

የመጨረሻው መልዕክቱ በወጣትነትህ ባሉህ ውድ ሀብቶች ምን ብታደርግ እንደሚሻል ስታስብ ሕይወትህን በሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት ላይ ጣል። እምነትና በጎ ኅሊና ካላቸው ሰዎች ጋር ዘወትር መገናኘትንም ቀጥል።» የሚል ነው። እኛም ምክረ ሀሳቡን እንመልከተው እያልን በዚህ ተሰናበትን። ሰላም!

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2011

ጽጌረዳ ጫንያለው