ለልማት እየተጋች ያለችው የመቐለ ከተማ

33

የዚህ ሳምንት የፖለቲካ አምዳችን ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቐለ ይወስደናል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በመቐለ ከተማ ተገኝቶ የከተማዋን የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የሥራ አጥነት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ በቤት አቅርቦት፣ የፀጥታ ሁኔታ እና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍስሃ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የበጀት ዓመቱ ትኩረት የተደረገባቸው ሥራዎች

የዚህ ዓመት እቅድ ሲዘጋጅ በዋናነት ህብረተሰቡን ያሳተፈ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ነዋሪውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሰርቶባቸዋል፡፡ የከተማው ካቢኔ እቅዱን አይቶ ለምክር ቤቱ በማፅደቅ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ከመሰረተ ልማት አንፃር ከተማዋ በርከት ያለ ህዝብና ተሽከርካሪ እያስተናገደች ከመሆኑ አንፃር በመንገድ መሰረተ ልማት በኩል የነዋሪው ጥያቄ ከፍተኛ ስለነበር ጥያቄውን ለመመለስ በርካታ ሥራ ተሰርቷል፡ ፡ በዚህም መሰረት በዚህ ዓመት የአስፋልት፣ የኮብልስቶን እና የገረጋንቲ መንገድ ተደርቷል፤ በመሰራትም ላይ ይገኛል፡፡

በ2010 ዓ.ም የከተማ አስተዳደሩ በአንድ ዓመት የሚጠናቀቅ የ21 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራ ከተቋራጭ ጋር ውል ገብቶ የነበረ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተፈለገው ጥራት እየተከናወነ ቢሆንም በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ አልተጠናቀቀም፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት ውስጥ 3 ኪሎ ሜትር የሚሆን ሥራ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ቢዘገይም 18 ኪሎ ሜትር ግን በሁለት ዙር ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ የቀረው 3 ኪሎ ሜትር መንገድ ቢቻል በዚህ ዓመት ካልሆነ ግን በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ይጠናቀቃል፡፡

ሌላው ደግሞ በ2011ዓ.ም ውል የተያዘለትና በ2012/13 ይጠናቀቃል ተብሎ የተያዘው 44ነጥብ5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራ ሲሆን ፕሮጀክቱ ከሚጠበቀው በላይ በፍጥነት እየሄደ ነው፡፡ የዚሁ አካል የሆነው ከመሀል ከተማ ወደ ደብሪ የሚወስደው አስፋልት መንገድ ተጠናቆ ተመርቋል፡፡ መንገዶቹ ሲጠናቀቁ በከተማዋ የሚገኙ ሰባት ክፍለ ከተሞችን እርስ በርስ የሚያገናኙ በመሆናቸው ፋይዳቸው ከፍተኛ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡

በኮብል ስቶን መንገድ በኩል በዚህ ዓመት 10 ኪሎ ሜትር መንገድ የሰራን ሲሆን 82 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡ በግንቦት ወር መጀመሪያ አካባቢ ያስመረቅነው ይህ መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ሆኖ እየሰራ ነው፡፡

የመንገዶቹ በጀት

ለፕሮጀክቶቹ በጀት አመዳደብን በተመለከተ ሥራውን የሚያሰራው የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ወጪ ስለሆነ አንድ ጊዜ የተመደበ በጀት የለም፡፡ ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከሚሰበሰብ ገንዘብ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ እንደአጠቃላይ ግን ለሁለቱም ፕሮጀክቶች ከ3ነጥብ6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል ፡፡ ይህም ከከተማዋ በየዓመቱ ከሚሰበሰብ ገቢ የሚሸፈን ነው፡፡

ለመንገድ ፕሮጀክቶቹ ስኬት እና አሁንም እየተከናወነ ላለው ተግባር የከተማዋ ነዋሪዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ በወሰን ማስከበር በኩል ከጥቂት ችግሮች ውጪ ህብረተሰቡ ተባባሪና በባለቤትነት መንፈስ ሲሰራ ነበር፡፡ የከተማ አስተዳደሩም የነዋሪውን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ ሆኖ መንቀሳቀሱ እና ፕሮጀክቶቹን በመከታተልና በመቆጣጠር በኩል ጠንክሮ እየሰራ መሆኑ ለስኬት እንዳበቃቸው አቶ ዘመንፈስቅዱስ ይናገራሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የሥራ ተቋራጮች ሥራውን በተፈለገው ደረጃ እንዲሄድ በማድረግ በኩል ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡

ጎርፍን መከላከል

አሁን የምንገኝበት የክረምት ወቅት እንደመሆኑ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍና መሰል አደጋዎችን ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ በተለይ የመቐለ ከተማ ካለው አቀማመጥ አንጻር ለጎርፍ የመጋለጥ እድል ያለው ነው፡፡ ስለዚህ አደጋ ከመከሰቱ በፊት የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ ጥንቃቄ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዚህ መሰረት በከተማው ተፋሰስ ያልነበራቸው የከተማዋ አካባቢዎች የተፋሰስ ሥራዎችና የድልድይ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ይህም ቀደም ብሎ በክረምት ወቅት ይደርስ የነበረውን የፍሳሽ ቆሻሻ ልቀት እና የጎርፍ አደጋ ይቀርፋል ብለን እናምናለን፡፡

የመኖሪያ ቤት አቅርቦት

በመቀሌ ከተማ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ አንዱ የመኖሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ቢኖርም ችግሩን በሚፈለገው ደረጃ መፍታት አልተቻለም፡፤ በዚህም የተነሳ የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በዚህም መሰረት ማህበራትን አደራጅተን የተለያዩ ሥራዎች ተሰርቷል፡፡ ባለፈው አመት ለ1 ሺህ 158 በማህበር ለተደራጁና ቤት ላልነበራቸው ነዋሪዎች እንዲሁም ለመምህራን የቤት መስሪያ ቦታ ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ አመትም 344 ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በሃያ ሃያ በማደራጀት ማህበራት ቦታ ተሰጥቷል፡፡ 590 ለሚሆኑ በትግሉ ወቅት አካላቸው ለጎደለ ወገኖችም የቤት መስሪያ ቦታ ተሰጥቷል፡፡ 9 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችን የመሬት ባለቤት ለማድረግም አስፈላጊው የማጣራት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት በከተማዋ በአጠቃላይ ጥሩ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡

መሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት

በከተማዋ ለአመታት የቆየ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ቢኖርም አሁን አሁን ግን ጥያቄዎቹ እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ የከተማዋ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶች ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ በዚህ አመት ብቻ ለ222 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ ወደሥራ ሲገቡም የሥራ እድል ከመፍጠርና ከተማዋን ከማሳደግ አንፃር ጉልህ ድርሻ ስለሚኖራቸው መሰረተ ልማቶቹ ለኢንቨስትመንቱም የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡

የሥራ አጥነት ችግር

በከተማዋ ጎልተው ከሚታዩ እና ካልተመለሱ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሥራ አጥነት ችግር ነው፡፡ በከተማዋ ያለው የሥራ አጥነት ችግር የከፋ ነው ፡፡ እንደ ሀገር ችግሩ ያለ ቢሆንም በከተማችን ደግሞ የባሰ የሆነበት ሁኔታ አለ፡፡ ለማነፃፀር ያክል የሥራ አጥ ችግር እንደ ሀገር 22 በመቶ ፣ በክልላችን 29 በመቶ ሲሆን ወደ ከተማችን ሲመጣ ደግሞ ከዚህ በላይ ነው፡፡ ወጣቶቹን በጥቃቅንና አነስተኛ በማደራጀት እራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ሥራ ቢኖርም በቂ አይደለም፡፡ የወጣቶቹ የሥራ ተነሳሽነት ጥሩ ቢሆንም ከአቅም እና ብድር ጋር በተያያዘ የመንግሥት ውስንነቶች ሥራ አጥነቱን አባብሶታል፡፡ ወጣቶቹ በከተማዋ እየጨመረ ካለው ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራን ነው፡፡ ወጣቶቹ የሥራ እድልና ተጠቃሚነት ላይ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው፡፡ ወጣቶቹ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ስልጠናዎችን የመስጠት ሥራም በቀጣይ ለመስራት እቅድ ተይዟል፡፡

የኑሮ ውድነት

በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ አንዱ የኑሮ ውድነት መባባስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በመቐለ ከተማ የኑሮ ውድነት ደግሞ በጣም አስከፊና አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በተለይም በሚያዝያ እና ግንቦት ወሮች ውድነቱ እየተባባሰ ሄዷል፡፡ የምግብ ፣የፍጆታ እቃዎች እና የግንባታ እቃዎች ዋጋ እየናረ መጥቷል፡ ፡ ከመብራት በፈረቃ መሆኑ ጋር በተያያዘ ደግሞ በተለይ በሲሚንቶ ዋጋ ላይ የእጥፍ ጭማሪ ታይቶ የነበረ ቢሆንም እሱን በፍጥነት ለመቆጣጠር ችለናል፡፡ የአቅርቦት ችግር አለ ብለን አናምንም፤ ነገር ግን በሀገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ተጠቅመው መክበር የሚፈልጉ ነጋዴዎች ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ ያደርጋሉ፤ ያከማቻሉ፤ ይደብቃሉ፤ ክልላችንን ጨምሮ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚመረቱ ምርቶች ዋጋ እየጨመረ ነው፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ገበያ ወጥቶ ለራሱና ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ሸምቶ ለመምጣት ፈተና እየሆነ ነው፡፡ የመንግሥት የቁጥጥር ማነስ እና የነጋዴዎች ከተገቢው በላይ ትርፍ መፈለግ የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ነው፡፡ ይህም በከተማችን ተፅዕኖ እያሳደረ ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ሥራ

በከተማችን የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴው እንደከዚህ ቀደሙ ባይሆንም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፡፡ በሀገሪቱ ካለው የሰላም ሁኔታ ጋር ተያይዞ ሁሉም እንቅስቃሴ ቢዳከምም በዘርፉ ያን ያክል የከፋ ችግር አልገጠመንም፡፡ መብራት በፈረቃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የማምረቻ ተቋማት ሲሚንቶ የሚረከቡ ነጋዴዎች አላስፈላጊ ጭማሪ ማለትም ዋጋውን እስከ እጥፍ የማድረስ ሥራ ሰርተው ነበር፤ ነገር ግን የከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላትና ክፍለ ከተሞች ጋር በመሆን ምርት የደበቁና ያከማቹ ነጋዴዎች ላይ መጋዘናቸውን እስከማሸግ የደረሰ እርምጃ ወስዷል፡፡ ፋብሪካዎቹ መብራት በፈረቃ በመሆኑ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ አለማድረጋቸውን ስለገለፁልን ከተማ አስተዳደሩ የሲሚንቶ ዋጋ ወደነበረበት እንዲመለስ አድርጓል፡፡

የከተማ ፀጥታ

አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ለው መሰረታዊ ችግር የሰላም ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ በሀገራችን የፀጥታ ሁኔታ የተናጋበት እና ዜጋ እንደ ዜጋ በነፃነት የማይንቀሳቀስበት ብሎም በርካቶች የሚፈናቀሉበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ይሁን እንጂ መቐለ ከተማ በዚህ በኩል ከተፅዕኖ ነጻ ናት ባይባልም አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ ሲታይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በነጻነት እየኖረባት እና በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባባት ከተማ ናት፡ ፡ መንቀሳቀስ ብቻም ሳይሆን ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ሰርቶ የሚያድርባት ከተማም ናት ፡፡ የኢንቨስትመንት ፍሰቱም እየጨመረ የመጣው በከተማዋ ያለው ሰላም ጥሩ በመሆኑ ነው፡፡ የንግድ እንቅስቃሴም ሳይስተጓጎል እየተከናወነ ሲሆን አለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ስብሰባዎችንም እያስተናገድን ነው፡፡ቱሪስቶችምበሰላም አርፈው ወደተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚሸጋገሩባት ሁኔታ ይታያል፡፡

በከተማዋ ለሰላሙ መጠበቅ ህብረተሰቡ ሰፊውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥት የራሱን ሚና ይጫወት እንጂ ህብረተሰቡ የራሱን ሰላም እያስጠበቀ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በትጥቅ ትግሉ ያየውና የከፈለው መስዋዕትነት ከባድ ስለነበር ከጦርነት ምንም ትርፍ እንደማይገኝ ጠንቅቆ ስለሚረዳ ነው፡ ፡ በዚህም ሂደት ውስጥ ደግሞ ወጣቱ ከፀጥታ አካል ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል፤ ውጤትም ተገኝቶበታል፡፡

የችግኝ ተከላ

ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሐግብር በመቀሌም ተጠናክሮ ይካሄዳል፡፡ በርግጥ በክልሉ የችግኝ ተከላና አካባቢ ጥበቃ ሥራን እንደ ክልልም እንደ ከተማም ሁሌም በየአመቱ የምናከናውነው ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በዘንድሮ አመት በከተማዋ ዙሪያና ውስጥ ለውስጥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ ሥራ ለመስራት እና አረንጓዴ ልማትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

በአጠቃላይ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት መዲና በሆነችው የመቀሌ ከተማ በርካታ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ የከተማዋ አስተዳደርም በከተማዋ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ እንዲሆንና ህብረተሰቡም የጀመረውን የልማት ሥራ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲያስቀጥል ከህብረተሰቡ ጋር እጅና ጓንት በመሆን በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም በአጠቃላይ በክልሉ ያሉትን የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ለመመለስና የክልሉን እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011

በድልነሳ ምንውየለት