የጥሞና ጊዜ ይኑረን

7

 “የምትሄድበት እንዳይጠፋህ የመጣህበትን አትርሳ” የሚል የአገራችን አባባል አለ፡፡ ይህ አባባል በህይወታችን ውስጥ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ቀደም ሲል ያለፍንባቸውን መንገዶች ሁሉ ቆም ብለን እንድንመለከትና ከባለፈው ተምረን ለቀጣዩ የተሻለውን መንገድ እንድንይዝ የሚያስተምረን ነው፡፡

ዛሬ ያለውን የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታም ስንመለከት ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ አንዳንድ ክስተቶችን እንመለከታለን፡፡ ምክንያቱም እኛ በአንድ ወቅት ገናና ታሪክ የነበረን ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ምክንያቶቹ በውል በማይታወቁ ክስተቶች ወደ ኋላ የተመለስንና የኋልዮሽ ጉዞአችንን ያፈጠንበት ወቅት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እነዚያ ደማቅና ጊዜ የማይሽራቸውን የታሪክ ቅርሶች ትተው ያለፉ የዘር ሃረጎቻችን ኢትዮጵያ ወደኋላ ተመልሳ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የረሃብ ተምሳሌት ተደርገን በመዝገበ ቃላት ጭምር እንደማሳያ ስማችን መስፈሩን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን?

እነሆ ያም አልፎ ደግሞ አሁን ላይ በዚያ ቁጭት ተነስተን ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በተነሳንበትና በዓለም ማህበረሰብ ዘንድም አንገታችንን ቀና አድርገን መራመድና መናገር በጀመርንበት ወቅት አገራችንን ለማበጣበጥና የማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለማስገባት በር የሚከፍቱ እና የሚደረጉ ጥረቶች አንዴት ይታያሉ? እውን እንዲህ አይነት ግጭቶችና አልፎ አልፎ እየታዩ ያሉ ድርጊቶችስ ወዴት ይወስዱናል?

እንደ መታደል ሆኖ አገራችን ሰፊ የማደግ እድል ያላት አገር ናት፡፡ አብዛኛው ህዝቧ ወጣት መሆኑ ሰርቶ አገርን ለመለወጥ የሚያስችል አቅም እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የህዝብ ቁጥራችንም ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡ ከዓለም በ12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ህዝባችን ለልማት ትልቅ አቅም ነው፡፡ የአገራችን የመሬት አቀማመጥና የቆዳ ስፋት፣ እንዲሁም መልካ ምድራዊ አቀማመጣችንና ያለን የተፈጥሮ ሃብትም አገራችንን ወደቀደመው ስልጣኔ ለመለወጥ የሚያስችል እድል ነው፡፡ ዛሬ ላይ የሚያስፈልገን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ በአንድ ልብ ሆነን ድህነትን ለማሸነፍና አገራችንን ለመለወጥ በቁርጠኝነት መነሳት፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ በርካታ ፈተናዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የእድገት ጎዳና የማይፈልጉ በርካታ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ኃይሎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡ ፡ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ በአገራችን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችና የህዝብ ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ በዚህ ቀዳዳ ሾልከው በመግባት በተለይ ወጣቱን ኃይል መጠቀሚያ ለማድረግ ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የግጭት መነሳት ለአንዳንዶቹ ሰርግና ምላሽ ይሆንላቸዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያው የሚለቀቁ አንዳንድ መረጃዎችን ስንመለከት ኢትዮጵያን ለማበጣበጥ ተግተው የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ያስገነ ዝበናል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ህዝቦቿ እርስ በርስ እንዳይተማመኑና እንዳይቀራረቡ ከዚያም አልፎ እርስ በርስ ወደመጠራጠርና ከዚያም ከፍ ሲል ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እነዚህ አካላት ልጆቻቸውንም ሆነ የቅርብ ዘመዶቻቸውን በአሜሪካና በአውሮፓ በማሸሽ እዚህ የጦርነት ቀጣና ለመፍጠር የሚሞክሩ ናቸው፡፡ አቀራረባቸውም ተቆርቋሪ በመምሰልና አንዱ በሌላ እየተበደለ እንደሆነ በማቅረብ እና ሆድ እንዲብሰው በማድረግ የሚሰራ ሴራ ነው፡፡ በአገራችን አንድ አባባል አለ፡፡ አገራችን ውስጥ የእርስ በርስ ችግሮች ቢፈጠሩ ተጎጂውም ሆነ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እኛው እዚሁ የምንኖር ዜጎች ነን፡ ፡ እነዚህ ግፋ በለው የሚሉ የፌስ ቡክ አርበኞች ሁል ጊዜ ከውጭ ሆነው ከማበጣበጥ በዘለለ አንዳችም የሚፈይዱት ነገር አይኖርም፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን መረዳት ያለብን ይህም ሰላም ምንያህል አስፈላጊያችን እንደሆነ ነው፡፡ አሁን ኃላፊነት የሚሰማው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ የሚያስብበት ወቅት ነው፡፡ አዕምሮአችንንም በአግባቡ መጠቀም የሚያስፈልገን አሁን ነው፡፡

ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ በአገራችን የተፈጠ ረውን ችግር እልባት ለመስጠት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ የሚያሰላስልበትና ለአገሩ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡ እያንዳንዳችንም ሁለት ምርጫዎች ቀርበውልናል፡፡ አንድም የምናነሳቸውን ጥያቄዎች በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ በማንሳት ሰላማዊ የትግል አቅጣጫን መከተል አልያም የተበታተነችና የጦርነት ቀጣና የሆነች አገር መፍጠር፡፡ ከዚህ አንፃር ማንም ሰላም ወዳድ ዜጋ ሁሉ ሁለተኛውን አማራጭ ይመርጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አገሩ እንድታድግና የቀድሞ ገናና ታሪኳ ተመልሶ የተከበረችና የበለፀገች አገር ባለቤት መሆን ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሰከነና በበሰለ አእምሮ አገራችንን ማዳን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዉያን በራሳችን አእምሮ የምናመዛዝንበት የጥሞና ጊዜ ሊኖረን ይገባል፡ ፡ የተሟላ አዕምሮ ባለቤቶች እስከሆንን ድረስ ለምን የሌሎችን ቅስቀሳና አውቅልሃለሁ የሚል ፕሮፓጋንዳ እንከተላለን፡፡ የአገር መበታተን የሚመቻቸው ጥቂት አካላት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ አካላት አንድም በግርግሩ መነሻነት የሌላውን ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ ቋምጠው የሚጠብቁ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት በላባቸውና በጉልበታቸው ሰርተው ከመኖር ይልቅ ዘርፈው ለመኖር ፍላጎት ያላቸውና በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ስለሌላው ወይም ስለአገር ግድ የሌላቸው ናቸው፡፡

ሁለተኛውና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት ደግሞ በውጭ የሚኖሩት እና በተለያየ ምክንያት ከአገር ወጥተው በውጭ የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት አንድም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ እኔ ከሌለሁ ምን አገባኝ በሚል ስሜት ሆን ብለው የጥላቻ ፖለቲካን እያራመዱ በአገሪቷ ውስጥ ብጥብጥ እንዲፈጠር ፍላጎት ያላቸው ሲሆን በሌላም በኩል ደግሞ ለአገሪቷና አገሪቷን ለሚመራው መንግሥት ባላቸው ከፍተኛ ጥላቻ ምክንያት ሆን ብለው አገርን በማበጣበጥ ከዳር ቆመው የሚነደውን እሳት ለመሞቅ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

እነዚህ አካላት በዚህ አጋጣሚ ምናልባት አገር ስትበታተን እኔም ቀዳዳ ከተገኘ ገብቼ ልፈተፍት እችላለሁ የሚል ቀቢፀ ተስፋ ያላቸውና ራስ ወዳዶች በመሆናቸው ራሳቸውንና ራሳቸውን ብቻ ማየት የሚችሉ ናቸው፡፡

ሌላው አካል ደግሞ ችግሩ ሳይገባው ተጃምሎ የሚሄድ ነው፡፡ በአገራችን የዚህ አይነት ችግር ውስጥ የሚገቡ አካላት በርካታ ናቸው፡ ፡ ለምሳሌ በአንድ በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ የሚካሄድ ሰልፍ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ጥቂት ናሙና ወስደን ለምን ሰልፍ እንደወጡና ለዚህ ድርጊት ኃላፊነቱን ምን እንደሚወስድ፣ ምናልባት የሰልፉ ውጤት ቢያስገኝ ምን እንደሚፈጠር እንዲሁም በትክክል ከማን ምን እንደሚጠብቁ ቢጠየቁ ብዙም ግንዛቤው የሌላቸው ይበዛሉ የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ በኛ አገር ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም በእውቀት ላይ የተመሰረተ መነሻ ሃሳብ ይዞ ከሚንቀሳቀሰው ይልቅ ሌሎች ስላደረጉት ብቻ አብሮ የሚጓዝ አጃቢ እየበዛ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡

እኛ በርካታ ኃላፊነትና የቤት ሥራ ያለብን ዜጎች ነን፡፡ ገና ያልሰራነውና ለዘመናት ሲደማመር የመጣ ድህነት የሚባል ታሪካዊ ጠላት ያለብን ዜጎች ነን፡፡ ይህ ጠላት ደግሞ እንኳንስ እርስ በርስ ተከፋፍለንና ያለንን ጥቂት ልማት እያወደምን ቀርቶ ሰርተንም ብዙ ጥረትና ልፋትን የሚጠይቅ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ለዘመናት በላያችን ላይ ከተጫነው ከዚህ የድህነት በሽታ ለመላቀቅ መድኃኒቱ ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው፡፡ ለዚያውም ከጀመርነው ፍጥነት በላይ በፍጥነት መጓዝ፡፡ እናም ከዚህ አንፃር ቆም ብሎ ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡

ከዚህም ባሻገር ብልህ ከሌላው ስህተት ይማራል እንደሚባለው እኛ በርስ በርስ ግጭት ሳቢያ መከራና ፈተና ከበዛባቸው የአረብ አገራት በርካታ ቁምነገሮችን ልንማር ይገባል፡፡ ለምሳሌ የሶርያን ነባራዊ ሁኔታ ያየ የእርስ በርስ ግጭት ምን ያህል አስከፊና አስፈሪ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ ይወስድበታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የዚች አገር ህዝቦች በአንድ ወቅት ከኛ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ ህዝቦቻቸውም ቢሆኑ ሰላማዊና የጥይት ጩኸት የማያውቁ፣ ህፃናትም ጨዋታና ደስታ እንጂ ጦርነት ማለት ምን ማለት እንኳ በቅጡ የማይገነዘቡባት አገር ነበረች፡፡ ያ ግን አሁን ላይ ታሪክ ሆኗል፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት የምናየው የዚያች አገር ህዝቦች ስቃይ ከማሳዘን አልፎ በየቤቱ ስንቶችን ያስለቀሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ስለዚህ በአንድ በኩል መንግሥት ህዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ህዝብን የማረጋጋት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ህብረተሰቡም ደግሞ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚገኝ ትዕግስት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሮም በአንድ ምሽት አልተገነባችም እንደሚባለው መንግሥት ችግሮቹን ለማስተካከል ጊዜ መፈለጉ ትክክልም፣ እውነትም በመሆኑ ህብረተሰቡ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ሌላውና ዋናው ጉዳይ ደግሞ ልማትን እያወደሙ ልማትን መጠየቅ የሚቃረኑ ተግባራት ናቸውና ከዚህ መቆጠብ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዉያን ባህላችንም ሆነ ማህበራዊ አኗኗራችን እርስ በርስ እንድንከባበርና እንድንተሳሰብ እድል የፈጠረልን በመሆኑ ይህንን ጥሩ ባህልና ማህበራዊ ልማድ ይዘን አዕምሮአችንን ይበልጥ ለመልካም ነገር ልናውለው ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011

ሰላም ከአዲስ አበባ