ፅዱነትና አረንጓዴነት ለምንና እንዴት ?

21

በአዲስ አበባ ሰባት ታላላቅ ወንዞችን ጨምሮ በአጠቃላይ 76 ወንዞች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ወንዞቹ ከመኖሪያ ቤቶችና ከተለያዩ ተቋማት በሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ለብክለት የተዳረጉ ናቸው። ወንዝ ከሚባሉ ይልቅ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ቢባሉ ይቀላል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪችና እንግዶቿም ይገልጻሉ፡፡

ይህን የወንዞቹን ገጽታ ትርጉም ባለው መልኩ መቀየር የሚያስችል ታላቅ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ከእንጦጦ በመነሳት ከተማዋን ሰንጥቀው ወደ አቃቂ በሚፈሱት ሁለት ትላልቅ ወንዞች ላይ ተመስርቶም ነው ልማቱ የሚካሄደው፡፡ ይህም ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን ሲሆን፣ከወንዞች ግራና ቀኝ ያለው 50 ዳርቻም እንዲለማ ይደረጋል፡፡

የዚህ የ29 ቢሊየን ብር ፕሮጀክት ግንባታ በሦስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል፡ ፡ የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሸራተን አዲስ ፊት ለፊት ባለው ክፍት ስፍራ ላይ ለመተግበር በይፋ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህም 2ቢሊየን ብር እንደሚፈጅ ታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን ወንዞችና ከተማዋን በብዙ መልኩ ይታደጋል፡፡ የአረንጓዴ ሽፋን እንዲጨምር ያደርጋል፤የቱሪስት መስህብ ይሆናል፤በርካታ የሥራ ዕድሎች የሚፈጠሩበትም ነው። ፕሮጀክቱ በውስጡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስሪያ ቦታዎችን፣ የአዋቂዎችና የሕፃናት መዝና ኛዎችን እንዲሁም የማንበቢያ ስፍራዎችንም የሚያካትት ተደርጎ ነው የሚገነባው።

ቀደም ሲልም ከተማዋ በወንዝ ዳርቻ ልማት አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በ20 ዓመት ውስጥ በወንዞቿ ላይ ለውጥ ለማምጣት ራእይ ሰንቅ መሥራት ውስጥ ገብታም እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ችግሩ ሰፊ እንደ መሆኑ አዲሱ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ ቀደም ሲል በልማቱ ሲሠሩ የነበሩ ወገኖችም የወንዝ ዳርቻ ልማቱ በከፍተኛ አመራር እውቅና ማግኘቱን በአድናቆት ተመልክተውታል። ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም አሻራውን ማኖር እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል፡፡

የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለከተማዋ ሌላ ሳምባ የሚፈጠርላት ያህል ነው ሲሉ የገለጹ አካላትም አሉ። እነዚህ አካላት አየርን የመለወጥ ትልቅ ሃሳብ ነው። በወንዞች ማፅዳት ሥራ ላይም ትልቅ ተመክሮ ይሆናል፤ስለዚህ ሊበረታታና ሊደገፍ ይገባል ይላሉ፡፡

ሀገሪቱ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ተስፋ ሰጪና የብዙዎች ድጋፍ የተቸረው ቢሆንም ፣አንዳንድ ወገኖች ግን በፕሮጀክቱ ላይ ቅሬታዎች፤ ጥርጣሬዎችና ጥያቄዎችን ያነሳሉ። ፕሮጀክቱ መንግሥት የፖለቲካውን አቅጣጫ ለማስቀየር አስቦ የጀመረው ነው፤ በአዲስ አበባ በሚካሄደውም የአረንጓዴ ልማት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ህዝቡ እንፈናቀላለን የሚል ስጋት አድሮበታል፤ ሊተከል በእቅድ የተያዘው የችግኝ ብዛት ድጋፍ ለማግኘት ካልሆነ በቀር ሊሳካ አይችልም የሚሉ አስተያየቶችም ይሰነዘራሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ ውይይት በቅርቡ ባካሄደበት ወቅት ፕሮጀክቶቹ ሊተገበሩ የሚችሉና ወቅቱ የሚጠይቃቸው እንደሆኑ በመጥቀስ፣ ሌላ ምንም ዓይነት ድብቅ አጃንዳ የተያዘባቸው እንዳልሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፤‹‹ፕሮጀክቱ ለወረትና አቅጣጫ ለማሳት ታስቦ የተጀመረ አይደለም፤ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታው ከግምት ገብቶ የተጀመረ ነው።›› ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ በጣም ተጎሳቁላለች፤ አየር ንብረቱ ተጎሳቁሏል፤ በወንዝ ዳርቻዎች ላይ የነበሩ ዛፎች ተመንጥረው አፈሩ እየተሸረሸረ ይገኛል። አእዋፍና እንስሳትም የሉም፤ ይሄ የሚያሳየን አጠቃላይ ምህዳሩ መዛባቱን ነው ሲሉ ያብራራሉ። በዚህም በቂ ምርት አለማምረትና የግጦሽ መሬት እጥረት ተከስቷል። ይሄን የመለወጡ ሥራ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ በጣም ዘግየተናል።›› ነው የሚሉት፡፡

‹‹የሀገሪቱ የደን መጠንም ከአራት በመቶ ተነስቶ 15 በመቶ ቢደርስም ዛሬም በርካታ ሥራዎች ይቀሩናል። የገጠር አረንጓዴ ልማት አስተዳደር በማስፈንና ጥበቃ በማድረግ ታዳሽ ኃይልን በማስፋፋት እየጨመረ ያለውን የህብረተሰባችንን ጤና መጠበቅ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም›› ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤አዲስ አበባ የኢትዮጵያም የአፍሪካም መዲና እንደመሆኗ ለከተማዋ የተለየ ትኩረት ቢሰጥም ፕሮጀክቱ በመላው ሀገሪቱ ይተገበራል፤ በአሁኑ ወቅትም በተመረጡ ሃያ ሦስት ፕሮጀክቱን መተግበር ተጀምሯል።

ለደን ተከላ የተቀመጠውም ቍጥር የተጋነና የማይደረስበት አይደለም። አርባ ዛፍ በነፍስ ወከፍ ይተከላል ሲባል መላውን ኢትዮጵያዊ ከግምት በማስገባት ነው አንድ ሰው በቤቱ ያሉ አዛውንትና ሕፃናትን አስቦ ከዚያም በላይ መትከል ቢችል በሦስት ወር ከዚህም በላይ መትከል ይቻላል። በመንግሥት በኩል በቂ የችግኝ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተጀምሮ እንዳይቆም ባለቤት እንዲኖረው ከተማሪዎች ጀምሮ በየደረጃው የመንግሥት መዋቅር ድረስ ተሳትፎ በዘላቂነት እንዲቀጥል የሚሠሩ ሥራዎችም ይኖራሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን በበኩላቸው በሀገሪቱ ተላላፊ የሆኑትም ሆነ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት እኩል እየሆነ መጥቷልይላሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት 52 በመቶ ህመምና ሞት እየተከሰተ ያለው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎችና አደጋ ነው። ለእነዚህ በሽታዎች መፈጠርም ሆነ መስፋፋት ደግሞ የአካባቢ ብክለት ትልቅ ድርሻ አለው። በአዲስ አበባ ያሉ ወንዞች በሙሉ በተዋህስያን የተበከሉ ሲሆኑ አንዳንዶቹ በዓለም ካለው ዝቅተኛ የብክለት ደረጃም በላይ የደረሱ ናቸው።

በቅርቡ በአዲስ አበባና በአራት ክልሎች የተከሰተውን የአተትና የኮሌራ በሽታ ጨምሮ በትንፋሽ ለሚተላለፉትም የአካባቢ መበከል ዋናውን ድርሻ ይይዛል። የባንቧ ውሃ የሚቀርብባቸው ቧንባዎችም አብዛኛዎቹ በቦይ ውስጥ የሚያልፉ በመሆናቸው ውሃውን እየበከሉ ተጠቃሚውን ለካንሰር የሚዳርጉት ይሆናል። የአየር ንብረት ለውጥም በመተንፈሻ አካላት በተለይም በልጆች ላይ እያደረሰ ያለውም ጉዳት ሰፊ ነው። በመሆኑም እነዚህን በሽታዎች በመከላከል የህብረተሰብን ጤና ለመጠበቅ የአካባቢ ልማትን ማከናወን የግድ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ፕሮጀክቶችም ቅድሚያ ሊያገኝ የሚገባው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የፕሮጀክቱ የቴክኒክ አማካሪ ወይዘሮ መስከረም ታምሩ ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ትልቅ የሚባለውና ግዙፍ በመሆኑ ላይተገበር ይችላል የሚል ስጋት ቢፈጠር አይገርምም፡፡”ይላሉ፡፡አስፈላጊው ቅድመ ጥናት ስለተደረገ ውጤታማ መሆኑ እንደማይቀርም ያስገነዝባሉ፡፡

እንደ አማካሪዋ ማብራሪያ በፕሮጀክቱ በቅድሚያ የሚለሙት ከእንጦጦ ተነስተው ቃሊቲ የሚደርሱ ሁለት ወንዞች ናቸው። በእነዚህ ወንዞች ላይ ላለፉት አራት ዓመታት አስፈላጊው ጥናት ተደርጓል፤ከሀገር ውስጥም ከውጭም ለፕሮጀክቱ የሚረዱ መረጃዎች ተሰብስበዋል። የገንዘብ አቅርቦትንም በተመለከተ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹም ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቁ ገቢ የሚያስገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠርም የሚከናወኑ ተግባሮች ይኖራሉ።

ከእንጦጦ ጀምሮ አብዛኛዎቹ የወንዝ ዳርቻዎች ታሪካዊ ቦታዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ በልማቱ አካባቢ ያሉት ቅርሶች በሙሉ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ይገልጻሉ፡፡ የሚነሱት ቢኖሩም ታሪካቸውን ሊያሳታውስ በሚችል መልኩ ልማቱ እንደሚካሄድ ነው ያመለከቱት። እንደ ፍልውሃ እና ሂልተን ያሉት አካባቢዎች የፓርኩ አንድ አካል ሆነው እንዲቀጥሉ እንደሚደረግ የታችኛው ቤተ መንግሥት በተወሰነ በፓርኩ እንደሚካተት ያብራራሉ።

ህዝብን አፈናቅሎ ለመሥራት የታሰበ ነገር የለም ያሉት አማካሪዋ፣ ከተማ መስተዳድሩ ከአካባቢው ለልማቱ የሚነሱትን እያወያየ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ከማህበራዊ ህይወትና ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከቦታው መራቅ ለማይፈልጉ እዚያው አካባቢ ቦታ ፈልጎ ለማስፈር፤ ፈቃደኛ የሆኑትንና በተለይም የግል ይዞታ ያላቸውን ተለዋጭ ቦታ በመስጠት እንዲነሱ እንደሚደረግ እና በዚህ በኩል ቅሬታ እንደማይፈጠር ያብራራሉ።

ይልቁንም ያለውን ክፍተት በመጠቀም ቦታው እንደሚነሳ ሲታወቅ እዚያ ያልነበሩ በአሮጌ ቆርቆሮ ቤት እየሠሩ የሰፈሩ አዳዲስ ግለሰቦች እንዳሉ በመጥቀስ እነዚህ ለከተማ መስተዳድሩ ችግር መሆናቸውን ጠቁመዋል። አተገባበሩን በተመለከተ ከውጪም ከውስጥም በርካታ ጥናቶችን ለመዳሰስ እንደተሞከረና ከዚህም በኋላ ህዝቡንም ምሁራንንም በሚያሳትፍ መልኩ አስፈላጊው ግብአት እየተሰበሰበ ፕሮጀክቱ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011

 ራሰወርቅ ሙሉጌታ