የዘር ወቅቱን ለዘር ብቻ !

17

ሀገራችን የተለያየ ስነ ምህዳር ቢኖራትም ፣ ሰኔ ለአብዛኛው አርሶ አደር የዘር ወቅት ነው። ሲያርስ፣ ሲያለስለስ የቆየውን ማሳውን በዘር መሸፈን የሚጀምረው እንደ ብሂሉ ከሆነ ከሰኔ12 /ከሰኔ ሚካኤል/ እንስቶ ነው ይባላል፡፡ ሰኔ ሚካኤል ደግሞ ነገ ነው። ስለሆነም ሰኔ የአርሶ አደሩ ዋልታና ማገር ቢባል ማጋነንም አይሆንም፡፡ ‹‹አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አያነሳውም›› የሚባለውም ለእዚህ ነው፡፡

በ2011/12 የመኸር እርሻ 406 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። 13 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ነው ይህን ያህል ለማምረትም የታቀደው፡፡

አንድ ሚሊዮን 613 ሺ 246 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ ይጠበቃል፡፡ ከእዚህ ማዳበሪያ ውስጥ የተወሰነው ለአርሶ አደሩ የደረሰ ሲሆን፣ የተወሰነው ደግሞ እየተጓጓዘ ይገኛል፡፡ በምርት ዘመኑ የብርእ እህል፣ጥራ ጥሬና የቅባት እህል አንድ ሚሊዮን 160 ሺ 521 ኩንታል የዘር ፍላጎት የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ይገኛል፡፡

በክልሎች ከ12 ሺ በላይ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ ከዘርፉ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ጋርም ምክክር መደረጉን ነው የሚኒስቴሩ መረጃ የሚጠቁመው፡፡ መረጃዎቹ ከዝግጅት አንጻር ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ መሆናቸውን ያስገነዝባሉ። አሁን ፍልሚያው በማሳ ውስጥ እንደመሆኑ አርሶ አደሩ ሲያርስና ሲያለሰልስ የቆየውን ማሳ በተገቢው መንገድ በዘር እንዲሸፍን የግብርና ባለሙያው የቅርብ ድጋፍ ወሳኝ ይሆናል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ላይ እስከ አሁን ለታየው እድገት የባለሙያው ድጋፍ ወሳኝ እንደ መሆኑ ያለፉትን ዓመታት ልምድ በመቀመር አዳዲስ አሰራሮችን በመያዝ አርሶ አደሩን የመደገፉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የሜትሮሎጂ መረጃዎችን በመከታተል አርሶ አደሩን መደገፍ የሚጠበቅበትም ባለሙያው መሆኑ ይታወቃል።

አርሶ አደሩም በቤተሰብ አቅምና በደቦ በመጠቀም እየጣለ ያለውን ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም ማሳውን በዘር መሸፈን ይኖርበታል፡፡ ስራው አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ እንደሚባለው እንዳይሆንም ለአረም ምቹ ሁኔታ በማይፈጥር መልኩ ጎልጉሎ መዝራት እንደሚያስፈልግም ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡

እንደሚታወቀው የሀገራችን የግብርና ምርት ፍላጎት በተለያየ ምክንያት እየጨመረ መጥቷል፡፡ የህዝብ ብዛቱ፣ የወጪ ገበያው፣ በቀጣይ ወደ ስራ ሊገቡት የሚችሉት የአግሮ  ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችም የግብርናውን ምርት ነው የሚጠብቁት፡፡ ይህን ፍላጎት ለማሟላት አንዱና ዋናው መንገድ ደግሞ የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ነው፡ ፡ ይህ ደግሞ አስፈላጊዎቹን ግብአቶች ማቅረብን፣ ማሳን በሚገባ ማዘጋጀትን ፣ አርሶ አደሩ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ ማድረግን ይጠይቃል።

ከአንዳንድ ክልሎች የተገኙ መረጃዎች በዚህ የምርት ዘመን በባለሀብቶች የተያዘ መሬትም ቢሆን ስራ ላይ እስከ አልዋለ ድረስ ጦሙን እንደማያድር አስታውቀዋል።ይህም ትክክለኛ እርምጃ እንደመሆኑ ይህን ያላደረጉ ክልሎችም ካሉ ሊሰሩበት ይገባል።

እንደሚታወቀው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ለመፈናቀል ተዳርገው ነበር። ይህ ደግሞ የአርሶ አደሮቹን ህይወት በቀጥታ የተገዳደረ ከመሆኑ በተጨማሪ እንደ ሀገር የግብርና ምርት በማምረት ፣በመሰብሰብ እና በማጓጓዝ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉ ይታወሳል።

ክልሎች በየአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ከመኽር እርሻ አስቀድሞ ወደ ቀዬቸው እንዲመለሱ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሁን አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው ተመልሰዋል፡፡ መንግስትም ለእነዚህ ተፈናቃዮች አስፈላጊ የሆኑ የምርት ግብአቶችን የእርሻ መሳሪያዎችን እንደሚያቀርብ ቃል ሲገባ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ቃሉን ግብአቶችንና የግብርና መሳሪያዎችን በማቅረብ እርሶ አደሮቹን መደገፍ ይኖርበታል፡፡ ይህን በማድረግም ለሀገራዊው ምርትና ምርታማነት እድገት የሚያደርገውን ርብርብ ማጠናከር ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር ነው፡፡

ሀገራችን ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ራእይ ሰንቃ እየሰራች እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው እንድም ግብርናው ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ አቅም ሲሆን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር የግብርናው ምርትና ምርታማነት እያደገ ቢመጣም የሚጠበቅበትን ያህል ለሀገር እድገት አስተዋጽኦ እንዳላደረገ ይታወቃል።

የግብርናውን ምርትና ምርታማነት የማሳደጉ ስራ እንድም ይህን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ መንግስት በሚቀጥለው ዓመት በመስኖ እርሻ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ ይህ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነውን ግብርና ለመለወጥም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ የመኸር እርሻውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተካሄዱ ለሚገኙ ተግባሮች አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አያነሳውም የሚለውን አባባል በመያዝ ይህን የዘር ወቅት ለዘር ብቻ በማዋል መስራት ይገባል እንላለን።

አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2011