የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ያስገኛቸው፤ያጎደላቸው                                                                              

30

የብሄር ብሄረሰቦች በዓል የአገሪቱ ክልሎች በተራ መከበሩ በህዝቦች መካከል መቀራረብንና መተዋወቅን ከመፍጠር ባሻገር በተለይ በአዳጊ ክልሎች የምጣኔ ሃብት መነቃቃት እንዲመጣ እያደረገ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት ይገልጻል። የሀረሪ ባህል ፣ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አዮብ አብዱላሂ  ይህን የፌደሬሽን ምክር ቤት ሃሳብ ያጣጥሉታል፡፡

ቀኑ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር፣ የእርስ በርስ ትውውቅ መድረክ ለመፍጠርና የህዝቦችን ባህልና ወግ ለማሳደግ በሚል መሰረታዊ ዓላማ ነው። ክብረ በዓሉ የብሄርና ብሄረሰቦች መብትን ከማስከበር ባሻገር ባህላቸውን ጨምሮ አጠቃላይ ማንነታቸው እንዲታወቅ፣ አስፈላጊው ጥበቃና ክብካቤም እንዲደረግለት መልካም አጋጣሚ እየፈጠረ ያለ ክዋኔ እንደሆነ ይነገራል።በዓሉ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዙር እንዲከበር መደረጉ ደግሞ ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳንም እያመጣ መሆኑን ነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚገልፀው።

አቶ አዮብ አብዱላሂ በሀረሪ ክልል በዓሉ ሲከበር አዘጋጅ ኮሚቴ ነበሩ፡፡ በየዓመቱ የሚከበረው በአንድ አይነት መልኩ ነው፡፡የየብሄረሰቦቹ ጭፈራዎች በትርዒት መልክ ይታያል፡፡ይህ በየዓመቱ ቦታው ከመለዋወጡ በስተቀር የተለየ ነገር የለውም፡፡ እርስ በእርስ ከመተዋወቅና የአንዱን ብሄረሰብ ባህል ሌላው እንዲያውቀው ከማድረግ ውጪ የረባ ጥቅም የለውም፡፡በየዓመቱ መከበሩ ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ምክንያቱም አምናና ካችአምና የታየውን ጭፈራ ነው መልሰህ የምታየው፡፡እናም ዕለቱን ለማስታወስ ካልሆነ በስተቀር ጥቅም አለው የሚያስብል ፍሬ ነገር አልታየበትም ሲሉ ይተቻሉ፡፡

የዛሬ 13 ዓመት ያሳያነውን ጭፈራና ትርኢት አሁንም ደግመን የምናሳየው፡፡ለምሳሌ አፋሩም ጭፈራውን ያሳያል፣ አማራውም እስክስታውን  ይመታል፣ ኦሮሞውም ውዝዋዜውን ያቀርባል፣ ሁሉም የየባህሉን ጭፈራ ያቀርባል፡፡እናም ከጊዜ ወደ ጊዜ የባህል ዕድገት የለም ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በቂ ዝግጅት አድርገው ያላቸውን እሴቶች የሚያሳዩበት መድረክ ተፈጥሮ ውድድር በሚፈጥር መልኩ ቢከበር የተሻለ ይሆናል፡፡ በባህል፣በኪነ ጥበብና ስነ ቃል ረገድ ይህ ክልል የተሻለ ስራ ይዞ በመቅረቡ ቢሸለምና አድናቆትን ቢያተርፍ ፉክክር ይፈጥራል፡፡እናም አዳዲስ ነገሮች መምጣት አለባቸው፡፡

እርግጥ ነው በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድ አንዳንደድ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህ  ሂደትም ከተሞችን ለማሳመር የሚያደርጉት ጥረት አለ፡፡ይህ በበጎ መልኩ የሚታይ ቢሆንም አንዱ ክልል ስታዲየም ስለሰራ አፈላጊነቱና በክልሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ልማት መሆኑ ሳይጤን ሌላውም ስታዲየም የሚሰራበት ሁኔታ ይታያል፡፡በዚህ ምክንያትም ክልሎች በጀታቸውን ሁሉ  ለስታዲየሙ ግንባታ አውለውታል፡፡በዚህ ምክንያት ሌሎች ለህዝብ አስፈላጊ የሆኑ  ልማቶች ቆመዋል፡፡ እንዲሁም ስታዲየሞቹ ከተጀመሩ ብዙ ዓመት ቢሆናቸውም እስከ ዛሬ ድረስም ያልተጠናቀቁ አሉ፡፡ውጤት ታይቷል ከተባለም ይኸ  ነው ፡፡

ስለዚህ በተከታታይ አምስት ዓመት ከተከበረ በኋላ ቆም ብሎ ገምግሞ  በተሻለ መንገድ ለማክበር አቅጣጫ መቀየስ ነበረበት ይላሉ፡፡ስለዚህ ወደ ፊት ይበልጥ መስተጋብር፣ መቀራረብ፣ የባህልና የልማት ዕድገትን በሚያሳይ እንዲሁም ውድድር  በሚፈጥር መልኩ መከበር ይኖርበታል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

በተጨማሪም በዓሉ ህዝቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መከበር አለበት፡፡ለአብነትም በሀረሪ ክልል የተከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ያስታውሳሉ፡፡ ወጣቶችን በማደራጅት ለበዓሉ ማድመቂያ የዕደ ጥበባት ስራ እንዲሰሩ በመደረጉ ዛሬ ሚሊየነር የሆኑ ወጣቶች መኖራቸውን በማሳያነት ይጠቀሳል፡፡ ስለዚህ  በዓሉ ሲከበር ህብረተሰቡን በኢኮኖሚና በባህል ተሳትፎ በሚያደርግ በኩል ቢሆን ይመረጣል፣በዓሉም በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ይሆናል ባይ ናቸው፡፡

ሌላው ብሄር ላይ አተኩረን ለረጅም ጊዜ በመስራታችን አንድነታችን ላይ ክፍተት ፈጥሯል፡፡ በበዓሉ ላይ  ስለ አንድነታችን መሰራት አለበት፡፡

አቶ ቻላቸው ፈረጅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጥበባት ኮሌጅ መምህር ናቸው፡፡ከስድስተኛው  የብሄር ብሄረሰቦች በዓል አከባባር ጀምሮ እስካሁን ድረስ በበዓሉ  ላይ የስነ ጥበብ ውጤቶችን በማቅረብ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡በዓሉ ማህበራዊ ትስስር በመፍጠር ማለትም አንዱ የሌላውን ባህል እንዲያውቅ በማድረግ ረገድ የበኩሉ ሚና ቢኖረውም ግን የሚጠበቀውን ያህል አይደለም ይላሉ፡፡ባለፉት 12 ዓመታት በዓሉ የተለያዩ አዳዲስ ነገሮችን የትርኢቱ አካል በማድረግ ብዝሃነትን የሚያንጸባርቁ ባህሎች፣ጭፈራዎችና ትርኢቶች ታይተዋል፡፡

በመሰረተ ልማትም ረገድ እንዲሁ በዓሉ በሚከበርበት ክልሎች መሰረተ ልማቶችን በማልማት የበዓሉ ተሳታፊዎች የአገልግሎት ችግር እንዳይ ገጥማቸው አድርገዋል፡፡ጎን ለጎንም ከተማቸውን በማሳመርና ሳቢ በማድረግ ረገድ በዓሉ ጉልህ ሚና አድርጓል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ለአብነትም በዓሉ የሚከበርባቸው ከተሞች ክልሎች አዳዲስ መንገዶች፣ ስታዲየሞችና ሆቴሎችና መሰል ግንባታዎች መካሄዳቻውን ጠቅሰዋል፡፡ለምሳሌ 11ኛውን ብሄር ብሄረሰቦች በዓል ሀረር ስታከብር መሰረተ ልማት ግንባታ ሰፊ እንቅስቃሴ እንደነበር በዝግጅቱ ተመልክቻለሁ ነው የሚሉት፡፡

ሌላው ‹‹ሰብዓዊ ግንኙነቱ በራሱ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ቀደም ሲል  በብዙ መንገዶች የምንግባባውን ያህል በብዛት አንተዋወቅም ነበር፡፡ለምሳሌ የሱማሌው ሰው የደቡብን አለባበሱን፣ አመጋገቡን፣ ጭፈራውን፣ ባህሉና በአጠቃላይ ስነ ልቦናዊ እሳቤውን መረዳት ተቻችለን እንድንኖር ያደርጋል፡፡ ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም በዓሉ ይህን ለመፍጠር ታስቦ መከበሩ ብቻ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው ባይ ናቸው፡፡ባህላዊ ማንነታችንን በማስተዋወቅ ረገድም ከእኛ አልፎ በሌሎች ሀገራትም ሚና ይኖረዋል፡፡

እናም አሉ አቶ ቻላቸው እስካሁን በሚከበሩ በዓላት የጎደሉ ነገሮች ምንድን ናቸው በሚል ጥናት በማጥናት ክፍተቶችን መሙላትና አከባበሩን ማሳደግ፣ሳቢና ተወዳጅ ማድረግ ይገባል፡፡ለምሳሌ ብራዚሎች በየዓመቱ ባህላቸውን የሚያንጸባርቁበት ፌስቲቫል አላቸው፡፡ በዚህ ፌስቲቫልም ለመካፈል ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ብራዚል ያቀናሉ፡፡ይህም የቱሪስትን ፍሰት በእጅጉ እየጨመረላቸው ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያም ብሄር ብሄረሰቦችን በዓል በፌስቲቫል ደረጃ በማሳዳግ አንዱ የቱሪስት መሳቢያ ማድረግ ይቻላል፡፡ስለዚህ በዚህ ላይ አተኩረን ብንሰራ ጥሩ ውጤት የሚመጣ ይሆናል፡፡

በተለይ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸውን ባህል ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የሌላላውንም ማወቅና መልመድ ይገባል፡፡በተለይ ለብሄራዊ ማንነታችን የሰጠነው ትኩረትና ለህብረ ብሄራዊነታችን የምንሰጠው ትኩረት ሚዛኑን የጠበቀ አይደለም፡፡እናም አንዱ ለሁሉም፤ ሁሉም ለአንዱ በሚል እሳቤ ህብረብሄራዊነታችንን ማጠናከር ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሃሳብ አላቸው፡፡በዓሉም ሲከበር ጎልቶ መውጣት ያለበት ፖለቲካዊ አንድምታው ሳይሆን ባህላዊ እሴቶች መሆን አለባቸው፡፡

የብሄር ብሄረሰቦች ቀን መከበሩ  ብሄር ብሄረሰቦች  አኗኗራቸውን፣ አለባበሳቸውን፣ ጭፈራቸውንና በጥቅሉ ባህላዊ እሴቶቻቸውን አጎልተው እንዲያሳዩ አድርጓል የሚሉት የ13ኛው ብሄር ብሄረሰቦች ቀን ማስተባበሪያ ጸህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነስረዲን ማህሙድ፣ በተለይ ለታዳጊ ክልሎች ደግሞ በመሰረተ ልማት የተወዘፉ ስራዎችን ያወራረዱበት ነው፡፡ ለምሳሌ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ሆቴሎችን፣መንገዶችን፣የመሰብሰቢያ አዳራሾችን፣ባህላዊ ቅርሶች ማስቀመጫ ሙዚየሞችን መገንባት መቻላቸውን በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡እነዚህ መሰረተ ልማችን ሲታዩ በታዳጊ ክልሎች እመርታዊ ለውጥ የመጣ በዓል ነው  ሲሉ ይመሰክራሉ፡፡

እንዲሁም የብሄር ብሄረሰቦች በዓል መከበሩ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ከማጠናከር፣ትክክለኛ ገጸታ ከማንጸባረቁ፤የህብረሰተቡን እንግዳ ተቀባይነት ስሜት  አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡በተለይ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በዓሉ ተማሪዎች ባህላዊ አልባሳታቸውን ለብሰው ውዝዋዜያቸውን ለማሳየት በጉጉት እንደሚጠበቁና በሞቀ ሁኔታ እንደሚከበር አውስተዋል፡፡

ሆኖም አሉ አቶ ነስረዲን ባህላችንን በሚፈለገው መልኩ አበልጽግናል ወይ የሚል ጥያቄ ካለ መልሱ አይደለም ነው፡፡13ኛው በዓል ጋር ስንደርስ ብዙ የሚቀሩንና ብዙ የምንሰራቸው ስራዎች ይጠብቁናል፡፡ምክንያቱም በዓሉ ሲከበር ከዓመት ዓመት አጓጊና እያደገ መሄድ አለበት፡፡ሁሉም ነገር ተመሳሳይ ሆኖ የሚቀጥልበት ሁኔታ ነበር፤ይህ መቀየር አለበት ሲሉ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 29/2011

ጌትነት ምህረቴ