ግሪኮች፣ አርመኖች እና አሜሪካዊያን – በአዲስ አበባ

49

በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ግሪኮች፣ አርመኖች፣ የመኖች ፣ ህንዶች፣ ጃማይካዎች እና የሌሎችም አገራት ዜጎች  በኢኮኖሚውና ማህበራዊው መስኮች አሻራቸውን በሚገባ አሳርፈዋል። እነዚህ በኢትዮጵያውያን አጠራር “ፈረንጆቹ” እየተባሉ ሲታወቁ የኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች በግንባታ፣ በንግድ ስራ፣ በኪነ-ጥበቡ እና በተለያዩ መስኮችም ተሰማርተው ኖረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ቻይናውያን በኢትዮጵያ በመብዛታቸው ‘አንድ ብሔር ነን ውክልና ይሰጠን’ ሊሉ ይችላሉ እየተባለ ይቀለዳል። እዚህ ላይ ባለፈው አመት አንድ አዛውንት ያነሱት ሃሳብ ትዝ ይለኛል። የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ሲከበር ለ50 እና 60 ዓመት በኢትዮጵያውያን ባህል ፣ወግና እና ታሪክ ውስጥ ከማለፍ በተጨማሪ፣ ባህሉን፣ ወጉንና ታሪኩን ሲያስተላልፍ የቆየ አንድ ግሪካዊም ሆነ አርመናዊ ወይም የሌላ አገር ዜጋ ቦታ ተሰጥቶት በበዓሉ ቢሳተፍ መልካም ነው ብለው ነበር።

የዘንድሮው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ እየተከበረ ይገኛል። መዲናዋ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትሆን የመላው ዓለም ህዝብ ዜጎች መዳረሻም ናትና የውጭ ዜጎቹን ታሪክና የከተማዋን ቁርኝት እናወሳለን። ለእዚህም የግሪካውያን፣ የአርመናዊቷን እና የአሜሪካዊውን የአዲስ አበባ ቆይታ እያነሳሳን እንጨዋወታለን።  አማርኛ የሚያነቡ በርካታ የውጭ ዜጎች መኖራቸውን አውቃለሁና በቅድሚያ እንኳን ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አደረሰን መልዕክቴ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ አገር ዜጎችም ይድረስልኝ። ቋንቋውን ለማይችሉትም መልእክቴ በአስተርጓሚ ይደረሳቸው።

እዚህ ላይ አንዳንዶቹ በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የቆዩ እንደመሆናቸው  የውጭ አገር ዜጋ ሲባሉ አይወዱምና ለጽሁፉ ሲባል አርመናዊ ወይም ግሪካዊ አሊያም አሜሪካዊ እያልኩ ብጠቅሳቸው ለአንባቢ እንዲረዳው ያህል ነውና ከስህተት አይቆጠርብኝ።

በዓሉ ስለሚከበርባት አዲስ አበባ ስናነሳ ግሪካውያኑ በመዲናይቱ ታዋቂ መሆናቸው ሊረሳ አይገባም። ስለግሪኮች ሲታሰብ ባምቢስ ሱፐርማርኬት ካለው ታዋቂነት አንጻር ቀድሞ በሃሳባችን ቢመጣ አይገርምም።

በግሪክ ርዕሰ መዲና አቴንስ የተወለደው ግሪካዊ ቻራላምቦስ ትሲማስ ኤ.ኬ.ኤ. ባምቢስ ወይም ሚስተር ባምቢስ በአጎቱ ጥያቄ መሰረት በዘመነ አጼ ኃይለስላሴ ወደኢትዮጵያ ሲመጣ የ20 አመት ወጣት ነበር። አጎቱ ቀደም ብለው ከቅኝ ግዛት ነጻ ወደሆነችው የምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር በመምጣት ከአፄ ሚኒሊክ ዘመን ጀምሮ ተደላድለው ኖረዋል።

ወጣቱ ባምቢስም ወደኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ከአጎቱ ጋር ለአምስት ዓመት ተኩል ያህል ከዘመዶቹ ጋር በግሮሰሪ ንግድ ይሰማራል። ይሁንና ከግሮሰሪው ንግድ ጋር በተያያዘ በዘመዳሞች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፤ወጣቱ ባምቢስም በዚህ የተነሳ ስራውን ያጣል። ይህ ወቅት ለባምቢስ በችግር የተገረፈበት ነበር። በወቅቱ በአዲስ አበባ  ከነበሩ ጓደኞቹ ጋር እየዋለም ጊዜውን ለማሳለፍ ይገደዳል።

በወቅቱም 20 ሺ ብር የሚያበድረው ያገኛል። ገንዘቡ በወቅቱ ከፍተኛ በመሆኑ ሰንጋ ተራ አካባቢ ሰፊ መሬት ላይ የራሱን ግሮሰሪ ያቋቁማል። ስራውም እየዳበረ ገንዘብም ማግኘት ይጀምራል። የራሱን የግሮሰሪ ስራ ከጀመረ ከሁለት ዓመት በኋላም ሁለት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ገዝቶ አሁን ያለበትን ባምቢስ ሱፐርማርኬት ከፈተ።

የአሁኑ ባምቢስ አካባቢ በ1950 ዎቹ እልም ያለ ጫካ ነበር፤ ብዙም የሰዎች እንቅስቃሴ የማይታይበት እንደነበር ሚስተር ባንቢስን ያስታውሳሉ።  የሱፐርማርኬት ልምዱም ብዙም ያልዳበረ ነበርና ስራው ልፋትን መጠየቁን ሚስተር ባምቢስ ያስታውሳሉ፡፡

ሚስተር ባምቢስ ስለያኔዋ አዲስ አበባ ሁኔታ ሲገልጹ ያኔ መዲናዋ በዙም የአስፋልት ጎዳና እንዳልነበራት፣ ነገር ግን ጽዱ እንደነበረች ፣ነዋሪውም በሺዎች የሚቆጠር ብቻ እንደ ነበር ያስታውሳሉ። ይሁንና በመንገድ ላይም ሆነ በየግሮሰሪው የማይተዋወቅ ሰው ሲገናኝ ሰላምታ ይለዋወጥ እና አክብሮቱንም ይገልጽ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ነዋሪው ለግሪኮች የነበረው አክብሮት ለከተማዋ ተወላጆች ከነበረው የሚተናነስ አልነበረም። በወቅቱ  ንጉሱ አፄ ኃይለስላሴ የተለያዩ አገራት አማካሪዎች እና የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዎችን ያስጠጉ ስለነበር ኢትዮ ጵያውያን ለውጭ አገር ሰዎች እንደዘመድ ያህል ሆነው ጉርብትናቸውን አሳይተዋል።

ሚስተር ባምቢስ አሁን እድሜያቸው ወደ ዘጠናዎቹ ይጠጋል። የአንድ አዛውንት እድሜንም በኢትዮጵያ አሳልፈዋል። አልፎ አልፎ ወደዘመዶቻቸው አገር ግሪክ ብቅ ሲሉም ፣ ባለቤታቸው ግሪካዊቷ ወይዘሮ እሌኒ ቺማስ የሱፐርማርኬት ንግዱን ያቀላጥፋሉ።  በአዲስ አበባ የሰፈር ስያሜ ከመሆንም በላይ እንደ ”ብራንድ” ታዋቂ እየሆነ የሚያገለግለው ባምቢስ ሱፐርማርኬት ግሪካውያኑ ለአዲስ አበባ ያበረከቱት ስጦታ ሆኗል። ምክንያቱም የአገራቸውን የወጣትነት ዕውቀት ይዘው በኢትዮጵያ በዘርፉ መሰማራታቸው በሀገሪቱ እንደ እንጉዳይ ለበቀሉት ሱፐርማርኬቶች የገበያውን ጥርጊያ በማመቻቸት ይጠቀሳሉ።

ሚስተር ባምቢስ እና ባለቤታቸው ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በተለይም ስለአዲስ አበባ አውርተው አይጠግቡም። በአዲስ አበባ ከ60 እና 70 ዓመታት በፊት ዋነኛ የትራንስፖርት አማራጭ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ አህያዎች መሆናቸውን ያስታውሳሉ፤ በአህያ እቃ ሲጓጓዝ ሚስተር ባምቢስ እማኝ ነበሩ። አሁን በዘመናዊ ተሽከረካሪ በውብ መንገዶች ላይ ሲዘዋወሩ ያ ወቅትም ትዝ ይላቸዋል። አዲስ አበባ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ ሳይሆን ከውጭ አገራትም ለመጣ እንግዳ ጥሩ ማረፊያ መሆን የምትችል ከተማ መሆኗን በመጥቀስ ለከተማዋ ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ፡፡ አየሩን፣ የበዓል ወቅት ድባቡን፣ የስራ ቦታቸውን በአጠቃላይ የከተማዋን ሁነቶች ይወዳሉ።

“ኢትዮጵያዊ ነኝ ፤አገሬ ኩራቴ ነች” በሚለው ንግግራቸው ሚስተር ባምቢስ ይታወቃሉ። ሰውዬው በጎረቤቶቻቸው እና ሰራተኞቻቸው ሲወደሱ መስማት የተለመደ ነው። አዲስ አበቤዎችም ባምቢስ ባምቢስ እያሉ ታክሲ ሲሳፈሩ  ዕውቅናቸውን ይቸሯቸዋል።

በአንድ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ባምቢስ ሱፐርማርኬት በሚገኘው ቢሮአቸው ሄደው ሚስተር ባምቢስ እና ባለቤታቸውን ባነጋገሩበት ወቅት “እናንተ ከእኛ እንደ አንዱ ናችሁ፤ እናንተ የኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም የእናንተ ናት” ማለታቸው ይታወሳል።

አዲስ አበባ ግሪኮቹንም አቅፋ የያዘች የብሔር ብሔረሰቦች መዲና መሆኗን እዚህ ላይ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ምክንያቱም አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ብሔሮች ፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብቻ ሳትሆን “የፈረንጆቹ” መናሃሪያም ናትና።

ሌላው ግሪካዊ ደግሞ ፓና ዮቲስ ዲቫላንዲስ ይባላሉ። ግሪክኛ፣ እንግሊዝኛ ፣ ኦሮምኛንና አማርኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገራሉ። “ኢትዮጵያን ደግሞ ማናዬ” እያሉ ይጠሯታል።

እ.አ.አ. በ1951ደምቢዶሎ የተወለዱት እንግዳዬ አባታቸው ግሪካዊው ዲሚትሪ ቫሌንዲስ ይባላሉ፤ አጋም ተኩማ ጎኔ ደግሞ ኢትዮጵያዊ እናታቸው ናቸው። አባታቸው በግብጽ አርገው ነው የጎማ ዛፍ ፍለጋ ወደኢትዮጵያ የመጡት። ደምቢዶሎ ላይ የኢትዮጵያን የቡና ሃብት ሲያዩ ግን እዛው መቅረታቸውን ይናገራሉ።

ፓና ዮቲስ ዲቫላንዲስ አሁን በአትክልት ተራ ከሚገኝ ታሪካዊ ህንጻ የተወሰነውን ክፍል ከመንግስት ተከራይተው ሞተር በማደስ ይተዳደራሉ።አዲስ አበባ ከመጡ 40 ዓመት የሞላቸው ሲሆን፣ የተማሩትም በግሪክ ትምህርት ቤት ነው።

አትክልት ተራ የሚገኘው የጣሊያን ፖሊስ ጣቢያ ወይም ካዛ ዴልፋሾ /የፋሺስት ጽህፈት ቤት/ ይባል የነበረው ታሪካዊ ህንጻ ውስጥ የሚሰሩትን እኚህን ግሪካዊ፣ በብረታ ብረት እና የመዳብ ሽቦዎች በተከበበው ጠረጴዛቸው አጠገብ አገኘኋቸው።

“የግሪካውያኑ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት እንዴት ነበር?  አዲስ አበባንስ ሲያስታውሷት እንዴት ነበረች?” ብዬ ጠየኳቸው። ግሪክ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ በየወቅቱ ይከሰት ስለነበር ያንን ሽሽት ግሪካውያን ወደተለያዩ አገራት ይስደዱ እንደነበር ይላሉ። በዚህ ሳቢያ በርካታ ግሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። በተለይ ደምቢዶሎ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ግሪካውያን ነበሩ። ግሪኮች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በጨርቃጨርቅ ቆዳ እና ዘይት ፋብሪካዎች ላይ ተሰማርተው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ግሪካውያን ለኢትዮጵያ መብት የቆሙ እና ከአርበኞች ጋር የተዋጉ መሆናቸውንም በመረጃ የሚገልጹት እንግዳዬ ፣አንድ ወረቀት መዘዙ። የአገር ፍቅር ማህበር ብለው ጣሊያንን ለመከላከል ባቋቋሙት ማህበር ምክንያት በጣሊያን የጦር ፍርድ ቤት የተከሰሱ የ47 ሰዎች ስም ዝርዝር አሳዩኝ፣ ከእነዚህ መካከል ስድስቱ ግሪካውያን መሆናቸውን አመለከቱኝ። ከዝርዝሩ ውስጥ ደግሞ አባታቸው እና የቀድሞው ፕሬዚዳንት የዶክተር ነጋሶ አባት ጊዳዳ ሶሎን እንደነበሩነትም ጠቆም አደረጉኝ።

ስለአዲስ አበባ ከተማ ትዝታ ደግሞ ሲገልጹ አሁን ያሉበትን ህንጻ ራስ አደፍርሰው ይናዱ የተባሉ የአርበኞች ኃላፊ እንዳሰሩት አጫወቱኝ። የአዲስ አበባ አትክልት ንግድ የሚካሄድበት ቦታ ያኔ የአህያ ትራንስፖርት ብቻ እንደነበረው ያስታውሳሉ። ግብይቱ በ 1930ዎቹ በአነስተኛ ሰዎች አማካኝነት ይካሄድ ነበር። ይሁንና በየመንገዱ ተቆፈረው የሚተው ጉድጓዶች እና የባህል መበረዝ መጠነኛ ችግር  እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህን አስመልክቶ የታዘቡትን በሪሳ በተሰኘው የኦሮምኛ ጋዜጣ ላይ “ይግለጡ አቻምየለህ” በሚል የብዕር ስም እና በተለያዩ ስሞች አማካኝነት ጽሁፎችን ይልኩ እንደነበር አጫወቱኝ።

አሁን  ቦሌ የሚባለው አካባቢ ከ40 ዓመታት በፊት ጫካ ነበር ይላሉ። በአካባቢው ቤታቸውን እና መጋዘናቸውን ሲሰሩ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ነበሩ። በወቅቱ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ጉርብትና ትልቅ ግምት ይሰጠው ነበር። ጎረቤት የስጋ ዘመድ ያህል ቅርበት አለው። ሰው ሲያዝን አጫዋች፤ ሲደሰት የደስታ ተካፋይ የሚሆነው ጎረቤት ነው።

በሌላ በኩል የከተማዋ መንገዶች ለእግረኛ የሚመቹ እና በተለያዩ ዲዛይኖች የተዋቡ ህንጻዎች የሚታዩበት ነበር። በተለያዩ ዜጎች የተሰሩት የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ህንጻ ፣የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና የፒያሳ ጥንታዊ ህንጻዎች የከተማዋ ውበቶች ነበሩ።

ወደኢትዮጵያ በብዛት ከመጡ የውጭ አገር ዜጎች መካከል አርመናውያንም ይጠቀሳሉ። አርመናውያኑ በአዲስ አበባ ምህንድስና ኮንስትራክሽን ዘርፉ እና ሙዚቃ ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ ከጥንት ጀምሮ ወደኢትዮጵያ እንደመጡ ይገልጻል፤በተለይ በአፄ ቴዎድሮስ ፣በአጼ ዮሐንስ እና በአፄ ምኒሊክ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ በብዛት መጥተዋል። በአንደኛው የአለም ጦርነት የመጡት ግን ከሁሉም ይልቃሉ።

በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1915 የኦቶማን ቱርክ መንግስት በግዛቱ በነበሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አርመኖች ላይ ጭፍጨፋ ይፈጽማል። በዚህም የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮኖቹ ህይወት ማለፉ በተለያዩ የታሪክ ጸሃፊዎች ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ አደጋ ህይወታቸውን ለማዳን ደግሞ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አርመናውያን አገራቸውን ለቀው ለመሰደድ ይገደዳሉ። አርመኖች ተሰደው ከሄዱባቸው አገራት መካከል ደግሞ የእንግዳ ተቀባዮች አገር ኢትዮጵያ አንዷ ነች። በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ አርመኖች በግብጽ አድርገው ወደኢትዮጵያ ገብተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ልዑል አልጋወራሽ በነበሩበት ወቅት እ.አ.አ. በ1924 እየሩሳሌምን ለመጎብኘት ሲሄዱ በስደት የነበሩ 40 ወጣት አርመናውያንን በገዳም ያገኛሉ። በቦታው ከነበሩት አርመናዊ ጳጳስ ጋር ህጋዊ ስምምነት በማድረግ ልጆቹን ወደኢትዮጵያ ያመጧቸዋል። እነዚህ አርመናውያን በኢትዮጵያ እንደሃገራቸው መኖር የሚችሉበት እድል የተመቻቸላቸው ሲሆን “አርባ ልጆች”  በመባልም ይታወቃሉ።

ከነዚህ ልጆች መካከል የኢትዮጵያ ሙዚቃ እንዲሻሻል ከጣሩ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑትን ነርሲስ ናልባንዲያን ያፈራው ቤተሰብ የመጀመሪያ ትውልድ ይገኝበታል። ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ወደ ዘመናዊነት መሸጋገር ባደረጉት አስተዋፃኦ የሚታወቁት አርመናዊው ነርሲስ ናልባንዲያን የመጀመሪያው የብሔራዊ ቴያትር የሙዚቃ መምህር ናቸው። የአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ መዝሙር በአርመናዊያኑ እንደተቀናበረም ይነገርለታል።

በኢትዮጵያ ግዙፉን የጫማ ፋብሪካ የከፈተው ዳርማር፣ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘውን አረቄ ፋብሪካ ያቋቋመው ኤልያስ ፓፓሲኖስ እና አርሾ የህክምና ላቦራቶሪን የከፈቱት  በኢትዮጵያ የኖሩት ትውልደ አርመናዊን ነው።

እንዲህ እንዲህ እያለ በርካታ አርመናውያን ወደአዲስ አበባ መጥተው በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተዋል። በተለይ አርመኖች በፒያሳ እና በራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ሰፍረው ነበር። ሰባ ደረጃን እና በርካታ የከተማዋን ድልድዮችም እንደገነቡ ታሪክ አዋቂዎች ይመሰክራሉ። ራስመኮንን ድልድይ አጠገብ ያለውን ምንጭ በማጎልበት የመጠጥ ውሃ ለከተማው ህዝብ ያቀርቡ ነበር። በወቅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አርመናውያን በአካባቢው ይኖሩ እንደነበርም ይነገራል። ለዚህ ምስክር የሚሆነው አንዱ ደግሞ ከራስመኮንን ድልድይ ወደ አራት ኪሎ መንገድ 200 ሜትሮችን እንደተጓዙ የሚያገኙትና በአሁኑ ወቅት በመንግስት የተያዘው ጥንታዊ አፓርታማ ነው።

ህንጻውን ወደውስጥ ዘልቀው ሲገቡ ከመግቢያው ትይዩ ባለው ግድግዳ ላይ የበርካታ አርመናውያን ቤተሰብ ስሞች በብረት ታፔላ ላይ ተጽፎ ይገኛል። በወቅቱ በአፓርታማው ይኖሩ የነበሩ አርመናውያን ቤተሰቦች ስም ቁልጭ ብሎ አሁንም ድረስ ታሪክን ያስታውሳል። ከህንጻው አጠገብም የአርመናውያን አፖስቶሊክ ቤተክርስቲያን ይገኛል።

አሃ ሂድ ካቻዱሪያን ኤፕሬም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ አርመናውያን ወላጆቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያደጉ አዛውንት ናቸው። አባታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ በከፈቱት ሱቅ ወርቅ አንጥረው በማስጌጥ ይሸጡ ነበር። እርሳቸው እንደሚያስታውሱት በወቅቱ በርካታ አርመናውያን በወርቅ ንግድ ላይ ተሰማርተው ነበር።

በወቅቱ በአዲስ አበባ ከሁለት ሺ በላይ አርመናውያን ስለነበሩ ትምህርት ቤት ከፍተው ልጆቻቸውን ማስተማር ጀመሩ። ከሰባ ደረጃ በላይ ናዝሬት ትምህርት ቤት አካባቢ በተከፈተው የአርመኖች ትምህርት ቤት በአርመንኛ ተምረዋል። ትምህርት ቤቱን ኬ ቬርኮፍ የተባሉ አርመናዊ ናቸው የመሰረቱት።

አሁን ደግሞ እንግዳዬ አሃ ሂድ ካቻዱሪያን በኃላፊነት ይመሩታል። እንግዳዬ በአዲስ አበባ 1948 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፣ ወደ አርመኒያ ሄደው አያውቁም። አዲስ አበባ ላይ እትብታቸው ከተቀበረ በኋላ እንደ ኢትዮጵያዊ መኖርን መርጠዋል። አማርኛ እና አርመንኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ።

ስለልጅነት ትዝታቸው እና ስለወቅቱ  የአዲስ አበባ  ከተማ ሲናገሩም፤ በወቅቱ የከተማዋ ጽዳት ለኑሮ ይመች እንደነበር ያስታውሳሉ። አዲስ አበባ እንደስሟ ነበረች፤ ምክንያቱም ቆሻሻ በየቦታው አይጣልም። ነዋሪው በአገር ባህል ልብስ አጊጦ ነው የሚንቀሳቀሰው። ጥብቆ እና ሐበሻ ቀሚስ የለበሱ ጎረምሶች እና ኮረዶች በመዲናዋ ዋናዋና መንገዶች ሲመላለሱ አይን ይስቡ ነበር ይላሉ።

የጎረቤት ፍቅሩ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የቤተሰብ ያህል ስለነበር፣ ጎረቤት ልክ እንደ ቤተሰብ ይታያል። ከ50 እና 40 ዓመት በፊት በስነምግባር እና ግብረገብነታቸው ለማንም ተመልካች የሚያስመሰግኙ ልጆች በብዛት ነበሩ።

አሁን የከተማዋ ሁኔታ ውጥንቅጡ መውጣቱን የሚናገሩት አሃ ሂድ ካቻዱሪያን፤ አለባበሱ ስርዓት ማጣቱን፣ የአገር ባህል ልብሱ ለበዓል ቀናት ብቻ ካልሆነ በአዘቦት ቀን የሚያዘወትረው እንደሌለ፣ ወጉን ያልጠበቀ ልብስ በሴቱም በወንዱም በጣም መለመዱን ይናገራሉ፡፡

አየሩም እየተቀየረ ነው። ምክንያቱም ቆሻሻማ ቦታዎች በዝተዋል። ስለአዲስ አበባ ንጽህና የሚያስቡት ጥቂቶች ብቻ በመሆናቸው የብዙዎች ጤና እየተጓደለ ይገኛል። የመከባበሩ፣ የጉርብትናው በአጠቃላይ የግብረገብነቱ ወግ እየላላ በመምጣቱ የድሮው እንደሚናፍቃቸው ይናገራሉ። አዲስ አበባ የሁሉም ብሔሮች መናሃሪያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያንም መዲና ናት የሚሉት አሃ ሂድ ካቻዱሪያን፣ የዓለም ህዝቦች መቀመጫ በመሆኗ ሁሉም ንጽህናዋን ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።

አርመናውያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ባይተዋር ተደርገው እንዳልኖሩ ከራሳቸው ህይወት ጋር እያነጻጸሩ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። እንደማን ኛውም ኢትዮጵያዊ ልባቸው በፈቀደው ላይ ተሰማርተው ይኖሩ ነበር። ይሁንና ሶሻሊስታዊው ደርግ ነገሮችን መቀያየሩን ያስታውሳሉ፤ የአብዛኛውን የውጭ ዜጋ ንብረት መውረሱ በአርመናውያኑ ላይ ከባድ ጫና አሳድሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። የሰባ ደረጃው የአርመኖች ትምህርት ቤት በመወረሱ በአቅራቢያው ያለ ሌላ ቅጠረ ግቢን ለትምህርተ ቤትነት  ለመጠቀም ተገደዋል።

የአዲስ አበባም ሆነ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅርን እየለገሰ አብሮ መኖርን የሚያውቅ መሆኑን የሚናገሩት አርመናዊው፣ የብሔር ብሔረሰቦና ህዝቦች ቀን በዓል መከበሩ ብዙም አልደነቃቸውም። ትውልደ አርመናውያኑም እንደሃገራቸው በኖሩባት ኢትዮጵያ በስነጥበብ፣ በምህንድስና በኢኮኖሚና በሌሎችም የሙያ መስኮች አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

አሁን ደግሞ ወደአሜሪካውያኑ የኢትዮጵያ ወዳጅ እናቅና፡፡ -ቻርለስ ሳተን ይባላሉ። አማርኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ። ማሲንቆ በአግባቡ ይጫወታሉ። በማሲንቆ የታጀበ ሙዚቃም አላቸው። በርካታ ሰዎች ”አዝማሪው ፈረንጅ” እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ቆይተዋል።  ነጭ የአገር ባህል ልብሳቸውን ለብሰው፤ ማሲንቋቸውን እየገረፉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስከ አለም አቀፍ መድረኮች ድረስ በመገኘት ኢትዮጵያን አስተዋው ቀዋል።

አሜሪካዊው ቻርለስ ሳተን በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ነበሩ። ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ አሜሪካ በተለያዩ ዓለማት የሰላም ጓድ አባላቷን ስትልክ እግር ይቀናቸውና ወደኢትዮጵያ ይመጣሉ። ከመምህርነታ ቸው ጎን ለጎን የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ አባልም ሆኑ። ታዋቂ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሰዎች ተባብረው ማሲንቆ ሲጫወቱ የአዝማሪ ያህል እንዲጫወቱ አድርገዋቸ ዋል።

ይሁንና የእራስ ጥረት ዋናው ነገር ነውና ቻርለስ ሳተንም በሙዚቃው ገፉበት። በወቅቱ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞችም እየተዘዋወሩ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በማሲንቆ በማስተዋወቃቸው ከአፄ ኃይለስላሴ እጅ የክብር ሽልማት ተቀብለዋል።

ቻርለስ ሳተን ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ውያንን ብሎም ስለመዲናይቱ ነዋሪ አንስተው አይጠግቡም። የህዝቡን መከባበር ይወዳሉ፣ አመጋገቡን ያደንቃሉ ፤ስለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቱባ ባህል እና የሙዚቃ ችሎታ ጠቅሰው አይጨርሱም ። በአንድ ወቅት በዩቱዩብ ገጽ በተለቀቀው ምስለ ድምጻቸው እንዳሉት፤ ምንም እንኳን አሁን መኖሪያቸው በአሜሪካ ቢሆንም፣ ረጅም አመታትን ለኖሩባት አዲስ አበባ ልዩ ትዝታዎች አሏቸው፡፡ አቀላጥፈው በሚናገሩት አማርኛቸው በተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ማሲንቆ ሲገርፉ የታዘቡ ሁሉ ”አንተ ካሁን በኋላ ሐበሻ ነህ” ብለዋቸዋል። አዲስ አበባ የነጻነት አገር መሆኗን ይናገራሉ። በተለይ በባርነት የነበሩ አፍሪካውያን በተለያየ ጊዜ ወደመዲናዋ ሲመጡ ልዩ ክብር ይሰማቸው ነበር።

እንደ እርሳቸው፤ ህዝቡም እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ እንደዘመድ የሚቀርቡ ጓደኞችን ማግኘት አይከብድም። አዲስ አበባንም ከድሮው የኃይለስላሴ ቤተመንግስት እስከ አሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነህንጻ ውበት እንዲሁም እስከ ተጎሳቆሉት የጨርቆስ ሰፈሮች ታሪክ ያለት መሆኗን ይመሰክራሉ።

ከተማዋ በማርቼዲስ እየተዘዋወሩ አረንቻታ የሚጎነጩ እስከ ውስኪ የሚያንቆረቁሩ ሰዎችን አስተናግዳለች። አሁን ደግሞ ጊዜው የቢራ ሆኗል። ሱሪውም ከቫልስ ተቀይሮ ወደ ትልትል ጅንስ ዞሯል። ይሁንና የድሮውን የሚያስንቅ የለም  ይላሉ።

አዲስ አበባ ከየትም ይምጣ ከየት ተዋዶ እና ተፋቅሮ የሰው ልጅ የሚኖርባት ከተማ መሆኗን በመጥቀስም፣ ሁሌም እንሚናፍቋት ይናገራሉ። በርካታ አሜሪካውያንም ከኢትዮጵያውያን ጋር ወዳጅነት መስርተው ይኖራሉ። የቻርለስ ሳተንም የኢትዮጵያ ወዳጅነት ለአገራቱ ግንኙነት እንደአንደ ልድይ ያገለግላል።

እናም ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ ብቻ ሳትሆን የበርካታ የአለም ሀገሮች ህዝቦች መኖሪያም ስለመሆኗ እነዚህ ግሪኮች፣ አርመኖችና አሜሪካኖች ማሳያ ናቸው፡፡መልካም በዓል!!!

አዲስ ዘመን ህዳር 29/2011

ጌትነት ተስፋማርያም