በገበያና በፋይናንስ ችግር እየተፈተኑ ያሉት ህብረት ስራ ማህበራት

37

ኡርጊሳ ቶማ የበቾ ወሊሶ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ ናቸው። ዩኒየኑ የተቋቋመው በ1992 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱም 140ሺ ብር ካፒታልና 11ሺ አርሶ አደሮች አባል በማድረግ የተመሰረተ መሆኑን ያስታውሳሉ። ዩኒየኑ ትርፋማነቱን ከዓመት ወደ ዓመት እያሳደገ ሄዶ በአሁኑ ጊዜ 123 ሚሊዮን 600 ሺ ብር በላይ ካፒታል አፍርቷል። የአባል አርሶ አደሮች ቁጥርም 52ሺ600 በላይ መድረሱን ነግረውናል ።

ዩኒየኑ ለአርሶ አደሩ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል የግብርና ግብዓቶችን ያቀርባል። ከአባል አርሶ አደሮችም ምርታቸውን በመቀበል ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።በተለይ ዩኒየኑ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ከአዲስ አበባ ህብረት ስራ ሸማቾችና ከሆስፒታሎች ጋር በፈጠረው የገበያ ትስስር በቀላሉ የአርሶ አደሩን ምርት ለገበያ ያቀርባል። በዚህ አርሶ አደሩ በልፋቱ ልክ በዋጋም ተጠቃሚ የማድረግ ተግባሩን እየተወጣ ነው ይላሉ።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ሸቀጣ ሸቀጥ ፋብሪካዎች ጋር ስምምነት በማድረግ ለአርሶ አደሩ በተመጣጠኝ ዋጋ ሸቀጣ ሸቀጦችን ያቀርባል። ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በኩል በቾ ወሊሶ ላይ አንድ የማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አቋቁሟል። በተጨማሪም ሽንብራ፣ጤፍና ስንዴ ምርጥ ዘሮችን የማባዛት ስራ እየሰራ ነው።

ዩኒየኑ በዚህ ብቻ ሳይወሰን አርሶ አደሩ ወደ ዘመናዊ ግብርና እንዲሸጋገርም ስድስት ትራክተሮችን፣ 6 መውቂያ መሳሪያዎችን ገዝቶም ለአባሎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እየሰጠን ነው። በአሁኑ ጊዜም ተጨማሪ 20 የእርሻ ትራክተሮችን ለመግዛት ዕቅድ መያዙንም፤የመስኖ ልማት ለማካሄድ የጉድጓድ ውሃ ለማስቆፈር ጥናት አስጠንቶ በማጠናቀቁ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮው በመጪው ዓመት የሚጀመር መሆኑን ስራ አስኪያጁ አብራርተውልናል።

በቾ አካባቢ በስንዴ፣በጤፍና በሽንብራ የታወቀ ቢሆንም እነዚህን ምርቶች እሴት ጨምሮ ለገበያ የሚያቀርብ ፋብሪካ አለመኖሩን ያነሳሉ። ዩኒየኑም ይህን በመገንዘብ የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ትላልቅ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ቢያስብም የፋይናንስ ችግር ሊያላውሰው አለመቻሉን ነው የተናገሩት። የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ለዩኒየኖች የብድር አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም ገንዘቡ በቂ አይደለም፤ ወለዱም የተጋነነ ነው ይላሉ። ስለዚህ ዩኒየኖችንና ማህበራትን የፋይናንስ ፍላጎት በማሟላት ረገድ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ቢያደርግልን የሚል ጥያቄ አላቸው።

በምዕራብ ሀረርጌ ቡርቃ ቃልቲ ዩኒየን ሊቀመንበር አቶ አህመድ ማህመድ በበኩላቸው ደግሞ ቡርቃ ቃልቲ ዩኒየኑ ለአርሶ አደሩ በምርት ሂደት ላይ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች በማሟላትና ብድር በመስጠት ካፒታል እንዲፈጥር እያደረገ ነው። ጎን ለጎንም ለአርሶ አደሩ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጣ ሸቀጦችን በጨረታ በመግዛት ለአባላት በቅናሽ ዋጋ ያቀርባል። በተጨማሪም ምርጥ ዘሮችን በማፈላለግ የዘር ብዜት ስራ በስፋት በመስራት እያከፋፈለ እንደሚገኝም ያብራራሉ።

በምዕራብ ሀረርጌ ቡርቃ ቃልቲ ዩኒየን 41 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዳፈራ የሚናገሩት አቶ አህመድ በዓመትም አማካይ ከ6 እስከ 9 ሚሊዮን ብር ያተርፋል። ለአብነት ዘንድሮ 9ሚሊዮን ብር ማትረፉን ነግረውናል። ዩኒየኑ በሬዎችን እያደለበ ለገበያ ያቀርባል። የወተት ላሞች በመንከባከብ ለከተማ ነዋሪዎች ወተት ያቀርባል። ባላፈው ዓመትም ሶስት ቶን ቡና ለውጭ ገበያ አቅርቧል።

መንግስት የንግድ ትርኢት ማዘጋጀቱ ማህበራት ከገዥዎች ጋር ቀጥታ ግንኙነት በመፍጠር የገበያ ችግርን ለመፍታት አስችሎናል ባይ ናቸው። ሆኖም አሁንም ቢሆን የቡናና የጫት የገበያ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

አቶ ገነነ ሸረፋ ምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ወረዳ የቅሊንሶ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ ናቸው። ማህበራቸው አባላት የሚያመርቷቸውን ቡና፣በቆሎ፣ስንዴና ሌሎች ምርቶች ለገበያ ያቀርባሉ። በተመሳሳይ ደግሞ ስኳር፣ ዘይትና ሌሎች ሸቀጣሸቀጦችን ለአርሶ አደሩ በተመጣጠኝ ዋጋ ይሸጣሉ። በእነዚህና መሰል ስራዎችም 3ሺ 960 ብር ካፒታል የተመሰረተው ማህበር ከጊዜ ወደ ጊዜ ትርፉ እያደገ መጥቶ 21ሚሊዮን 700ሺ ደርሷል።

በአሁኑ ጊዜ ማህበሩ ሶስት መኪና ፣ሁለት የቡና መፈልፍያ ማሽኖችና ያሉት ሲሆን በቡሌ ሆራ ከተማ ባለ አራት ፎቅ ህንጻ ግንባታ ሊያካሂድ ማቀዱን ገልጸውልናል። የገበሬውን ምርት እሴት ጨምሮ ገበያ ለማቅረብም ዕቅድ ይዘዋል።

በተለይ ለገበያ የምናቀርበው ቡና በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት የታጠበ ቡና አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ቡና ማቅረባቸውን ያወሳሉ። ዘንድሮም አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ያቀረቡ መሆናቸው ጠቅሰዋል። ሆኖም የገበያ ችግር በመኖሩ ገበሬው በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ አልሆነም። ለአብነትም ቀይ ቡናን ከገበሬዎች በ10ና በ15 ብር እንደሚረከቡ ገልጸውልናል። ለገበያ የሚቀርበው የቡና ምርት እየጨመረ ቢመጣም ዋጋው ግን ብዙም ለውጥ አላሳየም።ይህ ደግሞ የገበያ ችግር እየፈጠረው ነው የሚል ሃሳብ አላቸው።

ቀደም ሲል ሀዋሳ ወስደን ነበር የምንሸጠው የሚሉት አቶ ገነነ፣ በምዕራብ ጉጂ ቡሌ ሆራ ከተማ የምርት ገበያ ቢኖርም የገበያና ተመጣጠኝ ዋጋ የማግኘት ችግር አለ። በዚህ ምክንያትም አምራቹ እየተጎዳ መሆኑን በመግለጽ መንግስት ድጋፍ ቢያደርግ የሚል አስተያየት አላቸው።

የኦሮሚያ ህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ የህብረት ስራ ማህበራትን የገበያ ችግር ለመፍታት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የንግድ ትርኢት ያዘጋጃል።ይህም ገዥውና አምራቹ ቋሚ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ያስችላል። ገበያን ከማረጋጋት አኳያም የራሱ አስተዋጽኦ አለው። በዘላቂነትም የህብረት ስራ ማህበራት የገበያ ችግራቸውን ለመፍታት በየከተሞች ትልልቅ የገበያ ማዕከል እንዲያቋቁሙ ድጋፍ እያደረግን ነው የሚሉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ለዚህ የሚቀርብ የመሬት ይሰጠን ጥያቄ ለመመለስ ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ነግረውናል።

የፋይናስ አቅርቦቱን በተመለከተ ገንዘብ እስከ ገጠር ማዕከላት ድረስ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራን ነው።አሁን ግን የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ያለምንም ተያዥ ለዩኒየኖችና ለህብረት ስራ ማህበራት ብድር እየሰጠ ይገኛል።ይህም ቢሆን ማህበራቱ እሴት የሚጨምሩ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ በቂ ሆኖ አልተገኘም ።ወለዱም ከፍተኛ ነው።

የህብረት ስራ ባንኮች በንግድ ህጉ ስለሚተዳደሩ 17 በመቶ ነው ወለድ እያስከፈሉ ያሉት ።ይህ ለህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች ከፍተኛ የወለድ መጠን ነው። ስለዚህ የፖሊሲም ችግር ስላለ መንግስት አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ግፊት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ነው ያወሱት።

ዛሬ የብልጽግና ጣሪያ ላይ ለደረሱት አገራት የህብረት ስራ ማህበራት ለዕድገታቸው መፋጠን ጉልህ ሚና እንደተጫወቱ ይነገራል። ያደጉት አገራትም ለኢኮኖሚያቸው ዕድገት የተለያዩ የህበረት ስራ ማህበራት ፋብሪካዎችን በማቋቋም የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየርና ዕድገታቸው በማፋጠን ረገድ እንደ ሞተር የተጠቀሙባቸው መሆኑን ታሪክ ይመሰክራል።

የህብረት ስራ ማህበራት በግለሰብ ደረጃ በቀላሉ የማይገኙትን ካፒታልን፣ ዕውቀትንና ቴክኖሎጂን በማሰባሰብና በማቀናጀት ትላልቅ፣ ተፅእኖ ፈጣሪና ትርፋማ የሆኑ ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ አይነተኛ መሳሪያ ናቸው።

እነዚህ ማህበራት ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቁ ኢንቨስትመንቶችን ለማ ካሄድ፣ የዜጎች የቁጠባ ባህል ለማጎልበት፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲፈጠርና ገበ ያን በማረጋጋት፣ ምርታምነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው። እንዲሁም የማህበራቱን አባላት ጥቅም ከፍ ለማድረግና የአገርን ልማት በማፋጠን አይነተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ከሶስቱ ዩኒየኖች መረዳት ይቻላል። እናም በመንግስት በኩል የሚታይባቸውን ክፍተቶች በመለየት ተገቢው ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋቸዋል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2011

 ጌትነት ምህረቴ