ደፋር፣ ጀግናና ታማኝ ታጋይ

48

 አቶ እዘዝ ዋሴ ከአባታቸው ዋሴ መንግስቱ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ የውብዳር ቢወጣ በ1957 ዓ.ም በቀድሞ ጎንደር ክፍለ ሃገር በደብረታቦር አውራጃ ፤በአሁኑ ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ በስኳ በርጉት ቀበሌ ተወለዱ ።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በተወለዱበት አካባቢ የቅዳሜ ገበያ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፤የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመካነ እየሱስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

አቶ እዘዝ ዋሴ የመደበኛ ትምህርታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት በወቅቱ የነበረውን የደርግ አገዛዝ በመቃወም ትምህርታቸውን አቋርጠው ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ ከመሰል ጓደኞቻቸው ጋር ህዝባዊ ትግሉን ዳር እንዲደርስ የበኩላቸውን አበርክተዋል፡፡ በሽግግሩ ወቅት በክፍለ ህዝብነት በሰሩበት በእስቴ ወረዳ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነትና በታማኝነት በመወጣት በወቅቱ ደፍርሶ የነበረውን የአካባቢውን ሰላም በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

የሃገራችን ሰላም ተረጋግቶ መደበኛውን ሥራ መስራት ሲጀመር ከዚህ በፊት አቋርጠውት የነበረውን ትምህርታቸውን በመቀጠል እስከ ማስትሬት ዲግሪ በመማር የእውቀት ድረስ ትምህርታቸውን በመከታተል የእውቀት አድማሳቸውን አስፍተዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንትና የማስተርስ ዲግሪያቸውን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አጥንተው ተመርቀዋል።

አቶ እዘዝ በደቡብ ጎንደር አስተዳደር እስቴ ወረዳ በልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው፤ በነበራቸው የህዝብ ተቀባይነት ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም የእስቴ ወረዳን ህዝብ ወክለው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በአባልነት አገልግለዋል።አቶ እዘዝ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ቀን ከለሊት የሚተጉ፤ ችግር ነው ብለው ያመኑበትን ነገር ያለምንም ፍርሃት ፊት ለፊት የሚታገሉ የቁርጥ ቀን ከአማራ ህዝብ አብራክ የወጡ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ከምርጫ 2002 ማግስት የክልሉን ህዝብና አካባቢውን ለማገልገል በነበራቸው ቁርጠኝነት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመልሰው ከ2003 ዓ.ም እስከ 04 ዓ.ም የደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን የብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል ።ከ2004 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል። በዚህ ወቅት የዞኑን ህዝብ የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራቸው ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተለይ መላ የዞኑን ህዝብ በማነቃነቅ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ፤የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራና በሌሎች ስራዎች የዞኑ አፈጻጸም እየተሻለና ዞኑን ተሸላሚ በማድረግ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ የቻሉ የህዝብ ልጅ ናቸው ።

አቶ እዘዝ ዋሴ ደፋርና ጀግና ነበሩ ።ታማኝ ታጋይም ነበሩ ።ለአላማቸው ጽኑ ታጋይ ነበሩ ።የትግል ጓደኞቻቸውን መቼም የማይረሱ ከወደቁበት ፈልገው የሚያነሱ የዓላማ ሰው ነበሩ ለሚያምኑበት አላማ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ቆራጥ የህዝብ ልጅ ነበሩ። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደርና አጋጥሞ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላም ለመመለስ የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ወደ አካባቢው በመሄድ

 ተልኳቸውን ከሥራ ባልደረባቸው ከገነቡት ከአቶ ምግባሩ ከበደ ጋር በመሆን በብቃት የተወጡና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ አክብሮት የተቸራቸው እንቁ ሰው ነበሩ ።

አቶ እዘዝ አሁን በክልላችንና በሃገራችን ለታየው ለውጥ ከትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ፊት ለፊት የሚሰማቸውን በአደባባይ የታገሉ ፤ለውጡ መሬት እንዲነካ በየመሃሉ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች መልክ እንዲይዙ ከትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ታግለዋል። ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ በኃላፊነት በታማኝነት፣በቆራጥነትና በጀግንነት መርተዋል ።መሪ ድርጅቱ አዴፓ ታሪካዊ የሆነውን የ12 ኛውን መደበኛ ጉባዔ ካካሄደ በኋላ የአዴፓን ማዕከላዊ ጽህፈት ቤትን በጠንካራና በቁርጠኛ የአማራ ልጆች እንዲመራ በማሰብ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም ጀምሮ መስዋዕትነት እስከ ከፈሉበት ድረስ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት አማካሪ በመሆን በተለመደው ህዝባዊ ባህሪያቸው ለአማራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም መረጋገጥ ታግለዋል።

አቶ እዘዝ ዋሴ ለስራቸው እጅግ ታታሪ ከመሆናቸው የተነሳ ሙሉ ጊዜያቸውን ለስራ የሚያውሉ በመሆኑ ጠዋት ለስራ ሲወጡ የተኙ ልጆቻቸው ማታ ከስራ አምሽተው ሲመለሱ ተኝተው ስለሚያገኟቸው ለልጆቻቸው ራሱ ሙሉ ጊዜ ሳይሰጡ መስዋዕት የሆኑ አባት ነበሩ። አቶ እዘዝ በአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተመድበው በክልሉና በሃገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ያለምንም እረፍት ሌት ተቀን እየሰሩ ባሉበት በክልሉና በሃገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ባሉበት የክልሉን መንግሥት በሃይል ለማስወገድ ፣ክልሉንና የሃገራችንን ኢትዮጵያ የከፋ አደጋ ለመጣል ታስቦ የተቀነባበረውና ተሞክሮ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በክልሉ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የመስተዳድሩ ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስብሰባ ላይ በነበሩበት በተደረገ ጥቃት ከሌሎች ሁለት ባልደረቦቻቸው ከዶክተር አምባቸው መኮንንና አቶ ምግባሩ ከበደ ጋር በጥይት ተመትተው በ48 ዓመታቸው ተሰውተዋል። አቶ እዘዝ ዋሴ ባለትዳርና የሁለት ሴቶችና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።

አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011