ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በባሕርዳርና በአዲስ አበባ በግፍ የተገደሉትን ከፍተኛ አመራሮች በተመለከተ ያስተላለፉት የኅዘን መግለጫ

65

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች

በቅድሚያና ከሁሉም በፊት በባሕርዳር እና በአዲስ አበባ በሀገራችን ከፍተኛ የጦርና የሲቪል አመራሮች ላይ በተፈፀመው ሕገ ወጥና ዘግናኝ ፋሺስታዊ ግድያ የተሰማኝን ጥልቅ እና ልባዊ ኅዘን በራሴና በኢፌዴሪ መንግሥት ስም እየገለጽኩ ለሟቾች መንግሥተ ሰማያትን፣ለቤተሰቦች እና ለወዳጅ ዘመድ መጽናናትን፣ለመላው የትግል ጓዶችና ለሥራ ባልደረቦች ደግሞ ብርታትን እመኛለሁ፡፡

አንድ ዓመትን ባስቆጠረው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞና የመደመር ጎዳና ላይ እያለን በጓዶቻችን ላይ የተፈጸመውን ልብ ሰባሪ ጥቃትና ሀገራችንን የገጠማትን ብርቱ ፈተና ስናስብ ልባችን በከፍተኛ ኅዘን የሚደማው ያለምክንያት አይደለም፡፡ እነዚህ ሰማዕታት እንደ አለት የጸኑ፣ እንደ አልማዝ የጠነከሩ፣ ሀገራቸውን ከምንም ነገር በላይ የማገልገል ዓላማን ያነገቡ፣ ዓላማቸውን ሳያሳኩ አንገታቸውን ላለማዞር የቆረጡ፣ ይህንንም በተግባር ያረጋገጡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ነበሩ፡፡

ከዚያ በላይ ልብን የሚያደማው እነዚህ ሰማዕታት የለውጡ የምስራች ገብቷቸው፣ የሚገኘውን ሀገራዊ ዋጋ ተረድተው ሌሎቻችንን ሁሉ እነርሱ ወደታያቸው ራእይ ሊወስዱን አቅሙ የነበራቸው ግንባር ቀደም የለውጡ ተፋላሚዎች መሆናቸውን ስናስብ ነው፡፡ ነገሩ ከምንገምተው ጊዜ የቀደመ፣ ከምናስበውም ውጭ ልብ የሚያደማ ሆነብን እንጂ ሀገርን አንድ ማድረግ፣ ሕዝብንም በሰላምና በዴሞክራሲ ጎዳና መውሰድ ከባድ መስዋዕትነትን እንደሚጠይቅ ተረድተነው ነበር፡፡ ትግሉ ከሰውነት በታች ከወረዱ፣ ከሥልጣን ውጭ ሌላ ከማይታያቸው፣ ከመግደል ውጭ ሌላ ዕውቀት ካልዞረባቸው፣ ከጉልበት ሌላ መፍትሔ ያለ ከማይመስላቸው፣ ከግል ጥቅም ባሻገር ለማየት ከማይችሉ ጋር እንደሚደረግ ተረድተነው ነበር፡፡ ይህን እኛም ጠላቶቻችንም እናውቃለን፡፡

ታላቂቱን ሀገር ማሳነስ፣ የከበረውም ሕዝብ ማዋረድ፣ ለግስጋሴያችን ልጓም፣ ለመንገዳችን እንቅፋት ማኖር ሙያ የሚመስላቸው እዚህም እዚያም አሉ፡፡ ከዴሞክራሲ ሕዝብ ያተርፋል፤ እነርሱ ግን ይከስራሉ፤ ከሥልጣኔ ሕዝብ ይጠቀማል፤ እነርሱ ግን ይጎዳሉ፤ ከኅብረ ብሔራዊነት ሀገር ይበለጽጋል፤ እነርሱ ግን ይደኸያሉ፤ በፍቅርና በይቅርታ ኢትዮጵያ ትታከማለች፤ እነርሱ ግን ይታመማሉ፡፡ ይህ ነው የጠላቶቻችን ትልቁ መለያቸው፡፡

ለሕዝብና ለሀገር ለመሥራት የሚችል ብርቱ ልብ፣ ሰብአዊ አንጀት፣ ጠንካራ ክንድ፣ አርቆ አሳቢ አእምሮ፣ አመዛዛኝ ኅሊና፣ ጠቢብ ልቦና የላቸውም፡፡ አርበኝነታቸው ለአሉባልታና ለሐሜት፣ ጀግነታቸው ለሤራና ለነገር፣ ጉብዝናቸው ለተንኮልና ለጭካኔ ነው፡፡ በአእምሯቸው ካለው ሃሳብ ይልቅ በወገባቸው ያለው ዝናር፣ በልባቸው ካለው ጥበብ ይልቅ በእጃቸው ያለው ሽጉጥ የሁሉም ነገር መፍትሔ ይመስላቸዋል፡፡

ሐሳቡን ማሸነፍ ሲያቅታቸው፣ አሳቢን ለማጥፋት ተነሱ፤ አእምሮ ሲጎድላቸው ባለ አእምሮውን ለማጨናገፍ ቆረጡ፤ ጥበብ ሲሰፋባቸው ጠቢባኑን ለማስወገድ ፈጠኑ፡፡ ሀገር ወደ ዘመነ አብርሆት ስትጓዝ እነርሱ ተቃራኒውን መረጡ፡፡ በፈጣሪም ሆነ በሰው ዘንድ የተጠላውን የጥፋትን መንገድ ተከተሉ፡፡

ዓላማቸው ሦስት ነገሮችን ማስከተል መሆኑ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ በአንድ በኩል የለውጡን ሐዋርያት በመግደል ለውጡን ማስቆም፤ በሌላ በኩል ሕዝባችንን በተሳሳተ ምስል እርስ በርሱ እንዳይተማመንና እንዲጠራጠር ማድረግ፤ በሦስተኛ ደረጃም የፀጥታ አካሎቻችንን ሞራልና ክብር በመንካትና አንድነቱን በጎጥ በመከፋፈል ሀገርን ለአደጋ ማጋለጥ ነበር፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ለቅዥታቸውና ለእኩይ ተግባራቸው አሳልፎ አልሰጠንም፡፡ ወደፊትም አይሰጠንም፡፡

እነዚያን ጀግኖች እንዲህ በቀላሉ ማጣት እንደ እግር እሳት ይለበልባል፤ እንደ ጎን ውጋት ያስቃስታል፡፡ ኢትዮጵያ እነርሱን ለማግኘት ስንት ደክማለች፤ ስንት ተስላለች፤ ስንት ወጥታ ወርዳለች፤ ይህን በማይረዱ የገዛ ልጆቿ ልጆቿን አጥታለች፡፡ በሀገር እየኖሩ፤ በሀገር እየከበሩ ሀገር በማይገባቸው የልጅ ደመኞች ውድ ልጆቿን ተቀምታለች፡፡ ያን መሰል ሀገርን የካደ ሠንካላ ክፉ ምኞት ሲጀመርም የከሸፈና የተሸነፈ አስተሳሰብ በመሆኑ ሕዝባችን በተለመደ ሀገር ወዳድነትና በፅኑ የአርበኝነት መንፈስ በእንጭጩ አምክኖታል፡፡ በአገሩና በወገኖቹ ጥቃት የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአባቶቹ እንደለመደው ከሀገሩ ልጆችና ከጀግኖቹ ጋር በአንድነት በመቆም ክፉውን ሴራ አክሽፎታል፡፡

በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ፖለቲከኞቻችን በአብሮነትና በጽናት በመቆም ኢትዮጵያዊነት እንደ ጥሬ ወርቅ ተፈትኖ እንደ ጥሩ ወርቅ ነጥሮ እንደሚወጣ ዳግም ለዓለም አረጋግጠዋል፡፡ ክልሎች በጋራ በመቆም በትብብርና በመደጋገፍ የመኖርን ፋይዳ አልቀው አሳይተዋል፡፡ ጀግኖው የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፖሊሲ ኃይላችን እና የፀጥታ አካሎቻችን እዝና ተዋረዳቸውን በላቀ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ጠብቀው ተልዕኳቸውን በከፍተኛ ደረጃ በመወጣት አኩሪ ገድል በመፈፀም ዛሬም እንደ ትናንቱ እንድንኮራና እንድንመካባቸው አድርገዋል፡፡ በዚህም የተሰማኝን ክብርና ለእነርሱም ያለኝን አድናቆት እየገለጽኩ በዚሁ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በቀጣይነት ይወጡ ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

የከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች

ሀገር በተስፋና በደስታ ዘመናት ብቻ ሳይሆን በመከራና በችግር ዘመናትም ውስጥ እንደምታልፍ ከታሪክ ብቻ ሳይሆን ከመኖርም የምንረዳው ሐቅ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሃሳበ ስንኩላን ሲነገራቸው ባይሰሙም፤ ሲመከሩ ባያደምጡም፤ ምሕረትና ይቅርታ ባይገባቸውም፤ የሀገራችን ጠላቶች ደግመው ደጋግመው መገንዘብ የሚኖርባቸው አንድ ዘለዓለማዊ እውነት አለ፡፡ ሀገራችን አእላፋት አዝማናትን አልፋ አሁን ከምትገኝበት ታሪክ ምዕራፍ የደረሰችው ጉዞዋ በፀጥታና በሰላም ውስጥ ብቻ ስለነበር አይደለም፤ ጨለማውን እየገለጠች፤ ጉድባውን እየተሻገረች፤ ማዕበሉን እያለፈች፤ አቀበቱን እየዳኸች በእሳትና በአውሎ ነፋስ መካከል እየሰነጠቀች በመጓዝ ጭምር ነው፡፡

በየዘመናቱ እኩያን እየተነሱ ከመንገዷ ሊገቷት፣ ከግሥጋሤዋ ሊመልሷት፣ ከክብሯ ሊያወርዷት ሲዳዳቸውና ሲውተረተሩ ዝም ብላ ተቀብላ አታውቅም፡፡ እንደገና እየተነሣች፣ እንደገናም እየገሠገሰች፣ እንደገናም ወደ ገናናነቷና ወደ ክብሯ እየተመለሰች ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ እናቶቻችንና አባቶቻችን ትተውልን ያለፉት ቅርሶች ይህንን ሃቅ ደጋግመው ይነግሩናል፡፡ ቀጥና የማትበጠስ፣ ተዳፍና እሳቷ የማይጠፋ፣ ተናግታ የማትፈርስ፣ ተናውጣ ሥሯ የማይበጠስ ሀገር ናት ኢትዮጵያ፡ ሕግ አክባሪ ዜጎቻችን ደግመው ደጋግመው በተለያዩ መድረኮች የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ሲመክሩ በጥሞና አድምጠናል፡ ፡

መግደል መሸነፍ ነው ስንል የሐሳብና የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት በሉዓላዊ ሐሳብ እንጂ በጥይት እንደማይሸነፍ በመረዳታችን ነበር፡፡ መግደል መሸነፍ ነው እንደ እነርሱ የፀብ ብረት መወልወልና ባሩድ መቀመም ስለማንችልበት አይደለም፡፡ ታላቁ ጀግንነት ፍቅርና ይቅርታ፣ እርቅና ሰላም ስለሆነ እንጂ፡ ፡ መግደልና መገዳደል፣ ጦርነትና ግጭት ምን ዓይነት መቀመቅ ውስጥ ሀገርን እንደሚከት ከኢትዮጵያውያን በላይ የሚረዳው የለም ብለን ስለምናምን ነው፡፡ ውረድ እንውረድ፣ ግደል ተጋደል የት እንዳደረሰን ከእኛ በላይ ምስክር ስለሌለ ነው፡፡

በተመሳሳይ መንገድ እየሄድን የተለየ ውጤት አናመጣም ብለን አመንን፡ ፡ ከመግደልና ከመጨፍጨፍ፣ ከማሠርና ከማሳደድ የተለየ መንገድ እንከተል ብለን ወሰንን፡፡ አግላይና ዝግ የነበረውን የፖለቲካ ምኅዳር አፋን፤ ክፍትና እካታች በማድረግ፣ አቃፊና ደጋፊነቱን ለማረጋገጥ ጥረት አደረግን፡፡ የወኀኒ በሮቻችን ተከፍተው አእላፍ እሥረኞች የነጻነትን አየር ተነፈሱ፤ በሀገር ቤትና በዳያስፖራ መካከል ያለው ድልድይ ሠርተን ሺዎች ወደ ሀገራቸው ገቡ፤ ብረት አንግበው የትጥቅ ትግል ያካሂዱ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ ሀገር ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ተቀላቀሉ፡፡

አንዳንዶቹን ረጅም ምዕራፍ ተጉዘን ከጎናችን ተሰልፈው አብረውን እንዲሰሩ ስንፈቅድ ዴሞክራሲን አምጦ መውለድ ብቻን እንደማይበቃ አምነን ነው፡፡ ጽንሰን ማዋለድ ብቻ ሳይሆን በልበ ሰፊነትና በክብካቤ ሙሉዕ እንዲሆንና እንዲጎለብት ማድረግ ታላቅ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ኃይል፤ ጉልበትና ጭካኔ ለፈጻሚው ቀላል ነው፡፡ ለሚፈጸምበት ግን ያማል፡፡ ትዕግሥት፤ ሆደ ሰፊነትና ሁሉን ቻይነት ደግሞ ከማንም በላይ አድራጊውን ያመዋል፡፡ እኛም የመረጥነው ሁለተኛውን ነበር፡፡ ትዕግሥታችንና ሆደሰፊነታችን ብዙ ትችትና ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ጫናም እንድናስተናግድ አድርጎን ነበር፡፡

አዲስ መንገድ አዲስ ፈተና ያመጣል፡፡ በምክንያት የማይመሩት የሥልጣን ጥመኞች ይህ ስለማይገባቸው በጀብደኛና በእብሪተኛ እርምጃ የጥፋት ሰይፋቸውን በጠራራ ፀሐይ፣ በአደባባይ መዘው የደማቅ ጌጦቻችንን ውድና ክቡር ሕይወት ቀጥፈዋል፡፡

የለውጥ እርምጃችን ኢትዮጵያን አዲሲቱ የተስፋ አድማስ፣ የአፍሪካ ፈርጥና ተምሳሌት ማድረግ እንጂ ኢትዮጵያን የኀዘን ማቅ ማልበስ አይደለም፡፡ ሀገርን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር እስከተረዳን ድረስ እየመረረንም ቢሆን የምንቀበለው ሐሳብ ይኖራል፡፡ በሀገር አንድነት፣ሉዓላዊነት፣ዘላቂ ጥቅምና ክብር ላይ ግን ድርድርም ሆነ ትዕግሥት ፈጽሞ አይኖረንም፡፡ ከኢትዮጵያ የሚበልጥ፣ ከሕዝባችን የሚቀድም ምንም ነገር የለም፡ ፡ ለዴሞክራሲና ለሰላም ስንል እንታገሳለን፤ ለሀገርና ለሕዝብ ስንል ደግሞ መራር ውሳኔን እንወስናለን፡፡

እያለቀስን ብንቀጥል የጓዶቻችንን ዓላማ አናሳካም፤ ተስፋ ብንቆርጥ የጓዶቻችንን ስንደቅ ከፍ አናደርገውም፡፡ ለምን እንዲህ ሆነ? ድክመታችን ምን ነበር? ምንስ ማድረግ ነበረብን? የሚሉትን በትክክለኛ ጥናት እንለያለን፡፡ ካጋጠመን ፈተና እንማራለን፤ እንዳይደገም አድርገን የሕገ-ወጥነት ቢሮችን ሁሉ እንዘጋለን፡፡ ለአፍታም ግን ከጉዟችን አንገታም፡፡ ከዓላማችንም አንዛነፍም፡፡ መንገዳችንንም አንቀይርም፡፡

በመጨረሻም በፈተናችን ወቅት ከጎናችን በመቆም ድጋፋችሁና ማጽናናታችሁ ላልተለየን ወዳጅ ሀገራት በራሴና በኢፌዴሪ መንግሥት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ለመከላከያ ሠራዊታችን፣ ለማቾች የሥራ አጋሮችና ለሟች ቤተሰቦች ፈጣሪ መፅናናትን እንዲሰጥ እመኛለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ሀገራችንን ይባርክ!

አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2011