የአየር ንብረት ለውጥ ትንበያና ትግበራው

271

ከአየር ጠባይ፣ ከአየር ሁኔታ ለውጥና ሌሎች ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን አስቀድሞ ከማወቅና ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የአየር ንብረት ለውጥ ትንበያና ትግበራ ስራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በተለይም ድርቅ፣ የአፈር እርጥበት እጥ ረትና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የእርሻ ምርታማነትን በመቀነስ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ ረሀብና እርዛትን ከማስከተሉ በፊት መፍትሄ እንድናፈላልግ፤ በጎርፍ እና በንፋስ አደጋዎች የሚወድመውን ሀብትና ንብረት አስቀድመን መታደግ እንድንችል፤ የአፈር ጤንነትን በማሻሻል፣ አካባቢን በመጠበቅና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንዲቻል ከማድረግ አኳያ የአየር ለውጥ ትንበያና ትግበራ ያለው ፋይዳ ቀላል አይደለም።

በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የከፋ ችግር እንዳይከሰት፣ አሳሳቢውን የምድር ሙቀት ለመቀነስ የሚቻልበትን ዘዴ ለማመንጨት ማስቻሉ፤ ምድራችን የምትተማመንባቸው የተፈጥሮ ሃብቶቿ ወድመው ለኑሮ አስቸጋሪ ወደሆነ መልክአ ምድርነት እንዳትቀየር ከማድረግ አኳያ የአየር ንብረት ለውጥ ትንበያና ትግበራ በአሁኑ ጊዜ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስለ አየር ለውጥ፣ አየር ጠባይ፣ ከባቢ አየር ብክለትና የመሳሰሉት አብዝተን እንድንጨነቅ ያደርገናል። ከሁሉም በላይ የአየር ትንበያንና ትግበራን ጉዳይ ቅድሚያ እንድንሰጠው አበክሮ ያሳስበናል።

ከላይ በጠቀስናቸው ዋና ዋና ምክንያቶች የአየር ንብረት ለውጥ የወቅቱ አለም አቀፍ ተግዳሮትና ስጋት ከሆነ ቆይቷል። በመሆኑም ከአካባቢ እንክብካቤ እስከ የአየር ለውጥ ትንበያና ትግበራ ድረስ ያላቋረጠና የተቀናጀ ተግባርን ይጠይቃል። በተለይ ወቅቱ የክረምት መግቢያ፣ በግብርናው ዘርፍ ደግሞ ወሳኝ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ተግባሩ በምንም መንገድ ቸልታን አይጋብዝም። ሁኔታዎችን በቅርብ መከታተል፣ ከነሱ ተነስቶም መተንበይ፣ የተተነበየውንም ለሚመለከታቸው አካላት ባስቸኳይ ማስታወቅና ወደ ተግባር መለወጥን ግድ ይላል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያስ ምን እያደረገች ነው? የሚለው የዚህ ፅሁፍ ማእከላዊ ጭብጥ ነው።

የአካባቢ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት መንግሥቱ ውቤ በዚሁ ዙሪያ ባደረጉት ጥናት “የአየር ንብረት ለውጥ (Climate Change) የዓለም ሁሉ ችግር ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ግን የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ ፈተና እንደሚገጥማቸው አመላክተዋል።” ይህ ከሆነ፤ በአገራችን ያሉ የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማእከላትና ባለድርሻዎቻቸው ምን እያደረጉ ነው የሚለውን መመልከት ተገቢ ይሆናል።

ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ትንበያና ትግበራ ጋር በተያያዘ መዲናችን አዲስ አበባ ሰሞኑን አንድ ትልቅ ክፍለ-አህጉራዊ መድረክን አካሂዳ ነበር። ይህ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከምስራቅ የልማት በይነ-መንግስታት የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማእከል (ICPAC) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ፎረም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን የመጪዎቹን ወራት (ሀምሌ፣ ነሀሴ እና መስከረም) የአየር ጠባይ በመተንበይ፣ መተንተንና ተግባራዊ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በጉባኤው በቀንዱ አገራት የቀረበውን ምክረ-ሀሳብ ተቀብለው ወደ ተግባር እንዲገቡና አካባቢያቸውንም የአየር ጠባይ ለውጥ ከሚያመጣው ጉዳት እንዲታደጉ ተመክሯል።

ምክክሩም ለምስራቅ አፍሪካ አገራት እጅግ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ በግብርናው ዘርፍ፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከማሳካት አኳያ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ ተረድተው እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ የጋራ ስምምነት ላይ ከመደረሱም ባሻገር ለተግባራዊነቱም መፍጠን እንደሚገባ ተነግሯል።

ይህንኑ አስመልክቶ አዲስ ዘመን ከብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም ጋር ቆይታ አድርጓል። ቆይታውም በተለይ ከመተንበይ፣ ለመተ ግበር የሚያስችለውን ፈጣን መረጃን ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ ከማ ድረግና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ከማስቀረት አኳያ ስላለው ወቅታዊ የአየር ንብረት ሁኔታ፤ በተለይም የመስሪያ ቤታቸው ተልእኮ “የሚቲዎሮሎጂ እና መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀት፣ በመተንተን፣ የአየር ሁኔታ፣ የአየር ጠባይ፣ የአየር ጠባይ ለውጥና የከባቢ አየር ብክለትን በመከታተል እና በመተንበይ አገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖ ሚያዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ለህይወትና ንብረት ከአደጋ መጠበቅ እገዛ የሚያደርግ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት መስጠት።” ላይ ያተኮረ ነው።

አቶ አህመዲን እንደሚሉት በአሁኑ ሰአት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ስለሚስተዋለው የአየር ሁኔታ፣ የአየር ጠባይ ለውጥ፣ የዝናብ መጠን እና ተያያዥ ጉዳዮች፤ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በአርሶ አደሩ፣ ከፊል አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ አካባቢ በሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን አውታሮች አማካኝነት አስፈላጊው መረጃ ሁሉ እንዲ ደርስ ተደርጓል።

“የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በአየር ትንበያ የሰላሳ አመት የዳበረ ልምድ ያለው ተቋም ነው” የሚሉት የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ኤጀንሲው 52ኛው የምስራቅ አፍሪካ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንተናና ትንበያ ፎረም ከመካሄዱና የመረጃ ልውውጥ ከመደረጉ በፊት መረጃ እንዳሰባሰቡና ለሚመለከታቸው አካላት እንዳሰራጩ ተናግረዋል።

አቶ አህመዲን እንደተናገሩት ምንም እንኳን የምስራቅ የልማት በይነ-መንግስታት የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማእከል የምስራቅ አፍሪካን የአየር ለውጥ ሁኔታ እንደ አጠቃላይ ቢያይም መረጃን የማደራጀት፣ መተንበይ፣ መተንተን፣ ማሰራጨትና ተግባራዊ ማድረግ እያንዳንዱ አገር ከራሱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የሚሰራው ጉዳይ ነው። በዚሁ መሰረት፤ በተለይም በግብርናው ዘርፍ፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከማሳካት አኳያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ መረጃ በመሰብሰብ የተለዩ በመሆኑ በአሁኑ ሰአት በአገራችን ብዙም የሚያደናግር ነገር አላጋጠመም። በተለይም በየጊዜው ተከታታይ ትንበያን በማድረግ፣ ውጤቱንም ለሚመለከታቸው አካላት፤ በዋናነት ለግብርና ሚኒስቴር በማቀበል መረጃው በዛው ፍጥነት ለአርሶ አደሩ፣ ከፊል አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ በኩል ያለማቋረጥ እየተሰራ ሲሆን በአሁኑ ሰአትም ምንም አይነት የመረጃ ክፍተት የለም።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ መረጃዎች እንደየአይነት እና ባህርያቸው በገጠርና በከተማ፤ ክረምት፣ በጋ፣ በልግ፤ በአካባቢ – ምስራቅ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ሰሜን . . . በመለየት የሚሰበሰቡ ሲሆን ይህም በየ15 ደቂቃው ከሚደረገው ጀምሮ የሰአት፣ የቀን፣ የ10 ቀን፣ የ15 ቀን፣ የሶስት ወር ወዘተ እያለ የሚሰራና ወደ ማእከል የሚላክበት አሰራር ነው ያለው። በዚሁ መሰረትም መረጃው ይሰበሰባል፣ ይደራጃል። በዚሁ መሰረትም የመጪው ጊዜ የአየር ሁኔታ፣ የአየር ጠባይ፣ የአየር ጠባይ ለውጥና የከባቢ አየር ብክለት ሁኔታው ይተነበያል፤ ውጤቱም በሚመለከታቸው በኩል በተዋረድ ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል።

የአየር ትንበያን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም በተመለከተ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አውታር የሆኑትን የግብርና፣ የውሀ ሀብት፣ የሀይል፣ የቱሪዝም፣ የጤና ወዘተ ሁሉ የሚነካ እንደሆነ የሚገልፁት አቶ አህመዲን ከፖሊሲ አውጪዎች ጀምሮ እስከ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድረስ የአጭር፣ መካከለኛና የረጅም ጊዜ የአየር ለውጥ ትንበያ ውጤት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን፤ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ፣ ድርቅና የመሳሰሉትንም አደጋዎችን አስቀድሞ በማወቅ ለመቆጣጠር ባይቻል እንኳ ሊደርስ የሚችለውን አደጋም ትርጉም ባለው ደረጃ ለመቀነስ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ለማድረግ እንደሚያገለግል ያስረዳሉ።

ያለንበት ወቅት የክረምት መግቢያና በግብርናው ዘርፍ እጅግ ተፈላጊና ወሳኝ ወቅት ከመሆኑ አንፃር “የዘንድሮው የአየር ሁኔታና የዝናብ መጠን ምን ይመስላል?” ብለን ዳይሬክተሩን ጠይቀናቸው ነበር። እንደ እሳቸው መልስ ከሆነ የዘንድሮው የአገራችን የዝናብ መጠን መደበኛ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከመደበኛም በላይ ነው።

እየገባ ያለውን የክረምት ወቅት በተመለከተ አስተያየት የሰጡት አቶ አህመዲን እንደሚሉት የዘንድሮው ክረምት ከምእራብና ደቡብ ምእራብ እንደሚጀምርና በሂደትም ወደ መካከለኛውና ቀሪዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ እንደሚሄድ ትንበያው ያሳያል። ይህም ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ለሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ሁሉ በወቅቱ እንዲደርስ ተደርጓል።

ክረምቱ ወደዚህ፤ ወደ ኋላ ይመጣል የሚባል ጭምጭምታ ይሰማልና እውነታነቱ ምን ያህል ነው በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “ይህ እንደየአካባቢው የሚወሰን እንጂ እንደ አገር እንደዚህ ነው የሚል ነገር የለም። ትንበያው እንደሚያሳየው የዘንድሮው ክረምት በምስራቅና ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች ዘግይቶ እንደሚመጣ፤ ምስራቅና ምእራብ ሀረርጌ፣ ድሬዳዋ፣ ምስራቅ አማራ – ኮምቦልቻ፣ ባቲ . . ቀድሞ ከሚመጣው ዝናብ ዘግይቶ (ክረምቱ መውጫ ላይ) ከሚመጣው ዝናብ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ነው መረጃው የሚያመለክተው” ብለዋል።

አቶ አህመዲን አብዱል ከሪም እንደሚሉት በአገራችን እስካሁን ባለው የአየር ንብረት እና የዝናብ መጠን ሁኔታ ምንም አይነት ችግር የለም፤ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው። ከዚህ የተለየ ነገር ካለና ምንአልባት ለውጥ የሚታይ ከሆነ ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ወዲያውኑ ለህዝብ የሚያሳውቅ ነው የሚሆነው።

ባጠቃላይ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው ብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከተገኘው መረጃ መረዳት እንደተቻለው የዘንድሮው የአየር ንብረት፤ በተለይም ያለው የዝናብ ሁኔታ እስካሁን ምንም አይነት ችግር እንደሌለበትና በጥሩ ሁኔታም እየሄደ ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት የሚከሰት ችግር ካለም ኤጀንሲው ያለውን የካበተ ልምድ በመጠቀም እየተከታተለ ለሚመለከታቸው አካላት ያደርሳል፡ ፡ ስለዚህ አርሶ አደሩ አንዳንድ ጊዜ ከፍ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ እያለ በሚዘንበው ዝናብ ሳይደናገጥ ወቅቱን ጠብቆ የግብርና ስራውን እንዲያከናውን ኤጀንሲው ጥሪውን አቅርቧል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2011

 ግርማ መንግሥቴ