«ለልጆቼ የማወርሰው ገንዘብ አይደለም፤ የሥራ ባህልን ነው» - ወይዘሮ አንጋቱ ኃይሌ

16

ትውልድን በበጎ ማነፅ፣ አገር ለሁሉም የምትመች አድርጎ መገንባት ብሎም የተሳሳተ አስተሳሰብ ለማጥፋት ዋነኛ መሣሪያው ሥራ ነው፡፡ በሥራ ከፍ የማይል ሸለቆ፣ የማይናድ ተራራ፣ ሜዳ የማይሆን ስርጓጉጥ …የለም! ታዲያ በታታሪነታቸው አንቱ የተባሉ ጠንካራ ሠራተኛ እንካችሁ። ታታሪ ሠራተኛነታቸውን ለማረጋገጥ የሚሰሩበት ቦታ መሄድ አይጠበቅብንም፤እጃቸው ላይ የታተመው አሻራ ብቻ አፍ አውጥቶ የሚናገር ምስክር ነው። እሳቸውም ድንጋይ በእጃቸው ፈጭተው ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ መብቃታቸውን በኩራት ይናገራሉ። በጥንካሬያቸው ልክ ደግሞ ሆደ ቡቡ ናቸው። ያሳለፉትን የኑሮ ውጣ ውረድ ሲያስታውሱ ዓይናቸው በእንባ ይሞላል። እንባቸው ቅርብ መሆኑን በተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚታወቅ ሳይሆን የአደባባይም ምስጢር ነው። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሚሌኒየም አዳራሽ በተገኙበት ወቅት በመድረክ ላይ ስጦታ ሊያበረክቱ ወጥተው እንባቸውን ሲያፈሱና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመዳፋቸው እንባቸውን ሲያብሱ በቴሌቪዥን መስኮት የተከታተልነው ሁነት ነው። የዛሬው የ«ሕይወት እንዲህ ናት» አምድ እንግዳችን አድርገን ያቀረብናቸው የአንጋቱ ጠጠር ማምረቻ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አንጋቱ ኃይሌ።

ከውልደት እስከ

ወለጋ ነቀምት ነው በ1946 ዓ.ም የተወለዱት። ዕድገታቸው እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ነው። መጀመሪያ ሸዋበር ቀርሶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ። በመቀጠል ወደ ጃቶ (ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት) አመሩ። ትምህርታቸውን እስከ 12ኛ ክፍል ከአጠናቀቁ በኋላ ታላቅ ወንድማቸው ወደ አዲስ አበባ እንዳመጧቸው ያስታውሳሉ።

«ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት በ1968 ዓ.ም ሀገር ታያለሽ ተብዬ ነው። ለአንድ ዓመት ወንድሜ ቤት ተቀመጥኩ። በቆይታዬ የሥራም፤ ትምህርትም ዕድል አልነበረኝም። ከዚያ አቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰው ይቀጠራል ሲባል ሰማሁና ከቤት ጠፍቼ ሄድኩ፡፡ ያን ዕለት ግን ቅጥር አልነበረም። በሌላ ቀን ግን ቅጥር ነበርና ሰባ ሰዎች ተሰልፈን ከእነዛ መሃል ዕድል ቀንቶኝ ተቀጠርኩ። ያኔ አንድ ሰው በቀን የሚከፈለው ሃምሳ ሳንቲም ነበር። እኔም ስሰራ ውዬ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ወደ ቤት ስመለስ ቤተሰቡ ጠፋች ብሎ ይፈልገኝ ነበር። ስደርስ ‘የት ሄደሽ ነው?’ የሚለው ጥያቄና ቁጣ ቀድሞ መጣ። ሥራ ገባሁ አልኳቸው። ከፈቃዳቸው ውጪ በራሴ ይሄንን በማድረጌ ቅር ተሰኝተዋል። ትንሽ ተቆጡ። ሆኖም ቁጣውንም ችዬ አደርኩ፤ በማግስቱ ተነስቼ እንጀራ ጋግሬ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሁሉ ጨርሼ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ወደ ሥራው ሄድኩ። የወንድሜ ቤት አቃቂ ቃጫ ፋብሪካ አካባቢ ቢሆንም ፋብሪካው ጋር ለመድረስ አቃቂ ወንዝን ተሻግሮ መሄድ የግድ ይላል። ይሄንን ሁሉ መንገድ ታዲያ የምጓዘው በእግሬ ነው ። «የእግር መንገድ ለእርሳቸው ከባድ እንዳልሆነ ይናገራሉ። እኔ እኮ ሥራው ይገኝ እንጂ መንገድ ምኔም አይደለም። ትምህርትም የተማርኩት በእግሬ ተጉዤ ነው። በእዚያን ወቅት ለእኔ ሥራ ተቀጥሮ ሃምሳ ሳንቲም ማግኘት በጣም ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል። ያም ሆኖ «የተማረና የበላ…» የሚባል አነጋገር አለ አይደል? ከምሰራበት የፋብሪካ ሥራ «የተማሩ ሰዎች» ተብዬ ወደ ቢሮ፤ ቀጥሎም ወደ መዝገብ ቤት ገባሁ። ወይዘሮ አንገቱ በዕድገት ላይ እድገት ቢያገኙም ኑሯቸው ግን አዲስ አበባ ላይ አልቀጠለም፤ በወንድሞቻቸው ጥሪ መሠረት ወደ ወለጋ ተመለሱ። ሆኖም ግን እህል ውሃቸው ሸገር ላይ ነውና ከወለጋ ጠፍተው አዲስ አበባ መጡ።

«በድጋሜ አቃቂ ፋብሪካ ሄጄ አመለከትኩ። ወደ ሥራዬ ተመለስኩ። ከእዛ በኋላ ግን አባቴ ከለቀምት ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የራሴን ሥራ መስራት እፈልጋለሁ ስል አማከርኳቸው። እሳቸውም አላሳፈሩኝም እሺታቸውን በሚገልጹበት በራሳቸው የንግግር ስልት «ሌላ ጊዜ ስመጣ እንነጋገርበታለን» ብለውኝ ሄዱ፤ ያው እሺ እንደማለት ነው። ከቆይታ በኋላ አባቴ ታመው አዲስ አበባ መጡ። በዚያን ወቅት የአሁኑን የልጆቼን አባት ተዋውቄያለሁ። ወንድሜ ጋር እየኖርኩ ሲመጣ ሲመጣ ስንገናኝ ብዙ ጊዜ አሳለፍን፤ ከዚያም አብረን መኖር አለብን አለኝ። ይሄንኑ ለአባቴ ነገርኩ። አባቴም «ከተመቸሽ ምን ችግር አለ» ብለው ፍቃደኛነታቸውን አበሰሩኝ፤ እንዲያውም ሥራ የምሰራበት አምስት ሺ ብር ሰጡኝ። ይሄ ትልቅ ብር ነው። እጮኛዬም አልፎ አልፎ ከጎጃም እየመጣ ያየኛል። ለማግባት ስወስን ለወንድሜ ነገርኩት፤ ወንድሜ ግን ብዙም ደስ አላለውም። ቢሆንም ግን «ከተመቸሽ» የሚል ቅሬታ አዘል መልሰ ሰጠኝ።ያም ሆኖ በወንድሜ ፈቃደኛነት አገባሁ።

ችግርን በብልሀት

«አምስት ሺ ብሬን ቋጥሬ እያለሁ አቃቂ ቃሊቲ ላይ ሁለት የገበያ አዳራሽ ጨረታ ሲወጣ ተወዳደርኩና አንዱን አሸነፍኩ። ክፍያው ደግሞ አምስት ሺ ብር ነበር። ከፈልኩ። ሆኖም ግን ሱቁ ውስጥ ዕቃ የማስገባበት ገንዘብ አልነበረኝም። ስለዚህ ዕቃ ለመግዣ ገንዘብ ሳስብ ከምሰራበት አቃቂ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሥራ መልቀቅ እንዳለብኝ ወሰንኩ፤ ምክንያቱም የአገልግሎት ትንሽ ብር አገኛለሁ። ይሄንን አስቤ ሥራዬን ለቀቅኩ። የተወሰነም ገንዘብ አገኘሁ፤ ያንን ገንዘብ ይዤ ዕቃ ከኮልፌ አምጥቼ አስገባሁ። ሆኖም ግን ፎቁ ላይ ወጥቶ የሚገዛን ሰው ስለሌለ… ሜዳ ላይ ቁጭ ብዬ መነገድ ጀመርኩ። ባለቤቴ ከጎጃም እየተመላለሰ ሲያየኝ አሁንም ፀሐይና ዝናብ ይፈራረቅብኛል። ያን ጊዜ ታዲያ በአራት ሺ 500 ብር ቦታ ገዛልኝ፤ እዚያው ሜዳ ላይ እየነገድኩ ቤት ሰራሁ»።ሲሉ ያኔ ብዙ ነገር ፈታኝ እንደነበረባቸው ያለፈውን ጊዜ ወደ ኋላ በትውስታ እያነሱ ዓይናቸው በእንባ ሞላ። የዛሬውን ስኬታቸውን አስበው ደግሞ ስሜታቸውን ዋጥ አድርገው ወጋቸውን ቀጠሉ። እኛም በተመስጦ ማድመጡን።

ሆኖም ኑሮ በሁለት እግሩ አልቆመምና የእሳ ቸውም ልብ አልሞላም። በድጋሜ የአባታቸውን እጅ ማየቱን መረጡ። «ሰፊ ግቢ አለኝ መስራትና መለወጥ እፈልጋለሁ እባክህ አንድ ወፍጮ አቁምልኝ» ሲሉ ጥያቄያቸውን አቀረቡ። አባትም የልጃቸውን ጥረት ቁምነገረኛነት እያዩ ነበርና የተጠየቁትን ለማድረግ ወደ ኋላ አላሉም። እንደተጠየቁት አንድ ወፍጮ አቁመው ይሄው እርሾ አሉ። የጉልት ንግዱን ይነግዳሉ፤ ጎን ለጎን ደግሞ ወፍጮም ይሰራሉ። ያኔ ታዲያ ሥራው ከባድ መሆኑን ይናገራሉ። ራስ ለመቻል ግብ ግብ ነውና ሌላ ሰው ከመቅጠር ብለው በራሳቸው የተፈጨን እህል እያፈሱ መራራን የሕይወት ውጣውረድ ጣፋጭ ለማድረግ ጥረታቸውን ቀጠሉ። ይሄ ጥረታቸው እያለ የተፈጥሮ ሕግ ነውና ሴት ሆኖ መውለድ አይቀርም። እሳቸውም በዚሁ መካከል ልጆች እየወለዱ ማሳደግ አንዱ የሕይወታቸው ገጽታ ነበር።

ይህም ሆኖ ወይዘሮ አንጋቱ እርካታ የላቸውም። ይሄንን የወፍጮ ቤት ሥራ እንዴት ላስፋፋ? ኑሬዬንስ እንዴት ከፍ ላድርግ የሚለው እንቅልፍ የነሳቸው ጥያቄ ነበር። ለዚህ ጥያቄያቸው በቂ ምላሽ ሳያገኙ እረፍት የላቸውም። አንድ ቀን ይሄንን ወፍጮ እስኪ በደንብ ላሰራው ብለው ይነሱና ጠጠር ለመግዛት ወደ ጠጠር ማምረቻ ቦታ ይሄዳሉ። ይሄ ቀን ታዲያ ለእሳቸው የዕድገት ጎህ የቀደደበት ልዩ ቀን እንደነበር ያነሳሉ።

የዕድገት ጎህ

ጠጠር ማምረቻ ቦታ ሲደርሱ ጠጠር በብዛት ይቸበቸባል። እና ገረጋኒቲውን ማየት ብቻ ሳይሆን ሥራውም ወደ ውስጣቸው ገባ። እኔስ በዚህ ሥራ ላይ ብሰማራ ሲሉ መንፈሳዊ ቅናታቸው ተቀሰቀሰ። በአንድ በኩል ደግሞ በምን ገንዘብ? እንዴትስ ወደእዚህ ሥራ መግባት እችላለሁ? ብቻ ብዙ ጥያቄ በአእምሯቸው ተመላለሰ። ሆኖም ሊገዙ ያሰቡትን ገረጋንቲ ጠጠር በሰባ ብር ገዝተው በኤንትሬ መኪና አስጭነውና እሳቸውም ተጭነው ወደ ቤታቸው መግባታቸውን ያስታውሳሉ።

«ያየሁት ነገር ወደ ውስጤ ገብቷልና ለባለቤቴ አማከርኩት። በአንድ በኩል እነግዳለሁ፤ ወፍጮም አለኝ። አሁን ግን የድንጋይ ወፍጮ (ክሬሸር) ሊኖረኝ ይገባል አልኩት» «እንዴት ይኖርሻል?» በምን ምክንያት ሲለኝ ይኖረኛል ፈጣሪ ይሰጠኛል አልኩት። ባለቤቴ አይሆንም አትስሪ የሚል ሰው አይደለም። ስለዚህ እኔም ሁሉንም ነገር ከመሞከር አልቦዝንም። ያሰብኩበት የጠጠር ማምረት ሥራ ላይ ለመሰማራት ሁለት ኪሎ ሜትር በእግሬ እየሄድኩ የድንጋይ ቦታ መምረጥ ጀመርኩ። ቦታው ጨፌ ቱማ ይባላል። በእግሬ እየተመላለስኩ ሲደክመኝ ድንጋይ ላይ ቁጭ ብዬ እያሳለፍኩ ድንጋይ ያለበትን ቦታ ማፈላለጉን ቀጠልኩ። በእዚያ ቦታ ብቻዬን ስዘዋወር ምን እሆን ይሆን ብዬ ሳልፈራ በድፍረት ነው። እናም ብዙ ድንጋይ ያለበት አንድ ቦታ አገኘሁ።

በወቅቱ የድንጋይ ወፍጮ (ክሬሸር) ዘጠና ሺ ብር ነው የሚሸጠው። ገንዘቡ ደግሞ የለኝም። ስለዚህ ካስማ የሚባለው ኩባንያ ሄድኩና ሁሉንም ነገር አስረዳኋቸው። ነገር ግን ክሬሸር የለኝም አልኩ። «አሁን ምን አለሽ?» ሲሉኝ ምንም የለኝም አልኳቸው። ከዚያም ሀብታሙ የሚባል ሰው ጠራና እሷ የያዘችውን ቦታ እይላት ብሎ ላከው። ቦታው ድንጋይ አለው ብሎ ተመለሰ።

ሂጂና ቦታ አስተካክይ ተባልኩና ቦታውን አስተካክዬ ክሬሼር በዱቤ ተተከለልኝ። ከዚያ ድንጋይ እፈልጣለሁ፤ባሬላ እሸከማለሁ። ያኔ ብዙ የቀን ሠራተኛ ቀጥሬ ማስተዳደር አቅም አልነበረኝም። ስለዚህ ሦስት የቀን ሠራተኛ ቀጥሬ አራተኛ ባሬላ የምይዘው እኔ ነኝ፡፡ እና ሥራው ከሴትነት፣ ከልጅ አሳዳጊነትና ከሌላ ሥራ ጎን ለጎን የሚሰራ ከመሆኑ ጋር ተደማምሮ ለእኔ እጅግ ከባድ ፈተና ነበር። ሆኖም ጥርሴን ነክሼ ቀጠልኩ። የሰው ልጅ ከጠነከረ ያሰበበት ደረጃ ይደርሳል። አንድ ሰው በሳምንት ስልሳ ብር ያገኛል። እኔም ከእነሱ እኩል ስልሳ ብር እወስዳለሁ። ወደ ገበያ የሄድኩ እንደሆነ ተቀንሶ ነው የሚከፈለኝ፤ ምክያቱም የሚገኘው ገንዘብ ትንሽ ነው። ስለዚህ ከምነግደው ገንዘብ ወስጄ ነው የክሬሽኑን ገንዘብ የምከፍለው።

ክሬሸሯ በቀን የምትፈጨው ሦስት መኪና ብቻ ነው። አንድ ሜትር ኩብ ሰባ ብር ይሸጣል፤ አሁን አራት መቶ ብር ነው። የተፈጨውን ጠጠር ደግሞ በፌስታል ይዤ ገበያ ፍለጋ ሄድኩ።አንድ ሴት አገኘሁ። ሴትየዋ መድኃኒት ፋብሪካ ያላት ናት። እሷ ያንን ጠጠር አይታ ሴት ስለሆንኩም ለማበረታታት በሚመስል መልኩ «እኔ ነኝ የምገዛሽ»ብላ ሁሉንም ገዛችኝ። ያኔ መኪና ላይ መጫኛ ሎደር ፣ስካቫተር… ሚባሉት በሙሉ የሉም ፤ የሚጫነው በእጅ ነው።

ሰው ለመርዳት

«ሰው ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው» የሚለውን አባባል በትክክልም ወይዘሮ አንጋቱ ተግብረውታል። ሥራ ሲሰሩ፣ ሀብት ሲያገኙ ሌሎችም ማግኘት መስራትና መለወጥ አለባቸው ብለው በማሰብ የባለቤታቸው ወገኖች 13 ሰዎችን አምጥተው አብረው እየሰሩ እንዲሻሻሉ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።» ሁሉም ሰው ሲሰራና ሲያገኝ ደስ ይለኛል፤ ሁሉም ሰው እንዲያገኝ ስለምፈልግ ነው ዘመድ አዝማድ፣ ባዕድ ሁሉ የማሰባስበው። እኔ ባጣ እነሱ ይሰጡኛል፤ እነሱ ቢያጡ እኔ እሰጣቸዋለሁ። ካልተሰባሰብንና ካልሰራን ገንዘብ ከየት ይመጣል? ይሄ አእምሮዬ ውስጥ የነበረ ነው። ስለዚህ የእኔንም የባለቤቴንም ቤተሰብ አመጣና ሁሉም እንዲሰሩ አደርጋለሁ። በዚህ ሁኔታ እየተደጋገፍን ነው የሰራነው።» ይላሉ።

አሁን ተመስገን ነው ድንጋይ በእጅ ከመፍጨት ወጥቻለሁ። ሁለት ጊዜ በደራሽ ወንዝ ልወሰድ የነበረበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። አንዴ ጨማዬን ሌላ ጊዜ ደግሞ ሻርፔን ደራሹ ጎርፍ ሲወስደው ከጎርፍ አምልጬ ከተሻገርኩ በኋላ ባጋጠመኝ ነገር አልቅሻለሁ፤ በመትረፌ ደግሞ ፈጣሪን አመስግኜ ያሳለፍኩትን ጊዜ አልረሳውም። የሰው ልጅ ከታገለ፣ ከለፋ፣ ትልቁንም ትንሹንም፤ጥሩውንም መጥፎውንም ካልተጠየፈ ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ የእኔ የሕይወት ቆይታና ተሞክሮ ማስተማሪያ ነው ይላሉ። የወጡበት ዳገት የወረዱበት ቁልቁለት ይሄንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

የተፈናቃዮች አለኝታ

ወይዘሮ አንጋቱ ከሱማሌ ክልል ተፈናቅለው ለመጡ የኦሮሞ ተወላጆች ገላን ከተማ ላይ በራሳቸው ገንዘብ አስር የመኖሪያ ቤት ሰርተዋል። ዱከም ላይ ደግሞ በተመሳሳይ ስድስት ቤቶችን በመስራት የወገን ደራሽነታቸውን አስመስክረዋል።

«ለተፈናቃዮች ቤት ስሰራ ግቢያቸው ባለው ትርፍ ቦታ ላይ ዳማከሴ (የምች መድኃኒት ፣ ጤናዳም ፣ ስጋ መጥበሻ (ሮዝመሪ ) እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ወጣ ብለን ቀጠፍ የምናደርጋቸውን አትክልት ሁሉ ተክዬ፣አብስለው የሚበሉበትን እንጨት አስፈልጬ ሰጠሁ። እንደገቡ ውሀ አልነበራቸውም ውሀ በቦቴ እወስድላቸው ነበር። አሁን ግን መንግሥት ውሀና መብራት አስገብቶላቸዋል። ያም ቢሆን ግን አሁንም ብቅ ብዬ እጠይቃቸዋለሁ። ቤተሰባዊ መተሳሰባችን አልተቋረጠም ይላሉ።

ጉዞ አሜሪካ

አልችልም ያሉት ሥራና ምንም ነገር ከመሞከር የተቆጠቡበት ጊዜ እንደሌለ ለራሳቸው ይመሰክራሉ።«በጣም የሚገርመው አንድ ወቅት ላይ አሜሪካ እሄዳለሁ ብዬ ተነሳሁ።ያኔ ልጆቼም አድገዋል። አንድ የማውቀው ሰው ለጉብኝት ወረቀት ላከልኝ። ኤምባሲ ስገባ የሁለት ዓመት ቪዛ አገኘሁ። እንግዲህ የማውቀው ሰው እሱን ብቻ ነው ። ስሄድም ‘ከአውሮፕላን ማረፊያ መጥተን እንቀበልሽ’ ሲሉኝ አትምጡ ራሴ እመጣለሁ ብዬ ከለከልኳቸው። ስሄድ ደግሞ ዲሲ ላይ የያዝኩት ቋንጣ ፍተሻ ላይ እንደ ቆሻሻ ተጣለብኝ። በዚህ በጣም ተናድጃለሁ። ሆኖም ግን ዲሲ ላይ ያገኘኋቸው ኢትዮጵያውያን በደንብ ተቀበሉኝ፤ ወገኖቼ በመሆናቸው ዕቃዬን ሁሉ ተሸክመው የኮሎምቦስን ትራንስፖርት ቆርጠው አሳፈሩኝ። ኮሎሞቦስ ገባሁ፤ ለሁለት ቀን ከሰዎቹ ጋር ሀገሩን ጎበኘሁ። ከሦስተኛው ቀን ጀምሮ ቤት ይዘጋብኝ ጀመር። ቤት ስለሚዘጋብኝም የቤት ውስጥ ሥራ እሰራለሁ፤ ግቢው ውስጥ ያለውን ሳር ሳጭድ እውላለሁ። ማታ ሲመጡ ምግብ እንበላለን። ምግብ የሚያድረው ፍሪጅ ነው ፤ጠዋት ያንን አውጥተን እንበላለን። ብቻ ኑሮውን አልወደድኩትም። ቀጥሎ ወደ አትላንታ ለጉብኝት ወሰዱኝ እዛ ስድስት ቀን ቆየሁ፤ ሌላ ከተማም ወሰዱኝ ኑሮ ያው ነው «ማን እንደእናት፤ ማን እንደ ሀገር…» እንዳለው አዝማሪ ሜዳው ሁሉ ገደለ መስሎ ተሰማኝ። በሄዱ በ29ነኛው ቀን «እኔነኝ ወይ እዚህ የምቀመጠው? ወይ ድንጋዬ! ባሬላዬ ጉልቴ!…ብዬ ካልሄድኩ አልኩ። መቆየት ያሰብኩት ለሦስት ወር ነበር። «ለምንድነው የምትሄጂው» ሲሉኝ «ባለቤቴ ናፈቀኝ ፤ልጆቼ ናፈቁኝ አልኩና መጣሁ።»አየር መንገድ ስደርስ አይ ሀገሬ! አየርሽ ፣ምድርሽ፣ዜጋሽ ፣ ምግብሽ … እያልኩ ምድሯን ስሜ እርም አሜሪካ ብዬ ቀረሁ።

የስኬቱ ማማ

ዛሬ ድንጋይ በእጅ ከመፍጨት ወጥተዋል። በቀን አርባ መኪና የሚፈጭ ክሬሸር አላቸው። በሰው ሎደር ነበር የሚሰሩት ዛሬ ባለ ሎደር፣ እስካቫተር ፣የጭነት መኪና ባለቤት ሆነዋል። ለራሳቸውም ሦስት አራት መኪና አማርጠው ይጠቀማሉ። ሌላም ሌላም… ሁሉን መዘርዘሩን አልወደዱምና ብቻ በአጭሩ የስኬት ማማ ላይ መድረሳቸውን አጫወቱን። ለዚህም ያበቃቸውን ፈጣሪን ጠርተው ለስኬታቸው ያገዟቸውን ሁሉ አመሰገኑ።

የኮንዶሚኒየም ቤት አሻራ

ለሀገራችን በተለያየ መልኩ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለብኝ አምናለሁ። ስለዚህ ለምን በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ላይ አንሰማራም ስል ልጆቼን አማከርኳቸው ይላሉ ሞራለ ብርቱዋ እንግዳዬ። ልጄ በኢንጂነሪንግ የተመረቀ ነው። እናም በስሙ ፈቃድ አውጥተን ወደ ሥራ ለመግባት አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ተመዘገብኩ። በሰባተኛ ወር ቦሌ አራብሳ ሁለት ብሎክ ቤት ግንባታ ተሰጠኝ። ይሄን የሀገር ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንዳለብን በማመን መንግሥት በጀት ከመስጠቱ ቀድመን በራሳችን ገንዘብ የግንባታ ወጪውን ሁሉ እያሟላን ፤ ልጄና ባለቤቴ ጭምር እስከ ምሽቱ ሰባት ሰዓት እያመሸን ፤ከቦሌ አራብሳ አቃቂ እየተመላለስን ሥራችንን በድል ተወጣን፡ ፡ በሰራነው ሥራም ከሁሉም ኮንትራክተሮች ጋር ተወዳድረን ሁለተኛ ደረጃን አገኘን። ይሄንን ሥራችንን በመገምገም በድጋሚ ባለሰባት ፎቅ ሦስት ብሎክ እንድንገነባ ተሰጥቶን አሁን እየሰራን ነው። ይሄንን አጠናቀን ሰኔ 30 ቁልፍ አስረክባለሁ። በማለት ምን ያህል ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ይናገራሉ። በሰራነው ሥራ እውቀትም ገንዘብም አግኝተናል።ከዚሁ ተነስተን ዛሬ ለራሳችን አሳንሰር ያለው ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃ በመገንባት ላይ ነን አሉ።

የቃልኪዳን ማሰሪያ

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የመታረቅ ዜና በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ምን ያህል ደስታን ያጫረ እንደነበር ይታወቃል። የወይዘሮ አንጋቱ ደስታ ደግሞ ከዚህም በላይ ድርብርብ እንደነበር አጫውተውናል።

«ሰባት ኤርትራውያን ጎረቤቶች ነበሩኝ። አምስቱ ንብረታቸውን አደራ ሰጥተው ሄዱ። ባል ከሚስቱ ልጅ ከወላጁ የተለያየበት መጥፎ ጊዜ በእርቅ መደምደሙ ታዲያ በጣም አስደስቶኛል። ጎረቤቶቼም ይመጣሉ ብዬ ተስፋ አድርጌያለሁ። የእርቁን ዜና ከሰማሁ ጀምሮም እንቅልፍ አልነበረኝም። ታዲያ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ሀገራችን ሊመጡ መሆኑን ስሰማ ለማንም ሳልናገር ስጦታ አዘጋጀሁ። ስጦታው ኤርትራና ኢትዮጵያ ከእንግዲህ አንለያይም የሚል መልዕክት ያለው ቃልኪዳን የምንገባበት መሆን አለበት ብዬ ስላሰብኩ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ የጣት ወርቅ ነው ያዘጋጀሁት። ይሄንን ስጦታ ሳበረክት ታዲያ ደስታዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ ያለፈው መጥፎ ትዝታም በፊቴ ተደቀነና እንባዬ በጉንጬ ፈሰሰ።

ጥምርታ ወለጋ ከጎጃም

ወይዘሮ አንጋቱ እንዲህ አሉ። «አንድ ሰው ብቻዬን ሰርቼ እራሴ እለወጣለሁ ቢል አይሆንም፤ አጉል ቦታ፤ የማይሆን ሰው ላይ መውደቅ አለ። ስለዚህ በምግባርም በሌላውም ሊመሳሰል የሚችል ሰው መምረጥ ያስፈልጋል ።» አርቆ አስተዋይዋ ወይዘሮ ታዲያ ይሄንን ሀሳባቸውን በልባቸው ይዘው ይበጀኛል፤ ይመስለኛል ያሉትን ሰው ዘር ሳይቆጥሩ ከጎጃሜው ባለቤታቸው አቶ ቃሲም ሀሰን ጋር በትዳር ተጣመሩ።

ከባለቤታቸው ጋር መኖር ከጀመሩ 40 ዓመታት በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመግባባት አሳልፈዋል። ስምንት ልጆችም አፍርተዋል። ሰባት ልጆቻቸውን ድረው ኩለዋል። የዘጠኝ ልጆች አያት ለመሆን በቅተዋል። ዘጠኝ እናትና አባት የሌላቸውን ልጆች ደግሞ ጉድፈቻ እያሳደጉ ናቸው። አሁን አንዷ ዲዛይነር፣ አንዷ ፋርማሲስት፣ ሌላው ደግሞ ኢንጂነር ነው። ስድስቱ ቤት ውስጥ አሉ። ከአብራካቸው ከወጡት ልጆቻቸው እኩልም የሀብት ንብረት ተጋሪ አድርገው እያስተማሩና እያሳደጉም በምድርም በሰማይም ትልቅ ዋጋ ያለው ሥራ በመስራት ላይ ናቸው።

«ለልጆቼ የማወርሰው ገንዘብ አይደለም፤ የሥራን ባህል ነው። ትንሽ ለኑሮ እርሾ ሰጥቼ ትልቅ እንዲያመጡ ነው መንገድ የማሳያቸው። ይሄ ካልሆነ እንጣላለን። እንቀያየማለን። ከፋ ሲልም እንለያያለን የሚል ቆራጥ የሆነ መመሪያ አለኝ። ፈጣሪ ይመስገን ልጆቼም አላሳፈሩኝም።

የወደፊት ምኞት

ፈጣሪ ሁሉንም ነገር አሟልቶልኛል። አሁን ችግረኛ ሰዎችን በተለያየ መልኩ መደገፍ እፈልጋለሁ የሚሉት ወይዘሮ አንጋቱ ችግረኛ ተማሪዎችን፣ ሴቶችንና እናቶችን መደገፍ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። በልማት ደግሞ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወላጅ ለሌላቸው ልጆች ትምህርት ቤት ሰርቼ ባስተምር፤ ምንም ዘመድ የሌላቸው ሴቶችና እናቶች የሚታከሙበት አነስተኛ የጤና ተቋም ብሰራ ደስ ይለኛል። በቀሪው ዕድሜዬ ለሀገሬና ለሕዝቧ በተለያየ ልማት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት አለኝ። እንዲሁም ሥራ ለሌላቸው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አለብኝ የሚል ዕቅድና ሀሳብ አለኝ አሉ። እኛም የወይዘሮ አንጋቱ ዕቅድና ሀሳብ እንዲሰምር ተመኘን፡፡ ሰላም!

አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2011

አልማዝ አያሌው