በቁጥጥር ሥር የማዋሉና ለሕግ የማቅረቡ ሥራ አጥፊዎችን በመቅጣትም ይደገፍ !

15

 አገሪቱ በለውጡ ዋዜማ ማባሪያ በሌላቸው ህዝባዊ ተቃውሞዎች ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ስትናወጥ መቆየቷ ይታወሳል። ይህም የመንግሥትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሞች ክፉኛ እንዲሽመደመዱ አድርጎም ነበር።

ከለውጡ በኋላም ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ተከስተዋል። በዚህም የንፁኃን ዜጎች ህይወት በከንቱ አልፏል፤ ለጉዳት ተዳርገዋል፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ መፈናቀል ደርሶባቸዋል። የኢኮኖሚ አሻጥሮች እና ህገወጥ ድርጊቶች ተከስተዋል። ኢኮኖሚው በተለይ የወጪ ንግዱ ክፉኛ ተጎድቷል።

እነዚህን በዜጎች እና በአገር ላይ የደረሱ ወንጀሎችን በየዕለቱ ከዚህም ከዚያም የተመለከው ህዝብም መንግሥት የሕግ የበላይነት እንዲያስከብር በየመድረኩ ሲጠይቅ ቆይቷል። በአገሪቱ አላባራ ላሉት የፀጥታ እና የመሳሰሉት ችግሮች መንስኤው መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ መለሳለስ በማሳየቱ ነው እያለም ይገኛል። መንግሥትም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2011 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት በአገሪቱ ላይ ተጋርጠው የነበሩትን አደጋዎች በመጀመሪያ ለመቀነስ ቀጥሎም ለማስቆም አያሌ እርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የተከናወነው ተግባር ነው። በዚህም አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት የሚያገኙባቸው ሥራዎች ተሠርተዋል።

በተደራጁ ቡድኖች ውስጥ በመንቀሳቀስ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የሥራ ሃላፊዎችና ግብረ አበሮች በሕግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ይገኛል። ለአብነትም በአገራችን ላይ ከፍተኛ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 48 የሽብር ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ያሰቡት የሽብር ጥቃት ሳይፈፀመ መከላከል ተችሏል።

ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በመቀስቀስና ጥቃቶችን በማድረስ እንዲሁም ዜጎችን በማፈናቀል ወንጀሎች ተሳትፈዋል የተባሉ አመራሮችና የፀጥታ አካላት 799 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ለሕግ ቀርበዋል። በኢኮኖሚ ወንጀሎች ላይ ከተሰማሩ 35 ተጠርጣሪ የባንክና የቴሌ ሠራተኞች መካከል 34ቱ ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል።

ከመሣሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ 235 በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ 634ሺ አንድ ዜጎችን አስኮብልለዋል የተባሉ 51 ተጠርጣሪ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ደላላዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል።

የእነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋልና ለሕግ መቅረብ ወንጀል እንዳይበራከት፣ አገር ይበልጥ እየተረጋጋች እንድትመጣ እንዲሁም ህዝቡ የሕግ የበላይነት ይጠበቅ እያለ ሲያቀርብ ለቆየው ጥያቄ ምላሽ በመሆን ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የእነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋልና ለሕግ መቅረብ አንድ እርምጃ ሆኖ በአስቸኳይ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ደግሞ በትኩረት መሥራት ይኖርበታል። ተጠርጣሪዎች አንድ ሰሞን ፍርድ ቤት ሲመላለሱና ምርምራ ሲደረግባቸው ከመሰማቱ ውጭ ጥፋተኛ ሲባሉም ሆነ ሲቀጡ ብዙም አይደመጥም።

በእርግጥ የፍትህ ሥራው በራሱ የሚፈልገው ጊዜ ሊኖር ይችላል። በህዝብ እና በአገር ላይ ጥፋት ባደረሱ ሃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ግን ከየትኛውም ወንጀል ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊታይ ይገባል። ተጠርጣሪዎቹ ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸው ተረጋግጦ ያጠፉት በአስቸኳይ ቅጣቱ ካልተፈፀመባቸው ህዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እየተሸረሸረ ይመጣል፤ ሌሎች ወንጀል ቢሠሩ የሚደርስባቸው ቅጣት እንደሌለ አርገው እንዲያስቡም ያደርጋቸዋል።

ግጭት በመቀስቀስ የዜጎችን ሕይወት ያጠፉ ወይም እንዲጠፋ ምክንያት የሆኑ ፣ ከኖረበት ቀዬ በማፈናቀል ባዶ እጁን ያስቀሩ ለጉስቁልና የዳረጉ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር መዋል ብቻውን በቂ እርምጃ አይደለም። ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማደረግ በትኩረት መሥራትም ያስፈልጋል።

ሌሎች በቁጥጥር ሥር ያልዋሉትም እንዲሁ አሁንም በባትሪ ተፈልገው ለሕግ መቅረብ ይኖርባቸዋል። በአንዳንድ ክልሎች በድርጊቱ ተሳትፈዋል የሚባሉ አመራሮችን አሳልፎ ላለመስጠት ማንገራገር ሲፈፀም እንደሚስተዋል መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህ እርምጃ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አመራሮችንም ሊምርም አይገባውም። በሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩትም እንዲሁ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።

በቁጥጥር ሥር የሚገኙት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ አንስቶ የፍርድ ሂደቱ በመገናኛ ብዙሃን እንዲሸፈን በማድረግ ህዝቡ የተጠርጣሪ ወንጀለኞቹ ጉዳይ የት እንደደረሰ እንዲከታተል ሌሎች ወንጀል ሊፈፅሙ የሚፈልጉ አካላትም ነገሮች ማምረራቸውን ተገንዘበው የጥፋት እጃቸውን እንዲሰበስቡ ብቻ ሳይሆን ፈፅሞም ወንጀልን እንዳይሞክሩት ለማድረግ ያስችላል።

የሕግ የበላይነት ይከበር ሲባልም በቁጥጥር ሥር ማዋል ብቻ አይደለም። እስከ አሁን በተጠቀሱት ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ጥፋተኛነታቸው ተረጋግጦ የተቀጡ ይፋ መደረግ አለባቸው። የተቀጡትም ከተፈፀሙት የወንጀል ድርጊቶች አኳያ የሚጠበቀውን ያህል ቅጣት ተፈፀሟል ለማለት አያስደፍርም፡፤

በመሆኑም የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ሥራ በቁጥጥር ሥር ከማዋል ወደ ቅጣት እርምጃ እንዲሸጋገር እና ሕዝቡ የሕግ የበላይነት ይከበር ጥያቄ በቅጡ እንዲመለስ መንግሥት በትኩረት መሥራት ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011