የሰበታ ወጣቶች የስራ ዕድል ጥያቄ ምን ያህል እየተመለሰ ነው?

9

 ሰበታ ከተማ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሥር የምትገኝ ናት፡፡ ከተማዋ ሀገራችን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ለምታደርገው ግስጋሴ መልስ ለመስጠት ከምንጊዜውም በላይ ተግታ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በከተማዋ ጥንታዊውን የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን ጨምሮ ከ7 መቶ በላይ የሚደርሱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ይገኙባታል፡፡

ሰበታ ለአዲስ አበባ ካላት ቅርበትና አመቺነት አንጻር ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ እየሆነች መጥታለች፡፡ ከተማዋ የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር የሚካሄድባት፣ ፈጣን መስፋፋትና እድገት የሚታይባት ሆናለች፡፡ በዚህ ሂደትም እስከ አሁን ስልሳ ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች በተለይም ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡

በቅርቡ የኮካ ኮላ ኩባንያ በኢትዮጵያ ትልቁን ፋብሪካ በሰበታ ከተማ ለመክፈት ግንባታውን በይፋ ባስጀመረበት ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ክላስተር ኃላፊ አቶ አህመድ ቱሳ ሰበታ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሁለተኛ ከተማ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል፡፡

የግል ባለሀብቶች በማህበራዊ ኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንዳሉ የተናገሩት አቶ አህመድ ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር በመንግስት ላይ የሚፈጠረውን ጫና በመቀነስ ከፍተኛ አቅም እንደሆነም አስረድተዋል ፡፡

የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሀኑ በቀለ ኢንቨስትመንቱ ለከተማዋ እድገት በይበልጥም የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ አሁንም በከተማዋ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እየመጡ መሆናቸውን የሚናገሩት ከንቲባው እነዚህም በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

ለአካባቢው ወጣቶች ቅድሚያ የመስጠቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ እስከ አሁን ከሌላም አካባቢ መጥተው የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ የሚሆኑ ዜጎች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ብርሀኑ ወጣቶች የሚፈጠሩላቸውን የሥራ ዕድል ተጠቅመው የራሳቸውንም ሆነ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው ከሚሰሩ ዜጎች ባሻገር ፋብሪካዎቹ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ በተፈጠረ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ገልጸው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሥራ አጥ ዜጎችን የመሸከም አቅሙ ትልቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በከተማው ሙሉ ለሙሉ የስራ አጥነት ችግር ተቀርፏል ማለት እንደማይቻል እና በየጊዜው የሚመጣውን ሥራ ፈላጊ ማስተናገድ እንዲያስችል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተመስገን ቂጣታ የሰበታ ከተማ ነዋሪና የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በሰበታ ከተማ የተለያዩ ፋብሪካዎች መተከላቸው ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል የፈጠረ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ይናገራል፡ ፡ ተመስጌን አሁን በኤልሚ ኮንስትራክሽን ውስጥ ሴፍቲ ኦፊሰር ሆኖ እየሰራ እንዳለና በወር የተሻለ ክፍያ እያገኘ እንዳለ በዚህም ህይወቱን በጥሩ ሁኔታ እየመራ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከአሁን በፊት በቀን ሥራና በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥሮ መሥራቱን የሚገልጸው ወጣቱ በከተማው የግል ካምፓኒዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱ የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ወጣቶች የተለያየ ሙያ ባለቤቶች እንዲሆኑም ያስቻለ ጥሩ አጋጣሚ ነው ይላል፡፡

በሰበታ ከተማ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው በመስራት ህይወ ታቸውን እየመሩ እንዳሉ የሚገልጽው ተመስጌን እንደውም ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሥራ ፈላጊዎችም እየተጠቀሙ ናቸው ይላል፡፡ በሰበታ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ መምጣታቸውም ወጣቶች ለሚያቀ ርቡት የሥራ ዕድል ጥያቄ መልስ እየሰጡ የመጡ እንደውም አማራጭ ሥራ ለመቀየርም ጥሩ ዕድል የፈጠሩ እንደሆኑ ይናገራል፡፡

በከተማዋ ኢንቨስትመንት መስፋፋቱ በአንድ በኩል በፋብሪካዎች ተቀጥሮ የመስራት አጋጣሚ ሲፈጥር በሌላ በኩል ደግሞ በፋብሪካ ለሚሰሩ ሰራተኞች የምግብ ፣ የቁሳቁስና መሰል አገልግሎቶችን በመስጠት ገቢ ለማግኘት የሚያ ሥችል አቅም ተፈጥሯል ይላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ወጣቱ ተደራጅቶ ፋብሪካዎቹ የሚያመርቱትን ምርቶች ለገበያ በማሰራጨት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችልም ወጣቱ ጠቁሟል፡፡

ይሁን እና እስከ አሁን ድረስ ይህ አሰራር በስፋት እንዳልተሰራበት የሚናገረው ወጣት ተመስጌን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በከተማዋ እየተስፋፋ የመጣውን ኢንቨስትመንት ተከትሎ ከባለሀብቶች ጋር በመነጋገር ለበርካታ ወጣቶች የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር በሚያሥችል አሰራር ሊቃኙ እንደሚገባ አሳስ ቧል፡፡

ሌላው ያነጋገርነው ወጣት ብርሀኑ ንጉስ ይባላል፡፡ ብርሀኑ በሰበታ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ እንደሰራና አሁን የኮካ ኮላ ኩባንያ እያስገነባ ባለው ግዙፍ ፋብሪካ ውስጥ / በፎርማልነት/ አጠቃላይ የግንባታ ስራ ኃላፊ በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡

‹‹እዚህ ድርጅት ውስጥ መስራት ከጀመርኩ በኋላ ህይወቴ ተቀይሯል›› የሚለው ወጣቱ በሚያገኘው ጥሩ ገቢ ቤተሰብ መስርቶ እየኖረ እንዳለ ይገልፃል፡፡ በሰበታ ከተማ ውስጥ የተገነቡት ፋብሪካዎች ለበርካታ የሰበታና የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን የሚናገረው ወጣቱ ከዚህ ጎን ለጎን የከተማዋን ዕድገትም እንዳፋጠኑት ይናገራል፡፡ ወጣቱ እንደሚለው በሰበታ እየተስፋፋ ከመጣው ኢንቨስትመንት ጋር የአብዛኛው የከተማው ነዋሪ ህይወት እየተቀየረ ነው፡፡ በመሆኑም የአካባቢው ማህበረሰብ በከተማው የሚገኙ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን መደገፍና እንደራሱ ሀብት መንከባከብ እንደሚገባው መልዕክቱን አስተላ ልፏል፡፡

ወጣት ብዙአየሁ አክመል የሰበታ ከተማ ነዋሪ ሲሆን በአካባቢው የሥራ አጥነት ችግር እንደነበር አስታውሶ አሁን ግን ለብዙ ወጣቶች መልካም የሥራ አጋጣሚ እየተፈጠረ እንዳለ ጠቁሟል፡፡ በሰበታ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ጥንታዊው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ እንደነበር በመጥቀስ አሁን ግን የፋብሪካዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ይላል፡፡

ፋብሪካዎቹ ለአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠራቸውን የሚናገረው ወጣቱ እርሱም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንደሆነና እስከ አሁንም በተለያዩ ፋብሪካዎች ውስጥ በመስራት ሙያውን እንዳዳበረ ተናግ ሯል፡፡ ዛሬ በሰበታ አካባቢ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ባሻገር በተለያየ ቦታ ሄደው መሥራት የሚያስችላቸውን ሙያም አግኝተዋል ይላል፡፡

ወጣት ብዙአየሁ እንደሚለው በሰበታ ከተማ ያሉ አንዳንድ ፋብሪካዎችም የሰራተኛውን ተገቢ ጥቅም አክብረው መስራት እንደሚገባቸውና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነትም ከግምት ሊያስገቡ እንደሚገባ ገልጾአል፡፡ በአንጻሩም ለአካባቢው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ አበርክቶ የሚያ ደርጉ ባለሀብቶችም ሊመሰገኑ ይገባል ይላል።

እንደ ወጣቱ አስተያየት በከተማው በርካታ ኢንዱስትሪዎች ያሉ ቢሆንም ዛሬም የሥራ አጥነት ችግር ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ማለት አይቻልም፡፡ የአካባቢው ወጣቶች ስራን ባለመናቅ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚመክረው ወጣቱ የአካባቢው ባለስልጣናትም በወጣቱ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመሥራትና ከባለሀብቱ ጋር በመነጋገር ያለ ስራ የተቀመጡ ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማገዝ ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡

ወጣት ሀለቱ ዓሊ በሰበታ 05 ቀበሌ ነዋሪ ስትሆን እርሷ እንደምትለው በአካባቢዋ የፋብሪካዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የተለያዩ የስራ አማራጮችን ለመጠቀም እንዳስቻላትና ስራ ፍለጋ ከአካባቢዋ እርቃ ብትሄድ ሊገጥማት ከሚችለው የኑሮ መመሰቃቀል እንደታደጋት ትናገራለች፡፡ እንደ እርሷ አባባል በዚህ ፈታኝ ወቅት ከምትኖርበት መንደር እርቃ ሳትሄድ እንዲህ አይነት ሥራ ማግኘቷ ቤተሰቦቿን በቅርበት ለመርዳትና የግል ህይወቷንም በአግባቡ ለመምራት እንዳስቻላት ትገልጻለች፡፡

ወጣቷ በዚህ ሥራ ላይ ተቀጥራ መሥራቷ ትልቅ የአዕምሮ እረፍት እንደሰጣት እና በምታገኘውም ጥቅም ህይወቷን እንደለወጠች በመናገር ለወደፊት ህይወቷም ጠቀሚ የሆነ ሙያ እያገኘች እንዳለች ትናገራለች፡፡ ከዚህ በፊት በቀን ስራ፣ በችርቻሮና በአበባ ልማት ውስጥ ትሰራ እንደነበር የገለጸችው ወጣቷ አሁን ባለችበት ኤሊኖ ኮንስትራክሽን ውስጥ በመሥራቷ ገቢዋ እንደተሻሻለና በዚህም በጣም ደስተኛ እንደሆነች ትናገራለች፡፡

ሥራው መንደሯ ድረስ መምጣቱም ለትራንስ ፖርት ፣ለምግብና ለቤት ኪራይ የምታወጣውን ወጪ እንደታደጋት ታስረዳለች፡፡ በሰበታ አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች የተመቻቸላቸውን የስራ ዕድል በመጠቀም ፋብሪካዎችን እንደራሳቸው ንብረት መንከባከብ እንደሚገባቸውም የምትናገረው ሀለቱ አንዳንድ ፋብሪካዎቹ ማህበረሰቡን የመንገድ የመብራት የውሃና የተለያዩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ በማድረግ ለአካባቢው ማህበረሰብ አጋርነታቸውን እያሳዩ ያሉ መሆናቸውንም አድንቃለች፡፡ ህብረተሰቡም ከኢንቨስትመንቱ የሚያገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ተረድቶ በከተማው ያሉ ኢንዱስትሪዎችን እንደራሱ ንብረት ሊንከባከባቸው ይገባል ትላለች፡፡

በአጠቃላይ ሰበታ ከተማ ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል የመፍጠር የተለያዩ አማራጮች ቢኖሯትም አሁንም የመሰረተ ልማት ጥያቄዋ ገና አልተሟላም፡፡ በመሆኑም ክልሉም ሆነ የከተማው አስተዳደር የወጣቱ የስራ እድል ፍላጎትና እየተፈጠረ ያለው የስራ እድል ብዙ ሊሰራበት የሚገባ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2011

 ኢያሱ መሰለ