ወርቃማው የመኸር ወቅትና የስንዴ ምርት

30

 እስከ ዛሬ የተከናወኑ በርካታ ጥናቶች ያለ ልዩነት እንደሚያረጋግጡት አገራችን ምቹ የተፈጥሮ ሀብትና ለተለያዩ ሰብሎች ምርታማነት ተስማሚ የአየር ንብረት ያላት መሆኗን፤ ነገር ግን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና አሠራሮችን በመጠቀም የምርታማነት ደረጃን ማሳደግ አልቻለችም። ይሁን እንጂ አሁን አሁን ይህ ችግር በመጠኑም ቢሆን እየተቀረፈ፤ ምርትና ምርታማነት እያደገ፤ ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደረገ ያለው ድጋፍ እየተሻሻለ በመምጣት ላይ ስለመሆኑ በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው፤ ከእነዚህም አንዱ የሆነው ስንዴ ተጠቃሽ ነው።

«ግብርና በአገራችን የኢኮኖሚ እድገትና ሽግግር ውስጥ ያለውን ሚና እውን ለማድረግ ከፍተኛውን ድርሻ ከሚያበረክቱ ሰብሎች መካከል አንዱና ዋነኛው ስንዴ ነው፡፡ ከ“hdl.handle.net” የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ስንዴ በኢትዮጵያ ከ1ነጥብ7 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን ሲሆን ከዚህም ወደ 3ነጥብ1 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ምርት በዓመት ይገኛል»፡፡ ስንዴ በሚሸፍነው መሬት ስፋት በሦስተኛ ደረጃ፤ በሚሰጠው ምርት መጠን በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያመለክተው ይኸው ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በርካታ ተመጋቢ ያለውና 15 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ኢኮኖሚ እንደሚሸፍን፤ ከሰው ልጅ አጠቃላይ ዓመታዊ የምግብ ፍጆታ 21 በመቶውን እንደሚይዝም ይገልፃል። ጥናቱ ይህን ይበል እንጂ እንደ አገራችን መልከአ-ምድርና የአየር ሁኔታ ምቹነት የስንዴ ምርት የሚፈለገውን ያህል እየተመረተ እንዳልሆነ ሁላችንም የዓይን ምስክሮች ነን።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና ግብርና መስሪያ ቤት (ኤፍ.ኤ.ኦ) «በ2050 የዓለማችን የሕዝብ ቁጥር ወደ 9ነጥብ6 ቢሊዮን ከፍ የሚል ሲሆን፤ የምግብ ፍላጎቱን ለማርካት ደግሞ የስንዴ ምርት ላይ 60 በመቶ ጭማሪ መደረግ አለበት።» ያለውን ስናገናዝብ አገራት ለስንዴ ምርት ምን ያህል ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው እንረዳለን። ኢትዮጵያም የዓለም አካል ስለሆነች በአርሲና ባሌ አካባቢዎች የሚታየውን የስንዴ ምርትና ምርታማነት ተሞክሮ ወደ ሌሎቹም የሀገራችን ክፍሎች ልታስፋፋ የግድ ይሆናል።

ለዚህ የምርት ዝቅተኛነት ምክንያቶቹን በተመለከተ «አስተዋፅዖ የሚያደርጉ በርካታ የምርት ማነቆዎች አሉ፡፡ ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ የተሻሻሉ ዝርያዎች አጠቃቀም አነስተኛ መሆን፤ የስንዴ በሽታዎች የሚያስከትሉት ጉዳት፤ አነስተኛ የምርት ግብዓት አጠቃቀም (ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር)፣ ኋላ ቀር የአመራረት ዘዴ፣ በዝናብ ላይ ብቻ የተመረኮዘ አመራረት፣ የአረም በተለይም የሳር አረሞች፣ የአፈር ለምነት መሟጠጥ፣ ደካማ የገበያ ትስስርና ሌሎች የተፈጥሮ ክስተቶች (ድርቅ፣ ውርጭ)»መሆናቸውን ይኸው ጥናት ያመለክታል።

በስንዴ አምራችነት ከ4ነጥብ7 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ኑሯቸውን የመሰረቱበት መሆኑ የሚነገርለት፤ በሔክታር 2ነጥብ7 ቶን የሚገኝበት ዘርፍ ከ90 በመቶ በላይ ምርቱ ግን በአነስተኛ ገበሬዎች በአነስተኛ የእርሻ ይዞታ የሚመረት ከመሆኑም ባሻገር ምንም ዓይነት መስኖ የማያውቀው በመሆኑ ለምርታማነቱ መውረድ በምክንያትነት የሚጠቅሱ ብዙዎች ናቸው። ይሁን እንጂ፤ የአሜሪካው ጌይን ሪፖርት በኢትዮጵያ በመጪው ዓመት ከ6ነጥብ3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያላነሰ የስንዴ ፍላጎት እንደሚኖር ግምቱን አስፍሯል፡፡

በአሁኑ ሰዓት እነዚህንና ሌሎች የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመፍታት ኢትዮጵያ ሰፊ ሥራን እየሰራች ስለመሆኗ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሲናገሩ ይሰማል፤ አቶ አባቡም ከእነዚሁ ወገን ናቸው።

የአርሲ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባቡ ዋቆ ለአዲስ ዘመን እንደሚናገሩት ከሆነ እሳቸው በሚመሩት የዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት እንቅስቃሴ ኩታ ገጠም መሬቶችን በማዋሀድ እያከናወነ ያለው ተግባር (Cluster ap­proach) ይህንን ሁሉ ችግር ለመቋቋምና የተሻለ ለማምረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ነው። በትግራይ ክልል የታየው ተሞክሮም ተጠቃሽ ነው።

ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ከሰጠው መረጃ «እ.አ.አ. እስከ መስከረም ወር 2017 ድረስ 72ሺህ 634 የሰብል እና ሆርቲካልቸር ዝርያዎች ናሙና በጂን ባንኩ ውስጥ» መኖራቸውን እንረዳለን። ይሁን እንጂ «ተቀምጠውስ?» የሚል ጥያቄ ደግሞ አለን።

ከእነዚህ 72ሺህ 634 ናሙናዎች ውስጥ በ2003 ዓ.ም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ደጀኔ ካሳሁን አማካኝነት ተወስዶና ከአካባቢው ሁኔታ ጋር ተጠንቶ ወደ ሥራ ተገብቶበት ውጤታማ የሆነውን «ዱረም» ዝርያ ይገኛል። ስድሳ አርሶ አደሮችን በመያዝ የተጀመረው ይህ ሙከራ ዛሬ ከ900 ያላነሱ አርሶ አደሮችን ያቀፈ መሆኑ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባን ለማግኘት በቅቷል።

የስንዴና ፋይዳው ጉዳዩ በእነዚህ ብቻ የሚቆም አይመስልም። ተመራማሪዎች የትኛውንም ዓይነት የአየር ጸባይ መቋቋም የሚችሉ የስንዴ ዘር ዓይነቶችን ማግኘታቸውን የገለፀው የነሐሴ 17 ቀን 2018 የቢቢሲ ዘገባ «ዓለምአቀፉ የተመራማሪዎች ቡድን ለምርምሩ እንዲረዳው ከ100ሺ በላይ የስንዴ ዘረ- መል ዓይነቶች መለየታቸውን ገልጸዋል።» ሲልም አስነብቧል።

ይህ በጆን ኢንስ የምርምር ማዕከል የሰብል ዘረመል ጥናት ክፍል መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ክሪስቶባል ኡዋይ «ሁላችንም ለብዙ ጊዜ ስንጠብቀው የነበረና በዓለማችን ያለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ወሳኝ ግኝት ስለሆነ፤ ሁሉም የሰው ዘር ደስ ሊለው ይገባል» የተባለለት አዲሱ ግኝት «የስንዴ ምርትን በአስገራሚ ሁኔታ የሚቀይር» መሆኑም ተነግሮለታል።

ሌላውና ዋና አላማውን «ደሃ በሚባሉ ሀገራት የሚገኙ ገበሬዎችን ሕይወት ለማሻሻል ብዙ ምርት የሚሰጡ ዘሮችን በምርምር ማግኘት» ያደረገው ዓለምአቀፉ የበቆሎና ስንዴ ምርት ማሻሻያ ማዕከል እንደሚለው የእስከ ዛሬዎቹ ምርቶች ብዙም አጥጋቢ አይደሉም። የማዕከሉ ዋና ኃላፊ ዶክተር ራቪ ሲንግ እንዳሉት ከሆነ የነበሩት የምርምር ውጤቶች ተለዋዋጭ የአየር ጸባዮችን መቋቋም የማይችሉ ናቸው። ከእንግዲህ ይህ ችግር አይቀጥልም። ምክንያቱም «ከ73 የተለያዩ የምርምር ተቋማትና 20 ሀገራት የተውጣጡ 200 ተመራማሪዎች የተሳተፉበት 21 የስንዴ ዘረ-መል ዓይነቶች ከነቦታቸው ተለይተዋል።» ዶክተሩ እንደሚሉት ይህ የምርምር ውጤት «የስንዴ ምርትን በብዙ እጥፍ የሚጨምር ሲሆን፤ ተለዋዋጭና አስቸጋሪ አየር ንብረት ላላቸው የሦስተኛው ዓለም ሀገራት ወሳኝ መፍትሄ ይዞ» የመጣ ነው።

ይህ የዶክተር ራቪ ሲንግ አስተያየት «አሁንም ቢሆን በዓለማችን የሚመረቱ ሰብሎች የዓለምን ሕዝብ ለመመገብ በቂ ናቸው። ዋናው ችግር ያለው ክፍፍሉ ላይ ነው።» ይህ የሚወራለት ግኝትም «በተገቢ መልኩ የማይከፋፈል ከሆነ አሁንም ብዙ ቁጥር ያለው የዓለማችን ሕዝብ መራቡ አይቀርም» ከሚል ትችት በስተቀር ምንም ተቃውሞ ያልገጠመው፤ አገራት፤ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ አገራት ይጠቀሙበታል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

ወደሀገራችን ስንመለስ በ2005 «የዳቦ ስንዴ አመራረት ቴክኖሎጂዎችና አሠራሮች መመሪያ» በሚል ርዕስ የቀረበ ጥናት እንደሚያሳያው ከሆነ በኢትዮጵያ ስንዴ በስፋት የሚመረትባቸው አካባቢዎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ሲሆኑ በትግራይና ሌሎችም ይመረታል፡፡ በተለይም አርሲና ባሌ ደጋማ ቦታዎች ስንዴ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ አርሲን እንደማሳያ እንመልከት።

አርሲ አቀማመጧም ሆነ የአየር ንብረቷ ልዩ ሲሆን ይህ «ልዩ»ነቷም ለግብርናው ዘርፍ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለማድረጉ መጠራጠር አይቻልም። በተለይ የዞኑን መልክአ- ምድር አቀማመጥ የግብርናውን እንቅስቃሴ በምንም መልኩ የማያውክ መለስተኛ ጉብታዎች – በዘርፉ ለመስራት፤ ሰርቶም ውጤታማ ለመሆን ያለውን ድርሻ በማየት ብቻ መረዳት ይቻላል።

የስንዴ ዝርያ ዓይነቶች ህዳሴ፣ ኦጎልቾ፣ ሁሉቃ፣ ጋምቦ፣ ሾርማ፣ ሆገና፣ ደንደኣ፣ ቀቀባ፣ አሊዶሮ፣ ዲገሉ፣ ከበጀ-01፣ መደወላቡ፣ ፖቨን-76፣ ኢት- 13A2፣ ኬ6295A4፣ ዱረም እና ቱሳ መሆናቸው በባለ ሙያዎች የተለዩ ሲሆን በአርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እየተዘሩ ከሚገኙት አንዱ «ተስማሚ ስለሆነ የተመረጠው» ኦጎልቾ ምርጥ ዘር ነው። ይህም በዘርፉ እመርታን እያሳየች ስለመሆኗ እየመሰከሩላት ይገኛሉ።

በዞኑ ስር የሚገኘው የዲገሉና ጢጆ ወረዳ፤ ፊቴ ከታራ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ሁሴን ሙሳ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፣ ከስድስት ዓመት በፊት ጀምሮ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተሻለ ምርት ማግኘት ችለዋል። ይሁን እንጂ የአሁኑን ዓይነት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አግኝተው ባለማወቃቸው ሊጠቀሙበት አልቻሉም።

አቶ ሁሴን ሙሳ እንዳሉት ከሆነ አርሶ አደሩ ይህን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም ከጀመረ ወዲህ በሄክታር ከ80 እስከ 85 ኩንታል የስንዴ ምርት ማግኘት ችሏል። በአሁኑ ሰዓት በቀበሌው ውስጥ 890 አርሶ አደር ሲኖር 400ዎቹ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ (ዘር መዝሪያ ማሽን) ተጠቃሚ ናቸው፤ ሌሎቹም እንዲቀርብላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።

በአሜሪካ የግብርናው መሥሪያ ቤት ሥር፣ የውጭ ግብርና አገልግሎት በተሰኘው ተቋም «ግሎባል አግሪካልቸራል ኢንፎርሜሽን ኔትወርክ- ጌይን» በተሰኘና የየአገራትን በስንዴ ምርትና ፍጆታ፣ ግብይትና አቅርቦት ረገድ መረጃዎችን ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ «ባለፈው ዓመት ኢትየጵያ 4ነጥብ5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ» ማምረቷን፤ «አብዛኞቹ የስንዴ ምርት ሰንሰለቶች በአሁኑ ወቅት የሜካናይዜሽን እርሻ በመጀመራቸው ጭምር ምርት ሊጨምር እንደሚችል፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለስንዴ ተስማሚ ሁኔታዎች በመኖራቸው በ1ነጥብ66 ሚሊዮን ሔክታር መሬት የሚለማ 4ነጥብ6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንደሚጠበቅ ትንበያው»ን አስቀምጧል።

ባለፈው ግንቦት ወር አዳማ ከተማ በተደረገ አገር አቀፍ ስብሰባ ላይ በመጪው ዓመት ከዋና ዋና ሰብሎች፣ ከአገዳ እህሎችና ከሌሎችም የግብርና ውጤቶች 406 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወቃል። በግብርናው መስክ ቅድሚያ ትኩረት ይሰጣቸዋል ከተባሉት መካከል ስንዴና በቆሎ ምርት ላይ ሞዴል አርሶ አደሮች በሔክታር የሚያመርቱትን መጠን በአገር ደረጃ ለማምረት ጥረት እንደሚደረግም የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሑሴን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ኡመር ሑሴን እንደሚሉት በአነስተኛ ገበሬው ዘንድ በሔክታር እስከ 40 ኩንታል፣ ሞዴል በሚባሉት ገበሬዎች ዘንድ እስከ 100 ኩንታል በሔክታር እየተመረተ ይገኛል። ይህን በአማካይ የተመዘገበ የስንዴ ምርት በአገር ደረጃ ማምረት ከተቻለ ስንዴ ከውጭ ማስመጣት ይቀራል።

በዚህ ፓስታ እና ማካሮኒ ፋብሪካዎች በጣም በተበራከቱበት፣ ፍላጎት እና አቅርቦት መጣጣም ቀርቶ መቀራረብ እንኳን አቅቷቸው ስንዴ በከፍተኛ ምንዛሪ ከውጭ ለማምጣት በተገደድንበት፣ የሕዝብ ቁጥር እድገት በሰከንድ በሚለካበት፣ የውጭ ምንዛሪ እያራገፈን ባለበት አስቸጋሪ ዘመን በግብርናው ዘርፍ፤ በተለይም የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ችላ ሊባል የሚቻል ምንም ነገር የለምና ልንበረታ፤ በአንድ ወቅት በባሌ/ጊነር ላይ በሄክታር 113ነጥብ5 ኩንታል ደርሰንበት የነበረው የማምረት አቅም ሊደገም ይገባል።

አዲስ ዘመን ሀምሌ 1/2011

 ግርማ መንግሥቴ