ፕሮጀክቶችን እንደ ልጅ

24

 የኢፌዴሪ አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛው ዓመት የስራ ዘመን ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ለ2012 በጀት ዓመት 386 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር በጀት አጸድቋል።

ከጸደቀው በጀት ውስጥ የፌዴራል መንግሥት የመደበኛ ወጪ 109 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር / 28 በመቶ/ ለካፒታል ወጪ ብር 130 ነጥብ 71/34 በመቶ/፤ ለክልሎች ድጋፍ 140 ነጥብ 77 /36በመቶ/፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 6 ቢሊዮን /2 በመቶ/ ተደልድሏል። ከበጀቱ ውስጥ የክልሎች ድጋፍ 36 በመቶውን እና የካፒታል ወጪ ደግሞ 34 በመቶውን በመያዝ ከአጠቃላይ በጀቱ ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል።

በጀቱ የተዘጋጀው የ2011 በጀት ዓመት የወጪ አፈጻጸምን በመገምገም፣ የፊሲካል ፖሊሲ አላማን መሰረት በማድረግ ነው። በጀቱ የመንግሥት የፋይናንስ አቅምን ያገናዘበ፣ራስን የመቻል አቅጣጫን የተከተለ፣የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ድህነት ተኮር ለሆኑ ተግባራት ትኩረት የሰጠ መሆኑን የምክር ቤቱ የገቢ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ የበጀት አዋጁ እንዲጸድቅ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተመልክቷል።

የፕሮግራም በጀት አሰራርን የተከተለ ለክልል መንግሥታት እና ለካፒታል ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ፣ በአጠቃላይ በ2012 በጀት ዓመት ለሚተገበሩ የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ቁልፍ የኢኮኖሚና ማህበራዊ አቅጣጫዎች ዓላማዎችን ማሳካት የሚያስችል በጀት መሆኑም በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ተጠቁሟል።

መንግሥት በጀት መድቧል። ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ደግሞ ይህን በጀት በሚገባ ሥራ ላይ ለማዋል በትኩረት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። የገቢ ፣በጀትና ፋይናስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ እንደተመለከተው በባለበጀት መስሪያ ቤቶች በኩል እየታየ ያለው ህግንና ደንብን አክብሮ በመስራት ረገድ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ጉድለት በማይደገምበት መልኩ ሥራ ላይ ማዋል ይገባል።

በጀትን በቁጠባ እና ውጤታማነትን መሰረት ባደረገ መልኩ መጠቀም የሚያስችል የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓት በጥብቅ ዲስፕሊን ሥራ ላይ እንዲውል የክትትልና ቁጥጥር ተግባርን ይበልጥ ማጠናከር ተገቢ ይሆናል ።

እንደሚታወቀው ፤የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ተቀዛቅዟል። ሀገሪቱ በተከታታይ ስታስመዘግብ የነበረው ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት ወደ ነጠላ አሀዝ ወርዷል። የሥራ አጡ ቁጥር በየዓመቱ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ከ11 ሚሊየን በላይ ደርሷል። የዋጋ ግሽበት በተለይ የድሃ ድሃ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል እያጠቃ ይገኛል።

ሀገሪቱ እደርስበታለሁ ያለችው ራዕይ አለ። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት የያዘቻቸው ግቦች አሉ፤ እያደገ የመጣውን የግብርና ምርት ፍላጎት ለማርካት ግብርናውን ማዘመን ትፈልጋለች። በሚቀጥለው ዓመት በመስኖ ልማት ላይ ለውጥ ለማምጣት አቅዳለች። እነዚህ ሀገሪቱ በትኩረት ከምትንቀሳቀስባቸው ተግባሮች መካከል ጥቂቱ ናቸው።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት ከፍተኛ ሚና ሊጫወት በሚችለው በዚህ በጀት ላይ ታዲያ ጥንቃቄ የተሞላበት አጠቃቀም እንዲኖር ማድረግ ወሳኝ ሥራ ይሆናል።

ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ተቋራጮች ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው። በተለይ መስሪያ ቤቶች ከትንሽ አንስቶ እስከ ትልቅ ውጪ የሚጠይቁ ግዥዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ግዥ ከፍተኛ የሀገር ሀብት የሚባክንበት አካባቢ መሆኑ ይታወቃል። ግዥዎች በህግ አግባብ ካልተመሩ ባለፉት ዓመታት በፕሮጀክቶች አፈፃጸም ላይ የታዩ ችግሮች እንዲደገሙ ያደርጋሉ። ይህ እንዳይሆን ከተቋራጮች ጋር የሚደረጉ መሞዳሞዶች ፈጽሞ ሊወገዱ ይገባል።

በፕሮጀክቶች ክትትል ላይ በትኩረት መስራትም ይገባል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በጀቱ በጸደቀበት ወቅት እንዳሉት ፤የመንግሥት ኃላፊዎች ፕሮጀክትን በሪፓርት ላይ ተመስርተው ከመምራት መውጣት አለባቸው። ‹‹ፕሮጀክት መታየትን ይፈልጋል፤ አንድ ልጅ ነው፤ ካላዩት አያድግም›› ሲሉ ነው የመንግሥት ኃላፊዎች ፕሮጀክቶችን ቦታው ድረስ በመሄድ መከታተል እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዘቡት።

በጀቱ በሚገባ ሥራ ላይ ውሎ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ የመንግሥት ኃላፊዎች ፕሮጀክቶችን በአካል ቦታው ድረስ እየሄዱ መመልከት ይኖርባቸዋል። ይህም ለይስሙላ የሚደረግ መሆን የለበትም። ተከታታይነት ያለው እና ለውጥ የሚያመጣ ሊሆን ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኃላፊዎችም ፕሮጀክቶችን የልጆቻቸው ያህል መመልከት ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት ይጠናቀቃሉ፤ የህዝብና ሀገር ፍላጎትም ይሟላል።

እርግጥ ነው ማንም በልጁ ላይ ደባ አይፈጽም።በመሆኑም ፕሮጀክቶች ተገቢው ክትትል ከተደረገባቸው በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት መሰረት ይጠናቀቃሉ፤ጥራታቸውም የተጠበቀ ይሆናል፤ይህ ሲሆን በበርካታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋለው መጓተት እና ሲያስከትል የኖረው ተጨማሪ ወጪ የጥራት ችግርም ይወገዳል። ለዚህም ነው ፕሮጀክቶችን እንደ ልጅ በመመልከት በጀቱን ባግባቡ ሥራ ላይ እናውል ማለታችን።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2011