መንግሥት ከሸጣቸው ድርጅቶች ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ አልሰበሰበም

190

 • 30 ድርጅቶችንም ከስሷል

አዲስ አበባ ፡- መንግሥት በፕራይቬታይዜሽን ወደ ግል ካዛወራቸው 46 ድርጅቶች 5 ቢሊዮን 129 ሚሊዮን 796ሺ 557 ብር መሰብሰብ እንዳልቻለ፣ ገንዘቡን ለማስመለስም 30 ድርጅቶችን መክሰሱን፤ በወቅቱ የማይከፍሉት ላይም ክስ እንደሚመሰርት አስታወቀ።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ያለባቸውን የካፒታል እጥረት ከግንዛቤ በማስገባት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ሲዛወሩ ጨረታውን እንዳሸነፉ 35 በመቶውን፤ ቀሪውን 65 በመቶ ደግሞ በአምስት ተከታታይ ዓመታት እንዲከፍሉ አቅጣጫ ቢቀመጥም፤ ድርጅቶቹ በገቡት ውልመሰረት ክፍያቸውን ባለመክፈላቸው እስከ ሰኔ መጀመሪያ 2011 ዓ.ም ድረስ ያልተከፈለው ገንዘብ 5ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ደርሷል።

ከድርጅቶቹ ያልከተፈለ ዕዳ 4ነጥብ9 ቢሊዮን፣ በርክክብ ወቅት ኦዲት ተደርጎ የሚገኘው ገንዘብና ንብረት 71.9 ሚሊዮን፣ በሊዝ ወይም ድርጅቱን በማከራየት የሚከፈል ገንዘብ 17ነጥብ6 ሚሊዮን፣ የአስተዳደር ኮንትራት ክፍያ 22ነጥብ7 ድርጅቶቹ ከትርፋቸው ለመንግሥት ገቢ የሚያደርጉት ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ከሚያተርፉት ገንዘብ ሳይከፍሉ ወደ ግል የተዛወሩ 34 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዕዳ እንዳለባቸው ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ከ46 ድርጅቶች መካከል የሊሙ እርሻ ልማት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን፣ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ድርጅት 934 ነጥብ 3 ሚሊዮን፣ ሳይገንዲማ ጨርቃጨርቅ አክሲዮን ማህበር 769 ነጥብ9 ሚሊዮን፣ ቴፒ ግሪንኮፊ 368 ነጥብ 4 ሚሊዮን፣ መካከለኛው አዋሽ እርሻ ልማት ድርጅት፣ 337 ነጥብ 8 ሚሊዮን፣ ባሌ እርሻ ልማት 135 ነጥብ 9 ሚሊዮን፣ አርሲ እርሻ ልማት 128 ነጥብ 03 ሚሊዮን፣ ባህር ዳር ጨርቃጨርቅ አክሲዮን ማህበር 115 ነጥብ 2 ሚሊዮን፣ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ አክሲዮን ማህበር 102 ነጥብ 4 ሚሊዮን፣ ባቱ ኮንስትራክሽን አክሲዮን ማህበር 100 ነጥብ 003 ሚሊዮን ሲሆኑ ቀሪዎቹ ድርጅቶች ከ10 ሚሊዮኖች እስከ 66 ብር ዕዳ ያላቸው ድርጅቶች ናቸው።

ዳይሬክተሩ፤ 65 በመቶ ሳይከፍሉ ፋብሪካውን ወስደው በአምስት ዓመታት ውስጥ እንዲከፍሉ መንግሥት አቅጣጫ ያስቀመጠው የአገር ወስጥ ባለሃብቶችን ለማበረታታትና ድርጅቶቹ በአገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲያዙ ፍላጎት በመኖሩ ነው። እንዲያም ሆኖ የሚሸጥላቸው ድርጅቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው እቅምና ሚና። ቀደም ሲል የመንግሥትን ድርጅት ገዝተው ከሆነ ያላቸው ውጤታማነትና ሌሎች መስፈርቶችን መሰረት በማድ ረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ድርጅቶቹ በገቡት ውል መሰረት በወቅቱ ገንዘቡን እንደሚከፍሉ በመተማመን ፤ እዳቸውን ባይከፍሉም ላልከፈሉት ገንዘብ በባንክ ማበደሪያ ወለድና ቅጣት ከዕዳቸው ጋር እንደሚከፍሉ በውል የታሰረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ መንግሥት ለኤጀንሲያቸው በሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አንስተው፤ ድርጅቶቹ በውላቸው መሰረት እዳቸውን እንዲከፍሉ በየጊዜውም በደብዳቤም በአካልም በመሰብሰብና እዳቸውን በወቅቱ ሳይከፍሉ ሲቀሩም ለገንዘቡ በባንክ ማበደሪያ ወለድ እና ቅጣት እንደሚከፍሉም በመግለጽ ከፍተኛ ውትወታ ማድረጋቸውን ያመለክታሉ።

ኤጀንሲው በወቅቱ ድርጅቶቹ ገንዘቡን እንዲከ ፍሉ ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ በውሉ መሰረት የህዝብና የመንግሥት ገንዘብ እንዲከፍሉ ለማድረግ እዳቸውን ያልከፈሉ ረዴድ ስፔክልድ ኢትዮጵያ ትሬዲንግ ኢንተርፕራይዝ፣ ፍራኤል አግሮ አንዱስትሪ፣ ሆራይዘን ፕላንቴሽን፣ ዳክሶስ ፊለርና ላይም ማምረቻ ድርጅት፣ አበባ ግደይ ትሬዲንግ፣ እነገብሩ ሚካኤል፣ ኤ.ቲ.ኤል የግል ማህበር፣ አሚባራ እርሻ ልማት በአርባምንጭ፣ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ሃ.የተ.የግል ማህበር፣ የተባሉ ድርጅቶችን በፍርድ ቤት ክስ በመመስረት አስወስኖ በፍርድ አፈጻጸም ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ብሉናይል ሪዞርት ሆቴል፣ ናስ ፉድስ፣ አሚባራ እርሻ ልማት በመካከለኛው አዋሽ፣ ሜዲሮክ ኢትዮጵያ በላይኛው አዋሽ፣ ሚስተር ፋቲህ መህመት ያንጊን፣ አሚባራ እርሻ ልማት በአባያ እርሻ ልማት፣ አፍሪካ ጁስ ታቪላ፣ ሉሲ እርሻ ልማት፣ ቢኤም ኢትዮጵያ ልብስ ስፌት ጨርቃጨርቅ ሠራተኞች ማህበር፣ ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን፣ ግሪን ካፌ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ዴክ ኦሮሚያ ቢዝነስ ኢንቨስትመንት ሳውዲ ስታር አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት ላይ ክስ መመስረቱን ተናግረዋል።

መንግሥት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 370 ድርጅቶችን እስከ ቅርንጫፎቻቸው ወደ ግል በሽያጭ አዛውሯል። ከዚህም 49 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል። ከሸጣቸው ድርጅቶች ከፍተኛ ዋጋ ያወጣው የትንባሆ ድርጅት ሲሆን፤ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ አስገኝቷል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2011

አጎናፍር ገዛኸኝ