የዛሬ ችግኞች ነገ ዛፍ እንዲሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን ይወጣ!

23

ለቤት ቁሳቁስ መሥሪያ የሚያገለግል ዛፍ አድጎ ለመቆረጥ እስኪደርስ ድረስ ከ60 እስከ 100 ዓመት ሊፈጅበት ይችላል። ዛፍ ቆርጦ ለመጣል የሚያስፈልገው ጊዜ ግን ከደቂቃዎች አይበልጥም። ታዲያ ደኖች ተመናምነው ማለቃቸው ሊያስደንቀን ይገባልን?

ከአፍሪካ ነዋሪዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ምግባቸውን የሚያበስሉት በእንጨት እንደሆነ ይነገራል። የደቡብ አፍሪካው ጌትአዌይ መጽሔት በሰሃራ በረሃ ደቡባዊ ጠርዝ በሚገኝ በረሃማ የምድር ክፍል ባሉ በአንዳንድ ሰፋፊ ከተሞች ዙሪያ እስከ 100 ኪሎ ሜትር የሚደርስ መሬት ደን አልባ ሆኗል።

እነዚህ ዛፎች እንዲሁ ያለምክንያት የተጨፈጨፉ አይደሉም።ለሰው ልጅ ፍጆታ እንጂ፡፡ መፅሄቱም ፕሮፌሰር ሳሙኤል ናና-ሲንካምን ጠቅሶ ሲፅፍ፡- ‹‹አብዛኞቹ የአፍሪካ ሕዝቦች የገዛ ራሳቸውን ከባቢ የሚያወድሙት ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ብቻ ነው›› ብሏል፡፡

የአፈር መሸርሸር ተፈጥሯዊ ሂደት በመሆኑ በሰው ልጅ መጥፎ አያያዝ ምክንያት እግሩ ካልተፋጠነ በስተቀር በጣም አሳሳቢ አይደለም። ለምሳሌ ቻይና ቱዴይ የተባለው መጽሔት ‹‹ አሸዋማ አውሎ ነፋሶች ከደን መጨፍጨፍና ከግጦሽ መሬት መራቆት ጋር ተዳምረው የበረሃማነትን መስፋፋት በጣም አፋጥነውታል ።

በቅርብ ዓመታት በተከሰተው ያልተለመደ ድርቅ ምክንያት የአገሪቱ ሰሜናዊና ሰሜን ምዕራባዊ ክፍሎች በቀዝቃዛው የሳይቤሪያ ነፋስ በእጅጉ ተጠቅተዋል። በሚሊዮን ቶኖች የሚመዘን አሸዋና የአፈር ብናኝ ተጠራርጎ እስከ ጃፓንና ኮሪያ ተወስዷል። በአሁኑ ጊዜ ከቻይና መሬት 25 በመቶ የሚሆነው በረሃ ሆኗል›› ሲል ዘግቧል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ እየተከሰተ ባለው የአየር ንብረት ለውጥና የደን መጨፍጨፍም የዝናብ አጥረት እየተከሰተ በመሆኑ የተራቆቱ ስፍራዎችን ለማዳንና ጥፋቱን ለመታደግ የችግሮቹን መንስኤ በመለየት በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ እንደሚገባ ሲነገር ቆይቷል ።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን የጀመረችው ጥረት የሚበረታታና በአፍሪካ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊስፋፋ የሚገባው ቢሆንም እንኳ የቱን ያክል ርቀት እንደተሄደ ለማወቅ በተግባር ማየት ያስፈልጋል።

የደን ይዞታዋ በተመናመነው ኢትዮጵያ የዘርፉን ልማት ለማጠናከር ያለመ የደን ልማት ብሔራዊ መርሃግብር ይፋ ቢደረግም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልቱን እውን ለማድረግ ምን ያህል ጥረት ተደርጓል የሚለውም ያነጋግራል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ‹‹ አረንጓዴ ኢኮኖሚ›› በዓለም አቀፍ ደረጃ ሞገስ እያገኘ የመጣ ጽንሰ ሃሳብ ነው። በ2002 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት የመጀመሪያውን የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲያስተዋውቅ በአሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ ሁሉም ዜጋ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያለው የሚያደርግ ኢኮኖሚ የመገንባት አላማን መሰረት አድርጎ እንደተነደፈ ይፋ አድርጓል፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ይህ መካከለኛ ገቢ ያለው ኢኮኖሚ አረንጓዴና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በዚሁ ዓመትም የኢትዮጵያ መንግሥት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ማውጣቱ ይታወሳል ፡፡ ይህ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ አፍ ሞልቶ መናገር ባያስደፍርም ውጤታማ አልነበረም ማለት ግን አይቻልም፡፡

ስለቀጣዩ ትውልድም ሆነ ስለ አገራችን ዕጣ ፈንታ ማሰብ የሰውነት ባህሪይ ሊሆን ከተገባ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለተያያዙ ምክንያቶች የመፍትሄ ርምጃዎች መውሰድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ የ4 ቢሊዮን ችግኞች ተከላ መርሐ ግብርን በይፋ ማስጀመራቸውም የሀገሪቱ ወቅታዊ የደን ሽፋንና የመሬት መራቆትን ያገናዘበ እንደሆነ ልብ ይሏል።

በዚህ ክረምት 4 ቢለዮን ችግኝ ይተከላል ተብሎ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ፤ የዛሬ 11 ዓመት በሚሊኒየሙ በጣም ብዙ ለመጥራት የሚከብዱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዛፍ ችግኞች እንደተተከሉ መነገሩ የታወሳል፡፡ ‹‹ ለመሆኑ እነርሱ ከምን ደረሱ? ደኖቹ የት አሉ?» ብለን ብንጠይቅ በቂና በመረጃ የተደገፈ መልስ የሚሰጥ ስለማይኖር በቀጣይ የምንተክላቸውም የሚሊኒየሙ ዕጣ እንዳይደርሳቸው ከወዲሁ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ፡፡

የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀምና ምድር እነዚህን ሀብቶች ለመተካት ባላት ችሎታ መካከል ያለው ልዩነት የሚለካበት ዘዴ ሥነ ምሕዳራዊ ዱካ ቢባልም እንኳ፤ ሰዎች የተፈጥሮን ሀብት ሊተካ በማይችል ፍጥነት እያሟጠጡት መሆናቸውን በመገንዘብ በራሳችን ፍላጎት ለጥፋት ከመዳረጋችን በፊት ራሳችንን ማቀብ ያስፈልገናል ፡፡

በአሁኑ ወቅት 4 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞች ለመትከል መታቀዱ መልካም ዜና ቢሆንም መረን የለቀቀ የግጦሽ ልማድ ባለበት ሁኔታ ውጤት ማየት የሚከብድ ይሆናል። ስለዚህም የተዘጋጁት ችግኞች አድገውና ለችግሮቻችን መፍትሄ ሆነው እንድናይ በያዝነው የሐምሌ 22 ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል በእቅድ የተያዙትን ጨምሮ በእንክብካቤ የዛሬ ችግኞች ጸድቀው ነገ ዛፍ እንዲሆኑ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆን አለበት፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2011