የክረምት ወቅት የሰላምና የልማት ተልዕኮ

30

 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመረጣቸው ሕዝብ እነማን እንደሆኑ እስኪዘነጓቸው ድረስ ከሕዝብ ጋር ያላቸው ግንኙነት የራቀ እንደሆነ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ይናገራሉ።

ምክር ቤቱ በክረምት ለሁለት ወራት ለእረፍት የሚዘጋው አባላቱ ተልዕኮ ይዘው ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት እድል እንዲያገኙ በመታመኑ እንደሆነም ይታወቃል። አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ሙሉ ለሙሉ ባይቀበሉትም ክፍተት መኖሩን ግን አልሸሸጉም።

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የመርቲ ወረዳን ሕዝብ ወክለው ሁለት የምርጫ ጊዜያቶችን በኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፉት ወይዘሮ ሰአዳ ከድር ምክር ቤቱ ለእረፍት በሚዘጋበት ወቅት ሁሉም አባላት እኩል ኃላፊነት ይዘው ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ይገናኛሉ ለማለት አልደፈሩም። ነገር ግን ሁኔታው እንደ አባላቱ ጥንካሬ እንደሚወሰን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

እንደ ወይዘሮ ሰአዳ ገለፃ በአመራርነትና በሥራ አስፈጻሚነት ላይ የሚገኙ የምክር ቤት አባላት የተባለውን ጊዜ ከሕዝቡ ጋር ላይቆዩ እንደሚችሉም ይናገራሉ። ሆኖም ግን ሥራ እንዳልተሰራ ተደርጎ የሚወሰድበትን አግባብ ይቃወማሉ።

አባላት ከወከላቸው ሕዝብ ጋር መወያየታቸው ተገቢ ነው። ብዙ ችግሮችን ለመፍታት፣ የጋራ መግባባት ለመያዝ፣ የመንግሥትን አቅጣጫ ለማሳወቅና ሕዝቡም በወከለው አባል ላይ አመኔታ እንዲኖረው ትልቅ ሚና ይጫወታል።

አባላቱ በየክረምቱ ከወከላቸው ሕዝብ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ ሙሉ ለሙሉ የተፈቱ ችግሮች አሉ ብለው ባያምኑም ችግሮችን ለመፍታት የሚወስዷቸው እርምጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ የሚያመጡ ሆነው እንዳገኟቸው አስታውሰዋል። በተለይ በአካባቢው ነዋሪዎችና አመራሮች ሊፈቱ በሚችሉ ችግሮች ላይ ጥሩ መግባባት መፈጠሩን እንደመልካም ተሞክሮ ይወስዳሉ።

አባላት አቅጣጫ ይዞ ወደተመረጡበት አካባቢ መሄድ በምክር ቤቱ የተለመደ አሰራር መኖሩን የሚጠቁሙት ወይዘሮ ሰአዳ በአሁኑ ክረምት ሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጠውና ከሕዝብ ጋር እንደሚወያዩ ገልጸዋል። ሀገር ከሌለ ውክልናም ሆነ በግለሰብ ደረጃ መኖር እንደማይቻልና ልዩነት ቢኖርም መለያየትን የሚያመጣ መሆን እንደሌለበት አመልክተዋል።

በደቡብ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሱርማ አካባቢን የወከሉት አቶ ባርዱላ ኦሎቡሴኒ በበኩላቸው የሕዝብ ውክልናን አለመወጣት አልፎ አልፎ እንደሚኖር ጥርጣሬ አላቸው። አብዛኛው ሕዝብም የወከለውን ሰው የማግኘት እድል አለው ብለውም አያምኑም። በእርሳቸው አካባቢ ግንዛቤው አነስተኛ እንደሆነም ለአብነት ይጠቅሳሉ።

እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ፣ሕዝብ የወከለውን እንዲጠይቅና ጥያቄውንም ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርብለት የማድረግ መብት እንዳለው ግንዛቤ እስከመፍጠር ድረስ ተወካዩ በመስራት ውክልናውን መወጣት እንዳለበት ይገልጻሉ።

የወከላቸው ማህበረሰብ አርብቶአደር በመሆኑ ከግጦሽ ጋር በተያያዘ ከአዋሳኝ ሀገሮች ጋር የሚከሰቱ አለመግባባቶችን እንዲሁም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስቀረት፣የተከናወኑ እና ያልተከናወኑ የልማት ሥራዎችን መከታተልና መደገፍም እንደሚጠበቅባቸው አስረግጠው ይናገራሉ። ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አንዱ በጋብቻ ወቅት ለጥሎሽ ሲባል እስከ ስርቆት የሚደርስ ከብት የማምጣት ሁኔታን ለማስቀረት ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ትኩረት ተችሮታል።

በአምስተኛው የምርጫ ዘመን መመረጣቸውንና በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሁቦ ጠበላ ወረዳ የተመረጡት አቶ አያሌው አይዛ ‹‹አባላት ከሕዝብ ጋር አይገናኙም› የሚለው ሐሳብ እኔን አይመለከተኝም፤ ጊዜዬን ለመረጠኝ ሕዝብ ነው የማውለው›› ብለዋል። ነገር ግን ክፍተት ካለ ለማሻሻል ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በክረምቱ ከሚኖራቸው ተልዕኮም ከሁሉም በላይ ሰላም መቅደም እንዳለበትና ከወከላቸው ሕዝብ በተለይም ከወጣቱ ጋርም ጠንከር ያለ ምክክር እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ። በመቀጠልም በሀገር ደረጃ አረንጓዴ ልማትን ለማጠናከር ሕዝብን ያሳተፍ የችግኝ ተከላ እንዲከናወን ከወዲሁ ተዘጋጅተዋል።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የአልቡኮ ወረዳን ሕዝብ ወክለው ለሶስት የምርጫ ጊዜ በምክር ቤቱ የቆዩት ወይዘሮ ብርቱካን ሰብስቤ ስለ ሌሎቹ አስተያየት መስጠት ቢቆጠቡም በግላቸው ሳያቋርጡ በአመት ሁለት ጊዜ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ለመወያየት ወደተመረጡበት አካባቢ በቀበሌ፣ በወረዳና በዞን በየደረጃው ሊፈታ የሚችለውን ከአመራሮች፣ከአስፈጻሚ ተቋማትና ከክልል ተመራጮች ጋር በጋራ ለመፍታት ጥረት አድርገዋል።

እንደሀገር የህብረተሰቡ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲፈቱና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት በማድረግ የሕዝብ ውክልናቸውን ለመወጣት ጥረት ያደርጋሉ። ከሌሎች ጋር በመሆን ሥራዎችን በየጊዜው በመገምገም ክፍተቶችን ለመቅረፍ የተደረጉት ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ሕዝብን የሚያረካ ነው ብለው ባያምኑም ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ አስተያየት የሰጡት የምክር ቤት አባላት በዘንድሮ የክረምት ወቅት በሚኖራቸው የእረፍት ቆይታ በሰላም እና በልማት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። በመሆኑም አባላቱ የሰላም እና የደህንነት ስራዎች ቁልፍ ተልዕኳቸው መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2011

 ለምለም መንግሥቱ