ያለ ጥናት የሚወጠኑ ፕሮጀክቶች ኪሳራን እንዴት እንታደግ?

16

የሀገራችንን የኢኮኖሚ እድገት እየተፈታተኑ ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ በተያዘላቸው ጊዜና ወጪ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። ባለፉት 7 ዓመታት ብቻ በተያዘላቸው ጊዜ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በእቅዳቸው ባለመጠናቀቅ በየዓመቱ በሚመደብ በጀት ላይ ጫና ከማሳደር ባለፈ ያስከተሉት ተጨማሪ ወጪ 43 ቢሊየን ብር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ደመቀ እንደሚገልፁት በ2011 ዓ.ም በፌዴራል ደረጃ እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች ከ1 ሺ በላይ ናቸው። የእነዚህ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ የኮንትራት ዋጋም 593 ቢሊየን ብር እንደነበር አስታውሰው አሁን አጠቃላይ ወጪያቸው 6 መቶ 34 ቢሊየን ብር ማሻቀቡን አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ታደለ ፈረደ በመጀመሪያውና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የተጀመሩ ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች እስከ አሁን ተፈጻሚ መሆን አልቻሉም ይላሉ።

ለዚህም እንደምክንያት የጠቀሱት መንግሥት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲል ብቻ በቂ የሆነ የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግባቸው ፣ተገቢ የሆነ የዲዛይን ሥራ ሳይሰራላቸው የተጀመሩ በመሆኑ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ። አብዛኛዎቹ ከተጀመሩ በኋላ ዲዛይን የተሰራላቸው እንደሆኑና የፕሮጀክት አስተዳደር ያለመኖሩ፣ ግምገማና ክትትል ያለመደረጉም ይህን ያህል ቢሊየን ብር ተጨማሪ ወጪ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴም የዶክተር ታደለን ሀሳብ ያጠናክራሉ፤ ባለፉት ዓመታት የተጀመሩት ፕሮጀክቶች በተገቢው መንገድ ሳይጠኑ፣ ሳይገመገሙ፣ የአዋጭነት ጥናት ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግላቸው እንደነበር ገልፀዋል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ወጪ እያስወጡ እንዳሉና በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ኢኮኖሚውን ለማገዝ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

 እነዚህ ፕሮጀክቶች አንዱ አልቆ ሌላው እንዲጀመር መደረግ ሲገባቸው ሁሉም በአንድ ላይ መጀመራቸው በመንግሥት ላይ ትልቅ ጫና ፈጥረዋል የሚሉት ዶክተር ታደለ ፕሮጀክቶቹ በውጭ ብደር የተጀመሩ በመሆኑ ተሰርተው አልቀው ዕዳ መክፈል ሳይጀምሩ የዕዳ መክፈያ ጊዜያቸው መድረሱ ሌላ ኪሳራ መሆኑን ተናግረዋል።

ገንዘብ ሚኒስቴር ይህን ሁሉ ኪሳራ ተጠያቂ ያደረገው አካል ያለማቅረቡና በአንዲት ደሀ ሀገር ይህ ሁሉ ሀብት እንደዋዛ መባከኑ የሚያስቆጭ እንደሆነ ዶክተሩ በቁጭት ይናገራሉ።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ እንደሚሉት እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ ለሀገራችን ዕድገት አስተዋጽዖ ያደርጋሉ በሚል ታስበው ነው። ነገር ግን ሀገሪቱ ያላት የሰው ሀይል፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ የፕሮጀክቶቹ አዋጭነት ፕሮጀክቱ በሚፈልገው ነገር ልክ ሳይጠና ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው በበለጠ ለፖለቲካ ፋይዳ ሲባል ብቻ ወደ ሥራ የተገባበት ነበር ሲሉ የዶክተር ታደለን ሀሳብ ያጠናክራሉ።

መንግሥት ከፕሮጀክቶቹ ውጤታማነት ይበልጥ ‹ልማታዊነቴ እየጨመረ ነው› የሚለውን አስተሳሰብ በእርዳታ ሰጪዎችና በህዝቡ አዕምሮ ውስጥ ለማስቀመጥ በማሰብ ያደረገው ትልቅ ኪሳራ ነው ሲሉ ዶክተር ዳዊት ይወቅሳሉ።

‹‹በእኛ ሀገር ኢኮኖሚ ይቅርና የተሻለ አቅም ባላቸው ሀገሮችም ቢሆን እነዚህን ትላልቅ ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ መጀመር ብቻ ሳይሆን ጀምሮ ማቋረጥም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ክስረትን ያስከትላል።

‹የነብርን ጭራ አይያዙ ከያዙ አይለቁ› እንደሚባለው በትልቅ ወጪ የጀመርነውን ፕሮጀክት ማቆም ትልቅ ዋጋ የሚያሥከፍል ይሆናል። መንግሥት ፕሮጀክት አስተዳደሩን ማስተካከልና ተጠያቂ የሀብት አጠቃቀምን ማስፈን ይኖርበታል።›› ሲሉ ዶክተር ዳዊት ምክረ ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው ለፕሮጀክት ሥራ መጓተት መንስኤ ነው ያሉትን ሀሳብ አንስተዋል። ‹‹ኮንትራክተሮቻችን ከዓመት ዓመት ለውጥ እያመጡ መሆኑ ቢታመንም መጥፎ ባህል አላቸው።

በተመደበው ገንዘብ እና ጊዜ እጨርሳለሁ በሚል ጨረታ ካሸነፉ በኋላ ሥራውን አስተኝተው ከሁለት ዓመት በኋላ ከመንግሥት ዕቅድ ውጭ ተጨማሪ ወጪ /price scala­tion/ በሚል አንዳንዴ እንዲያውም መጀመሪያ ከተዋዋሉት በጀት ጭማሪ ይጠይቃሉ።››

ኮንትራክተሮች ሁለት ኃላፊነት እንዳለባቸው ማስተዋል ይኖርባቸዋል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክረ ሀሳብ ያሉትን አስቀምጠዋል። አንደኛው የዕለት እንጀራቸውን ማከናወንና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ሲሆን ሁለተኛው ግን የሚሰሩት ሥራ የራሳቸው ጉዳይ መሆኑንና በቀጣይም ለልጆቻቸው የሚተርፍ እንደሆነ መረዳት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ፕሮጀክቶች በየዓመቱ ተጨማሪ ወጪ እያስወጡ የሚቀጥሉ ከሆነ በመጀመሪያ ደረጃ የሀገሪቱን በጀት ያናጋሉ፤ መንግሥት በጀቱን አመጣጥኖ ለተለያዩ ተግባራት ከማዋል ይልቅ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ በጀት እንዲመደብ ይገደዳል። ይህም የሀገሪቱ ሀብት ወደ አንድ ጉዳይ ብቻ እንዲከማች በማድረግ ተጽዕኖ ያሳድራል ሲሉ የችግሩን አስከፊነት አስረድተዋል።

በተደጋጋሚ ለነዚህ ፕሮጀክቶች ትልቅ ኢኮኖሚ በሚመደብ ወቅት ሌሎች በወቅቱ ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ፕሮጀክቶች ሳይሰሩ ይቀሩና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲቀጭጭ ያደርጋል። በአንድ በኩል እየወፈረ በሌላ በኩል እየቀጨጨ የሚሄድ ኢኮኖሚ ደግሞ ያልተመጣጠነ ይሆናል ሲሉ ዶክተር ዳዊት ይናገራሉ።

ያልተመጣጠነ ኢኮኖሚ በአንድ በኩል ምርት እንዲጨምር ያደርጋል፤ በሌላው በኩል ደግሞ ምርት እንዲቀንስ ትልቅ እንቅፋት በመሆን የዋጋ ንረት ሊከሰት ይችላል የሚሉት ዶክተር ዳዊት በሌላ በኩል ሥራ አጥነት እየተስፋፋ በመሄድ ሀገሪቱንም እዳ ውስጥ እንድትዘፈቅ የማድረግ እድሉ ከፍተኛ ነው ሲሉ የችግሩን አስከፊነት አስረድተዋል።

ይህ ችግር ሄዶ ሄዶ ሀገሪቱ የምታገኘውን ገቢ ልማት ላይ ከማዋል ይልቅ በዕዳ መክፈል ላይ እንድትታጠር ያደርጋል ብለዋል።

ስለዚህ በ2012 ዓ.ም የሚጀመሩት አዳዲስ ፕሮጀክቶች አቅምን መሰረት ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም አሁን ያለንበት ኢኮኖሚ እራሱ የሚያስፈልገው ምን እንደሆነ ይናገራል።

በዚሁ መሰረት በሚያስፈልገው ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠትና ወደ ሥራ ከመገባት በፊትም በቂ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ምሁራኑ ልዩነት አይታይባቸውም። ውጤታማ የሆነ ግምገማና ክትትል ማድረግም ግድ እንደሆነ መክረው በዚህ ሂደት መጓዝ ከተቻለ ቀደም ሲል የተከሰተውን ችግር ላለመድገም እድሉ ሰፊ ነው ብለዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2011