ፊላንድና ደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ይደግፋሉ

16

አዲስ አበባ፡- የፊላንድና የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያ በቀጣናውና በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በፅህፈት ቤታቸው የሁለቱን አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተቀብለው ካነጋገሩ በኋላ ሚኒስትሮቹ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በሱዳን የተከሰተውን ችግር መፍትሄ ለመስጠት እያደረገች ያለው ጥረት የሚያስመሰግናት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ አንስተው በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማት እንዲመጣ የምታደርገውን ጥረት በማድነቅ ድጋፋቸውም እንደማይለይ አመልክተዋል።

የፊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚስተር ፓካ ሃቪስቶ፤ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተው ኢትዮጵያ በሱዳን የሰላም ሂደት ላይ እየተወጣች ያላቸውን ኃላፊነት በማድነቅ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ፊላንድ በቀጥታና በአውሮፓ ህብረት በኩል በኢትዮጵያ ልማት ድጋፍ ስታደርግ እንደነበር አስታውሰው በቀጣይም አገሪቱን በትምህርት፣ በሥራ ፈጠራ እና በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዙሪያ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስ ካንግ ኩንግ ዋሃ፤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የምታደርገውን የሰላም ሥራ እንደግፋለን ብለዋል። ደቡብ ኮሪያ ኢትዮጵያን በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ሁለቱን አገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶችን እንደሚደግፉም አመልክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሰክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ ፊላንድ ኢትዮጵያ በሱዳንና በቀጣናው ሰላም እና ቀጣናውን ለማስተሳሰር የምታደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ማረጋገጧን ተናግረዋል።

ደቡብ ኮሪያም በኢትዮጵያ ልማትና በትምህርት ድጋፍ ታደርጋለች። በተለይም የገቢዎችና ጉምሩክ ተቋምን ለማሻሻል ባለሙያተኞችን ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ለማሰልጠን ፍቃደኛ ሆናለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደቡብ ኮሪያን እንዲጎበኙ ግብዣ ቀርቦላቸው መቀበላቸውን ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2011

 አጎናፍር ገዛኸኝ