አብሮነታችን ይጎልብት፤ መንደርተኝነትና ዘረኝነት ይክሰም!

18

የጥንት አባቶቻችን በየዘመኑ ከተነሱ ወራሪ ጠላቶች ጋር ተፋልመውና ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው ባቆዩልን የጋራ ሀገራችን ውስጥ እትብታችን በተቀበረበትና ለዘመናት በሰላም በኖርንበት መንደር አሁን ላይ አብረን መኖር እንኳን እየተሳነን አንዳችን ባለሀገር፤ ሌሎቻችን ሀገር አልባ፤ አንዳችን ተፈናቃይ፤ ሌሎቻችን አፈናቃይ፤ አንዳችን ተባራሪ፤ ሌሎቻችን አባራሪ እየሆን በእርስበርስ ጥላቻ ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡

በዚህ ሁኔታ አስከመቼ መዝለቅ እንችላለን? ይህ ሊሆን እንደሚችል ቀድሞውኑ ሲነገረን የነበረና አካሄዳችንን ካላስተካከልን በስተቀር አያያዛችን ሩቅ እንደማያዘልቀን፤ ወደፊትም ከአሁኑ በእጅጉ የከፋ ችግር ውስጥ ሊያስገባን እንደሚችል ቀደም ተብሎ ምክር ቢለገሰንም በጉዳዩ ለመስማማትም ለመግባባትም ባለመፍቀዳችን ይኸው ለዚህ ችግር ተዳርገናል፡፡

አሁንም ከዚህ ሁሉ ቀውስ በኋላ በመፍትሄው ላይ ለመስማማት ዝግጁነቱ እንደሌለን የሚያሳዩ ፍንጮችን እያየን ነው፡፡ በጋራ ችግሮቻችን ላይ ሳይቀር ሊያስማማን የሚችል መፍትሄ ማስቀመጥ ቢያቅተን ቢያንስ ችግር መኖሩን እንኳን አምነን ለመቀበል ፅኑ አቋም ሊኖረን ግድ ነው፤ ወቅቱም ከዚህ ውጭ ያስቀመጠልን መፍትሄ የለምና፡፡

እጅግ ጥብቅ የነበረው የእርስበርስ ግንኙነታችንና ለዘመናት የቆየው አብሮነታችን አደጋ ላይ መውደቁ አሳስቧቸው መፍትሄ እንዲፈለግ ገና ከጠዋቱ ሲያስጠነቅቁ የነበሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ሊደመጡ ይገባል፡፡

የአማራዎች ከደቡብ መፈናቀል፤ የትግሬዎች ከጎንደር መፈናቀል፤ በሶማሌና በኦሮሞ መካከል በተነሳው ቀውስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል፤ በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ‹መጤዎች› በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ ከአካባቢዉ መፈናቀል ሲታይ በሽታው በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተዛመተ መሆኑን መረዳት አያዳግትም፡፡

እናም የዚህ ዓይነቱ ቀውስ በትንሽም ቢሆን መከሰት እንደጀመረ ወደፊትም እየከፋ ሊሄድ እንደሚችል በአንዳንድ ወገኖች የተሰጠንን ማሳሳቢያ በግብዓትነት ብንወስድ ምን ያህል ያግዝ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡

እንደ አሁኑ ባይሆንም ያለመግባባታችን ጉዳይ በፊትም የነበረ ነው፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊትም የማንስማማባቸው ብዙ ጉዳዮች ነበሩን፡፡ ሌላው ቀርቶ ከአስርና ከሃያ ዓመታት በፊት በዚሁ አሁን ባለንበት ስርአትም ቢሆን ያልተስማማንባቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የቀድሞው አለመግባባታችን ኢትዮጵያን እንዴትና በምን ዘዴ እናበልጽጋት? የተሻለው የልማት መንገድ የቱ ነው? ዲሞክራሲያዊ ስርአትን እንዴት እንገንባ? ፍትህና መልካም አስተዳዳርን እንዴት እውን እናድርግ? ወዘተ… በሚል የአካሄድና የስልት ልዩነት ከመሆን ያለፈ አልነበረም፡፡

በአንጻሩ ዛሬ አለመግባባታችን የኢትዮጵያን ህልውና፣ የህዝቦችን ብሄራዊ ጥቅምና አንድነት የመፈለግና ያለመፈለግ፤ በአጭሩ ለኢትዮጵያ ጥብቅና የመቆም፣ የኢትዮጵያን ህልውና የማሳጣትና መቃብር የመማስ ጉዳይ እየሆነ ይታያል፡፡

እንደዚህ ባይሆን ኖሮማ፤ ለጋራ ሀገራችን ሁላችንም እኩል ፍቅር ቢኖረን ኖሮማ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅም በልጦብን በዚህ ደሃ ህዝብ ላይ ዓይን ያወጣ ዝርፊያ ባላከሄድን ነበር፡፡ ነባሩና ሌሎች ሀገሮችን ሲያስቀና የነበረው የአብሮነታችን እሴት ቀጭጮ በመንደር፤ በቋንቋና በጎጥ እየተቧደንን አርስበርስ ባልተጣላን ነበር፡፡

ለዚህች ሀገር ሁላችንም እኩል ፍቅር ቢኖረን ኖሮ አትዮጵያዊ መሆንና መባል አስጠልቶን ዜግነታችንን ባልካድን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን መሆኑ ያበቃ ይመስል በየዕለቱና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ ክልል፣ ስለመንደር፣ ስለጎጥ ፣ ስለ ልዩነታችን፣ ስለ ጥንቱ የጨቋኝና የተጨቋኝ፣ የወራሪና የተወራሪ የፈጠራ ታሪክ ካልሆነ በስተቀር በጋራ የሚያስማማን የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ የአደባባይ አጀንዳ መሆኑ አክትሟል፡፡

የአሁኑ አለመግባባታችን የርዕዮተዓለም ልዩነት ያመጣው ፤የልማትና የዲሞክራሲ ማሳለጫ ንድፈሃሳብ ልዩነት የፈጠረው፤ ፈጣን እድገት በማምጣት የተሻለ አቋራጭ መንገድ በመምረጥ ላይ የተፈጠረ ልዩነት ሳይሆን መሰረታዊ የሆነ የኢትዮጵያዊነትና የጸረ ኢትዮጵያዊነት የአቋም ልዩነት የፈጠረውና በርስበርስ ጥላቻ የታጀበ ባላንጣነት ነው፡፡ የአሁኑ ልዩነታችን ከራሳችን በላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም በማስቀደምና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ይልቅ የራስን ጥቅም በማስቀደም መካካል ያለ የፍላጎት ግጭት ነው፡፡

ልዩነቶቻችንና አለመግባባቶቻችን የኢትዮጵያዊነትን ፋይዳ ከጊዜያዊ ጥቅም አንጻር ብቻ በማየትና ኢትዮጵያዊነትን የህልውናችን መሰረትና የኩራታችን ምንጭ አድርጎ በማየት መካከል ያለ መሰረታዊ ልዩነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲደላን የምንኮራበት፤ ሲከፋን ደግሞ የምናፍርበት ሊሆን ባልተገባ ነበር፡፡

ኢትዮጵያዊነት ሲያሰኘን የምናጌጥበትና ካላሰኘን ደግሞ አውልቀን የምንጥለው ካባ ባልሆነም ነበር፡፡ አሁን እየሆነ ያለው እንደዚያ ይመስላል፡፡ ልዩነቶቻችን እየበዙ በሁሉም ነገር መግባባት የተቸገርንበት ዋነኛው መነሻም ይኸው ለሁሉም ጉዳይ የራስን ጥቅም ከሀገር በላይ ማስቀደማችን ነው፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2011