«በፖለቲካ ለውጥ ውስጥ የሚሞተውና የሚወለደው ስርአት የሚያደርጉት ግብግብ ከባድ ነው» መሪ አቶ አንዷለም አራጌ

19

ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አገራችን አስደናቂና ሙገሳን ያተረፈላትን የፖለቲካ ሽግግር ለማድረግ መንገዱን ጀምራለች። ለውጡ በህዝብ አመፅ እና በገዢው ፓርቲ ድርጅቶች መካከል የተፈጠረውን ሽኩቻ ተከትሎ የመጣም ነበር። ይህ ለብዙ ሀገር ወዳድ ዜጎች የልብ ስብራትን የጠገነ፣ ተስፋን ያለመለመ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ይህ አዲስ የዴሞክራሲ ሽግግር መደነቃቀፍ እየገጠመውም ቢሆን አሁን ላይ ደርሷል። ለውጡን እየተገዳደሩት ያሉ ችግሮች አይነታቸው ይለያያል። ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ስርአት አልበኝነት፣ ማፈናቀል እና በሁሉም ችግሮች ውስጥ የሚገኘው ግጭት እየተደረገ ባለው የፖለቲካ ሽግግር ላይ እንቅፋት እየሆኑ እና አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረጉ መሆኑ በግልፅ እየታየ ነው።

ግጭት ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉ አለማቀፍ እውቅና ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ግጭት ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መካከል በፍላጎት፣ በአመለካከት፣ በአላማ፣ በታሪክ፣ በእሴትና በባህል አለመስማማት የሚከሰት፣ በሰው ተወዳዳሪነትና በተፈጥሮ ሃብት ውስንነት ምክንያት የሚመጣ ማህበራዊ መስተጋብር ነው። ግጭቶች አሉታዊም፣ አውንታዊም ጎን አላቸው። በአውንታዊነት ችግሮችንና የችግሮችን መንስኤ ለመለየት፣ የአንድን ፓርቲ ህልውና ለመለካት፣ ፖሊሲዎችንና ሰትራቴጂዎችን ለመፈተሽና የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ይጠቅማል። በአሉታዊነቱ ደግሞ ለሰው ሞት፣ለሰላም መጥፋት፣ ለአካል መጉደል፣ ለንብረት መውደም፣ ለግንኙነት መበላሸትና ለሀገር አንድነትና ህልውና ስጋት ይሆናል።

አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ላለው ብሄር ተኮር ግጭት በማባበስም ሆነ በማነሳሳት የፖለቲካ ትርፍ እናገኛለን ያሉ ወገኖች መሆናቸው የአደባባይ ሚስጢር ሆኗል። የፌዴራሉ መንግስትም ይህንን ያምናል። የፖለቲካ ቁማር ሚሊዮኖችን እያፈናቀለ ስለመሆኑ ሁሉም ይስማማበታል። በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ማፈናቀልን የፖለቲካ መሪዎች የፍላጎቶቻቸው ፈረስ አድርገውታል። ግጭት ይኖራል፤ መፈናቀል ይከሰታል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ‹‹አይ ኦ ኤም›› ቁጥርም ይህንን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። 2011 ዓ.ም በወርሃ ጥር የወጣው የድርጅቱ ሪፖርት ከሶስት ሚሊዮን የሀገሪቱ ተፈናቃዮች ውስጥ ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑት ግጭትን ተከትሎ የተፈናቀሉ ናቸው ይላል። አጥኚዎቹ የሀገራችንን የውስጥ መፈናቀል በአራት ይከፍሉታል። እነዚህም የተፈጥሮ አደጋ ክስተቶች፣ የኢኮኖሚ ጫና፣ የልማት መፈናቀል እና ግጭት መር /ኮንፍሊክት ኢንዲዩስድ ዲስፕለስመንት/ መፈናቀል ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ግጭት መር መፈናቀል ብዙ ጊዜ በተጠና ሁኔታ ስለሚፈፀም የበለጠ አደገኛ መሆኑን ጉዳዩን የታዘቡ ሁሉ አይስቱትም።

ዶክተር መሀሪ ታደለ ‹‹ኮዝስ ዳይናሚክስ ኤንድ ኮንሲኮንሲስ ኦፍ ኢንተርናል ዲስፕሌስመንት ኢን ኢትዮጵያ›› በተሰኘ ጥናታቸው ግጭት መር መፈናቀል የህዝብ አሰፋፈርን /ዴሞግራፊን/ ለመቀየር ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ ነው ይላሉ። ይህም ለዓመታት በአስተዳዳሪዎች ሲሰራ እንደነበር ይናገራሉ። በሀገሪቱ ያለው የፌዴራል አወቃቀር ማንነት ላይ ስለሚያተኩር ‹‹በቁጥር መብዛት የመወሰንን እድል ከፍ ያደርግልናል›› በሚል እሳቤ ማፈናቀሉ እንደሚፈፀምም አጥኚው ይተነትናሉ። የፖለቲካ ልሂቃን የአካባቢያቸውን ሀብት በቁጥጥር ስር ለማዋል ማፈናቀልን ይጠቀሙበታል። በጉጂ ዞን ያለው የቡና ሀብት የአፈናቃዮቹን ትኩረት በግልፅ እንደሳበ ብዙዎች ይገምታሉ። ለዚህም እንደምሳሌ የሚገልፁት በዞኑ ያሉ የቡና መፈልፈያና መካከለኛ ፋብሪካ ያላቸው ሰዎችም የግጭቱ እና መፈናቀሉ ሰለባ መሆናቸውን ነው። ይህ የሀብት ቅርምት ተፈናቃዮች ዳግም ወደነበሩበት ቦታ ድርሽ እንዳይሉ ማሳዎችን እስከማቃጠል የሚደርስ ነው። በርካታ ተፈናቃዮችም መጥተው በሚጎበኟቸው የመንግስት ሰዎች በተደጋጋሚ የሚናገሩት ‹‹ዋናዎቹ አፈናቃዮች በቦታው እያሉ እንዴት እንመለሳለን›› የሚል ነው።

የሀገራዊው ምርጫ መድረስም ለማፈናቀሉ አንድ ምክንያት የሆናቸው አስተዳዳሪዎችም አሉ። ማፈናቀል ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ለማስ መለስ መደራደሪያም መሆኑ ይነገራል። በአን ዳንድ መፈናቀል ባለባቸው ቦታዎች ባሉ አስተዳ ዳሪዎች ‹‹ተፈናቃዮቹን መልሷቸው›› ሲባሉ ‹‹የአስተዳደርና ማንነት ጉዳያችንስ ምን ደረሰ›› ብለው በድፍረት እስከመጠየቅ ደርሰዋል።

የሚጓ ጓዝን እህል ‹‹ቅድሚያ ለኛ ይሰጠን›› በሚል የሚያግቱም አልጠፉም። አንዳንድ የትራንስፖርት አቅራቢ ድርጅቶችም በመንገድ መዘጋትና እገታ ተማረው በብሄራዊ የአደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን የተቀበሉትን ኮንትራት እስከመተው ደርሰዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ሊቀመንበር ደመቀ መኮንን ‹‹በከፍተኛ የሰላም ጥርጣሬ ውስጥ የሚወድቁ ዜጐች ብዙዎች ስለሆኑ፤ ያን የሚታደግ ጠንካራ የህግ ስርአት እውን መሆን አለበት። ›› ሲሉ ተናግረዋል። እንዲሁም ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች በተገመገሙበት እና አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በመሩት ስብሰባ ‹‹ለፀጥታ ጉዳይ መደፍረስ ከእኛ መዋቅር በላይ ተጠያቂ የለም ›› እስከመባል ተዘልቋል። ግንባሩ በእርግጥ ፖለቲካዊ ዋጋ ከፍሎ መዋቅሩን ከአፈናቃዮች ያፀዳል ወይ ʔ የብዙዎች ጥያቄ ነው። አፅጂውና የሚፀዳው ማን ነው ʔ ሌላ ፈተና ነው። ከአፈናቃይ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ሰባ አምስት በመቶ ገደማዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋለው መንግስት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በስተቀር ተጠርጣሪዎቹን እንደልብ አሳልፎ የሰጠ ክልል አልተገኘም። አንዳንድ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሳይቀሩ በግጭትና በማፈናቀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ሲያሸሹ እንደተያዙም ተነግሯል። አሁን ያለው መግባባት ግን የተፈናቃዮቹ ጉዳይ የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒሰቴር ሚኒስትሯ ሞፈሪያት ካሚል እንደሚሉት ፖለቲካዊ ነው። ይህም ቢሆን ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ሁሉንም ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት እንመልሳለን እንዳሉትም በርካቶችን እየመለሱ ነው።

ፕሮፌሰር ኢዝቄል ጋቢሳ ደግሞ አሁን ላይ እየታዩ ያሉ ግጭቶችን በሁለት አይነት መልኩ ይገልጿቸዋል። ከጥንት ጀምሮ በየአካባቢው ግጭቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ግጭቶቹን መፍቻ ባህላዊ መንገዶች ነበሩ። አሁን ግጭቶች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱ በኋላ እንዳይባባሱ፤ ከተባባሱም ደግሞ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ያደርገው የነበረው ባህላዊ መዋ ቅር ጠፍቷል። በመሆኑም ግጭቶቹን የሚያቆማቸው የለም። ግጭቶች እንዳይባባሱ፣ እንዳይፋፋሙ፣ ብዙ ጉዳት እንዳያደርሱ በየአካባ ቢው የነበሩት የግጭት መፍቻ መንገዶች ተዳክመው በምትካቸው የመንግስት ሀይል በሰፊው ሰፍኖ አስወግዷቸዋል ። ይህ ድርጊት በደርግ ጊዜ ጀምሮ በኢህአዴግ ወቅትም ቀጥሎ በምትካቸው በሰፊው የመንግስት ሀይል ሰፍኖ ይታያል። ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶቹ አያስፈልጉኝም በሚል አስተሳሰብ መጥፋታቸው አሁን ላይ የሚከሰቱ ችግሮች በተባ ባሰ መንገድ እንዲቀጥሉ አንዱ ምክንያት መሆኑን ፕሮፌሰሩ ያምናሉ።

እንደ ፕሮፌሰር ኢዝቄል በለውጡ የተከሰተው ግጭት ሁለተኛው ምክንያት በለውጥ ጊዜ ግጭቶች በምን መልኩ ይፈታሉ ተብሎ አስቀድሞ ዝግጅት አለመደረጉ ነው። ግጭቶቹ መዋቅራዊ እንዳልሆኑ ምሳሌ በመጥቀስ ያስረዳሉ። ለምሳሌ በምስራቅ ኢትዮጵያ በሱማሌና በኦሮሞ መካከል የነበረው ግጭት በሁለቱ ብሄሮች ምክንያት አይደለም። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የመንግስትና ወታደራዊ አዛዦች /በኮንትሮባንድ ስራ ውስጥ የነበሩ ሰዎች/ ጥቅማቸውን ለማቆየት ሲሉ ግጭቶችን ይፈጥሩ ነበር። እነዚህ አካላት ግጭቶች በነበሩባቸው አካባቢዎች በማባባስ መሳሪያ በሁለቱም በኩል ይሰጣሉ። በተመሳሳይም በደቡብም ሆነ በምዕራብ ኢትዮጵያ ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን ግለሰቦች ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ ጥቅም ብለው የፈጠሩት እንጂ ህዝቡ ተስማምቶ በገበያ ቦታ እየተገበያየ፣ በትምህርት ቤት እየተገናኘ አብሮ ይኖር ነበር። በተለይ መንግስት ወታደሮቹን ግጭት በተፈጠረባቸው ቦታዎች አካባቢ ማስፈር በጀመረበት ወቅት ግጭቶቹ ተባብሰዋል። በአማራ ክልልም የተከሰተው ግጭትም ሆነ ተብሎ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አካሄድ ለመለወጥ፣ ለውጡ ግቡን እንዳይመታ ለማሰናከል የተሰሩ መሰናክሎች ናቸው። በመሆኑም በለውጡ ሂደት እነዚህና መሰል ግጭቶች እንደሚፈጠሩ በመተንበይና ግንዛቤ በመውሰድ ቅድመ ጥንቃቄ እና ዝግጅት ያስፈልግ እንደነበር ያብራራሉ።

በእርግጥ ለውጥ ሁልጊዜም ተግዳሮቶች አሉት የሚሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ የለውጡ ፈተና ህዝቡ መንግስትን የሚያይበት አይን ነው። መንግስት በእኛ ሀገር ባህል ከቁጥጥር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። መንግስትና ተቆጣጣሪነት ተያይዘው የሚታዩ ነገሮች ሆነዋል። ‹‹ጀግናው፣ ቆራጡ መንጌ›› ሲባሉ እንሰማለን፤ አቶ መለስም እንደዚሁ አድናቂዎች ነበሯቸው። የሚደነቁበት ነገር ህዝብ ላይ ባደረጉት ጫና፣ በተከሰቱት አፈናዎች፣ በመቆጣጠር ብቃታቸው እንጂ ለህዝብ ባላቸው ከበሬታ አይደለም። መሪዎች እንደመሪ የሚቆጠሩት ሲያስጨንቁ፣ ሲገድሉ፣ ሲያፍኑ፣ ዘራፍ ሲሉ ‹‹ቆራጥ መሪ›› የማለት ባህልን ህዝባችን አዳብሯል። እናም በመከራ፣ በአፈና ውስጥ የኖረ ህዝብ አሁን ነገሮች ሲላሉ፣ አየሩ ሲከፈት ያለመረዳት ነገር ይታያል። በሌላ በኩል ብዙ ጊዜ ጨዋ ህዝብ እንዳለን ሲገለፅ ይሰማል። እንደሚባለው ጨዋዎች ነን ʔ ታዲያ ከበጎዎች ይልቅ ለአጥፊዎች የምንቀርበው፣ በቀላሉ ሁለት ሰዎች በቀን ውስጥ አንድ ትርክት ፈጥረው አርባና ሀምሳ ሺህ ሰው ለአመፅ የሚያነሳሱን፣ ደረትና ግንባሩን ሰጥቶ በሰላማዊ መንገድ ሲታገል የነበረ ዜጋ በአንዳንድ ሰዎች ቅስቀሳ ንፁህ፣ ያልታጠቀ ወገኑ ላይ በአንገቱ ገጀራ የሚያሳርፈው ለምንድን ነው ʔ ብለን ስንጠይቅ ባህላችን ውስጥ ያላየነው ጨለማ ክፍል እንዳለ አቶ አንዷለም ያስባል።

እንደ አቶ አንዷለም ገለፃ በተለይ ‹‹በፖለቲካ ለውጥ ውስጥ የሚሞተው ስርአትና የሚወለደው ስርአት የሚያደርጉት ግብግብ ከባድ ነው።›› የሚወለደው የመወለድ ጭንቅ ውስጥ፤ የሚሞተው ደግሞ የመሞት ጭንቅ ውስጥ ይገባል። ላለመሞት ግብግብ አለ። እውን የሚሆነው አንዱ በሌላው ህልፈት (መስዋዕትነት) ህልውና ላይ ነው። የሚሞተው ካልሞተ፣ የሚወለደው የመወለድ እድሉ ሞት ይሆናል። ስርአቶች ለዓመታት የተገነቡ ስለሆኑ በቀላሉ እጅ አይሰጡም፤ በቀላሉ አይፈርሱም። የሚፈጠረው ስርአትም በቀላሉ የሚሞት አይደለም። በተለያዩ ጊዜያት በአገራችን የተመለከትነው ይህንኑ ነው። ለውጥ ከህክምናም በላይ ጠቢባን አዋላጅ እጆች ያስፈልጉታል። እንደሰው ስጋ ለብሶ፣ ሰውን የሚያመውን ነገር ችሎ፣ ወደፊት ሊሆን የሚገባውን ነገር ጠንቅቆ ማሰብና ሌሎች የፖለቲካ ስሌቶችን ገምግሞ በማየት መውጫ መንገድ መፈለግ እጅግም ጠቢብ መሆንን ይጠይቃል። ይህም ከፖለቲከኞች፣ ከመሪዎች ብቻ ሳይሆን ከእያንዳንዱ ዜጋ ጠቢባን እጆች እንደሚጠበቅ አቶ አንዷለም ያሳስባሉ።

ጀርመን በሚገኘው ኪኤል ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አወል ቃሲምም በአቶ አንዷለም ሀሳብ ይስማማሉ። ለውጡ በነበረው የፖለቲካ ስርአት ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሀይሎች ውጪ ሲደረግ የነበረውን ትግል እንደሀይል፣ እንደድጋፍ በመያዝና በገዢው ፓርቲ የተፈጠሩ ተቃርኖዎች እንደእድል በመጠቀም የመጣ ለውጥ ነው።በዛ ትግል ውስጥ አሸንፎ የመጣው ሀይል በግልፅ ያሸነፋቸው ሀይሎች አሉ። ይህ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው ቅራኔ፣ውጥረት አሁን አገሪቱ ላይ ለምናየው ችግር በተወሰነ ደረጃ አስተዋፅኦ አድርጓል።

የዴሞክራሲ ባህል አለመኖርና በታሪክ በዜጎቻችን መካከል የነበሩ አለመግባባቶች በተለያዩ አካላት በተለያየ መንገድ ሲተረጎሙ መቆየታቸው አሁን ላይ በተግባር እየተንፀባረቁ ይገኛል። በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ጊዜ በየአካባቢው ተፈናቅሎ ያለው ህዝብ ቁጥሩ ከዚህ በፊት በአገሪቷ ያልታየ ችግር ሆኗል። እየታዩ ያሉ ግጭቶች መንስኤዎች መካከል አንዱና ዋንኛው ከዚህ በፊት በነበረው የአፈና ስርአት ባህል፣ቁጭት፣ንዴት ሳቢያ የመጣ ነው። ለውጡን ተከትሎ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ሲሰፋ አብዛኛው መናገር በመጀመሩ ችግሮች በተለያየ መልኩ እየገነፈሉ ወጥተዋል።

አንዳንዴ ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ እና የሀገሪቱን የመሻገርና ያለመሻገር እድልን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ እየተንፀባረቁ ነው። በጣም የተከማቹ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉ። እነዚህ ችግሮች እንደየአካባቢው ይለያያሉ። በአንዳንድ አካባቢ ያለ ህዝብ በሌላ አካባቢ ህዝብ ላይ ‹‹ ቁርሾ አለኝ፣ ቂም አለኝ ፣ ንዴት አለኝ ›› ብሎ ያስባል የሚሉት
ዶክተሩ አሁን የዴሞክራሲው ምህዳር ሲሰፋ የፖለቲካ ፍላጎቱን የሚገልፅበት አንደኛው መንገድ ቁርሾውን ንዴቱን የማንፀባረቅ አካሄድ መታየቱን ያነሳሉ።

ይህንን አደገኛ አካሄድ ለማስቆምና ለውጡን ከግብ ለማድረስ ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ግድ ይላል። መፍትሄውንም አቶ አንዷለም ይጠቁማሉ። እሳቸው እንደሚሉት በሆደ ሰፊነትና በህግ የበላይነት መካከል ያለውን ደረቅ መሬት ማግኘት ግድ ያስፈልጋል። ለለውጥ የሚያስፈልጉ ጠቢባን እጆች ትዕግስት ቢሹም በትዕግስትና በህግ የበላይነት መካከል ያለውን ደረቅ መሬት መገኘት አለበት።

በመንግስት የታየው የበዛ ትዕግስት ለውጡን ወደፊት መውሰድ እንዳልቻለ እያስቆጠረው ነው። ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች ከትግስቱ ሊማሩ ሳይሆን ሌላ ችግር እንዲፈጥሩ መዘጋጃ ጊዜ ሆኗቸዋል። አምባገነኖች ህግ ከሚፈቅድላቸው በላይ ይጠቀማሉ፤ህግ ከሚፈቅደው በታችም መጠቀም በራሱ ስህተት ነው። ስለዚህ ህግን በአግባቡ መጠቀም በሚያስፈልግበት ጊዜ መጠቀም ለለውጡ ወሳኝ ጉዳይ ነው። የክልል መንግስታት የማዕከላዊ መንግስቱን በመገዳደር ትንሽ ከስርአት የወጣ ነገር እያሳዩ ነው። ይህ ለለውጡ ስኬት ትልቅ ተግዳሮት በመሆኑ ልክ መያዝ አለበት።

ማዕከላዊ መንግስቱ በደንብ የተከበረ፣ የሚሰራቸው ስራዎች የክልል መንግስታት ታች ድረስ አውርደው የሚሰሩ፣ የሚቀበሉ መሆን አለባቸው። ለውጡን ተከትሎ የተከሰቱ ግጭቶች አንደኛው ምክንያት የሆነው ባለፈው ስርአት ውስጥ ተጠቃሚ የነበሩ ሰዎች /ጥቅማቸውን የተነጠቁ አካላት/ የነበራቸውን ጥቅም ለማስቀጠል ስርአት አልበኝነት እንዲፈጠር አድርገዋል።

መንግስትን አሳንሶ ለማሳየት፣ ለውጡን መምራት አይችልም ለማስባል፣ ትርምስ ለመፍጠር የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች አሉ። ስለዚህ ማዕከላዊ መንግስት በትክክል እንደሚችል ህግና ስርአትን እንደሚያስከብር ማሳየት አለበት። አሁን የጫጉላ ሽርሽር ጊዜው ለሁሉም አብቅቷል የሚሉት አቶ አንዷለም ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ እያንዳንዱ ዜጋ፣ የሚመለከታቸው አካላት እና መንግስት የየራሳቸውን ሚና በአግባቡ ለመወጣት ወደ ስራ የሚገቡበት ወቅት አሁን መሆኑን ያሳስባሉ።

ሁላችንም ብንዋደድ፣መንግስት ዴሞክራሲን እያሰፋ ቢሄድ፣ የህግ የበላይነት ቢከበር፣ የፍትህ ስርአቱ ለድሆችና ለተጨቆኑት ፍትህ መስጠት ቢችል፣ እና ሌሎች አዎንታዊ የሆኑ ነገሮችን ብናደርግ አሁን እየተፈጠረ ያለውን ችግር በቀላሉ መፍታት እንችላለን የሚሉ ወገኖች አሉ።

ዶክተር አወል ግን በዚህ ሀሳብ አይስማሙም። የተጠቀሱት ጉዳዩች ሁለተኛ ጉዳዮች መሆናቸውን ምክንያት አቅርበው ያብራራሉ። ስርአቱ ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ ‹‹እያንዳንዱ ግለሰብ የፈለገውን ነገር ማድረግ ይችላል›› ብለን ግለሰቡ ግን የፈለገውን ነገር ከማድረግ ባሻገር ከዴሞክራሲ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ኃላፊነቶች ምን እንደሆኑ የማያውቅ ከሆነ አደጋው የከፋ ነው።

‹‹እኔ ክልል እንደዚህ አይነት አመለካከት ያለው ፖለቲከኛ መጥቶ ቢሮ መክፈት ወይም ህዝባዊ ሰልፍ መጥራት አይችልም›› የሚል ከሆነ ዴሞክራሲን ወደፊት ማራመዱ ቀርቶ እንዲያውም ያቀነጭረዋል። በየአካባቢው የምናያቸው እንከኖች በረጅም ጊዜ የሚያመጡት ችግር ህዝቡ በዴሞክራሲ ተስፋ እንዲቆርጥና ‹‹ ከዚህማ አምባገነንነት ይሻላል ›› ወደሚለው የሚሄድበት ሁኔታ ይፈጠራል። ለዚህም በየአካባቢያችን የምናያቸው ምሳሌዎች አሉ።

እነዚህ እየሰፉ ሄደው ዴሞክራሲን ከማቀንጨራቸው በፊት ራሳችንን ማየት አለብን ።ሁላችንም ባለንበት ቦታ በጣም ጠለቅ ባለ ሁኔታ ራሳችንን፣ አቋማችንን መመርመር አለብን። እንደ ኢትዮጵያ አይነት በጣም ተቃራኒ የሆኑ የታሪክ ትርክቶች ባሉበት፣ ታሪክ ለፖለቲካ ፍጆታ በሚውልበት እና የጦር መሳሪያ ሆኖ በሚያገለግልበት፣ ብሄርተኝነት ብቸኛ የሆነ ህዝቡን የማነቃነቂያ እና የማደራጃ መሳሪያ በሆነበት አገር እንዲሁ በቀላሉ ተቋማቶችን ዴሞክራሲያዊ ብናደርግ፣ሁላችንም ገንቢ ብንሆን በሚል አይነት ቀላል ስልቶች እየታዩ ያሉትን ችግሮች መፍታት አይቻልም የሚሉት ዶክተሩ ‹‹ እኔ የማራምደው አቋም፣ የምቀበለው የታሪክ ትርክት ለምንድን ነው ብቸኛውና ትክክለኛው መንገድ እንደሆነ የማስበው ›› የሚለውን ነገር ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ አለብን ይላሉ።

አገር ሰላም ሆና ወደፊት እንዳትቀጥል፣ግርግር እንዲፈጠር፣ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባቱ ሂደት እንዲጓተት እንዲሁም ደግሞ እንዲሰናከል ለማድረግ በቁጥር ብዙ /ትልቅ/ ህዝብ መሆንን አይጠይቅም። ትንሽ ቁጥር ያለው ህዝብ ብዙ ችግር ሊፈጥር ይችላል። ለማጥፋት ለማፍረስ ብዙ መሆንን አይሻም። ሁሉም ትልቅ አቅም አለው። ስለዚህ ሁላችንም ከመረዳት ተነስተን እሴቶቻችንን ማዕከል ባደረገ መልኩ የራሳችን እምነት፣ አቋም፣ አመለካከት እንዳለን ሁሉ ሌላውም የራሱ እምነት፣ አቋም፣ አመለካከት መኖሩን መረዳት አለብን።

ራሳችንን ብቸኛው የአንድ ህዝብ ተከላካይ፣ ጠባቂ ሌላውን ደግሞ ያንን ህዝብ ለማጥፋት፣ የዛን ህዝብ ጥቅም ወይም ፍላጎት፣ ማንነት ለማጥፋት የሚንቀሳቀስ አድርገን ከማሰብ ይልቅ ሌላውንም በመገንዘብ ሆደ ሰፊ ሆነን መንቀሳቀስ አለብን። ቀስበቀስ መንግስትም መስራት ያለበትን ህዝቡን የማዋሀድ /ርኮንሳይል/ ስራ እንዲሰራ ጊዜ ቢሰጠው በሂደት ጫፍ ላይ የቆመው ወደ መሀል እንደሚመጣ ዶክተር አወል ያስባሉ።

ይህ እውን እንዲሆን ትልቁ ባለድርሻም መንግስት እንደሆነ ዶክተር አወል ያነሳሉ። መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች በጣም ወሳኝ ናቸው። መንግስት ለአጭር ጊዜ ፍጆታ ሊውሉ የሚችሉ ህዝብ ውስጥ ያሉ አመለካከቶችን ነገር ግን በረጅም ጊዜ መንግስት ለሚያስባቸው መሰረታዊ የለውጥ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ችግር የሚያመጣ ነገር የሚሰራ ከሆነ ራስን ማሰናከል ነው። በረጅም ጊዜ ውጤት የሚያመጡ ነገሮችን ስትራቴጂ ነድፎ መስራት ይኖርበታል። በተለይም ህዝቦችን የማቀራረቡ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ወጣቶች ከህይወት ትርጉም እንዲያገኙ የስራ እድል ሊፈጠርላቸው ይገባል። የስራ እድል የሚፈጠርላቸው ከሆነ በስራቸው

አድገው የሆነ ቦታ መድረስ እንዲችሉ የተለየ አላማ ይኖራቸዋል። አላማቸው ዝምብሎ ፖለቲካ ብቻ ሊሆን አይችልም። ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ፣ ሁሉም ሰው መሪ ሊሆን አይችልም። እንደአንድ ህብረተሰብ የሆነ ቦታ ለመድረስ ኢንጂነሮች ያስፈልጋሉ፣ አካውንታቶች ያስፈልጋሉ፣ እርሻ የሚያርስ ያስፈልጋል፣ ቧንቧ የሚሰራ ያስፈልጋል፣ የሚያስተምር ያስፈልጋል፣ ሁሉም ሰው የሚሰራው ስራ ላይ ትርጉም፣ እሴት ማግኘት መቻል አለበት። እንደአገር ወደ ፊት ለመሄድ በጣም የምር በሆነ መልኩ ራሳችንን መልሰን የማየት፣ የመገምገም፣ የመኮነን፣ ስራዎችን መስራት ይኖርብናል። ሁልጊዜ ‹‹ እኛ ብቻ ነን ልክ፣ ማሸነፍ አለብን፣ የምንፈልገውን ሁሉ መጠየቅ አለብን ›› በሚል ነገሮችን ከራሳችን ጎን ብቻ የምናይ ከሆነ አገር መገንባትም ሰላም ማስፈንም አንችልም።

ሰላም እንዲሰፍን፣ ሀሳቦች ለውይይት ቀርበው ሁሉንም ያማከለ በመረዳዳት ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ እንዲኖርና አገር መገንባት እንድንችል አመለካከትን የሚቀርፁ አካላት ሚናቸው የጎላ ነው። ለህዝቡ፣ ለፓርቲዎችም፣ ለመንግስትም የተለያዩ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካም ፖሊሲዎች ከየት ተነስተው ወዴት ይሄዳሉ፣ ምን ውጤት ያመጣሉ፣ በምን መልኩ ተግባራዊ ይደረጋሉ፣ የሚሉ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ የሚያፈልቁ እና በተለያየ መልኩ ሀሳብ የሚያሰባስቡ ተዋናዮች አሉ። እነዚህ ተዋናዮች ምሁራንን፣ የሚዲያ ሰዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን ሊጨምር ይችላል። እነዚህ አካላት በአገር እድገት እና ግንባታ ላይ አወንታዊ ሚና እንደሚጫወቱ የታወቀ ጉዳይ ቢሆንም በአገራችን ነባራዊ መልኩ ሁሉም በሚባል ደረጃ ‹‹አክቲቪስት›› ሆነው ይታያሉ። በእርግጥ ‹‹አክቲቪስትነት›› ህጋዊ የሆነ መሰረት ያለው ሙያ በመሆኑ አገራዊ ገንቢ ሚና መጫወት ይቻላል። ነገሮችን ከራስ የፖለቲካ አመለካከት አንፃር ብቻ ማየትና ከራስ አመለካከት የሚፃረሩ ማንኛቸውንም ሀሳቦች እንደማንኛውም ተራ ሰው በፌስ ቡክ ተደራጅቶ ግለሰቦችን ማጥቃት የ‹‹አክቲቪስትነት›› ሙያን አይገልፅም።

እንደዶክተር አወል ገለፃ ገንቢ በሆነ መልኩ መከራከር ስንችል፤ ለንግግርም እድል ስንሰጥ ለመገነዛዘብና ለመረዳዳት በሚያመች መልኩ ነገሮችን መቅረፅ የሚቻልበት ትልቅ እድል ይፈጠራል።አሁን እንዲህ እየተደረገ ሳይሆን አብዛኛው አመለካከት የሚፈጠረው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነው። በመሆኑም አብዛኛው ሰው ጧት ሲነሳ የመጀመሪያ ስራው የማህበራዊ ሚዲያን ማየት ነው። ቀንም ማታም ሲተኛ በአብዛኛው እንደእዛው ነው። የማህበራዊ ሚዲያ ስልት /አልጎሪዝም/ አንድ ግለሰብ ሁልጊዜ የሚያነባቸው፣ የሚያጋራቸው ዜናዎች ወይም አስተያየቶች እሱ ከሚፈልጋቸው ከተወሰነ ቡድን የሚመጡትን ብቻ ነው። ግለሰቡ አንድ መረጃ ከየት እንደሚመጣ ስለሚያውቅ መረጃው እውነት ወይም ውሸት መሆኑን ሳያጣራ እሱም ያራግባል። ሰዎች በመረጃ መልክ የሚያገኙትን ነገር እውነትም እውቀትም አድርገው ይወስዱታል። ከሌላ ሰው ጋር ሲነጋገሩ እንደመከራከሪያ ግብአት አድርገው ይጠቀሙታል። ይህ በሽግግር ላይ ላለ ህብረተሰብ ትልቅ ችግር ነው። በተለይ የዴሞክራሲ ባህል በሌለበት፣ ብሄርተኝነት ብቸኛው የሆነ ህዝብን ማንቀሳቀሻ፣ መሳሪያ በሆነበት አገር በጣም ትልቅ ችግር ነው። እናም እነዚህን መድረኮች /አጀንዳዎች/ በአግባቡ የመጠቀም ተገቢነት አያጠያይቅም። ለዚህም ስኬት ጋዜጠኞች፣ ምሁራን የገዘፈ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው። አሁን ያለው አስቸጋሪ የፖለቲካ አውድ የራስን አመለካከት ብቻ ማራመድ የማይቻልበት ነው። የምሁርነት ወይም የጋዜጠኝነት ትልቁ የስብዕና መገለጫ ለራስም ለህዝቡም ሲባል ገለልተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን አገራዊ ገንቢ ሚና መጫወት ነው። ይህ ሲሆን የዓለምን ቀልብ የገዛ የአገራችን የፖለቲካ ሽግግር ተስፋው ለምልሞ ውጤታማ ለውጥ እንዲካሄድ ጥርጊያ መንገድ ይከፍታል።

በእርግጥ ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ መንግስት ያከናወናቸው ተግባራት የብዙዎችን ስሜት የሳቡ እና ተስፋም ያሰነቁ ናቸው።ዶክተር አወል እንደሚሉትም በለውጡ የተጀመሩ ጅምሮች ከቀጠሉ፣በተለይም በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሀይሎች በየአካባቢው የሚደረግባቸውን ውስጣዊ ተፅእኖ ተቋቁመው እንደግንባር ግልፅ፣ ለዴሞክራሲ መስዋዕት የሆነ አቋም ይዘው መቀጠል የሚችሉ ከሆነ አገሪቱ አሁንም ትልቅ ተስፋ አላት። በተለይም የኦዴፓ እና የአዴፓ ትልልቅ ህዝቦችን እንደሚወክሉ ሁለቱ ሀይሎች የሚያሳልፉት ውሳኔ ለኢትዮጵያ ህልውና በጣም ወሳኝ ነው። ሁሉም አካሄዶች በአግባቡ መስተናገድ አለባቸው።

የኔ ብቻ መንገድ ተገቢ በሚል እሰጣ ገባ መግባት አያስፈልግም። አንዳንድ ሰዎች ‹‹ ስለብሄር፣ ስለብሄርተኝነት ለምን እናወራለን፤ የምናወራቸው ነገሮች መቀየር አለባቸው ›› የሚሉ አሉ። እውነታው ግን ብሄርና የብሄር ጥያቄ፣ የብሄር ፖለቲካ መሬት ላይ ያለ ለረጅም ጊዜ የነበረ ወደፊትም የሚቀጥል ነገር ነው። ብሄርተኝነት እኛ ስለፈለግን ዝም ብሎ ይጠፋል ከተባለ ተሳስተናል። በጊዜ ሂደት የሚያስተጋቡ ማንነቶች የፖለቲካዊ ጠቀሜታቸው እያነሰ ሌሎች እሴቶች ከፍ እያሉ መሄድ መቻል አለባቸው። ለምሳሌ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የህግ የበላይነት፣ ከእኔ አማራነት፣ ከእኔ ትግሬነት፣ ከእኔ ኦሮሞነት የተሻለ ዋጋ አለው ወደሚል ሂደት መሄድ መቻል አለብን። ይህ እንዲሆን ደግሞ ረጅም ጊዜ ይወስዳል።

ስለዚህ የነበሩ እሴቶች ይቀጥላሉ። ‹‹ሰዎች በቀላሉ የማይቀበለው፣ ሰዎችን ሊያንቀሳቅስ የማይችል አዲስ ርዕዮተ ዓለም መገንባት ይኖርብናል ›› በሚል መትጋት ሳይሆን በኢትዮጵያ መረጋጋት በመፍጠር ወደ ፊት ሊያስኬድ የሚችል፣ የዴሞክራሲ ባህላችንን ሊቀይር የሚያስችል ነገር መፍጠር ነው። ኢትዮጵያዊያን የዜግነት ፖለቲካ ብቻ መያዝ አለባቸው የሚለውን ሀሳብ የሚያራምዱ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች መጀመሪያ ነገሮች ፅኑ መሰረት ሊይዙ እንደሚገባ ማመን አለባቸው። ተቋማት መገንባት እና የዴሞክራሲ ባህላችን መቀየር መቻል አለበት። ኢትዮጵያዊ የሚለው ዜግነት ለህዝቡ ትርጉም የሚሰጥበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ለዛ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች እና መንገዶች አሉ። ኢህአዴግ በተለይም ሁለቱ ፓርቲዎች /ኦዴፓ እና አዴፓ/ መካከል እስካሁን የነበረው ስትራቴጂያዊ ትብብር በመሆኑ ትብብሩ በደንብ ጠንክሮ መቀጠል መቻል አለበት። ሁለቱ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን ወደፊት ሊያስኬዳት የሚችል ራእይ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

በአጠቃላይ የሀገራችን የሽግግር ሂደት ከሁለት አቅጣጫዎች ታላላቅ ተግዳሮቶች ገጥመውታል። እነዚህን ተግዳሮቶች መሻገር ለምንፈልገው የእኩልነትና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሕገ- መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ሽግግሩ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች፣ የተወሰነው ክፍል ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ ተደርጎ የሚታይበት ሥርዓት አክትሞ ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በእኩልነት የሚታዩበት፣ ያለአድልዖ የሚዳኙበት ሥርዓትን ለመፍጠር እንጂ ያለፈውን ለመድገም እንዳልሆነ ከግንዛቤያችን እንዳይርቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ይህ የሽግግር ሂደት የሚፈለገውን መሠረታዊ ውጤት እንዲያሰገኝ ሁሉም የተደራጀ ኃይልና ዜጎች ሁሉ ታላቅ ኃላፊነት አለባቸው። በዚህ እንቅፋት በበዛበት የሽግግር ሂደት ውስጥ የአጭር ጊዜ ድልን ለመጨበጥ በማተኮር ለውጡን የሚቃወመው አካል በሚፈጥረው ተጨማሪ ማደናቀፊያ በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር መደረግ የሚችልበትን መሠረታዊና ተቋማዊ ለውጥ እንዳያሰናክለው አርቆ ማሰብና በጥንቃቄ መራመድ ይገባል። ለውጡን የሚቃወመው አካል ራሱ በሚወሰደው አላስፈላጊ ትንኮሳና በሚቀሰቅሰው ግጭት የራሱ ትርክት ሰለባና አስረኛ እንዳይሆን አርቆ ማሰብ ይኖርበታል።

በትክክል መገንዘብ የሚገባው በሀገራችን የፖለቲካ ሽግግር ሂደት እያንዳንዱ ድርጅት ይገባኛል ብሎ የሚለውን ሳይሆን፣ ሁሉም ድርጅቶች (ገዥውን አካል ጨምሮ)ና ዜጎች መሠረታዊ መብታቸው ተከብሮ በሕግ ፊት እኩልነታቸው ተረጋግጦ ከማንም በላይም ሆነ በታች ሳይሆኑ የሚንቀሳቀሱበትን፣ በሕዝብ ነፃ ፍላጎትና ምርጫ ብቻ ወደ ሥልጣን የሚወጡበትና የሚወርዱበትን ሥርዓት መመሥረትና መገንባት፣ ለሁሉም ዜጋ የግልም ሆነ የቡድን መብት ቋሚ የመብት ማረጋገጫ ሊሆን እንደሚችል ነው። የዘመናት ትግል ተካሂዶ የብዙ ሰማዕታት ደም ተገብሮበት፣ እዚህ የደረሰው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዳይከሽፍና ወደ ግቡ እንዲደርስ ሁሉም ኃላፊነት የተሞላው ተግባር ማካሄድ ይጠበቅበታል። የለውጥ ኃይሉ ብቻውን ሽግግሩን ሊሸከም አይችልም፣ የተቃዋሚው ገንቢ ሚና ለዚህ ሂደት ውጤታ ማነት ወሳኝ ነው።

ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011

ሳሙኤል ይትባረክ