‹‹ያለዕውቀትና ምርምር ኢትዮጵያ ታድጋለች ማለት ዘበት ነው›› – ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ

22

ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ የአርሶ አደር ልጅ ናቸው። አባታቸው ለትምህርት ባላቸው ፍቅር ትምህርታቸውን ተግተው እንዲማሩ ከጅምሩ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ዶ/ር አዱኛም ግብርናን አስበውና ፈቅደው የተማሩት ትምህርት ስለሆነ የኢትዮጵያን ግብርና በምርምር ለማዘመን ላለፉት 38 ዓመታት ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ተግተዋል። የህይወትና የምርምር ተሞክሯቸውን እንደ ባለሙያ እንዲያካፍሉን ጋብዘናቸው የሰጡንን ምላሽ አቅርበናል። መልካም ንባብ!

ውልደትና ዕድገት

ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ የተወለዱት በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ዲሬ እንጭኒ ወረዳ፣ ወልዶ-ጉፍታ ቀበሌ በሚባል የአርሶ አደር መንደር ከአባታቸው ዋቅጅራ ገመላል እና ከእናታቸው ወ/ሮ ደመሺ ኢሬንሳ በ1951 ዓ.ም. ነበር። የቤተሰባቸው ሦስተኛ ልጅ ናቸው። በህፃንነታቸው ብቅል፣ ቡቃያ ከመጠበቅ ጀምሮ በግና ጥጆችን በማገድ እንዲሁም ወላጆቻቸውን በማገዝ ኃላፊነትን እንዴት መወጣት እንደሚቻል የተለማመዱበት ጊዜ እንደሆነ ይናገራሉ። በአካባቢው በሚገኙ ቁሳቁሶች ከልጆች ጋር በመሆን በራሳቸው የፈጠራ መንገድ የቤት እንስሳ፣ የግብርና መሳሪያዎች እንዲሁም ተሽከርካሪ መኪናዎች የመሳሰሉትን የራስ አሻንጉሊቶች እየሰሩ በመጫወት ራሳቸውን ያስደስቱ ነበር። ዋና መዋኘት፣ ፈረስ መጋለብ እና ኳስ መጫወት ይወዱ ነበር።

የትምህርት ጅማሮና ቀጣይ ሕይወት

አባታቸው የተማሩ አይደሉም፤ ነገር ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ከተማ ወጣ ሲሉ ጋዜጣ ገዝተው ይመለሳሉ። ለንባብ ከፍተኛ ጉጉት አላቸው፤የገዙትን ጋዜጣ ለሚያነብ ሰው ሰጥተው መረጃውን ያዳምጣሉ። ፍርድ ቤት ማመልከቻ ለሚጽፍ ይከፈላል፤ በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚናገር ሰው ወደ አማርኛ ለሚተረጉምለት ይከፍላል፤ ብዙ ወጪ አለው። ይህን ሁኔታ ፍርድ ቤት ሲሄዱ በትኩረት ተከታትለዋል። ስለሆነም ‹‹ልጆቼ ከዚህ አይነት ወጪ ነፃ መውጣት አለባቸው›› ብለው ልጆቻቸው ትምህርት ቤት እንዲሔዱና እንዲማሩ በከፍተኛ ሁኔታ ጥረዋል፤ እስከ መጨረሻው ሳይታክቱ ከመጀመሪያ ልጃቸው በስተቀር ሰባት ልጆቻቸው በትምህርት ራሳቸውን እንዲረዱና እንዲችሉ አድርገዋል።

የዚያን ጊዜው ብላቴና አዱኛ የአካባቢው ሰዎች በቀጠሩላቸው የኔታ አማካኝነት ፊደል ከመቁጠር ጀምረው እስከ ዳዊት ድረስ ተምረዋል። ስለየኔታ ግርማ፣ ልጆች ወዳድነትና ምክሮች እንዲሁም ከወሎ መጥተው በፍጥነት አካባቢውን፣ ህዝቡን፣ ባህሉንና ቋንቋውን ተላምደው በፍቅር አብሮ መኖር እንዲችሉ መንገዱን ያሳዩዋቸው መሆናቸውን ይናገራሉ። ለህይወት ጉዟቸውም ጥሩ አርአያ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። መስከረም 21 ቀን 1960 ዓ.ም. በመደበኛ ትምህርት ቤት በወቅቱ ጥቁር እንጭኒ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመባል በሚጠራው ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረዋል።

ትምህርቱ የሚሰጠው በአማርኛ እሳቸው አፋቸውን የፈቱት በኦሮሚኛ ስለሆነ ለጥቂት ጊዜ ግር ብሏቸው ነበር። ቀስ በቀስ ትምህርቱን እየለመዱትና እየወደዱት ስለመጡ ጎበዝ ተማሪ ሆኑ። አንደኛና ሁለተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ትምህርት የመቀበል ብቃታቸው ከተገመገመ በኋላ ቀጥታ አራተኛ ክፍል ገብተው በመማር አንደኛ ደረጃን በአጥጋቢ ውጤት አጠናቀዋል።

በመቀጠል ጉደር በሚገኘው በወቅቱ ባሻህ አቦዬ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተምረዋል። እንግሊዝኛ ቋንቋ ከፍተኛ የመቀበልና የመተግበር ብቃት ስለነበራቸው በሰላም ጓድ አስተማሪነት ከአሜሪካ በመጣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪ ‹‹ዲክሽነሪ/ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት›› ተሸልመዋል። አልገፉበትም እንጂ በሩጫ ውድድርም ውጤታማ የመሆን አቅም ነበራቸው። በተጨማሪም ጉደር ሲማሩ ከቤተሰብ ርቀው ከአራት ተማሪዎች ጋር እየኖሩ በስንቅ ተምረዋል። ጥሩ የነበረውን የትምህርት ደረጃቸውን ሳይለቁ ስምንተኛ ክፍልን በጥሩ ሁኔታ አልፈው አምቦ ሔዱ።

አምቦ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቁ ጎበዝ ተማሪዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የሚማሩበት ስለነበረ ፉክክሩ ከፍተኛ ቢሆንም የደረጃ ተማሪ መሆን ግን ችለዋል። አምቦ ከዘመድ ጋር እንደ ልጅ ታይተው እየኖሩ ስለተማሩ በጣም ደስተኛ ነበሩ። በ1969 ዓ.ም.እና 1970 ዓ.ም. የኢሕአፓ እንቅስቃሴ በአምቦ ከተማስለነበረ ት/ቤቶች በእነሱ ትዕዛዝ እየተዘጋ እሳቸውና መሰሎቻቸው ባለማወቅ ለመማር ሲሄዱ ጥቃት ይደርስባቸው ነበር። የተማሩት ሰላም መሆኑን እያረጋገጡ በመንቀሳቀስ ነበር።

የሚያገኙትን መጽሐፍ በሙሉ ያነቡ ስለነበረ ‹‹This Crowded Planet›› ማለትም ይህች የተጣበበች ዓለም የሚል በአሜሪካኖች የተጻፈ መጽሐፍ ስለሕዝብ ብዛት መጨመር እና ስለተፈጥሮ ሀብት እየተመናመነ መሄድ ይህንንም ለመለወጥ ምርምርና ምርታማ መሆን እንደሚያስፈልግ የሚጠቁም መጽሐፍ ያነባሉ። ይህን መጽሐፍ ካነበቡ በኋላ ‹‹ግብርና ባጠና ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፤ግብርና ደግሞ ምግብ አምራችና በጣም የሚያስደስት የሥራ መስክ ስለሆነ የምማረው ግብርና ይሆናል›› በማለት ለራሳቸው ቃል ይገባሉ። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከሦስት ነጥብ በላይ በማምጣት በ1971 ዓ.ም. ዓለማያ የእርሻ ኮሌጅ ለመማር ይሄዳሉ።

ከፍተኛ ትምህርት

በዓለማያ የእርሻ ኮሌጅ(የአሁኑ ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ) በእጽዋት ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1974 ዓ.ም. መጨረሻ አገኙ። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የአንደኛና ሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያሉ በአብዛኛው ወጣትና አዲስ ተመራቂ አስተማሪዎች ስለነበሩ ‹‹ዩኒቨርሲቲ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አይደለም፤ በራስህ ተፍጨርጭረህ ተወጣ፤ አለበለዚያ ትባረራለህ›› የሚሉ መኖራቸውን በትዝብት አስተውለዋል።

ተማሪዎችን እንደ ወላጅ ከሚወዱና ከሚያበረታቱ የኔታ እና ሌሎች መምህራን አንጻር ሲያዩዋቸው ለየት ብሎባቸው ግር ይላቸው ነበር። ሦስተኛ እና አራተኛ ዓመት በሚማሩበት ጊዜ ግን ቀደም ሲል እንዳስተማሯቸው ዓይነት በሳልና ጥሩ መምህራን እንዳጋጠሟቸው ይናገራሉ። የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሳሉ በግቢው ውስጥ የውሃ ወለድ በሽታ በመግባቱ ከታመሙ ተማሪዎች አንዱ ሆነው በሽታው ጠንቶባቸው ኮሌጁና ጓደኞቻቸው አሳክመዋቸዋል።

 በሐረር ሕይወት-ፋና ሆስፒታል እሳቸው ግን ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ ፍላጎታቸውን ሲገልጹ፣ ጓደኞቻቸው ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ከማበረታታት በተጨማሪ ተገቢውን እገዛ ስላደረጉላቸው ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ ለመመረቅ ችለዋል። ስለሆነም ‹‹ለእነዚያ ባለውለታዎቼና ለሌሎችም መልካም አድራጊዎች ልባዊ ምስጋናዬ በእናንተ በኩል ይድረሳቸው›› ብለዋል።

በመቀጠል ካናዳ በሚገኝ ሳስካቹአን ዩኒቨርሲቲ ተምረው በእጽዋት ሳይንስ በተልባ ማሻሻያ የድህረ-ምረቃ ዲፕሎማ በ1981 ዓ.ም.አግኝተዋል። በዚያን ወቅት እሳቸው መልካ ወረር የምርምር ማዕከል ከፍተኛ የሙቀት መጠኑ ከ30-40 ዲግሪ ሴንትግሬድ ከሚደርስበት ወደ ዝቅተኛ የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች ከ45 ዲግሪ ሴንትግሬድ የሚደርስበትወቅት ላይ (በጥር ወር) በመሄዳቸው ከፍተኛ ዝግጅት ቢያደርጉም ከአየር ለውጡ፣ ከውጪ የኑሮ ሁኔታና ከትምህርቱ ጫናዎች የተነሣ አንዳንዴ ያሉበት አቅጣጫ ይጠፋባቸው ነበር። በመጨረሻ የተማሩት ደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ፊሪ- እስቴት ዩኒቨርሲቲ በ1992 ዓ.ም.የማስተርስ እና በ1995 ዓ.ም. የፒኤችዲ(የዶክትሬት) ዲግሪያቸውን በእጽዋት ሳይንስ በተልባ ላይ ምርምር በማድረግ ነበር።

የሥራ ተሞክሮ

በሐረማያ የግብርና ኮሌጅ እጩ ተመራቂ ተማሪ ሳሉ በበቆሎ ላይ የሚያደርጉትን ምርምርና የትምህርት ውጤታቸውን መምህራቸው በማየት የቀድሞው የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት) እንዲመደቡ ያደርጋሉ። መልካ-ወረር የምርምር ማዕከል ዕጣ ስለደረሳቸው የቆላ ቅባት ሰብሎች (ሰሊጥ፣ ለውዝ እና ሱፍ) ማሻሻያ (Breeding) ለ10 ዓመታት ያህል ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው 11 የሰሊጥና የለውዝ ምርጥ ዝሪያዎችን ለተጠቃሚዎች አውጥተዋል። ከምርምሩ በተጨማሪ የሥራ ክፍሉን ከማስተዳደር በላይ ማዕከሉንም በሥራ-አስኪያጂነት ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል።

ከ10 ዓመታት የቆላ ቅባት ምርምር አገልግሎት በኋላ ወደ ሆለታ ምርምር ማዕከል ተዛውረው በደጋ የቅባት ሰብሎች ማሻሻያ (ተልባ፣ ኑግ እና ጎመን- ዘር) ምርምር እንዲሠሩ ዕድሉን አግኝተዋል። እዚያም ከምርምር ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን 10 ምርጥ የደጋ ቅባት (የተልባ፣ የኑግ፣ የጎመን ዘር) ምርጥ ዝርያዎችን ለአምራቾች አውጥተዋል። የሆለታ ማዕከልንም ለሁለት ዓመታት በዳይሬክተርነት ከመሩ በኋላ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ተዛውረው በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል። አሁን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪና የምክትል ዋና ዳይሬክተር አማካሪ በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ከሙያቸው እንዲሁም ከምርምር አመራር ጋር በተያያዘ ተቋማቸውንና አገራቸውን በመወከል በበርካታ የአፍሪካ፣ አውሮፓ እና የእስያ አገሮች አጫጭር ሥልጠናዎች፣ ትምህርታዊ ጉብኝቶችና አውደ- ጥናቶች ላይ ተካፍለዋል።፡ በዚህም እጅግ በርካታ የዕውቀትና የልምድ ልውውጦች አድርገዋል። ያገኙትን ዕውቀትና ልምድም ለሥራ ባልደረቦቻቸው አካፍለዋል፣ የምርምር ሥራዎች እንዲሻሻሉም በግብአትነት ተጠቅመውበታል። ከሌሎች ጋር በመሆንም የማስተርስና የዶክትሬት ተማሪዎችን በተገቢው ልክ በማማከር አጥጋቢ ሥራና ውጤት እንዲያመጡ የድርሻቸውን ተወጥተዋል።

የምርምር ትኩረት፣ ውጤትና ግምገማዎች

ዶ/ር አዱኛ ስለምርምር ሥራቸው ሲያስረዱ፤ ‹‹የምርምር ትኩረቴ በኔ ምርጫ ሳይሆን በዕጣና በአለቆች ውሳኔ የቆላና ደጋየቅባት እህሎች ማሻሻያ ላይ ነበር። በምርምር ቆይታዬ ወቅት ከሙያ ባልደረቦቼ ጋር ሆነን በድምሩ 21 ምርጥ ዝሪያዎችን ከአመራረትና የሰብል ጥበቃ ዘዴአቸው ጭምር አውጥተን ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ አድርገናል።

መነሻ ዘሮቻቸው (አራቢና ቅድመ መሥራች ዘር) በጥራት ተባዝተው፣ በሰፊው ለሚያበዙና የቅድመ ማስተዋወቅ ሥራዎችን ለሚከውኑ አካላት አስተላልፈናል። ይሁንና የቅባት ሰብሎች ከሌሎች የመስክ ሰብሎች (በቆሎ፣ ስንዴ፣ባቄላ… ወዘተ) አንጻር ሲወዳደሩ ምርታማነታቸው በተፈጥሮ አነስተኛ በመሆኑ፣ከውጪ በእርዳታና በግዥ የሚገቡ ዘይቶች አሉታዊ ጫናዎች እንዲሁም በሌሎች ተጽዕኖዎች ምክንያት እንደሌሎቹ የግብርናው ንዑስ-ሴክተሮች ሁሉ እንደተፈለገው አላደጉም። ስለሆነም በአንፃራዊነት ምርታማነታቸው የተሻሉ (የውጪ ሱፍ፣ ጎመንዘር፣ ተልባ፣ ሰሊጥ እና ለውዝ) ላይ የበለጠ ትኩረት ተሠጥቶ ምርምሩ ቢቀጥል መልካም ይመስለኛል›› ብለዋል።

በመቀጠልም፤ ‹‹በሳይንሳዊ ህትመት ረገድም ከሙያ ባልደረቦች ጋር በድምሩ ወደ 85 ህትመቶች (32 የጆርናል ወረቀቶች፣ 16 የመጽሐፍ ምዕራፎች፣ 35 የአውደ- ጥናት ጽሑፎች፣ የአመራረት መመሪያዎችና ዜና መጽሔቶች) አሳትመን ግኝቶቻችንን ልምዳችንን እና ዕውቀት ለሌሎች አካፍለናል።

የተማረ የሰው ሀብት ከመገንባት አንጻር፣12 የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች (4 ፒኤች ዲ እና 8 ማስትሬቶችን) ከሌሎች የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር አማክረን ዲግሪአቸውን በጥሩ ውጤት እንዲጨርሱ አድርገናል። በጥቅሉ ላለፉት 38 ዓመታት በነበረን የፖሊሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የማሕበረሰብ፣ የባህል ወዘተ.ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን፣ የበኩሌን የምርምርና የአስተዳደር ድርሻ ለመወጣት ሞክሬያለሁ። ይሁንና እነዚህ ጥረቶች በቂ ናቸው ማለቴ አይደለም። ስለዚህ የቀሩት ክፍተቶች በደንብ እየተለዩና የተሻለ ምርምር ለማድረግ ለልማት ትኩረት ተሠጥቶ በጉልህ ጥረቶቹና ድጋፎቹ መጠናከር አለባቸው›› በማለት ገልጸዋል።

የተልባ ምርምር

ዶ/ር አዱኛ ከካናዳ ዩኒቨርሲቲ በተልባ ላይ ምርምር አድርገው ተምረው ሲመጡ በቲሹ ካልቸር የተሻሻሉ 40 የተልባ ዝርያዎችንና ሌሎችንም የሰብል ዝርያዎችን ይዘው ቢመጡም ለሰብሎቹ ተስማሚ በሆኑት ደጋማ የምርምር ማዕከል መመደብ ሲገባቸው ቀደም ሲል በነበሩበት መልካ ወረር የምርምር ማዕከል ስለተመደቡ የተማሩበትንና ያመጡትን ዝርያዎች ወዲያው ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንዳልተፈጠረላቸው ይናገራሉ።

ይሁንና ከተወሰኑ ዓመታት ቆይታ በኋላ ሆለታ ስለተመደቡ ተልባ ላይ ምርምር ማድረግ በመጀመራቸው ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለሆለታ፣ ለአዴት፣ ለሲናና፣ ለቁሉምሳ፣ ለአዋሳ፣ የመሳሰሉ የምርምር ማዕከላትና በአካባቢያቸው ላይ ምርምር በመደረጉ ከካናዳ ካስገቡት ውስጥ በመረጣና በማዳቀል በአጠቃላይ ከአምስት የሚበልጡ የተሻሻሉ ምርጥ ዝርያዎች በብሔራዊና በክልል ደረጃ ማውጣት ተችሏል።

በፊት ተልባ በብሔራዊ ደረጃ በሔክታር ከሁለት እስከ አራት ኩንታል ይመረት ከነበረው፣ ምርጥ ዘርና የተሻሻሉና አሠራሮችን በመጠቀም በሔክታር ከስምንት እስከ አስር ኩንታል ማምረት ተችሏል። ‹‹በገበሬ ማሳ ላይ በተደረገው ምርምር ሁሉንም ግብአቶች በአግባቡ ተጠቅመን እስከ 15 ኩንታል በሔክታር ማሳደግ እንደሚቻል መረጃዎች ያሳያሉ። ስለዚህ አሁን ያለንበት በቂ ስላልሆነ የበለጠ ለምርምሩ ትኩረት ሰጥቶ ልማቱን ማፋጠን ይጠበቅብናል›› ይላሉ።

ያገኙት እውቅናና ሽልማት

በምርምርና በአመራር ሥራ ከሠሩበት ተቋም ዋና መሥሪያ ቤት ለረጅም ጊዜ ላስመዘገቡዋቸው ውጤቶችና ለሠጧቸው አገልግሎቶች የክብር እውቅናዎች፣ በርካታ የምስክር ወረቀቶችና ሽልማት ተሠጥቷቸዋል። አብረው ከሠሯቸው ዓለምና አገር አቀፍ ድርጅቶች፣ ከወረርና ከሆለታ ምርምር ማዕከላት እንዲሁም ከሆለታና ቡራዩ ከተማ መስተዳድሮች ላበረከቱት የልማት አስተዋፅኦ የምሥጋና እና የምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል።

በግብርና ምርምር ሥራ የሚያደንቋቸው

ዶ/ር አዱኛ በግብርና ምርምር ሙያ ሥራ አስተዋጽኦ ካደረጉ ባለሙያዎች ውስጥ ከሚያደንቋቸው መካከል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትን ለብዙ ዓመታት በዋና ሥራ አስኪያጅነት የመሩት ዶ/ር ስሜ ደበላ አንዱ ናቸው። ዶ/ር ስሜ ከልባቸው ሳይንሱ ላይ እምነት ስላላቸውና አገራቸውን ስለሚወዱ፤ በግብርና ምርምር ሳይንስ አገራቸው እንድትጠቀም በእውነት ተግተውና ከመንግሥት ጋር ተከራክረው የሠሩ የምርምር መሪ ነበሩ። አሁን በህይወት የሉም፤በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ አንድ የአስተዳደር ህንጻ በስማቸው ተሰይሞላቸዋል።

ከዶ/ር ስሜ ደበላ በመቀጠል የሚጠቅሷቸው ዶ/ር ህሩይ በላይነህ ናቸው። ዶ/ር ህሩይ ጠንካራ ተመራማሪ፣ ምርምር በጥራት እንዲሠራ የሚተጉ፣ ከራሳቸው ህይወት በላይ ለምርምሩ ሥራ ቅድሚያ የሰጡ እንዲሁም ስነምግባርን የተላበሱና ለምርምር ሥራ የተሰጡ ባለሙያ ነበሩ። አሁን በህይወት የሉም፤የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በስማቸው ሰይሞላቸዋል። ዶ/ር በዳዳ ግርማ በምርምር ሥራቸው ከሚያደንቋቸው ተጠቃሽ ባለሙያ አንዱ ናቸው።

ቀደም ሲል መልካ ወረር በጥጥ ላይ የምርምር ሥራ ይከውኑ ነበር፤አሁን ቁሉምሳ የምርምር ማዕከል የስንዴ ምርምር ላይ ይሠራሉ። ዶ/ር በዳዳ ረጋ ያሉ አስተዋይ ተመራማሪ፣ በህዝብም ሆነ በባለሙያ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የአመራር ክህሎት ጭምር ያላቸው መሆናቸውን ያወሳሉ። ከአገር ውጪም እንደ ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ እና ዶ/ር ዘሪሁን ታደለ የመሳሳሉት ህዝብና አገር ወዳድ ተመራማሪዎችን በዋናነት ለመጠቆም ያህል እንጂ በርካቶችን መዘርዘር ይቻላል ብለዋል።

መልካም አጋጣሚ

በሥራቸው መልካም አጋጣሚ የሚሉት ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ በመመ ደባቸው የምርምር ሥራዎችን በዝርዝር እንዲያውቁና እንዲከውኑ መንገድ የከፈተላቸው መሆኑን ነው። ከብዙ ተመራማሪዎች፣ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር አስተዋውቋቸዋል። በትምህርት ቤት ወይም ዩኒቨርሲቲ ያልተማሯ ቸውን በርካታ ዕውቀቶች፣ ከህሎት እና ልምዶች ያገኙት በምርምር ተቋም በኩል መሆኑን ይናገራሉ። በአጠቃላይ ለደረሱበት ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ፣ ላስመዘገቧቸው ውጤቶች እና ተሞክሮዎች ከዚሁ ተቋም ጋር የተገኙ መልካም አጋጣሚዎች ናቸው።

ተግዳሮት

በሥራ ላይ ስላጋጠማቸው ተግዳሮት ሲገልጹ ‹‹ከመነሻው መልካ-ወረር የምርምር ማዕከል ስመደብ፣ የማላውቀው ቆላማ የአየር ሁኔታና አካባቢው የወባ በሽታ ስላለበት እና አዳዲሶቹ ሰብሎች (ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ የቆላ ጥራጥሬዎች፣ ጥጥ… ወዘተ) በጥቅሉ ሁሉም ነገር አዲስ ሆኖ ፈተና ማስከተሉ አልቀረም። ተወልጄ ያደግሁት ደጋማ አካባቢ ስለነበር፣ በረሃውንና የአካባቢውን ተፅእኖዎች መቋቋምና አዲሱን የምርምር ሥራ መከወን ራሱን የቻለ ፈተና ነበር። የምርምር ሥራ በቂ ሀብት (ሰው፣ የሥራ መሣሪያ፣ ገንዘብ፣ ሙያ፣ ጥንቃቄ፣ ትኩረት፣ ጊዜ…) የሚፈልግ እና ታቅዶ የሚሠራ ሆኖ ሳለ፤ አንዳንዴ በጀቱ በድንገት ተቀንሶ እንደ ምንም አብቃቅታችሁ ሥሩ ሲባል ከሁሉም ተመራማሪ፣ ሠራተኛና ተገልጋይ ጋር ያጋጫል።

እንደ አፋር ላሉት አካባቢዎች በጊዜው የነበረው የምርምርና ልማት አቅጣጫና ትኩረት ከአካባቢው ህዝብ ፍላጎትና ዓላማ ጋር ስለማይጣጣም፣ እንደ ተመራማሪም ሆነ እንደ አመራር ሁነህ እነዚህ ኃይሎች በሚፈጥሩት ግጭትና ውዝግብ መካከል ላይ መንገላታት ይኖራል። በተለይም በበላይ አካላት ውሳኔ፣ አመራር ላይ ተመድቤ ወረር፣ ሆለታና ዋና መሥሪያ ቤት ያገለገልኩባቸው ዘጠኝ ዓመታት ከየጊዜው ውዝግቦች ጋር ተዳምረው ለእኔ ከባድ የፈተና ወቅቶች ነበሩ።

ከሚጠቀሱት ተግዳሮቶች ውስጥ ከደርግ ወደ ኢህአዴግ የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት ወቅት የወረር ማዕከልና አካባቢው እንዳይዘረፍ እና እንዳይፈርስ ከሥራ ባልደረቦቼና ከአካባቢው ህዝብ ጋር ተባብረን ጠብቀናል፤በወቅቱ ባደረግነው ትግል እስከ ዛሬ ምርምር እየተሠራበት በቀጣይነት ልማቱን እንዲያግዝ አድርገናል።

በሁለተኛ ደረጃ በመሠረታዊ የአሠራር ለውጥ (BPR) ምክንያት በተቋሙ ውስጥ ብዙ ነገሮች የተወሳሰቡበትና በውጥንቅጦች የተሞሉ ሁኔታዎች ስለነበሩ ወደ ነበረበት ጤናማ የሥራ መንፈስ ለመመለስ ብዙ ጥረቶችን ጠይቋል። ቀጥሎም በ2008 ዓ.ም.፣ በህዝብ ብሶትና በወጣቶች ተቃውሞ አገሪቱ ስትናጥ፤ተቋሙ የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር መዘጋጀት፣ መከወን፣ መምራትና ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ማሸጋገር ቀላል አልነበረም።

በርካታ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ፣ አከራካሪና አወዛጋቢ ነገሮችን ለመፈጸም ሁኔታዎች ያስገድዱ ስለነበር፣ ወቅቱ በጣም አስቸጋሪና በፈተና የተሞላ ነበር ማለት እችላለሁ። ይሁንና ከእነዚህ ፈተናዎች ብዙ ተምሬአለሁ። የሚገጥሙንን የኑሮና የሥራ ፈተናዎች በትዕግስት መያዝና ከህብረተሰቡ ጋር ለመፍታት መሞከር፣ በቅን ልቦና ማገልገል እና ሁሌ ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ መሞከር በሰውም ሆነ በፈጣሪ ዘንድም ተቀባይነት አያሳጣምና በዚሁ መንፈስ መኖርና ማገልገል ጠቃሚ ይመስለኛል›› ብለዋል።

የደስታና የሀዘን ጊዜ

በኑሮም ሆነ በሥራ አጋጣሚ ደስታና ሀዘን ይፈራረቃሉ፤ይህን አሰቀድሞ በመገንዘብ ሚዛን ጠብቆ አማካዩን ይዞ መኖር ነው። የእነዚህን ተፈራራቂ ክስተቶች አይቀሬነት ተገንዝበን አያያዛቸውን ማሳመር ይጠበቅብናል የሚሉት እንግዳችን በተለይ የዶክትሬት ዲግሪ ምርቃታቸው ዕለት ዋነኛ የደስታቸው ቀን ነበር።

በተቃራኒው እጅግ ያዘኑበት ቀን ደግሞ ‹‹እርሷ ሳትማር እኛን በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስተማረችን ታላቅ እህታችን እኛን እንዳስተማረችን ልጆቿን እያስተማርን እያለን በድንገት የሞተች ዕለት ነው›› በማለት ከገለጹ በኋላ ‹‹ግብርና መርጬ ስማር ዋናው ዓለማዬ ረሃብን ለመቀነስ ቢቻል ለማጥፋት ነበር። ይህ ደግሞ የሁላችንም ምኞት እንደሆነ አውቃለሁ፤ ሳናሳካው ሙሉ ደስታ ሊኖረን ከቶውንም አይችልም። ስለሆነም ይህ ራዕይና ተልዕኮ እውን እስኪሆን ድረስ፣ ሁላችንም በምንችለው ሙያና አቅም መረባረብ አለብን።

ለራሱም ሆነ ለህዝቡ ክብርና ደህንነት የሚጨነቅ ዜጋ ሁሉ በዚህ ረገድ የበኩሉን ጥረትና ትግል ሊቀጥልበት ይገባል። የአርብቶ/አርሶ-አደሩ ህይወትና ኑሮ እስኪለወጥ ብሎም የተመጋቢው ህዝብ ፍላጎት በተጨባጭ መቀየር እስካልተቻለ ድረስ ቁጭቱ፣ ትካዜውና አደጋው እንዳይቀጥል ጉዳዩ የሚመለከተን ሁሉ የየበኩላችን ድርሻ ማበርከት ግዴታችን ነው›› በማለት በተገቢው ልክ ባለመሳካቱ ሀዘን እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

የቤተሰብ ሁኔታ

ዶክተር አዱኛ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው። ባለቤታቸው ወ/ሮ ፀጋነሽ አባተ ይባላሉ፤ የቤተሰባቸው መሪና የራሳቸው አነስተኛ ንግድ እና በግቢያቸው ውስጥ የሚንከባከቡት ዕፅዋት አላቸው። ቤተሰባቸው መሳተፍ በሚያስፈልገው ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ወደር በማይገኝለት ሁኔታ ሁሉንም የሚሸፍኑት ባለቤታቸው ናቸው። ይህም በመሆኑ የምርምር ሥራቸውን ተረጋግተው እንዲሰሩ ከፍተኛ እገዛ አድርገውላቸዋል።

ለስኬታቸው ሁሉ የባለቤታቸው እገዛ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ ምስጋናቸውም ከልብ የመነጨ ነው። ዘመዶቻቸውም ሆኑ ጎረቤቶቻቸው በምርምር ሥራቸው ምክንያት ጊዜ እንደማይኖራቸው ተረድተው ስለሚተባበሯቸው በማህበራዊ ጉዳዮች ሙሉ ተሳትፎ ባለማድረጋቸው ብዙም ጫና እና ተቃውሞ አያቀርቡባቸውም፤ ለዚህም ምስጋና ያቀርባሉ። የመጀመሪያ ሴት ልጃቸው ኢንጂነር ቢፍቱ አዱኛ፣ እየሠራች የማስትሬት ዲግሪዋን እየተማረች ትገኛለች። ሁለተኛው ወንዱ ልጃቸው ብሥራት አዱኛ፣ 3ኛ ዓመት የኮምፕዩተር ሳይንስ (ICT) ተማሪ ነው። የሙያ ምርጫው የእነርሱ ሆኖ ግብርናን በተዘዋዋሪም ቢሆን እንዲረዱ ከልጆቻቸው ጋር ይወያያሉ።

ስለልጅ አስተዳደግ

ቤተሰብ ስለልጅ አስተዳደግ በደንብ ማወቅ አለበት። አካባቢ፣ትምህርት ቤት እና የአቻ ግፊት ተጽእኖ እንደሚያደርግ በደንብ መረዳት ያስፈልጋል። እንደ የኔታ ግርማ ያሉት ቅን መምህራንም ትውልዱን በበጎ መንፈስ የመቅረጽ ጉልህ ድርሻ አላቸው። አሉታዊ የአቻ ግፊት ተጽእኖን መከላከል ያስፈልጋል፤ አንዱ ብዙዎች ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ በአስተሳሰብና በድርጊት ተበክሎ ሌላውን ሊበክል ይችላል።

ወላጅ (ቤተሰብ) በተቻለ መጠን ሳይሰለች ማታ ማታ የትምህርቱን ሁኔታ፣የዕለት ተዕለት ውሎን ነጻ አድርጎ በማቅረብና በማወያየት ክትትል ማድረግ አለበት። ወላጆች ለልጆቻቸው በጎውን፣ በጎ ካልሆነው እንዲለዩና እንዳይታለሉ እገዛ ማድረግ አለባቸው፤ አለበለዚያ ልጆች እያየናቸው ይጠፋሉ፣ ሌሎችንም ያጠፋሉ በማለት በልጅ አስተዳደግ ላይ ወላጅ(ቤተሰብ) ከፍተኛውን ድርሻ ወስዶ ክትትል ማድረግ እንደሚገባውና ለቀጣዩ ጤናማ የህብረተሰብ ምሥረታ ግዙፍ ኃላፊነት መሆኑን በህይወት ተሞክሮ ካስተዋሉት አስተያየታቸውን ለግሰዋል።

የሕይወት ፍልስፍና

ጠንክሮ መሥራት፣ በቅን ማገልገል እና በመርሆ ተመርቶ በራስ መተማመን የሚከተሉት የህይወት ፍልስፍናቸው ነው።

ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011  

ስሜነህ ደስታ