ኃላፊነት የከበደው አራተኛው መንግሥት

25

የዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ማኅበር ‹‹ሲፒጄ›› በፈረንጆቹ ታህሳስ ወር 2018 ላይ ባወጣው የጥናት ሪፖርት እንዳስታወቀው 251 ጋዜጠኞች በተለያዩ ሀገራት በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ቻይና፣ ግብፅ እና ሳውዲ አረቢያ ብዙ ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚዎቹ ሀገራት ሲሆኑ፤ አፍሪካ ለጋዜጠኞች ከማይመቹ አህጉራት መካከል ግንባር ቀደም እንደሆነች ገልጿል፡፡ አፍሪካ ስንል ኢትዮጵያን እንደምናስታውሳት ግልፅ ነው፡፡

ይኸው ተቋም በሌላ ጥናቱ እንደገለፅው ደግሞ እ.ኤ.አ. እስከ 2004 በእስር ላይ ያለ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ያልነበረ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ ግን ቁጥሩ የበዛ ጋዜጠኛ እየተነዳ ቃሊቲ መወርወሩን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ እንግዲህ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ጀምሮ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ለነበሩ አስራ ሦስት ዓመታት የጋዜጠኛው እንባ በየእስር ቤቱ የሚፈስበት ጊዜያት ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ዓለም አቀፍ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን የአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ እስር ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ታስረው እንደነበር ጠቅሶ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ማረሚያ ቤቶች አንድም ጋዜጠኛ እንደማይገኝ አመልክቷል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ዓመት የለውጥ ጉዟቸው ለታገዱ የመገናኛ ብዙኃን እንደገና ወደ ሥራ እንዲገቡ ፈቃድ በመስጠት፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችን በመፍታት፣ ክልከላ የተደረገባቸውን የዜና እና የድረ-ገፅ ዘገባዎች ፈቃድ እንዲያገኙ በማድረግ «አስደናቂ ሥራ» መሥራታቸውንም ድርጅቱ ገልጿል ከዚህ በፊት ታግደው የነበሩ 263 ድረ- ገጾች እና ጦማሮች፣ 23 የሕትመት ውጤቶች እና መቀመጫቸውን በውጭ አድርገው የነበሩ ሁለት የቴሌቪዥን (ኢሳት እና ኦ.ኤም.ኤን) ጣቢያዎች ሀገር ውስጥ እንዲሠሩ፣ ስድስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ አዲስ የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቅሷል በእርግጥ ትናንትን እያነሱ ማውገዙ ለዛሬው ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ምላሽ ሊሆን አይችልም፡፡

ጥያቄው ዛሬ ላይ ጋዜጠኞች በነፃነት እንዲሠሩ አውዱን ለማስፋት እና መገናኛ ብዙኃንን ለመለወጥ መንግሥት ራሱ ምን እየሠራ ነው? የሚለው ነው፡፡ ዛሬ የተተካው አዲስ ትውልድ የሚፈቅደው የዘመኑ ዕድገት በሚመጥነው መልኩ አዲስ አስተሳሰብ እና አዲስ አሠራር ማየትን ነው፡፡ ለዚህ የሚመጥን ምላሽ ለመስጠት ሚዲያውም ሆነ የሚዲያው መሪዎች ብቁ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ የሚዲያ ተቋማቱም ሆኑ ጋዜጠኞች ሕገ ወጥ አሠራሮችን መታገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዴሞክራሲ መብት ዋነኛው መገለጫም ብዝኃነትን ያከበረ እና የሚያንጸባርቅ የሚዲያ ነጻነት መኖር እና መሥራት መቻሉ ነው፡፡

እንደ ዕድል ሆኖ የሀገራችን መገናኛ ብዙኀን ዴሞክራሲያዊ ሚናውን መወጣት ቀርቶ በተለያዩ ምክንያቶች በሀገር ደረጃ ማደግ እና መድረስ የነበረበትን ያህል ለመራመድ አልቻለም። የፕሬሱ ዕድገት ቢረጋገጥ ከአማራጭ የመረጃ ምንጭነቱ በተጨማሪ ብዝኃነትን በማጎልበት እና ዴሞክራሲያዊ ሚናውን በመወጣት ተጠቃሚው የሚሆነው መንግሥትም ሕዝብም ነበር፡፡

ለዕድገቱ መቀጨጭ እና ለሕልውናው መጥፋት የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የቢሮክራሲው ጣልቃ ገብነት፤ ግብር እና ታክስ መጨመር እና ከአቅሙ በላይ መሄድ፤ በሕትመት ወረቀት መወደድ እና መናር ምክንያት ብዙዎች ከገበያ በጫና መውጣታቸው፤ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸው የፋይናንስ አቅም ማጣታቸው፤ ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰቦች በሚመጡ ተደራራቢ ክሶች እና ቅጣቶች፤ ዘርፉ ካለበት የተለያየ ጫና በመነሳት በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ ዜጎች ፍላጎት ማጣት እና መሸሽ፤ የገበያ ሥርጭቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ለማለፍ አለመቻሉ በገበያው ተፎካካሪ ሆነው ለመቆየት ሳያስችላቸው መቆየታቸውን በዘርፉ ለበርካታ ዓመታት የተሳተፉ ባለሙያዎች ሲገልፁ ይደመጣሉ፡፡

ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ እንደ አዲስ ወደ ሥራ ተመልሰው አሊያም በአዲስ መልኩ ተቋቁመው የፈለጉትን፣ ያገኙትን፣ የመሰላቸውን ሀሳብ ወደ ማኅበረሰቡ እያቀረቡ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ቁጥር መጨመሩን በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው የዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ማኅበር ሪፖርት ያመላክታል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የታየው የመገናኛ ብዙኃኑ ቁጥር መጨመር ምን ያሳያል? በመገናኛ ብዙኃኑ ላይ የታዩት በጎ ለውጦች እና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? መገናኛ ብዙኃን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ ነው ወይ? የሚሉ ሀሳቦችን ለባለሙያዎች እና ለምሁራን በማቅረብ ዋንኛ የሚባሉትን መገናኛ ብዙኃን መሠረታዊ መልካም ጎኖችን አንስተው እንዲያበረታቱ፣ እንከኖችን ጠቁመው መፍትሔ እንዲያመላክቱ ማድረግ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ዓላማ ነው፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ዙሪያ ለውጦች ታይተዋል የሚል እምነት ካላቸው ምሁራን መካከል አንዱ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሂውማኒቲስ ፋካሊቲ ምክትል ኃላፊ አደም ጫኔ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ከለውጦች መካከልም የሚዲያ ምሕዳሩ መከፈት መጀመሩን በዋናነት ያነሳሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ወደ 20 የሚጠጉ አዲስ የሕትመት እና የብሮድካስት ሚዲያዎች መፈጠራቸው፣ ከሀገር ውጪ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸው፣ አይነኬ ይባሉ የነበሩ ጉዳዮች በመንግሥት ሚዲያዎች ሁሉ ሲቀርቡ እየታዩ እና በርካታ ድምጾችም እየተሰሙ በመሆኑ የሚዲያው ምሕዳር እየሰፋ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ሁለተኛ ዲግሪውን ለማጠናቀቅ የመመረቂያ ጽሑፍ እያዘጋጀ ያገኘነው ያሬድ ሰለሞን ደግሞ በዶክተር አደም ሀሳብ አይስማማም ያሬድ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ የታዩትን ለውጦች ‘’ከዚህ ቀደም ከነበረን ታሪክ እንደምንረዳው መንግሥታት ሲቀየሩ፤ ሚዲያውን የመክፈት ባህሪ አላቸው ሚዲያዎች አዲስ የመጣውን መንግሥት ማጀገን፤ ያለፈውን ደግሞ ማሳጣት ሥራዬ ብለው ይያያዙታል መንግሥትም ሚዲያዎቹ ፊታቸውን ወደ እሱ እስኪያዞሩ ድረስ በይሁንታ ይዘልቃል’’ ሲል ሀሳቡን ያስቀምጣል የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደርም ለሚዲያዎች ምን ያክል ክፍት መሆኑ የሚፈተነው በቀጣይ በሚኖሩ ሁነቶች እንደሆነ ያስባል

ዶ/ር አደም ግን ‹‹ባለፈው አንድ ዓመት የሚዲያ ምሕዳሩ መስፋትን ሊመጥን የሚችል ፣ በሥነ ምግባሩ የታነጸ፣ ሙያውን የሚያከብር ጋዜጠኛ እጥረት መኖር እንጂ ምሕዳሩ መስፋት እውነት ነው›› ይላሉ የሚዲያ ፍልስፍና ስለመኖሩ ከመንግሥት በግልጽ አልተ ነገረም፡፡ እንደእሳቸው ገለፃ ከዚህ ቀደም የነበረው ኢህአዴግ ባህሪው ሚዲያ ጠል ስለነበር ከሚከተለው ‘ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚያዊ ርዕዮተ ዓለም’ ጋር አብሮ ይሄድ ነበር

ዶ/ር አደም በሀገራችን መገናኛ ብዙኃን ዙሪያ ባለፈው አንድ ዓመት እንደ ችግር ተንፀባርቀዋል ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ ክልላዊ የሆኑ የሚዲያ ተቋማት ጽንፍ የያዙ ዘገባዎችን በስፋት እያስተናገዱ መምጣታቸውን ነው ‘’ከዚህ ቀደም በኢሳት እና ኢቲቪ መካከል እንመለከት የነበረውን ዓይነት የወገንተኝነት ዘገባ በክልል ሚዲያዎች መካከል እየታዘብን ነው’’ ይላሉ ፅንፈኝነት ማቆጥቆጥ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ሚዲያ ተግዳሮት፤ የምርመራ ጋዜጠኝነት ትኩረት ማጣት እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያዎች በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየፈጠሩት ያሉት ጫና ለአጠቃላይ የመገናኛ ብዙኃን ሥራ ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪ ስንታየሁ አባተ በበኩሉ “በሀገራችን ያሉት መገናኛ ብዙኃን ሳይሆኑ፤ የሕዝብ ግንኙነት ተቋሞች ናቸው’’ ይላል ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚያነሳው የክልል ሚዲያዎች የሚወክሉት እና የሚያንጸባርቁት የክልል መንግሥቱን ፍላጎት ብቻ መሆኑን ነው “ሚዲያው ለሚወግነው እና ለሚቀርበው የፖለቲካ ፓርቲ ከመከተል እና የተመረጡ ጉዳዮችን ብቻ ከመሸፈን ይልቅ ድምጻቸው ላልተሰማ የኀብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት መስጠት ይኖርበታል” ይላል

እንደሚታወቀው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የፕሬስ ነፃነትን አስመልክቶ፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሀሳቦች እና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል፤ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነት እና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል የሚል ግልፅ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡ ይህም ለሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መፋጠን የመገናኛ ብዙኃን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ያስችላል። በኢትዮጵያ የዘመናት የሕዝብ ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት፣ ሕልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛው ተልዕኮ እና ዓላማ መሆኑ አያጠያይቅም።

ይሁን እንጂ ይህ የመገናኛ ብዙኃን ተጠባቂ ዓላማ እና ሚና ከግብ እየደረሰ አይደለም የሚሉ በርካቶች ናቸው። በተለይ የሀገራችን መገናኛ ብዙኃን ምቹ አጋጣሚ ባገኙበት ባለፈው አንድ ዓመት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ሚናቸውን ‹አልተወጡም› ተብለው መወቀስ ያለባቸው የጋዜጠኝነት መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ብቻ መሆን እንዳ ለባቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ተሻ ገር ሽፈራው /ዶ/ር/ ይናገራሉ፡ ፡

የአብያተ ክርስ ቲያናት ወይም የእምነት ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የማስታወቂያ እና የሕዝብ ግንኙነት መገናኛ ብዙኃን ቢኖሩም፤ በአንድ ዓመት የሀገራችን የለውጥ ሂደት ላይ ዴሞክራሲያዊ ሚናቸውን ተወጥተዋል ወይም አልተወጡም ብሎ መገምገም የሚገባው የጋዜጠኝነት መገናኛ ብዙኃንን ብቻ መሆን አለበት የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡

በዴሞክራሲ ተቋም ቅርፅ ማደግ እንዳለባቸው የምናስባቸው፣ ልዩ ፀባያቸው የጋዜጠኝነት ሥነ- ምግባርን ማክበር እንዳለባቸው የሚያምኑ፣ መረጃ ሚዛናዊ እና ሥነ- ምግባራዊ በሆነ ሁኔታ መቅረብ እንዳለበት የሚያምኑ፣ ራሳቸውን እንደ ጋዜጠኛ የሚቆጥሩ፣ የቆሙበት መሠረትም በማኅበረሰቡ ካሉ ልዩ ልዩ ተቋማት የሚያገኟቸው ማስታወቂያዎች እንጂ በፖለቲካ ተቋማት የአባላት መዋጮ እየተደገፉ የፖለቲካ ቅስቀሳ የሚያካሂዱ መገናኛ ብዙኃን ያልሆኑትን እና መገናኛ ብዙኃንን ለይተን ሚናቸውን ተወጥተዋል አልተወጡም ብሎ መገምገም እንዳለባቸው ያወሳሉ፡፡

የፖለቲካ አቋም የያዙ፣ ያንንም አቋማቸውን እስከመጨረሻው ድረስ ተከራክረው ሄደው ሕዝብን ለማሳመን የሚሞክሩ፣ በማስታወቂያ ገቢ ሳይሆን በከፈቱት የባንክ አካውንት መዋጮ ከፖለቲካ ደጋፊዎች ሰብስበው የሚተዳደሩትን በሌላ መመዘኛ መመልከት አለብን የሚሉት ዶ/ር ተሻገር፡፡ እነዚህ በመገናኛ ብዙኃን ምሕዳር ውስጥ የተለየ ስፍራ እንዲይዙ ካልተደረጉ በስተቀር ሁሉንም አደበላልቀን እንደ ጋዜጠኝነት መገናኛ ብዙኃን የምንቆጥር ከሆነ ችግር ላይ እንወድቃለን ይ ላሉ፡፡

ዶ/ር ተሻገር ባስቀመጡት መሥፈርት መሠረት የጋዜጠኝነት መገናኛ ብዙኃን ባለ ፈው አንድ ዓመት ማናቸውንም ጉዳይ የማስተላለፍ ዕድል ቢያገኙም ዴሞክራሲያዊ ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው ወይ የሚል ጥያቄ አነሳን፡፡

 ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘትም የፖለቲካ አመራሮችን አነጋ ገርን። የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ግርማ ሰይፉም ምላሽ ሰጡን፡፡ አቶ ግርማ እንደሚሉት የጋዜጠኝነት የመገናኛ ብዙኃን ባለፈው አንድ ዓመት በተግባር እያየናቸው ያሉ ነገሮች በዴሞክራሲ ሂደቱ ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ሕዝብ መረጃ እንዲያገኝ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚዲያ ወድጀዋለሁ እና እጋራዋለሁ ‹ላይክ እና ሼር› በመንተራስ አላስፈላጊ ዕውቅና ለማግኘት እየሠሩ ነው፡፡ ዋና የተባሉት የመገናኛ ብዙኃን /ሜይንስትሪም ሚዲያዎች/ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ጋር ውድድር በመያዝ ‹ቀደሙን አልቀደሙን› በሚል እየሠሩ በመሆኑ፤ ለዴሞክራሲ ሂደት ያላቸውን ጠቃሚ ሚና እየተጫወቱ አይደለም፡፡

ሚናቸውን ለመወጣት ገና ብዙ ሥራ እንደሚጠብቃቸው እና ከእውነት ጋር መቆም እንደሚገባቸው አቶ ግርማ ያሳስባሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪው ቸኮል አበበ በበኩሉ ከለውጡ በኋላ የመገናኛ ብዙኃን ሚናቸውን ከመወጣት ይልቅ በሰልፍ ላይ ከተመሠረተው የሀገራችን ፖለቲካ ጋር ተሰልፈው እየሠሩ ነው ይላል፡፡ እንደእሱ ገለፃ መገናኛ ብዙኃኑ የሀገራችን ፖለቲካዊ ድባቡ ሰልፍ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ሰልፍን ለማሳመር፣ ለማደራጀት፣ ጥሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው።

 እዚያ እና እዚህ ሆነው መናቆር የሚፈልጉ አካላት የኔ የሚሉትን መገናኛ ብዙኃን ይዘውራሉ፤ ወይም ‹የኔ ድምፅ እየተሰማ ባለመሆኑ የራሴ ድምፅ ያስፈልገኛል› በሚል በአቅራቢያቸው የሚገኝ ሌላ መገናኛ ብዙኃንን የፖለቲካው መስመር አንዱ ተርታ እንዲሆን አድርገው እያሰሩት ነው። ይህ ዓይነቱ አካሄድ በጣም ፅንፍ የወጣ እና አድሏዊ የሆነ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እንዲፈጠር ምክንያት በመሆን አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ብሔረሰቦች /ህዳጣኑን/ ሙሉ በሙሉ ከጨዋታ ውጭ ያደርጋቸዋል።

 ምክንያቱም በርካታ ቁጥር እና የኢኮኖሚ አቅማቸው የደረጁ ብሔረሰቦች በሚያንቀሳቅሱት ሚዲያ የራሳቸውን ጉዳይ ለአደባባይ ሲያቀርቡ፤ በቁጥርም በኢኮኖሚም ዝቅተኛ የሆኑት ያለመ ሰማት ችግር ውስጥ ይገባሉ። ቸኮል በተለይ በየክልሉ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት የማጎልበት ሚናቸውን እየተወጡ ባለመሆኑ የተለያየ፣ የተፋጨ፣ በሀሳብ ሙግት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ ሰፋ ያለ ንግግር እንዳይኖር ያደርጋል ብሏል።

የመገናኛ ብዙኃን አንፃራዊ ብቻ ሳይሆን ሙሉ የሚባል ነፃነት አግኝተው ባሉበት ወቅት ሁሉንም ባይባልም እንኳ ብዙዎች በግልፅ ሚዛን ጠብቀው መሥራት ያልቻሉት ለምንድን ነው? በተለይ የክልል የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ቀርቶ ክልላቸው ያለ ሀገር አንድነት እንደማይቆይ የተረዱ እስከማይመስሉ ድረስ የሀገሪቱን ዋና ዋና ጉዳዮችን ሽፋን ከመስጠት ይልቅ ስለክልላቸው ጥቅም ወይም ችግር ብቻ በማቀንቀን ላይ የተወጠሩት ለምንድን ነው? ይህንንስ አካሄድ ማስቆም የሚችል አካል ለምን ጠፋ? ሥልጣን የተሰጠው መሥሪያ ቤትስ ምን እስኪመጣ ይጠብቃል? የሚሉ ጥያቄዎች ማንሳቱ ተገቢ ነው።

በሬዲዮ የምርመራ ጋዜጠኝነት አንቱ የተባሉት ጋዜጠኛ ንጉሴ ተፈራ (ዶ/ር) የትናንቷን ኢትዮጵያን ነገም ወደፊትም መሥራት የሚችለው ጋዜጠኛው ነውና ኃላፊነቱንም መደረብ ይገባዋል ይላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሚዲያውን በመጠቀም ለብሔራዊ ግንባታ እየሠሩ ያሉ ሚዲያዎች ጥቂት ቢሆኑም፤ በዛም አቅጣጫ የምናየው ምልክት ጠቃሚ ነው ያለንበት ጊዜ ለሚዲያው የሚያበረታቱ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው የሚዲያው ምሕዳር እየሰፋ መምጣቱን በግልፅ የምናየው ነው በሚዲያ ላይ የተሰማራ ባለሙያ የወደፊቷን ሀገር ከመገንባት እና የሕዝቡን ብሩህ ተስፋ፣ ዕውቀት ከማስፋት እና ሀገርን በአንድነት መንፈስ ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት።

የተገኘውን የሚዲያ ነፃነትም በኃላፊነት፣ በልክ፣ በመጠን ለመጠቀም ከምንጊዜውም በላይ የተመቸ እንደሆነ ያምናሉ።የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማይጠብቅ ጋዜጠኝነት ትርፉ መክሰር ነው የሚሉት ጋዜጠኛ ንጉሴ የሀገራችን መገናኛ ብዙኃን የሰከነ እና ገንቢ ውይይቶችን ከማካሄድ፣ ጠቀሜታ ያላቸው ሀገራዊ ጉዳዮችን ከማቅረብ እና ከማወያየት አኳያ በርካታ ችግሮች ይታዩባቸዋል ባይ ናቸው፡፡ በተለይ በየክልሎቹ የተቋቋሙት የመገናኛ ብዙኃን የጋራ ሀገራዊ ተልዕኮን ማሳካት ይልቅ ብሔር ተኮር መሆናቸው ለሚዲያው ችግር መስፋት ድርሻ እንዳላቸው ይገምታሉ፡፡

 ጋዜጠኛ ንጉሴ እንደሚሉት አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን አለፍ ሲልም ጠባብ የሆኑ አስተሳሰቦችን፣ ጎጠኛ የሆኑ አመለካከቶችን በመፈንጠቅ ሠላምን ከመገንባት ይልቅ ልዩነትን እና ግጭትን በማስፋት ሌላ እንቅፋት ሲፈጥሩ ይታያሉ፡፡ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት እና ጋዜጠኞች የሀገር ሠላምን ብሔራዊ ጥቅምን ሳይሆን፤ የፖለቲካ ወገንተኝነትንም የሚያንፀባርቁ፣ ሠላምን ሳይሆን አለመረጋጋትን የሚያበረታቱትንም እያየን በመሆኑ፤ ይህ ሕዝብን ከሕዝብ የሚለያይ፣ ጥላቻን የሚዘራ እና ግጭትን የሚነዛ፣ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትንምየሚጥስ ነው፡፡

ጋዜጠኝነት ማለት የተገኘውን እውነት ይዞ እንዳለ ማስተጋባት እንዳልሆነ ይታወ ቃል፡፡ እውነትን መናገር የሚለው የሙያውን ሥነ- ምግባር ለማክበር እና ለመተግበር መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉት፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ማንኛውንም እውነት ሁሉ የኅብረተሰቡን የአመለካከት አድማስ የሚያሰፋ እና ጠቃሚነት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ፣ አደጋ የማያስከትል እና መከፋፈልን የማያመጣ መሆኑን አስቀድሞ ማሰብ እና ማስተዋልን ይጠይቃል፡፡ ጋዜጠኛ በሳል እና ነገሮችን ከሥሩ የማጣራት ችሎታን እና አስተውሎትን መላበስ፣ የሌሎችን የሀሳብ ልዩነት በእኩልነት መቀበል፣ ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ መሆን ግዴታው ቢሆንም፤ አንዳንዶች ከመስመር ውጪ ኃላፊነትን ያላገናዘበ ተግባር ይከውናሉ፡፡

እየታዩ ያሉ ችግሮች ትኩረት ተሰጥቷቸው ፖሊሲ፣ መመሪያ ተዘጋጅቶ፣ መልክ ባለው ሁኔታ ሚዲያውን ማስተካከል እና ሚዲያው ኃላፊነቱን በተላበሰ መልኩ መሥራት አለበት፡፡ የምንሰማው ልቅ የወጣ፣ ኃላፊነት የጎደለው ጉዳይ፣ የምናነበው ማዕዘን የያዘ አዘጋገብ፣ የምንመለከተው ለወገን ያደላ ሀሳብ ወይም ጎጠኝነት በወቅቱ ሃይ ካልተባለ፣ የሚመለከተውም አካል ሥራዬ ለነገ ይቆይልኝ ካለ የሚያመጣው ችግር እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር እንኳን የሚያስቸግር መሆኑን ጋዜጠኛው ይናገራሉ፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዐብይ ወደሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት መገናኛ ብዙኃን በሁለት ጽንፍ ተለጥጠው የቆዩ ነበሩ የሚሉት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ዘላለም ተስፋዬ ናቸው ‘’በመንግሥት (የሕዝብ) እና በግል ሚዲያዎች ዘገባ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ነበር ዘገባዎቹ ጽንፍ የያዙ ነበሩ መካከል ላይ ቆሞ እውነታውን የሚያሳይ የሚዲያ አማራጭ አልነበረም ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡም በኋላ ይህ ሁኔታ እንዳለ ነው የተቀየረ ነገር የለም’’ ይላሉ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪው ቸኮል አበበ ገለፃ ሚዲያው በሕገ መንግሥቱ የተጎናጸፈውን መብት በአግባቡ ተጠቅሞ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚበጁ ሥራዎችን ሊሠራ እንዲችል መንግሥት የተለየ ትኩረት ለዘርፉ መስጠት ይጠበቅበታል መገናኛ ብዙኃን ለሀገር ልማት፣ ዕድገት፣ ሠላም፣ ለሕዝቦች በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት መሥራት የመቻላቸውን ያህል በጽንፈኛነት የሚቆመው ሚዲያ ደግሞ የሀገር ሠላም እና ደህንነትን በማደፍረስ በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዳይኖር ብሎም ወደ ብጥብጥ እና ግጭት እንዲያመሩ የማድረግ ሥራዎችን ሲሠራ በሀገራችንም በውጭውም ዓለም ታይቷል፡፡

 ስለዚህ ሚዲያውን የማጎልበት ሥራ የመንግሥትም የሕዝብም መሆኑን ቸኮል ያምናል፡፡ ነገር ግን የማኅበራዊ ሚዲያውን የፈጠራ ወሬ እና ፈጣን ሥርጭት ለመግታት መገናኛ ብዙኃን የሕትመቱም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ረዥም ርቀት ሄደው በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን የሚያስገኝ ተአማኒ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ይላል አያይዞም የኅብረተሰቡን ሕይወት፣ ትክክለኛ ችግሩን፣ መፍትሔዎቹንም በተጨባጭ የማሳየት ሥራ እስካልተሠራ ድረስ አሁንም ኅብረተሰቡ የማኅበራዊ ሚዲያ ምርኮኛ ከመሆን የሚወጣበት ምንም መንገድ እንደሌለ ያብራራል፡፡

መምህር ዘላለም በበኩላቸው በመንግሥት ፍላጎትም ይሁን በግለሰቦች አድርባይነት አንዳንድ ቦታዎች ለሚፈጠሩ ነገሮች የመገናኛ ብዙኃኑ ከሁሉም በፊት ትክክለኛ እና ኃላፊነትን የተላበሰ መረጃ ለማኅበረሰቡ ማድረስ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ ጊዜውን የጠበቀ ማኅበራዊ ኃላፊነት ያለው መረጃ ማቅረብ ካልተቻለ ግን በማኅበ ራዊ ሚዲያዎች የሚፈጠረውን ውዥንብር ለማስቀረት ምናልባትም ይረፍድብን ይሆናልም ይላሉ፡፡

ለተዘበራረቁት ነገሮች ፈጣን የሆነ ማስተካከያ መንገድን መዘርጋትም ሊያቅተን የሚችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሳችን በፊት መገናኛ ብዙኃኑ በመረጃ መፍጠንም ሆነ መዘግየት ምክንያት ላለመሆን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የሚራመዱ፤ ግብዓት እና ዕውቀት ከሚዲያ ባለሙያዎች ይጠበቃል፡፡ መገናኛ ብዙኃን ምንም እንኳን ሰው ሁሉ የየራሱ ዓይነት የሚመራበት ሕግ ቢኖረውም፤ ሁሉንም ሰው በእኩል ደረጃ ማስደሰት ባይቻልም ብዙሃኑን ሰው ያማከለ፤ የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ዘገባ እንዲሁም ፕሮግራሞች ሊያቀርቡ ይገባል ይላሉ ።

ዶ/ር አደም ደግሞ ከሚዲያው በተጨማሪ ማኅበረሰቡም የሚቀርቡለትን መረጃዎች በአስተዋይነት እና በጠያቂነት ባህሪ ሊያጤናቸው እንደሚገባ ምክር ይለግሳሉ ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም እየታዩ ያሉ ስኬቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተስፋ ሊያስቆርጥ አይገባም ባይ ናቸው ለውጡ ሥርዓታዊ ሆኖ ሚዲያውን አሥረው የቆዩ ሕጎችን መቀየር፣ ጠንካራ የሚዲያ ተቋማትን መገንባት እና በራሳቸው እንዲቆሙ ማድረግ፣ ለጋዜጠኝነት ሙያ ትኩረት መስጠት እና ለጋዜጠኞች እና ለሚዲያ ተቋማት ተገቢውን የሕግ ከለላ ማድረግ፣ የሚዲያ ካውንስል ማቋቋም ይደር የሚባሉ ጉዳዮች እንዳልሆኑ ጠቁመዋል በመንግሥትም ሆነ በግሉ ፕሬስ ባለፉት በርካታ ዓመታት የታየው ትንቅንቅ አንድን ወገን አጉልቶ ሌላውን የማኮሰስ፤ የማጥላላት በስሜት እና በጥላቻ ወጀብ ታጅቦ አንዱ በሌላው ላይ የመዝመቱ ሁኔታ ለሀገር እና ለሕዝብ ሠላም እና መረጋጋት፤ ልማት እና ዕድገት ጭርሱን የሚጠቅም እንዳልሆነ በአለፉት ዓመታት ተሞክሮ በተጨባጭ ታይቷል፡፡

በተለይ በብዙ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ ሲታይ የነበረው ትልቁ ችግር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወይም በሌሎች ጫና ለመንግሥት የሚያደሉ ነበሩ፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ለሕዝቡም ይሁን ለመንግሥት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝን ነበር፡፡ በዋናነትም መንግሥት ያጠፋቸውን ጥፋቶች፣ የሠራቸውን ስህተቶች ፈልጎም ይሁን ሳይፈልግ የማሻሻል ዕድሉን አሳጥተውታል እነዚሀ ነገሮች በተደጋገሙ ቁጥር ደግሞ መንግሥት እና ሕዝብ መካከል ከፍተኛ የሆነ ክፍተት ይፈጠራል፤ መንግሥት የሚያወራው ለሕዝቡ የማይገባ ይሆናል፡፡

ሚዲያው ከሁሉም ነገር የፀዳ መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ፣ ከዘር እና ከመሳሰሉት ነገሮች መቃቃር እና ሽኩቻ፤ ሁከት እና ብጥብጥ የራቀ ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ለማድረስ ጥረት ካላደረጉ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለሚኖረው እያንዳንዱ አሉታዊ ግንኙነት ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ በስህተት እንኳን ስለ አንድ ሕዝብ ወይም ሃይማኖት ማሠራጨት የሌለባቸውን ነገር ካሠራጩ ብዙ የሚበላሽ ነገር አለ፡፡ ሚዲያ በአንድ ሀገር ውስጥ (ከሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈጻሚ) ቀጥሎ እንደ አራተኛ መንግሥት የሚቆጠር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን በማወቅ ለሚያቀርቡት ለእያንዳንዱ ነገር ትኩረት በመስጠት፣ ጥንቃቄ በማድረግ፣ ጣጣው የማያልቀው የመገናኛ ብዙኃንን ተግባር ስክነትን በሰፊው፤ ስሜትን በሩቁ አድርገው ሊሠሩ ይገባል፡፡

ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011  

ሳሙኤል ይትባረክ