«ህገ መንግስቱ እያለ ኢሕአዴግ ወደ አንድ ፓርቲ የመቀየር ዕድሉ ለዜሮ የቀረበ ነው።» -ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት የኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) ሊቀ መንበር «ይሄ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም ብለን ኢሕአ ዴግን ባንከላከለው መልካም ነው።» -ዶክተር ጫኔ ከበደ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ምክትል ሊቀመንበር

27

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራ ሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል ግንባሩ አዲስ የመዋቅር እና የፖለቲካ አካሄድም እንደሚከተል እየተነገረ ነው የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎች ደግሞ ሂደቱን በጥርጣሬ ዓይን ያዩታል ጥርጣሬ በፈጠረባቸው ጉዳይ ዙሪያ አስተያየ ታቸውን ለዘመን መጽሔት ሰጥተዋል ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ ተንታኞችም “ኧረ ለመሆኑ! ኢሕአዴግ በሕይወት አለ?” ሲሉም ይጠይቃሉ ኢሕአዴግ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ወቅቱም ሆነ ባህሪው ይፈቅድለታልን? የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ይሞግታሉ።

በቅድሚያ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በየካቲት

ወር 2011 ዓ.ም የግንባሩን እንቅስቃሴ አስመልክተው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጡት ቃለ ምልልስ መሠረታዊ ሀሳብ ጭብጡን እንዲህ እናስታውስ መልካም ቆይታ።

ለመሆኑ ኢሕአዴግ በሕይወት አለ? ቀዳሚው ጥያቄ ነበር አቶ መለሰ እንዲህ ይላሉ “የኢሕአዴግን ድርጅታዊ ሕልውና በሚመለከት አንድ ፓርቲ ሊኖር የሚገባው ተቋማዊ አቋም አለው ምክር ቤት፣ ጉባዔ፣ ሥራ አስፈጻሚ እና ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ይዟል። የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ሲታገል እና ሲያታግል የቆየ ግንባር ነው፤ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ እየመራ ነው በሕዝብ ተመርጦ ሀገር የሚያስተዳድር መሪ ፓርቲም ነው ሌላው ቁም ነገር ኢሕአዴግ በተልዕኮ እና በይዘቱ፣ በባህሪው እና በዓላማው ተራማጅ ፓርቲ ነው በግልጽ እንደሚታወቀው ተራማጅ ፓርቲዎች በባህሪያቸው ለነጻነት፣ለእኩልነት እና ለፍትሕ የሚታገሉ ናቸው ኢሕአዴግም የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ ስልቶች የሚታገል ነው የተለያዩ ለውጦችንም ሲመራ ቆይቷል አሁንም በኢትዮጵያ ሕዝብ ተገፋፍቶ የመጣውን ለውጥ እየመራ እና እያስተባበረ ይገኛል የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎት ተገንዝቦም የለውጡን ዓላማ ለማሳካት ራሱን እያስተካከለ ያለ ፓርቲ ነው እናም ከእነዚህ ሁኔታዎች ተነስቶ ምላሽ መስጠት ካስፈለገ ኢሕአዴግ ዛሬም አለ

“በሐዋሳው ጉባዔ ኢሕአዴግ ግልጽ ውይይት በማካሄድ የውስጥ ዴሞክራሲ አሳይቷል የለውጡን መርሖዎች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክቶ መግባባት ላይ ተደርሷል የሥምሪት፣ የዝግጅት፣ የክትትል እና የድጋፍ ሥራዎች ይከናወናሉ ከዚህ አንጻር የጉባዔውን ውሣኔ የሚመጥን ዕቅድ በኢሕ አዴግ ጽሕፈት ቤት ተዘጋጅቶ እና በሥራ አስፈጻሚ ታይቶ፤ ብሔራዊ ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው ሁሉ ከተሳተፉበት በኋላ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል ስለውጤታማነቱም ክትትል እየተደረገ ነው።

“ጥናቱ በዋነኛነት ፓርቲዎቹ ሲዋሀዱ ከፕሮግራም፣ ከአመራር ሥምሪት፣ ከአባላት መብት እና ግዴታ፣ ከተልዕኮ እና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሉ ጥያቄዎች እንዴት ምላሽ ማግኘት አለባቸው የሚሉትን ነው የተመለከተው ፓርቲዎቹ ሲዋሀዱ ኢሕአ ዴግ ምን ዓይነት ቅርጽ መያዝ አለበት? ከኢሕአዴግ ጋር ተዋህደው የሚታገሉ ፓርቲዎች በዓላማ እና በትግል ስልቱ ላይ ምን ድርሻ ይኖራቸዋል? የሚሉ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ይመልሳል ኢሕአዴግ ከሀገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጥ ጋር ራሱን እንዴት እያጣጣመ ይሄዳል? የሚለውን ጭምር ይመልሳል በውህደቱ ሂደት የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለማለፍ፣ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ያስችላል ጥናቱ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮዎች እና የእኛን አገር ተጨባጭ ሁኔታዎች ይዳስሳል በአሁኑ ወቅት ጥናቱ እየተጠናቀቀ ነው በፓርቲዎቹ ውይይት ተካሂዶ የጋራ ስምምነት ላይ ሲደረስ ይፋ ይሆናል።

“ኢሕአዴግ የአራት ግንባር እና የአጋር ፓርቲዎች ድርጅት ነበር አሁን ግን ይህ ይቀየራል በመጀመሪያ የሚፈፀመው የኢሕአዴግ እና የአጋር ድርጅቶች ውህደት ነው የተቀራረበ ርዕዮት ዓለም ያላቸው ፓርቲዎች እንደሀገር ሰብሰብ ብለው መሥራት አለባቸው ይህን ታሳቢ ያደረገ የፖለቲካ ማሻሻያ አቅጣጫን ይከተላል ኢሕአዴግ ዓላማው ኋላ ቀርነትን ከማጥፋት እስከዳበረ ዴሞክራሲ ሀገሪቱን ማድረስ ነው ከድህነት ወጥታ የበለፀገች ሀገር መገንባት ነው ይህ ረጅም ጊዜ ይወስዳል ትግሉ በኢሕአዴግ ብቻ የሚያልቅ አይደለም የተለያዩ ፓርቲዎችን ትግል ይጠይቃል የፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን የትውልዶችን ትግል ይጠይቃል ከዚህ አንጻር ተመሳሳይ ዓላማ ላላቸው ተፎካካሪዎችም ቢሆን ኢሕአዴግ ማሻሻያ ሲያደርግ በሩን አይዘጋም አብረን እንሁን ብሎም አያስገድድም ውህደት ሲፈጠር ምን ሥጋቶች እና ዕድሎች ይመጣሉ? ብሎ በመለየት ዕድሎቹን እንዴት እንጠቀማለን? ሥጋቶችን እንዴት እንሻገራቸዋለን? የሚለውን ለማስቀመጥ ጥናት እና ውይይት ይካሄዳል በመሆኑም ግንባር ወይም ውህደት የሚፈፀመው ጥናቱን መሠረት በማድረግ ይሆናል ዋናው ዓላማ አንድ ጠንካራ፣ ተፎካካሪ እና ሀገሪቱ በደረ ሰችበት ደረጃ ሊያታግል የሚችል ፓርቲ መፍጠር ነው ከአገራዊ ለውጡም ጋር ተያይዞ ማስተካከያ የሚደረግባቸው አቅጣጫዎች ተለይተዋል አንዱ ሀገራዊ የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ ነው የዚህ ማስተካከያ ባለፉት ወራት የተወሰዱት ርምጃዎች ማሣያዎች ናቸው በሰብዓዊ መብት፣ በፓርቲዎች አያያዝ፣ በዲያስፖራ ዲፕሎማሲ እና በሌሎች ሁኔታዎችም ይገለፃል።

“አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመርን ትለውጣላችሁ? በሚል ጋዜጣው የጽሕፈት ቤቱን ምክትል ኃላፊ ጠይቆ ነበር “አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ልማት እና ዴሞክራሲ ማለት ነው ይህን መስመር አልለቀቅንም በዚህ ሀገር መሠረታዊ ችግር የሚባለው የድህነት እና የዴሞክራሲ ጉዳይ ነው ድርጅቱ በነዚህ ላይ አተኩሮ ይሠራል ከዚህ ቀደምም እንደተገለፀው ፕሮግራሙ ልማታዊ ዴሞክራሲ ነው ተራማጅ ከመሆኑ አንጻር በቀጣይ ማሻሻል ሲያስፈልግ የሚስተካከል ይሆናል እስካሁን የቀየርነው ፕሮግራም ግን የለም” ነበር ያሉት።

እነዚህን መሠረታዊ ነጥቦች ተከትሎ የሁለት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ሰባት የብሔር እና ኅብረ ብሔራዊ ፖለቲካ አራማጆች ውህድ ፈጥረው የመሠረቱት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ አንዱ ናቸው።

የኢትዮጵያውያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) ሊቀ መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሌላው አስተያየት ሰጪ ናቸው።

ዘመን መጽሔት፤ በቅድሚያ ስለድ ርጅታችሁ አደረጃጀት ይግለጹልን?

ዶክተር ጫኔ ከበደ፤ የኢዜማ አደረጃጀት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተለየ አስተሳሰብ እና አሠራር ይዞ መምጣት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ይህን የፓርቲ መዋቅር መረጥን ከዚህ ቀደም የፓርቲ መሪ እና የፓርቲ ሊቀ መንበር አንድ ላይ ሆነው ሲጓዙ ኖረዋል ከዚህ ተሞክሮ እንዳየነው የፓርቲው ሊቀ መንበር የሆነ ሰው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የመሆን ሚና ነበረው። ስለዚህ የመንግሥትን እና የፓርቲ ሥራን ለይተን ሳንሠራ ነው የመጣነው የፓርቲን እና የመንግሥትን ሥራ ለይቶ ያለመሄድ ሁኔታ በኢሕአዴግም ሆነ በአፍሪካ ሀገራትም ይኼ ተሞክሮ በስፋት አለ ይህ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈጠር እና ለሙስና ትልቅ በር የከፈተ አካሄድ ነው በእኛ ጥናት ይኼ አስተሳሰብ መለወጥ አለበት ብለን አመንን የፓርቲ መንግሥታዊ መዋቅር እና የፓርቲ ድርጅታዊ መዋቅር መለያየት አለባቸው የሚል አስተሳሰብ ይዘን መጣን ይኼንን በሁለት መንገድ ስናየው የፓርቲው መሪ ምርጫን ተከትሎ ዕጩ ሆነው የሚቀርቡ አባላትን እና የምርጫ ዘመቻዎችን የሚመራ እና ተወዳድረን ብናሸንፍ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ሥልጣን አለው።

ሌሎች መንግሥታዊ መዋቅሮችን እና ካቢኔዎችን ሊያደራጅ የሚችለው ይኼው የፓርቲ መሪ ነው። ስለዚህ መንግሥታዊ ሥራዎች በዚያ መሥመር በፓርቲው መሪ እንዲካሄዱ ይደረጋል ማለት ነው። የፓርቲው ሊቀመንበር ደግሞ የዕለት ተዕለት ተግባራትን እና ድርጅታዊ ሥራዎችን ብቻ የሚያከናውን ይሆናል የሰው ኃይል የማፍራት፣ የድርጅቱን ፕሮግራም እና ወደፊት የሚዘጋጀውን ማኑፌስቶ ተከትሎ ለኅብረተሰቡ እና ለአባላቱ በግልጽ ማሳወቅ እና ማስረፅ የድርጅቱ ሊቀመንበር ባለው አደረጃጀት ይሠራል ይህ ዓይነቱ አወቃቀር ኢዜማ አዲስ የፈጠረው ሳይሆን አሠራሩ በዓለም ላይ ዴሞክራሲን ባዳበሩ እንደአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን እና ፈረንሣይ ባሉ ሀገሮች የተለመደ አደረጃጀት ነው ትልቁ ጉዳይ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱበት የአደረጃጀት መሥመር መሆኑ ነው፤ ለኢትዮጵያም ይመጥናል ብለን ስላሰብን መርጠነዋል ።

ዘመን መጽሔት፤ ፓርቲዎቹ የሚ መሩበት ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ምንድነው?

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ የምንከተለው ርዕዮተ ዓለም ከመሐል ወደ ቀኝ የሚለውን ነው ቀኝ ዘመም እንደ ማለት ነው። እኛ ሀገር ገና ማኅበራዊ ፍትሕ የለም፤ ጠንካራ መካከለኛ መደብ የለም፤ ስለዚህ በምጣኔ ሀብቱም፣ በማኅበራዊ ዘርፉም የመንግሥት ሚና የሚናቅ አይደለም። ነጻ ገበያን ማበረታታት ይገባል ጠንካራ መካከለኛ መደብ ባልተፈጠረበት፤ የሀብት እና የንቃተ ሕሊና ልዩነት ባለበት ሁኔታ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል በጤናው እና በትምህርቱ በአጠቃላይ በማኅበራዊ ዘርፍ ሆነ በምጣኔ ሀብቱ ላይ መንግሥት ሚናው የጎላ ነው ይኼ ሲደረግ የግሉን ዘርፍ ተክቶ ሳይሆን የግል ዘርፉን እያበረታታ እና ብድር እያመቻቸ፣ የመንግሥትን ድጋፍ በሚፈልጉት ላይ ደግሞ አስተዋጽዖ እያደረገ የሚሄድ የፖለቲካ የሽግግር ሂደት ፖሊሲ አለን። ሂዶ… ሂዶ ግን ወደ ማኅበራዊ ፍትሕ እና ሊበራሊዝም ይሰነጠቃል ማለት ነው። መካከለኛ መደብ በተፈጠረ ጊዜ ሶሻል ዴሞክራሲ ሊፈጠር ይችላል፤ ሊበራል ዴሞክራሲም ከዚያ በኋላ የሚፈጠር ይሆናል። አሁን ባለንበት የዕድገት ደረጃ ግን የመንግሥትም የግለሰብም ሚና ይኖራል እነዚህን ሁለቱን ሚዛን አስጠብቆ የሚሄድ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ነው።

ዶክተር ጫኔ ከበደ፡ ኢዜማ በግልጽ የተለየ ርዕዮተ ዓለም ገና አላዘጋጀም ምክንያቱም እስካሁን ድረስ ሶሻል ዴሞክራሲ፣ ሊበራል ዴሞክራሲ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እየተባለ ሲዘመር ነው የመጣው በእርግጥ ርዕዮተ ዓለሙን ተከትሎ የሠራ ፓርቲ የትም አልታየም በኢዜማ በኩል ማኅበራዊ ፍትሕን እናስባለን አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው ምንድነው? የሚለው ላይ ትኩረት አድርገናል ምጣኔ ሀብቱ በጣም የደከመበት ሁኔታን እያየን ነው ማኅበራዊ ግንኙነታችን እና መስተጋብራችን በጣም እየወረደ እና እየወደቀ፤ የግጭት መናኸሪያም እየሆነ ነው። ስለዚህ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ይዘቶችን በተመለከተ ከሶሻል ዴሞክራሲ የሚወሰዱ አስተሳሰቦች ይኖራሉ ከሊበራል ዴሞክራሲም እንዲሁ የሚወሰዱ ይኖራሉ። በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የትኛው ርዕዮተ ዓለም የተሻለ ነው ብለህ ለመሄድ ገና መካከለኛ ገቢ ያለው እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ መፍጠር ሲቻል የሚመጣ ይሆናል ለጊዜው ግን የሚመጥነው ማኅበራዊ ፍትሕ ነው ተብሎ ይታሰባል ስለዚህ ማኅበራዊ ፍትሕ ላይ የሚታዩት የሕግ ክፍተቶች፣ የትምህርት፣ የጤናና የግብርናው መሥመር አሳታፊና አቃፊ አይደሉም በእርግጥ ጎን ለጎን ኢንዱስቲሪያላይዜሽኑን አብሮ ያስኬዳል። የፈጠራ ሥራዎች እየተበረታቱ ወደ ኢንዱስትሪ መዞር አለባቸው።

የማኑፋክቸሪንግ ሥራውም በዚያው መጠን፤ የአገልግሎት ዘርፉም በዚያው ልክ እየተደገፈ በነፃ ገበያው ሥርዓት የሚንቀሳቀስበት ዕድል አብሮ መፍጠር ያስፈልጋል። የአቅርቦት እና የፍላጎት ነገሮችን ማመጣጠን እስኪቻል ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅድሚያ ማኅበራዊ እና ፍትሐዊነቱ መቅደም አለበት። ፍትሕ የጠማው ርትዕን፣ የሚበላው ያጣ መብልን እንዴት ማግኘት አለበት ተብሎ ይታሰባል ለትምህርት ክፍያ ያጣ ደሃ እንዴት ልጆቹን ሊያስተምር፣ ሥራ አጡ እንዴት የሥራ ዕድል ሊያገኝ ይችላል? እናስ የመንግሥት ሚና ምን መሆን አለበት? ምላሽ የሚጠብቁ ጉዳዮች ናቸው ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ኢዜማ የሚከተለው ግልጽ የሆነ ርዕዮተ ዓላማ ይኼ ነው ብሎ አላስቀመጠም።

ዘመን መጽሔት፡ ኢሕአዴግ ከነበ ረበት የግንባር አደረጃጀት ወደ ኅብረ ብሔ ራዊ ፓርቲነት ሊለወጥ ነው ይባላል ለዚያም እንዲረዳው አንዳንድ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነ እንዳለ ይሰ ማል እናም አስፈ ላጊነቱ፣ ሥጋቶቹ እና አተገባበሩን እንዴት ያዩታል?

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ በቅድሚያ ከኅብረ ብሔራዊ ፓርቲነት ትርጓሜ እንነሳ ኅብረ ብሔር የሚለውን አገላለፅ ለሀገር አቀፍ ፓርቲ እና ከብሔረሰብ ውጭ ለሆኑ የአደረጃጀት አመለካከቶች የሚሰጥ ስም እየሆነ መጥቷል እሱ ግን ትክክል አይደለም። ኅብረ ብሔር ማለት ፖለቲካ በብሔረሰብ ስብስብ (ጥርቅም) እንደማለት ነው። ብዙ ብሔር ማለት ነው። ኅብረ ብሔር የብሔር ኅብር ማለት ነው አንድ ብሔር ሲደመር ሁለት፣ ሲደመር ሦስት ብሔር… ሰማንያ ብሔር ይሆንና ፖለቲካ ብሔር ተኮርን መሠረት አድርጎ ከተመሠረተ እና የእነዚያ ድምር ከሆነ ኅብር ይሆናል ማለት ነው። ኅብረ ብሔር ማለት ብሔረሰብን መሠረት አድርጎ የሚመሠረት ፖለቲካ ማለት ነው እንጂ ሀገር አቀፍ ወይም በሀሳብ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ማለት አይደለም፤ ይለያያል ኢሕአዴግ ኅብረ ብሔር ነው ማለት ይቻላል። ለሀገር አቀፍ አደረጃጀት ወይም በዜግነት ላይ ተመሥርቶ ለሚደረግ የፖለቲካ አመለካከት ሊበራል፣ ዴሞክራቲክ፣ ሶሻል ዴሞክራሲ፣ ወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) ፓርቲ ልትለው ትችላለህ።

ኢሕአዴግ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት ሊቀየር ነው ለተባለው በቅርቡ የሚሆን አይመስለኝም። ምክንያቱም ኢሕአዴግ ችግሬ የሚለው በፊት ጠባብነት እና ትምክህተኝነት ነበር አሁን ደግሞ አክራሪ ብሔርተኝነት እና ጽንፈኝነት ብሎ የዳቦ ስም አውጥቷል አክራሪ ብሔርተኝነት እና ጽንፈኝነት ችግር ከሆኑ እንደ ሀገር እነዚህ የበቀሉ አመለካከቶች እያሉ ኢሕአዴግ ወደ አንድ ፓርቲነት የሚቀየረው ምን አድርጎ ነው? ሕገ መንግሥቱ፣ ፖለቲካው በብሔረስብ ላይ የተመሠረተ፣ ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ነው የሚያስተዳድሩት፣ ከፈለጉም ይገነጠላሉ ካለ ይህ እንዳለ ሆኖ ኢሕአዴግ አንድ ፓርቲ ለመሆን ነባራዊ ሁኔታ ተፈጥሯዊ ተክለ ሰውነቱም አይፈቅድለትም። ይኼ ሕገ መንግሥት እያለ ኢሕአዴግ ወደ አንድ ፓርቲ የመቀየር ዕድሉ ለዜሮ የቀረበ ነው

ዶክተር ጫኔ ከበደ፤ ኢሕአዴግ በእውነት ከልብ በመነጨ ሁኔታ ወደ ኅብረ ብሔራዊነት አስተሳሰብ መምጣት የሚችል ከሆነ በእኔ በኩል ጠቃሚነቱ ይኼ ነው አይባልም በእርግጠኝነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ የፖለቲካ ምሕዳር ተከፈተለት ብዬ አስባለሁ የተለያየ አስተሳሰቦችን የሚያመነጩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተለያየ አስተሳሰብ ይዘው ወደ ኅብረተሰቡ ይገባሉና አማራጭ ሀሳብ ይዞ መቅረብ እና የእኔው የተሻለ ነው ብሎ ለማለት ኅብረ ብሔራዊ ሆኖ መደራጀት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ አዎንታዊ ነው ብዬ አስባለሁ ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢሕአዴግን እንደምናውቀው በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ብሔር ተኮር አደረጃጀት እና የቋንቋ ፌዴራሊዝምን ሲጠቀም የቆየ ነው። ይኼም በብሔር ላይ የተመሠረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲደራጁ እና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ለማለት ብቻ እንደ አሸን የተፈለፈሉ በርካታ ፓርቲዎች አሉ እነዚህ ድርጅቶች ስለእውነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥን አስተሳሰብ አላቸው ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ ብሔረሰቤን በዚህ መንገድ እመራዋለሁ፤ አስተዳድረዋለሁ ብለው በኢትዮጵያ ጥላ ሥር ሆነው ሕዝቡን ለመምራት እንደሚባለውም የአካባቢውን ኅብረተሰብ ሲጠ ቅሙ አላየናቸውም።

አሁን ውህደት እፈጥራለሁ ያለው ኢሕአዴግ ከጥላቻ በዘለለ እንደ አንድ አማ ራጭ የፖለቲካ ድርጅት ጥሩ ዓይነት ስሜት በኅብረተሰቡ ውስጥ ሊፈጥር ይችላል። እናም የክልል መንግሥታት እና እንዲሁም የብሔር ፖለቲካ ላይ ትኩረት አድርገው እየተፈጠሩ ያሉ የገዢው ፓርቲ አጋርም እንበላቸው ተባባሪ ድርጅቶች ይኼ አስተሳሰብ ለእነሱም ጥሩ አጋጣሚ ነው ተብሎ ይታሰባል ምክንያቱም ለአብነት የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የሶማሌ ክልሎች እስካሁን ድረስ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ውድድር እንኳን ሊያስመጣቸው የሚያስችላቸው አደረጃጀት አልነበራቸውም የላቸውም። ብቃት እና አቅም ያለው ኢትዮ ጵያዊ ዜጋ ከሶማሌ ይሁን ከአፋር ወይም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚወዳደርበት ዕድል ይፈጠራል። ከዚህ አንጻር በእውነት ኢሕአዴግ ራሱን አድሶ፤ ወደ ለውጡ መጥቻለሁ ካለ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ጥሩ አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት ልታገኝ ትችላለች ማለት ነው ።

ዘመን መጽሔት፤ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ኢሕአዴግን ወደ ኅብረ ብሔራዊነት እንዲለወጥ ያግዘዋል ተብሎ ይታሰባል?

ዶክተር ጫኔ ከበደ፤ በእርግጥ ለኢሕ አዴግ ትልቅ ፈተና ነው። በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ሁሉም ድርጅቶች ሊካተቱ ይችላሉ በእዚህ ውስጥ አልካተትም የሚል ሊኖር ይችላል። ይኼ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ሆኖም በኅብረ ብሔራዊነት ፓርቲ ውስጥ አልካተትም የሚል ካለ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል ተፎካካሪ ሆኖ ማሸነፍ እስኪችልም ትልቅ ፈተና ሊገጥመው ይችላል።

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ውጥንቅጥ አንጻር ኮትኩተው ያሳደጉት ጥላቻን፣ ባድነትን እና ልዩነትን ሰበኩ፤ ሁሉም ነገር በዚያው ልክ ተቃኘ፤ አሁን ራሳቸው ያሳደጉት ዘንዶ በአንገታቸው ተጠም ጥሞ ሲበላቸው፤ እርስ በርሳቸው መተያየት አቅቷቸው በአሽሙር ሆነ ፊት ለፊት መግለጫ እየሰጡ ባለበት ጊዜ አንድ ልንሆን ነው ቢሉን እንዲያው ፀሐይ በምዕራብ ወጥታ በምሥራቅ ትገባለች እንደማለት ነው ኢሕአዴግ አንድ ይሆናል የሚባለው ለእኔ አሁን ላይ የሚሆን አያደለም ከጋራ እሴቶቻችን ይልቅ ልዩነታችን ላይ አተኩረን መለያየት በዛ፤ ማዕከላዊ መንግሥት እየተዳከመ ነው፤ ክልሎች ወደ ሥርዓተ አልበኝነት እየሄዱ እና አልታዘዝ እያሉ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን እየደበዘዘ፤ ልዩነታችን እየበዛ ስለሄደ ይኼ ነገር ውሎ አድሮ ሀገርን እስከ ማፍረስ ይደርሳል። ስለዚህ የፌዴራል ሥርዓቱን እንደጠበቅን ሆነን የጋራ እሴቶቻችንን እያዳበርን ልዩነታችንን አክብረን ለመሄድ ወደ አንድ ፓርቲ መሄድ ሳይሻል አይቀርም የሚል አመለካከት አለኝ።

ዘመን መጽሔት፤ የኢሕአዴግን ወደ ኅብረ ብሔራዊነት ለመለወጥ የመነሳሳት ሂደትን በጥርጣሬ ዓይን የሚያዩ እንዲያውም ባህሪይው ገና ከፍጥረቱ ይዞት ያልተነሳው ነው በሚል የሚከራከሩ አሉ። ወደ ኅብረ ብሔራዊነት የመሸጋገሩ ሁኔታ ለኢሕአዴግ አይሳካለትም፤ ጊዜ ለማግኘት የሚከተለው ታክቲክ ነው በሚል የሚገልጹም አሉና ምን ትላላችሁ?

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ ኢሕአዴግ ለመለወጥ ካሰበ የተፈጠረበትን መሠረታዊ አስተሳሰብ ጨምሮ ያንን የሠራውን ሕገ መንግሥት ማሻሻልን ምናልባትም በቅድሚያነት ትኩረት መስጠት አለበት። ያንን ካደረገ በኋላ በዚያው መሠረት ሌሎች ፓርቲዎችም ሆኑ ኢሕአዴግ ራሱን በሕገ መንግሥቱ እየቃኘ የሚመሠረት እና ራሱን የሚያሻሻል ድርጅት ይሆናል። ሕገ መንግሥቱ የኢሕአዴግ ግልባጭ ሆኖ የተከፋፈለች ሀገር ከተመሠረተች በኋላ ኢሕአዴግ ለብቻው ቢያያዝም ሕገ መንግሥቱ ለያይቶናል እና ምንም ርባና የሌለው ነገር ነው ማለት ነው። ምናልባትም ለራሱ ውድቀት ሊሆን የሚችለው። ከራሱ ጋር ይጋጫል፤ ከመርሑ ጋር ይጋጫል ይኼ አልሞት ባይ ተጋዳይነት ነው። ኢሕአዴግ ራሱን ያጠፋ እንደሆን እንጂ ለሀገሪቷ ችግር መፍትሔ አይሆንም ባይ ነኝ።

ዶክተር ጫኔ ከበደ፤ የግንባሩ ድርጅቶች ወደዚህ አስተሳሰብ ለመምጣት ሳይመካከሩ አሊያም ሳይደራደሩ ኢሕአዴግ ይኼንን አመለካከት ያመነጫል የሚል እምነት የለ ኝም። በእርግጥ ይኼ በራሱ ሕገ መንግሥታዊ የሆኑ የራሱ አንቀፆች አሉት እና ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የሚከራከሩ ሊኖሩ ይችላሉ። በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተደራጀን የክልል ፓርቲዎች መፍረስ የለብንም፤ እንደ ቀድሞው መቀጠል አለብን የሚሉ ፓርቲዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ኢሕአዴግ እንደ ባህሪይው ሲሰብክ የኖረው ነገር በጣም የሚታወቅ ነው። ከኅብረ ብሔራዊነት ይልቅ ብሔርተኝነትን ነው አግዝፎ ሲያስተምር የመጣው። በአገዛዝ ዘመኑ የተፈጠሩ ወጣቶች በተለይ ይኼንን የብሔር ጥያቄን ነው አጎልብተው የመጡት የእኔ ማንነት የሚል ትልቅ አስተሳሰብ ይዘው ብቅ ያሉት ይኼንን መልሶ ወደ ኅብረ ብሔራዊነት እና ወደ አንዲት ኢትዮጵያ ለመመለስ ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ይመስለኛል። ሆኖም ግን ይህ ተፈርቶ ወደዚህ አስተሳሰብ መገባት የለበትም የሚል እምነት የለኝም። የሕግ ማዕቀፍ ይፈልጋል፤ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ይኼንን አስተሳሰብ በዚያው ውስጥ አካቶ ወደ ኅብረተሰቡ ውስጥ እንደገና የማስተማር፣ የማስረፅ እና የፖለቲካ አደረጃጀቱን እንደገና የመዘርጋት ሂደት ሊጠይቀው ይችላል።

ይኼ አስተሳሰብ ትልቅ አስተሳሰብ ነው። ይኼ ትልቅ አስተሳሰብ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ነው። በፊት የነበረውን የልዩነት አስተሳሰቦች ለመመለስ አታካች እንደሚሆን ይታወቃል። ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ እንደሚሻሻል ተስፋ መስጠት፤ ለሕዝቡ ለፖለቲካ ድርጅቶች አባላትም ቢሆን ሕገ መንግሥቱ መሻሻል እንዳለበት በአንድነት ለዚች ሀገር በሚጠቅም መንገድ አደረጃጀታችንን ብናስተካክል የተሻለ ይሆናል የተሻለ ልማት ሊያመጣ ይችላል። የተሻለ ፖለቲካ እና መንግሥት መመሥረት ያስችላል የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በፊት የተፈፀሙትን መጥፎ ሥራዎች ይቅርታ አድርጓል ይጠቅመኛል ብሎ ካሰበ ይኼኛውን ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀቱን ሊደግፍ የሚችል አካል ሊያገኝ ይችላል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም በላይ ከልዩነት አስተሳሰብ አንድነትን እየመረጠ፤ ከመነጣጠል በጋራ የመኖርን ሁኔታ እያስቀደመ የመጣ ኅብረተሰብ ነው። አሁን እየተሄደበት ያለው ይኼ መንገድ ለእኔ ትልቅ አስተሳሰብ ነው ብዬ አስባለሁ።

ዘመን መጽሔት፤ የኢሕአዴግ ወደ ኅብረ ብሔራዊነት ለመለወጥ ማሰብ ሕገ መንግሥቱ ቀድሞ ሳይሻሻል እንዴት? ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ የሚሉ አሉና ምን ትላላችሁ?

ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ ውህደቱን በተመለከተ በአስፈላጊነቱ ላይ በመርህ ደረጃ ችግር የለውም። ነገር ግን ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ነው የሚባለው። መጀመሪያ ሀገሪቷን በዚህ በተመሠረተው ሕገ መንግሥት መሠረት ብሔረሰቦች ራሳቸውን ያስተዳድራሉ፤ የራሳቸው ክልል አላቸው፤ ከፈለጉ መገንጠል ይችላሉ ብለህ ካወጅክ በኋላ ያንን የኢሕአዴግን ፕሮግራም ግልባጭ ሕገ መንግሥት አድርገህ አስቀምጠኸዋል። ስለዚህ ኢሕአዴግን ከቀየርህ አብረህ ሕገ መንግሥቱንም መቀየር ግዴታ ነው። ኢሕአዴግን ቀይረህ ሕገ መንግሥቱ እንዳለ ቢሆን ኢሕአዴግ ይከስምና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሌላ አዳዲስ ፓርቲዎች ነው የሚወጡት።

ዶክተር ጫኔ ከበደ፤ በዚህ ሀሳብ አልስ ማማም ግድ የለም ከፈረሱ ጋሪው ቢቀድምም እስቲ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለማጣጣም ጥረት ማድረግ የተሻለ ይሆናል ይኼ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም ብለን ኢሕአዴግን ባንከ ላከለው መልካም ነው። ምክንያቱም እዚህ ላይ የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋትና የሀሳብ ግንባታን ለማጎልበት የሁሉም ድርሻ መኖር ይገባዋልና ።

ዘመን መጽሔት፤ ለሰጡን ቃለ ምል ልስ እናመሰግናለን!

ዘመን መፅሄት ሰኔ 2011  

ጋሻው ጫኔ