በማስተዋል መጓዝ ይበጃል

27

ኅብረተሰቡን ወደ ከፍተኛ ንዴትና ስሜት ውስጥ የሚያስገቡ በቸልተኝነት የሚሰጡ አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡ አስተያየቶቹና አንዳንዴም መግለጫዎች በስሜት የታጀቡ በመሆናቸው ህዝቡን ላልተገባ ተግባር የሚያነሳሱ ቢሆንም፤ እስከአሁን ህዝቡ በትዕግስት እየታዘበ በአስተዋይነት እያለፈ ነው፡፡ እነዚህ ስሜት ኮርኳሪ አስተያየቶች በገፉት ልክ ህዝቡ ከመነዳት ይልቅ በማስተዋል እየታዘበ መጓዝን በመምረጡ ዛሬን ማየት ተችሏል፡፡

ይህ የአስተዋይነት ተግባር አሁንም መቀጠል ቢኖርበትም፤ በተለይም ምሁራኖች፣ ትልልቅ የሥራ ኃላፊዎችና የፓርቲ አመራሮች ሳይቀሩ ከስሜት ራሳቸውን ማቀብ፤ በአስተዋይነት መንቀሳቀስ ካልቻሉ ነገን ማየት ያሰጋል፡፡

አንዳንዴ ኅብረተሰቡ የሆዱን በሆዱ አድርጎ ሁሉን እያየ እንዳላየ ማለፉ አያውቅም ሊያስብለው አይገባም፡፡ ህዝብን የሚያስቆጣ ነገር እንኳን የመንግስት እና የፓርቲ አመራሩ ቀርቶ ተራው ህዝብ ለይቶ ማወቅ ግድ ይለዋል፡፡ ቢቻል እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን በፍጥነት መፍታት፤ ካልቻለም በስሜት የሚነዱትን ማረቅ ይገባል፡ ፡ ‹‹የበላችው ያገሳታል በላይ በላይ ያጎርሳታል›› እንደሚባለው ሁሉ፤ የተፈጠረው ችግር መቋጫ ሳያገኝ ሌላ ችግር ለመፍጠር የሚካሄዱ ስሜት አዘል አስተያየቶች ለማንም ሳይባል ለራስ በማሰብ በማስተዋል መጓዝ ግድ ይላል፡፡

ዜጎች በሙሉ እኩል መሆናቸው ጥያቄ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በእኩል አልተዳደርም እኔ ነኝ የበላይ አይነት አምቧጓሮዎች በየጊዜው መፈጠራቸውና አንዳንድ ቦታዎች ላይ መታየታቸው ለአገሪቱ ስጋት በመሆኑ ቀናው መንገድ እንዳይንሻፈፍ ያሰጋል፡፡ በሁሉም ዘንድ ታጋሽነት፤ አስተዋይነት ግድ ይላል፡፡ ተጨባጭ ችግሮችን በትክክል ለመፍታት ህዝቡ ብቻ ሳይሆን አመራሩን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊያን ማስተዋልን ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በፖለቲካ ጉዳይ ላይ እየተሰጡ ካሉ አስተያየቶች እና ከሚነሱ ሃሳቦች ጀምሮ የሚሰጡ መግለጫዎች ሳይቀሩ ከስሜታዊነት መፅዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁሉም ለማለት ቢያዳግትም አብዛኛው ሰው የሚሰማውን ስሜት በየካፍቴሪያው እና በየቤቱ የሚያስተጋባው ቀጣዩን ውጤት ታሳቢ አድርጎ አይደለም፡፡ ያልሰሙትን ጉዳይ መሰለኝ ብለው ከመናገር ይልቅ አይተው እንዳረጋገጡት አስመስለው ያለምንም ጥርጥር መናገር ከዛም ጉዳዮችን ማቀጣጠል ይስተዋላል፡፡ ይህ ለማንም አይበጅም፡፡

ሰዎች ሃሳባቸውን ሲሰነዝሩ ግራ ተጋብተው ህዝቡን ግራ ማጋባት የለባቸውም፡፡ ማስተዋል የሚገባው አንድ ህዝብ በምንም መልኩ ሌላውን ህዝብ አልጨፈጨፈም፤ በታሪክ ሲጨፈጭፍም ሆነ ሲያስጨፈጭፍ ሲዘርፍም ሆነ ሲያዘርፍ አልተመዘገበም፡፡ የሆነ አካባቢ ህዝብ ቢታሰር ቢገረፍ ቢሰደብ አሳሳሪው፣ አስገራፊውም ሆነ አስዘራፊው ራሱ አብሮ የሚዘርፈው እና የሚያስገብረውም የዛ አካባቢ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ተበድያለሁ የሚል ብሔር ካለ የተበደለው በቅድሚያ በራሱ ብሔር ተወላጅ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦች አጥፍተዋል፡፡ ነገር ግን አንዱን ህዝብ በተለየ መልኩ እንደበዳይ ሌላው ደግሞ እንደተበዳይ የሚያሳይ መሆን የለበትም፡፡

አማራም ኦሮሞም ደቡብም ሆነ ትግራይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ይህንን የማያምኑ ፅንፈኞች ሲፈነጩ ጦር ይዞ መነሳት የለበትም፡፡ መፍትሄው ኢትዮጵያዊነትን መስበክ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን እያስተዳደሩ ጥያቄ አያቅርቡ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት የሚቀርቡ ጥያቄዎች በእርግጥ በዚህ መልክ መቅረብ ነበረባቸው ወይ የሚል ጥያቄ ሲቀርብ ያስተዛዝባል፡፡ ዛሬውኑ ምላሽ ካላገኘሁ አይነት ማስጠንቀቂያ እጅግ ያስተዛዝባል፡፡

ኢትዮጵያን እናሳድግ፣ ለውጥ ይምጣ፣ ዴሞክራሲ ይስፈን ሲባል፤ አንዱ ዞን ልሁን፣ ሌላው ወረዳ መሆን አለብኝ፤ አንዳንዱ ክልል መሆን ይገባኛል፡፡ በሌላ ፅንፍ ደግሞ ብሔሬ ተጎድቷል፣ የኔ ህዝብ ተሰቃይቷል፤ በአፋጣኝ ልካስ ይገባኛል የሚል ሃሳብ ይንፀባረቃል፡ ፡ የልዩነት ሃጎበር እንደገና ይጎመራል፡፡ ዛሬ ተሻለ ሲባል ለሊቱን ተቀጣጥሎ ያድራል፡፡ ይህ አካሄድ ለሰላማችን የማይጠቅም ስለሆነ ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡

አጉል ድጋፍ ለማግኘት፤ ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል የሚደረግ በብሔር የመጠቀም ሩጫ መጨረሻው ለራስም ሳይሆኑ አጓጉል መሆን ያመጣል፡፡ መቼም የሚያስማማን ኢትዮጵያ የምትባለዋ አገር ከፈረሰች ማን ወረዳ፣ ማን ዞን፣ ማን ክልል፣ ማን ወዴት ያድጋል? ለነገሩ እንጂ ኢትዮጵያማ እንዲህ በቀላል የምትረታ አይደለችም፡፡ ነገር ግን ትንሽ ሰከን ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡

የማንም ብሔር ወርቅ አይደለም፡፡ የየትኛውም ሰው ብሔር ደግሞ ጨርቅ አይደለም፡ ፡ አንዱ ሌላውን የመናቅ መብት የለውም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አገሪቷ የሁሉም ናት፡፡ የኦሮሞ፣የደቡብ፣ የሶማሌ… መሬትም ሆነ የተፈጥሮ ሃብት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቷ ምድር ውስጥ ሰርቶ የማግኘትና ቤት ሰርቶ የመኖር መብት አለው፡፡ በየትኛውም ቦታ አንድ ኢትዮጵያዊ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሊቆጠር አይገባም፡፡ ይህን መገንዘብ በአስተዋይነት መናገር እና አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በስሜት ከመነዳት በመታቀብ በማስተዋል መጓዝ ይበጃል – ለኢትዮጵያ ሲባል፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2011