ክልል የመሆን ጥያቄው ለሰላም እጦት መንስኤ ሊሆን አይገባም!

172

ቀደም ሲል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ተወያይቶ ውሳኔ ከሰጠባቸው ጉዳዮች አንዱ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምክር ቤቱም የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄውን ከተቀበለ በኋላ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲፈጸም አቅጣጫ ማስቀመጡም ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ምክር ቤቱ የክልልነት ጥያቄ ላቀረበው ብሔረሰብ ሕዝበ ውሳኔ ያደራጃል ማለት ነው፡፡

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 መሠረት ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት ይህ መብት ተግባራዊ የሚሆነው የክልል መመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ወይም ሕዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልል ምክር ቤት ሲቀርብ ነው፡፡

ጥያቄው የቀረበለት ምክር ቤት ጥያቄውን በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣ ክልል የመመሥረት ጥያቄው በብሔር፣ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍና የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብ እንደሆነና ይህ አዲሱ ክልል የፌዴራል መንግሥቱ አባል እንደሚሆን ይደነግጋል፤ ህጋዊ አካሄዱም ይህን የመሰለ መልክ እንዲይዝ ይፈለጋል፤ ይጠበቃልም፡፡

ይሁንና አገሪቱ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራል ሥርዓትን ተከትላ ክልሎችንና የከተማ አስተዳደሮችን ካዋቀረች ወዲህ፣ በአገሪቱ ክልል መሥርቶ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት አባል የሆነ ብሔር፣ ብሔረሰብም ሆነ ሕዝብ የለም፤ በዚህ ገና ልምድ የለንም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. የተሰበሰበው የሲዳማ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የዞኑን የክልልነት ጥያቄ በመደገፍ ያፀደቀ ሲሆን፣ ይህም ሕጉን ተከትሎ ለክልል ምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ በዚህም ምክንያት የፌዴራል ስርዓት በኢትዮጵያ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመሪያው ክልል በመሆን በታሪክ ሊመዘገብ ተቃርቧል፡፡ ይህ ሂደትም አሁን ላለንበት ለውጥ ቁልፍ ማሳያ ነው፡፡

ክልል የመሆን ጥያቄው የህዝብን ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ ጥያቄ መሆኑ ለዚህ መብት የሚታገሉትን ኃይሎች ጨምሮ ሁላችንም በቂ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ በመሆኑም መብቱ ሕገመንግስታዊ መሰረት እንዳለው ምንም ጥርጥር የለም። ይሁንና የአፈፃፀም ሂደቱ ህጋዊነት እና ስክነት የተሞላበት መሆኑ ላይ ግን ሁላችንም ልንግባባ ይገባል፡፡

ከዚህ መሰረታዊ ሁኔታ በመነሳት የክልልነት ጥያቄው ህጋዊና ተገቢነት ያለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የጥያቄው ተገቢነት ላይ ምንም ልዩነት ባልተፈጠረበት በዚህ ወቅት ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በጣሰ መንገድ መብትን ለማስከበር የሚደረግ ተግባር ግን በፍጹም መኖር የለበትም፡፡

አሁን ያለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያስረዳን የክልልነት ጥያቄውን ጨምሮ የትኛውንም ዓይነት ህጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ለመጠየቅ እድሉ የሰፋ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ይህን እድል ተጠቅመን፤ ያቀረብነው ሕገ-መንግስታዊ ጥያቄ እንዲፈፀምልን የምንፈልገውና የምንጠብቀው ምላሽ ህገመንግስታዊና የመልሱን ዘላቂነት ያረጋገጠ ጭምር ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ምንም ዋጋ ሳያስከፍል በሰለጠነ መንገድ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ይረዳል፡፡

የክልልነት ጥያቄውን ያነሱ አካላትም ሆኑ ህዝቡ እስከ አሁን የሄዱበት ሰላማዊና የሰለጠነ ሂደትና ትዕግስት የሚያስመሰግን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ሰላማዊና ምላሽ የሚያገኝ ጥያቄ ጸረ ሰላም ሀይሎች ለእኩይ ዓላማቸው  ሊጠቀሙበት እንደሚችሉና ከዚያም አልፎ የክልሉን ሰላምና ደህንነት በማወክ ለግርግርና ለዝርፊያ ያንዣበቡ አካላት እንዳሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ለእነዚህ ሀይሎች እጅ እንዳይሠጥ አሁንም ትዕግስቱ የበዛ ሊሆን ይገባል፤ ምላሽ ማግኘቱ ለማይቀር ጥያቄ አንድም ሞትና አንድም ንብረት መጥፋት የለበትም በሚል ፅኑ እምነት መብቱን ማስከበር ይቻላል፤ ይገባልም፡፡

በመሰረቱ ሰላም ለሁሉም መሰረት ነው፤ ከዚህ እውነታ በመነሳትም የሲዳማና የወላይታ ህዝብን ጨምሮ ሌሎች ብሄረሰቦች ተመሳሳይ የመብት ጥያቄ በማንሳት እስከ አሁን የተጓዙበትን ትዕግስት የተሞላበት አካሄድ በማስጠበቅ ሕገ- መንግስታዊ መብታቸውን ለማስከበር መካሪ መጠበቅ የለባቸውም፡፡ እነዚህ ህዝቦች ለዚህ መብት አፈጻፀም መዘግየት የጠሯቸው ሰልፎች ጭምር እጅግ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከናወናቸው የሚያስመሰግንና ዴሞክራሲያችን ማደግ መጀመሩን የሚያመላክት ነው፡፡

ክልል የመሆን ጥያቄው በህጋዊ መንገድ ቀርቦ ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ የፖለቲካ ምህዳሩ ምቹ ነው። የለውጥ ሀይሉም የህዝብን ጥያቄ ለመስማትና ለመመለስ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው። ጥያቄው ለዓመታት ታፍኖ የቆየ መብት መሆኑም ሊረሳ አይገባም። ስለሆነም ይህን ህጋዊ የመብት ጥያቄ ለማስከበር የሚኬድበት ሂደት ለሰላም እጦት መንስኤ እንዳይሆን ሁሉም ወገን በየደረጃው ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011