ህዝብና ሀገር ይቅደም !

24

አሁን ባለንበት ወቅት ህዝብ የተሻለ ተስፋን የሰነቀ የዲሞክራሲ ጭላንጭል እያየ ነው። ኢኮኖሚው በተለያየ መልኩ አድጎ የተሻለ ኑሮ እኖራለሁ ብሎ ነገን በናፍቆት እየጠበቀ ይገኛል። ሀገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የምትሰለፍበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብሎ እያለመና እየለፋም ነው ። ይሁን እንጂ አሁን አሁን የሚታዩ ችግሮች የፖለቲካ አለመግባባቶች የህዝብን ተስፋ እያለመለመ ሳይሆን ተስፋውን እያጨናገፈ ነው ብሎ ለመናገር ይቻላል።

“ዝሆንና ዝሆን ሲጣላ የሚጎዳው ሳሩ ነው“ የሚባል ሀገርኛ አባባል አለ። አሁን በሀገራችን እያየንና እየሰማን ያለነው ከፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ከክልል አመራሮች የሚወጡ መግለጫዎች ይሄንን ለማለት የሚያስደፍሩ ናቸው። አካፈን አካፋ ብሎ ለማለት ያህል ሰሞኑን ከህወሓት እና ከአዴፓ የወጡት መግለጫዎች ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን፣ ከተስፋ ይልቅ ስጋትን፣ ከሰላም ይልቅ ለሁከት በር የሚከፍቱ ናቸው፡፡ ህዝብ እንዲጨነቅ የሚያደርጉ ናቸው። በአጠቃላይ ህዝብና ሀገርን ወደ ከፋ ችግርና አዘቅት የሚያስገቡ ከአንድ እህትማማች ፓርቲዎች የማይጠበቅ እንዲሁም እንመራዋለን፣ ቆመንለታል የሚሉትን ህዝብና ሀገር የማይመጥኑ መግለጫዎች ናቸው ።

ዲሞክራሲያዊ አገር እንገነባለን ብለው በአንድ ዓላማና በአንድ ጥላ ስር ከተሰባሰቡ ድርጅቶች በዚህ ደረጃ ለፍቅር ሳይሆን ለብጥብጥ፤ ለልማት ሳይሆን ለጥፋት የሚዳርጉ፣ ሆድ የሚያስብሱ፣ ቂምና ቁርሾን የሚቀሰቅሱ መግለጫዎችን ማውጣት አሁን ህዝብና ሀገር እየመሩ ካሉና ወደፊትም በምርጫ አሸንፈን በተሻለ ደረጃ እንመራለን ከሚሉ ፓርቲዎች የሚጠበቅ አይደለም። ድርጊቱም ፓርቲዎቹንም ሆነ የሚወክሉትንም ህዝብ የማይመጥንና አሳዛኝም ነው። በወጡት መግለጫም ህዝብ አዝኗል፤ ወደየት እየሄድነው በሚልም ተደናግጧል። ህዝብና ሀገርን የሚመራ ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ ከሚል አመራርና ድርጅት የሚጠበቅ አይደለም። ይሄ ሊታረምና ሊስተካከል ይገባል።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመምራት ዴሞክራት መሆን ይገባል። ዴሞክራሲ ደግሞ የሀሳብም ሆነ የርዕዮተ ዓለም ልዩነትን የሚያስታርቀው በጠረጴዛ ዙሪያ በሰከነ መንፈስ በመወያየት እንጂ በእንካ ሰላምታ አይደለም። ማንኛውም ፓርቲም ሆነ ቡድን አንድ አይነት ዓላማና ግብ ይዞ መንቀሳቀስ አለበት ተብሎ አይገደድም። እንደ ወቅታዊ የዓለም እና ሀገራዊ ሁኔታ ለሀገርና ለወገን ይበጃል ብሎ ባመነበት መልኩ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ወይም ማሻሻያ ሊያደርግ ይችላል።

ሆኖም ግን ህዝብን በሚያሳዝን ሀገርን በሚያፈርስ መልኩ መሆን የለበትም። እንደማንኛውም ስልጡን መሪ በውይይት በመግባባት ወይም ደግሞ ላለመግባባት በመግባባት በሀሳብ መሸናነፍ ይኖራል። ይሄም ሲሆን ህዝብንና ሀገርን በማይረብሽ መልኩ ሊሆን ይገባል። በፓርቲ ዲስፕሊን ሊመራ ይገባል። ይሄ ካልሆነና በፓርቲዎች መካከል ያለውን ንትርክ ወደ ህዝብ በመወርወር ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት መሞከር ለማንም አይጠቅምም። ነገ እመራዋለሁ ያልነውን ህዝብና ሀገር የሚያፈራርስ እንጂ የሚገነባም አይደለም።

በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ሃገራት የሀሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። የአቋም ለውጦችም ሊፈጠሩ ይችላሉ። ይሄ የነበረ፣ አሁንም የሚታይ፣ ወደፊትም የሚኖር ነው። አለመግባባቶችና የሀሳብ ልዩነቶች ሲኖሩ ታዲያ ከዚህ ቀደምም በኢህአዴግ ውስጠ ድርጅት እንደሚታወቀው በሰለጠነና ዴሞክራሲያዊ በሆነ በሀሳብ የበላይነት መሸናነፍ ይገባል፡፡ የሰለጠነ ህዝብና ሀገርን የሚያስብ አመራር ችግሮችን የሚፈታው በዚሁ መንገድ ነው።

አሁን ህዝብን ከሚመሩና ከሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች የሚጠበቀው ሀገር ካለችበት ሁለንተናዊ ችግር ወጥታ ወደ ተሻለ ደረጃ የምትደርስበት፣ የህዝቡ ኑሮ የሚለወጥበት እና የተሟላ ሰላም ኖሮ ህዝብ ህይወቱን ያለስጋት መምራት እንዲችል በጋራ መስራት ነው። ለሀገር አንድነት በጋራ ዘብ የሚቆምበት ወቅት መሆኑ ለደቂቃም ሊዘነጋ አይገባም። ስለዚህ ይሄ ወደታሰበው ከፍታ እንዲወጣ የሀሳብ ልዩነት ቢኖርም በጋራ የሚመከርበት በጋራ የሚሰራበት ሁሉም የአቅሙን የሚወረውርበት እና የለውጡን ፍሬ አብሮ ለመቅመስ ጥረት የሚደረግበት ወቅት ነው። ለዚህ ደግሞ በጋራ መምከርና በጋራ መስራት ይገባል።

ይሁን እንጂ አሁን ከህወሓት እና ከአዴፓ የተሰጡ መግለጫዎች በህዝብና በሀገር ጥቅም ላይ ከማነጣጠር ይልቅ የይዋጣልን አይነት የቃላት ጦርነት ነው፡፡ይሄ የትም አያደርሰም። ስለዚህ ሰከን ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ በሀገራችን አንድ አባባል አለ፡፡ ቃላትን ከአንደበትህ ሳታወጣ ሁለት ሶስት ጊዜ አስብ የሚል። ህዝብ የሚያስተዳድርና የሚመራ አካል ሲሆን ደግሞ ብዙ ጊዜ ደጋግሞ መምከር፣ ማሰብ እና መነጋገርን መግለጫ ከማውጣት በፊት ማስቀደም ያስፈልጋል። ከሁሉም ነገር በፊት ህዝብና ሀገርን አስቦ ሰከን ብሎ በሰለጠነ መንገድና በጥበብ ችግሮችን ማየትና መፍታት ይገባል፤ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ከሁሉም በላይ ህዝብና ሀገር መቅደም አለበትና፡፡

አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011