“አቧራው ይራገፍ ወርቁም ይውጣ” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

8

«ወርቅ የሆነ ባህላችንን ለማየት ዓይናችንን ቀና፣ ልቦናችንን ከፈት እናድርግ። እነ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ባሌ ተራሮች፣ አርባምንጭ … ባለቤት በመሆናችን ብዙ ለፍተን የምናስተዋውቀው ነገር የለም። ያለንን ማሳየትና ሀብታቸውን በቀላሉ እንዲያፈሱ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅብን። ስለዚህ ህዝቡና መንግስት በጥምረት ይህንን ካደረግን በአጭር ጊዜ አቧራውን አራግፈን ወርቁን አውጥተን ባህላችንን እናሳድጋለን፤ ተጠቃሚም እንሆናለን።» አሉ ጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ባህላችንን፣ ታሪካችንንና ቅርሶቻችንን በማስተዋወቅና በሀብቱ በመጠቀም ዙሪያ ያለን ልምድ አነስተኛ መሆኑን ሲናገሩ ነው ይሄንን ያሉት። እናም በቀጣይነት «አቧራው ይራገፍና ወርቁ ወጥቶ ሀብት ይሁን» ሲሉ ተደመጡ። የትኛው አቧራ ካላችሁ ከአጠገባችን በተለያዩ ነገሮች ተሸፍኖ እንዳይታይ የጋረደንን ነው። በስንፍና፣ ባለማወቅ፣ ለእያንዳንዱ ነገር ትኩረት ባለመስጠት…የጋረደንን መጋረጃ ማለት ነው።

ኢትዮጵያውያን በጋብቻና ሞት፣ በግጭት አፈታት… የተለያዩ ሥርዓተ ክንዋኔዎች፣ የተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ያሉባት፣ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶች፣ የህክምና ለችግር መፍቻነትና ለአብሮነት የምትጠቀምበት ቱባ ባህል ያላት አገር ነች። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ዜጋ እጅ ላይ ያሉትን በማየት ሀብት አላደረጋቸውም።

እንደ ሀብት ተቆጥረው ገንዘብ እንዲያመጡ ከማድረግ ይልቅ የሌላ ተመልካች ሆኖ በአለባበስ፣ በአጋጌጥ፣ እንዲሁም በሌሎች ነገሮች የባዕድ ሀገራትን ባህልና ልምድ ናፋቂ ሆነናል። «በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል » አይደል የአበው ተረት። የምንለብሳቸው የየብሔረሰቡ አልባሳት የክት እንዲሆኑ ብቻ ፈቅደናል። ዘመናዊነት የራስን ባህል ትቶ የውጪን መናፈቅ ብቻ መስሎናል። ይህ ደግሞ ወርቁን እንዳናወጣ ገድቦናል። ቁሳዊ ባህል በአይን በማየት ብቻ የምንለያቸው ቢሆኑም አሰራሩንና አብሮ ያለውን አተያይ ማጥናትና ሀብት ማድረግ የዜጋው ግዴታ ቢሆንም ይህንንም እንዳናደርግ «ዘመንኛ» በምንለው የውጪ ባህል ራሳችንን ጋርደነዋል።

ለምሳሌ በእኛ ባህል ቡና ፍሬው ብቻ ሳይሆን አፈላሉና የሚፈላበት ጀበናና ምክንያቶች የኢትዮጵያዊያን ባህላዊ እሴት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህ ሀብት ሆኖ የመጠቀሙ ነገር ግን በእጅጉ ያነሰ ነው። ለዚህ አንድ አብነት አድርጌ የማነሳው ጉዳይ አለኝ። በአንድ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ የነበረውን የጀርመናዊቷን እንስት ጉዳይ። እንስቲቱ ባለቤቷ ኢትዮጵያዊ ነው። የጀበና ቡና አፈላል ባህሉን አገሯ ወስዳ ስርዓቱን ክብ ተሰርቶ በተቀመጠ ስፍራ ላይ ታከናውናለች። ይህ ደግሞ አገርን በማስተዋወቅም ሆነ የተሻለ ገቢ በማግኘት ጥሩ አቅም እንደፈጠረላት ይታያል። ታዲያ እኛ ወዴት አለን ከተባለ በአቧራችን ተጋርደናል ከሚል ውጪ መልስ አይኖረንም። አገር እንዲያየን የምንፈልገው በባህላችን በታሪካችን በጥበባችን ሳይሆን በጉልበታችን ነው። በአጠቃላይ የእኛ ሳንሆን የሌላ የሆንበት ብዙ ነው።

ለዚህም ይመስለኛል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቁጭት መንፈስ ይህ ሀሳብ ትኩረት እንዲሰጠው ያሳሰቡት። አቧራው ተራግፎ የቱሪዝም ሀብታችንን ለአገር በማሳየት ተጠቃሚ እንሁን ያሉት። ለዚህም በቢሮአቸው ዙሪያ ያለውን ስፍራ ለቱሪስት መስህብ አድርገው ለመስራት እቅድ ተይዞም ብዙዎቹ እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል። እስከዛሬ በቤተ መንግስቱ ብዙ አዳራሾች ሀብት መሆን ሲችሉ ተዘግተዋል። ስለዚህ ዛሬ መንቃት ላይ በመሆናችን እንሰራለን ብለዋል።

ከቤተመንግስቱ የተጀመረው የቱሪዝም መስህብ የሆኑ ስራዎችን መስራት በአገር ላይ የሚያመጣውን ጥቅም ተረድተው ታላቁ ብሄራዊ ቤተመንግስት (የፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስት) ሙሉ ለሙሉ ለህዝብ ክፍት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀብቶቻችን በጥንቃቄና በቁጠባ መጠቀም ያስፈልጋልና የላይኛው ቤተመንግስትም (ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኖሩበት) ግማሹ ለህዝብ ክፍት ይሆንና ግማሹ ለጠቅላይ ሚኒስትርና ለፕሬዚዳንቷ መኖሪያ ይሰራበታል። በዚህ ደግሞ አገሪቱ ካላት ሀብት ብዙ እንድትጠቀም ትሆናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ሀብቶቻችን ምን ያህል እየተጠቀምንባቸው እንዳልሆነ የሚያመላክት ነገርም አክለው አንስተዋል። ይኸውም የአጼ ኃይለሥላሴ ውድና የቆዩ መኪናዎችን ነው ለአብነት የጠቀሱት።

“ንጉሱ በጣም የቆዩና ውድ የሚባሉ መኪኖችን ይሰበስባሉ። ሆኖም እንደማንኛውም እቃ በግምጃ ቤት ውስጥ ተጥለው ይገኛሉ። ሀብት አጠቃቀማችን ምንም ትኩረት ያልተሰጠው ነው። ለዚህም አብነት የምትሆነን ብራዚል ስትሆን፤ በምታደርገው የቱሪስት ስበት ብቻ አንድ የቆየ መኪና በመስተዋት ከልላ ብዙ ዶላርን ታፍሳለች። የቱሪስት መስህቧንም ታጠናክራለች። እዚህ ቤት ግን ይህ አልሆነም። ያለን ብዙ የምንመለከተው ጥቂት ነው” በማለት ነው ቁጭት አዘል ሀሳብ የሰነዘሩት።

«የአጼ ሀይለስላሴ መኪና ሁለት የሚለዩበትና ሊጎበኙ የሚችሉበት መሰረታዊ ምክንያት አለ። የመጀመሪያው የንጉስ መኪና መሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛው የቆየና በጊዜው ውድ የሆነ መኪና መሆኑ ነው።» የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ይህንን አቧራ አራግፎ ወርቁን ማውጣት ለነገ የሚባል መሆን የለበትም። ለዚህም ደግሞ በቅርብ ጊዜ የመኪና ኤግዚቢሽን አዘጋጅቶ ማስጎብኘት ላይ ይሰራል። በሌላ በኩል ቱሪስትን ያለንን ተጠቅመን ለመሳብ የቤተመጽሀፍትና ሌሎች ፓርኮች ጉዳይም በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቀው ለእይታ ክፍት ይደረጋል።

“ቢላዋ ይወጋል፤ ይገላል። ሆኖም ሽንኩርትና ሌሎች ነገሮችን በመቁረጥም ልዩ አገልግሎት ይሰጣል። የውጪ ባህሎችም የሚጥሉብን ነቀርሳ እንዳለ ሁሉ የሚያስተምሩንም በጎ ነገር አለ። ለአብነት ያላቸውን ብቻ ሳይሆን ታሪክ ሳይኖር እንኳን ታሪክ ፈጥረው ለማስጎብኘትና የአገርን ገጽታ ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት ከእነርሱ መማር ያለብን ጉዳይ ነው። “ብለዋል።

ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች አገራት ውስን ሀብት ነው ያላቸው። ይህንን ሀብት ዘላቂ ልማታቸውን ለማረጋገጥ ሽጠው፣ ለውጠው ገንዘብ ማድረግ ካልቻሉ ግን ያለንን ማቆየት አይቻላቸውም። ምክንያቱም የተመረተ ሁሉ በሙሉ ቢበላ የሚያስፈልግ ሌላ አንድ ነገር ቢኖር ያንን ማሟላት ይቸግራል። እናም ከባህላችን የሚገኙ ሀብቶችን በሚገባ መጠቀም ለነገ የሚባል አለመሆኑን ይናገራሉ። በዚህም በቅርቡ አርባ ምንጭ ላይ በአፍሪካ ሲሸልስ ብቻ በጣም ዘመናዊ ሆቴልና ሪዞርት አገር ውስጥ ለማምጣት እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል።

ሲሸልስ «ሲሸልስ ፎር ሲዝን» ከሚባለው ሪዞልት የምታገኘው የዓመት ገቢ አጠቃላይ ከተለያዩ ሴክተሮች ከምታገኘው ሀብት የበለጠ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት። እንደሀገር ትልቁ የውጪ ምንዛሬ ማግኛ ምንጫቸው አንድ ሆቴል ነውና በእኛም አገር ይህ መጥቶ ቢያንስ አርባምንጭን ተጠቃሚ ቢያደርግ አገር ይጠቀማል። ከዚያ ሥራውን አይተንም ሌሎች ሀብታቶቻችንንም የምንጠቀምና የምናመቻች ይሆናል ብለዋል።

ዛሬን ለዛሬ ያዋለ ሰው በቀጣይ ለሚከሰቱትና ለሚሰራቸው ሥራዎች ምንም አይጨነቅም። ምክንያቱም ዛሬን አውቆ አሳልፏልና። እናም በእድሜ ልክ ለዛሬ መስራት መልመድ ይኖርብናል። ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በእጃችን ያሉ ቅርሶችንም አቧራቸውን አራግፈን ወርቃቸውን ማግኘት ይጠበቅብናል። ይህ የሚሆነው ደግሞ ለዛሬ ሲሰራ ብቻ ነው። ዘመን ስለ ሰው ወይም ስለ ፍጥረት እንደተሰጠ መረዳት ያስፈልጋል። ዘመንን እንደሩቅነቱ ለክተን ሀብት የሚሰጥበትን መንገድ ማመቻቸትም ይገባናል። ምክንያቱም ከጎናችን ያለን ሀብት እንድናይና በአቧራ ሸፍነን እንዳናልፈው የምንሆነው ይህንን ስናደርግ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን አንድ የመጨረሻ ነገር እናንሳና ሀሳባችንን እንቋጭ። ዘላለማዊ ጉጉትን ለማምጣት፤ የሚኖሩለትንና የሚናፍቁትን እንዲሁም የሚደክሙለትን ለማግኘት የጎናችንን አይተን አቧራን ማራገፍ ያስፈልጋል። ብዙ ሰዎች የሚተቹን ቆሻሻን በጠዋት ተነስተን ከሳሎን ብንጠርገውም ከበር ሳያልፍ በመከመራችን ነው። ስለዚህ ያልጠራውን ነገር ይዘን ለመጓዝ ከማሰባችን በፊት ያለንን ትክክለኛ ባህል ማጎልበት ላይ እንታትር። ከጎናችን በአቧራ የተሸፈነ ወርቅ መኖሩን እንወቅ። ቅርሳችን ከአቧራ ተላቆ ሀብት የሚሆንበትን ባህል እናዳብር። ታሪክ ሳይኖረው ታሪክ ፈጥሮ የሚሸጥ አለም ላይ ተቀምጠን ታሪክ እያለን በአቧራ ሸፍነን መቀመጥ ዋጋ ከማስከፈሉም በላይ የታሪካችንና የባህላችን ተጠቃሚ አያደርገንምና ለዛሬ ባህልና ታሪካችን ዛሬን ሰጥተን እንጠቀምበት። ሰላም!

አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011

 ጽጌረዳ ጫንያለው