አምስቱ በሮች

93

የሀረሪ ክልል ህዝብ ታሪክ ፣ ባህል እና ማንነት ከሀረር ከተማ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ሀረሪዎች በረዥም ዘመን የስልጣኔ ታሪካቸው ያፈሯቸው ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ በርካታ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች ባለቤት ናቸው። ከእነዚህ ቅርሶች መካከልም የከተማዋ ልዩ መለያ ምልክት ከመሆንም አልፎ እ.ኤ.አ በ2006በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ግንብ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በግንቡ ውስጥ ከ82 በላይ መስኪዶች እና በርከት ያሉ የሀረሪ ባህላዊ ቤቶች ይገኛሉ። የኢትኖግራፊ ወግች በመጻፍ የታወቀው የሀረሪን ባህሎች በጥልቀት ከአጠኑት መካከል አንዱ አፈንዲ ሙተቂ ስለ ሐረር አምስቱ በሮች ይነግረናል። ደራሲው እንደሚለው በልጅነቴ የሰማሁት አንድ ግጥም አለ እንዲህ ይላል፡-

Adaree biyyoodhaa shani karri ishii

Halaalaa mulata ifaan fuula ishii.

ትርጉሙ

የአደሬ ቢዮ (ሀረር) በሮች አምስት ናቸው

ብርሃናማው ፊቷ ከርቀት ነው የሚታየው

እንዲህ የሚለው ማን መሰላችሁ? ይናገራል ባለሙያው ከሀረር ከተማ በከፍተኛ ርቀት ላይ የተደላደለው የጨርጨር ምዕራብ ሀረርጌ ገበሬ ነው። ወጣቶች ይህንን ግጥም የሸጎዬ ጭፈራ ማዳመቂያ አድርገው ሲደጋግሙት እንደሚሰማ ይናገራል። ሆኖም እነዚያ ወጣቶች የግጥም ማጣፈጫ የሆኑላቸውን የሀረር በሮች ለአንድም ቀን ያዩዋቸው አይመስለኝም ይላል።

ባለሙያው ሲያስረዳ የሀረር በሮች እዚያ ድረስ መሰማታቸው ከተማዋ ከነበራት ዝና የመነጨ ነው። ታዲያ የጨርጨር ገበሬዎች በርቀት ስለሚያውቁት ነገር እንዲህ የሚሉ ከሆነ ለአምስት ክፍለ ዘመናት ከበሮቹ ጋር የኖረው የሀረሪ ህዝብስ ምን ይላል? ስለ“ሐሚስቲ በሪያች” ወይም አምስቱ የሀረር በሮች ባለሙያው ያጫውቱናል።

ሁለቱ መንትያዎች

ሀረር ጌይ የሁለት መንትያ ከተሞች ውጤት ናት። እነዚህ መንትያዎች ልዩ ልዩ ስሞች ነበሯቸው። ከስሞቹ መካከል አንዳንዶቹ ከስራ ውጪ ሆነዋል

በዚህ ዘመን። ታሪካዊና ባህላዊ ጠቀሜታቸው ግን መቼም ቢሆን አይሻርም። ስለሆነም እነዚያን መንትያዎች የ“ሐሚስቲ በሪያች” ወጎቻችን ማሟሻ ብናደርጋቸው መልካም ነው።

ከሁለቱ መንትያ ከተሞች መካከል አንዱ ከዚህ ቀደም በርካታ ወጎችን በቀመርኩበት “ጌይ ጁገል” (የሀረር ግንብ) የታጠረው ክልል ነው። “ጌይ ጁገል” በጥንት ዘመናት (ከ1875 በፊት) ብቸኛው የከተማ ክልል ሲሆን የሀረር አሚሬት መናገሻ፣ የሀረሪዎች መኖሪያና የዝነኛውና ዓለም አቀፋዊው የሀረር ገበያ መገኛም ነበር። በግንቡ ዙሪያ የነበረውና በእርሻ መሬቶች፣ በግጦሽ ስፍራዎች፣ በደኖችና በውሃ ምንጮች የተሞላው መሬት ደግሞ “ጌይ ፈጋይ” የሚል ስያሜ ነበረው (ጌይ ፈጋይ “የከተማዋ ዳርቻ” ማለት ነው – በሀረሪ ቋንቋ”)።

ግብጾች በ1875 ሀረርን ከያዙ በኋላ ከዋናው ከተማ (“ጌይ ጁገል”) በምዕራብ በኩል በሚዋሰነው የ“ጌይ ፈጋይ” ክልል ላይ የመኖሪያ ቤቶች ተቀለሱ። እያደር አነስተኛ የገበያ ትዕይንቶችም መታየት ጀመሩ። በዚህን ጊዜ በሀረር ዙሪያ የሚኖረው የኦሮሞ ህዝብ ሁለቱን የገበያ ማዕከላት በሁለት ስሞች በመለየት መጥራት ጀመረ። በዚህም መሰረት በ“ጁገል” ለተከበበው ክልል “አደሬ ጉዶ” (ትልቋ አደሬ)፣ በ“ጁገል” ዙሪያ ለተቆረቆረው ከተማ ደግሞ “አደሬ ጢቆ” (ትንሿ አደሬ) የሚሉ ስሞች ተሰጡ።

ሁለቱ መንታ ከተሞች የተፈጠሩበት ሂደትና ከስሞቻቸው ጋር የተያያዘው ታሪክ ከላይ የተገለጸውን ይመስላል። ታዲያ ስሞቹ በዘመናችን ብዙም እንደማይጠቀሱ (ከጁገል በስተቀር) ነግሬአችኋለሁ። በርግጥም “ጌይ ፈጋይ የት ነው?” ተብሎ ቢጠየቅ ለመመለስ የማይችል የከተማዋ ነዋሪ ብዙ ነው በቅርበት እንዳየሁት። “አደሬ ጢቆ” የት እንደሆነ ለመናገር የማይችል ሰውም ሞልቷል። ሆኖም እድሜ ጠገብ በሆኑ የዓለም ከተሞች እንደሚታየው “አዲሱ ከተማ” እና “አሮጌ ከተማ” የሚባል የከተማ አከፋፈል ዘይቤ እልፍ ዓመታትን ባስቆጠረችው ሀረር ጌይ በጭራሽ አናገኝም::

“አምስቱ በሮች” እና የሀረሪ ህዝብ ትውፊት

ከላይ የገለፅኳቸው ሁለቱ የከተማዋ ክፍሎች የሚገናኙት በ“ሐሚሲቲ በሪያች” (አምስቱ በሮች) አማካይነት ነው። “ሐሚስቲ በሪያች” ከተሰሩበት ዓላማ ዝንፍ ሳይሉ ህዝብን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። በታሪካዊ ጉዟቸውም ታላቅ የጥበብና የባህል መዘክር ሆነዋል። በሮቹን እንደ አብራኩ ክፋይ የሚሳሳላቸው የሀረሪ ህዝብ ስለነርሱ የሚናገረው ታሪክ ደግሞ በጣም ያስደምማል።

“የሀረር በሮች አምስት የሆኑበት ምክንያት ምንድነው”” የሚል ጥያቄ መጥቶባችሁ ያውቃል? እንደዚያ ከሆነ ምክንያቱን ልንገራችሁ። ሀረሪዎች ለእስልምና እምነታቸው በጣም ቀናኢ ናቸው። ይህ ሁኔታ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ሲገለጽ ይታያል። ለዚህ ትልቅ አብነት የሚሆነውም የአምስቱ በሮች ተምሳሌት ነው። የሀረሪ ሽማግሌዎችና ምሁራን እንደሚናገሩት “አምስቱ በሮች” አምስቱን የ“ፈርድ ሰላት” (እያንዳንዱ ሙስሊም ሊፈጽመው የሚገባ ስግደት) ወቅቶችን ያመለክታሉ። አንዳንድ ሀረሪዎች ግን ከዚህ ብዙም ያልራቀ ተምሳሌታዊ ገለጻ ነው ያላቸው። በነዚህኛዎቹ አባባል አምስቱ በሮች አምስቱን የእስልምና ማዕዘናት ያመለክታሉ።

ከአንድ የአዲስ አበባ “ጆሊ” ጋር ብትተዋወቁና “የየት ሰፈር ልጅ ነህ?” ብላችሁ ብትጠይቁት “የመርካቶ ልጅ ነኝ!”፣ “የፒያሳ ልጅ ነኝ!” ወይንም “የቦሌ ልጅ ነኝ!” የሚል አይነት ምላሽ ታገኛላችሁ። የድሬዳዋ “ቀሽቲ”ም ሰፈሩን ብንጠይቀው “የሳቢያን ልጅ ነኝ!”፣ “የከዚራ ልጅ ነኝ!”፣ “የለገሐሬ ልጅ ነኝ!” ወዘተ… በሚል ይመልሳል። እኔም ይላል አፈንዲ “በገለምሶ ከተማ የየትኛው ሰፈር ልጅ ነህ?” ተብዬ ብጠየቅ “የሐድራ ሰፈር ልጅ ነኝ” እላለሁ። እንደዚህ አይነቱ ጥያቄና መልስ ግን በ“ጌይ ወልዲ” (የሀረሪ ልጅ) ዘንድ አይሰራም፤ እርሱ የሚያውቀው የተለየ የሰፈር አጠያየቅና የመልስ አሰጣጥ ዘይቤ ነውና!

“ጌይ ወልዲ” የሰፈሩን ስም እንዲነግረን ከፈለግን “አይ በሪ ሊጂ ኢንተኽ?” በማለት እንጠይቀዋለን። ይህም “የየትኛው በር ልጅ ነህ?” ማለት ነው። እርሱም ስረ መሰረቱ የተገኘበትን “በሪ” ካገናዘበ በኋላ “አን በድሪ በሪ ሊጂ ኢንተኝ” ወይ ደግሞ “አን አስማእዲን በሪ ሊጂ ኢንተኝ” በማለት ይመልስልናል። “የቡዳ በር ልጅ ነኝ!” ወይንም “የሸዋ በር ልጅ ነኝ!” እንደማለት ነው። ጌይ ወልዲ (የሀረሪ ልጅ) እንዲህ የሚልበት ታሪካዊና ባህላዊ መሰረት አለው።

የጥንቷ ሀረር ጌይ በአምስት ክፍለ ከተሞች የተከፋፈለች ነበረች። እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ በአቅራቢያው ያለውን የሀረር በር መሰረት በማድረግ የተዋቀረ ሲሆን በክፍለ ከተማ ገዥነት የሚሾመውም “ገራድ” የሚባል አስተዳዳሪ ነው። የጥንቱ የከተማዋ ነዋሪዎችም የአንድን ሰው አድራሻ የሚገልጹት ሰውየው በሚኖርበት በር ስም ነው። ታዲያ ሀረሪዎች ጥንታዊ አሚሬታቸውን በጨለንቆው ጦርነት ማግስት ቢያጡትም ከጥንቱ የአሚሬታዊ አስተዳደር ዘመን የወረሱትን በበር የመጠራራት ባህል እስካሁን ድረስ ቀጥለው በታል።

“ጌይ ወልዲ” የሰፈሩን ስም የገለጸበትን ዐረፍተ ነገር ከአማርኛ ፍቺው ጋር በደንብ አመሳክራችሁታልን? ምን የተለየ ነገር አገኛችሁ? የናንተን ምላሽ ለናንተው አድርጉት። በበኩሌ በዚህ ላይ ለማለት የምፈልገውን ነገር በአንድ ገጠመኝ በማጀብ እነግራችኋለሁ።

ኢትኖ ግረፈር አፈንዲ ሙታቂ ያሳለፈውን ሲያትት “የሀረር ጌይ ኑሮዬን ከጀመርኩ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በ“ጁገል” ደቡብ ምስራቃዊ ክፍል በሚገኘው “ሰንጋ በር” አካባቢ ስንሸራሸር አንድ አዛውንት “ሰደቃ” (ምጽዋት) ለመኑኝ። እኔም ሰደቃውን ከሰጠኋቸው በኋላ በኦሮምኛ “Karri kun maqaan isaa maal ja’ama” ብዬ ጠየቅኳቸው -ሰንጋ በርን በእጅ ምልክት እያሳየኋቸው። “ይህ በር ምን ይባላል?” ማለቴ ነበር። አዛውንቱ በአማርኛ የማውቀውን “ሰንጋ በር” በኦሮምኛ “Karra Sangaa” በማለት ያስተዋውቁኛል ብዬ ስጠብቅ “Karra Soofii” አሉና አረፉት!

“Karra” በኦሮምኛ “በር” ወይም “ከተንበር” ማለት ነው። “ሶፊ” ግን “ሰንጋ” ማለት እንዳልሆነ አውቃለሁ። በዚህም አንድ ነገር ጠረጠርኩኝ። እናም ሌላ ጥያቄ መድገም አስፈለገኝና “Karra gama oliitiin jiru san yoo maal Ja’aniin?” አልኳቸው ። በአማርኛ ሲመነዘር “ከላይ በኩል ያለው በር ምን ይባላል?” እንደ ማለት ነው። እሳቸውም ፈጠን ብለው “Karra Hammarreessaa” የሚል ምላሽ ሰጡኝ። ከአዛውንቱ የሰማኋቸው ስሞች (“ከረ ሶፊ” እና “ከረ ሀማሬሳ”) አዲስ ስለሆኑብኝ ጉዳዩን የበለጠ እንዲያስረዱኝ የሀረሪ ወዳጆቼን ጠየቅኳቸው:: እነሆ በነርሱ ሰበብም ሌላ “ዐጃኢብ” ለማወቅ ቻልኩ።”

አምስቱ የሀረር በሮች በአምስት ቋንቋዎች የተለያዩ ስሞች ነው ያሏቸው፡፡ በሮቹ በሀረሪ፣ በኦሮምኛ፣ በአማርኛ፣ በዐረብኛ እና በሶማሊኛ ቋንቋዎች የሚጠሩባቸው ስሞች የሚከተሉት ናቸው ፡፡

. መካከል ላይ ያለው በር አስማእዲን በሪ ከርረ ሀማሬሳ ሸዋ በር ባቡል ነስር አልባብ ሀማሬይሳ

. በስተግራ በኩል ከላይ ያለው በር አስሱም በሪ ከርረ ፈልኣና ፈላና በር ባቡል ፉቱሕ አልባብ ፈልዳኖ

. በስተግራ በኩል ከታች ያለው በር አርጎብ በሪ ከርረ ኤረር ኤረር በር ባቡል ራሕማህ አልባብ ኤረር

. በስተቀኝ ከላይ ያለው በር በድሮ በሪ ከርረ ቡዳዋ ቡዳ በር ባቡል ሓኪም አልባብ ቢዳ

. በስተቀኝ በኩል ከታች ሱጉድ አጥ በሪ ከርረ ሶፊ ሰንጋ በር ባቡ ሰላም አልባብ ቢሲዲሞ

እያንዳንዱ ስም የራሱ የሆነ ታሪካዊ መነሻ አለው፡ ፡ “ሀረር ጌይ፡ የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ እንዲሁም “The History of hareri” ላይ በዝርዝር ታሪኩ ተገልጾዋል እንድታነቡት እጋብዛለው፡፡

ሰላም!!

አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011

 አብርሃም ተወልደ