«ከሰራተኞቼ ጋር አብሬያቸው ስመገብና ስሰራ ውስጤ ይረካል» - አቶ ሀብታሙ እናውጋው

18

እጅግ አስከፊና አሳዛኝ የህይወት ፈተናዎችን በሰው አገር አሳልፏል። ታርዟል፣ ተርቧል ፣ተጠምቷል። ሆኖም እጅ አልሰጠም። ይልቁንም ይህንን ሁሉ ችግር በድልና በጥበብ አሸንፎ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ደርሷል። እናም ዛሬ እንደ”ባለሀብት“ አለባበሱን አሳምሮ ይህንን አድርጉ፤ ይህን አታድርጉ የሚል ትዕዛዝ ሰጪ ሳይሆን ሰርቶ አሰሪ ነው። ከዳር ሆኖ ለተመለከተው ሰራተኛ እንጂ ባለቤትም አይመስልም። የዛሬው የ«ህይወት እንዲህ ናት» አምድ እንግዳችን የከቡሽ ኢንተርናሽናል ሎጂ ባለቤት አቶ ሀብታሙ እናውጋው።

ልጅነትን በልፋት

አቶ ሀብታሙ ትውልዱ በቀድሞ አሰበ ተፈሪ በአሁኑ ጭሮ ነው። አባቱ ፖሊሲ ስለነበሩ ዕድገቱ በአንድ ቦታ የተወሰነ አልነበረም። እንደ ልጅነቱ ከልጆች ጋር የመጫወት እድል አልገጠመውም ። የአባቱ ደመወዝ ዝቅተኛና እርሱም የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑ በርካታ የሥራ ጫናዎች አስተናግዷል። ስለዚህ ሀብታሙ ሰርቶ ቤተሰቡን የማገዝ ግዴታ አለበት። እናም በልጅነት ጉልበቱ ያልሰራው ሥራ አልነበረም።

« ልጅነቴን ሳስብ ችግርና የእናቴን ስቃይ ነው የማስታውሰው» የሚለው ሀብታሙ፤ እናቱ ያለውን ምግብ ለቤተሰቡ አካፍለው በቡና ያድሩ እንደነበር ያነሳል። እርሱም በዚህ ምክንያት ሲሳቀቅ እንደቆየ ያስታውሳል። ይህ ደግሞ በቆሎ እየጠበሰ በመሸጥና ሰዓታትን በእግሩ ተጉዞ እንቁላል በመግዛትና በመሸጥ ሥራ ላይ እንዲሰማራ ያደረገው መሆኑን ይናገራል። ከዚያ ከፍ ሲል ደግሞ አነስተኛ ሱቅ ከፍቶ ከትምህርት መልስ ለመነገድ ሞክሮም ነበር። ነገር ግን እናቱ ዱቤ በብዛት እየሰጡ ለኪሳራ ስለተዳረገ ተዘጋ ።

ሀብታሙ ቤተሰብን የሚያግዘው የተለያዩ ነገሮችን ነግዶ ባመጣው ገንዘብ ብቻ አልነበረም። የሽንት ጨርቅ በማጠብ፤ ምግብ በማብሰል፣ ልጅ በማዘልና እንጨት በመልቀም ፣ ውሃ በመቅዳት ጭምር ነው። በተለይ የቤት ውስጥ ሥራ ላይ ከእናት ቀጥሎ ጥሩ ሙያ ያላት ሴት የሚመስለው እርሱ እንደነበር ያስታውሳል። በዚህ ደግሞ የእናቱን የሥራ ጫና እንደቀነሰ ይሰማዋል።

ለቤተሰብም ሆነ ለአካባቢ ሰው መታዘዝን የሚወደው አቶ ሀብታሙ፤ያየውን ነገር ቶሎ ተቀብሎ መተግበር ላይ ልዩ ችሎታ አለው። የፈጠራ ክህሎቱም ላቅ ያለ ነው። ይህ ደግሞ ለዛሬ ህይወቱ መለወጥ መሪ እንደሆነለት ይናገራል። በሚሰራቸው ሥራዎች ሁሉ የሚያገኘውን ገንዘብ እንደልጅነቱ ለከረሜላና ለሌሎች ነገሮች ሳያውል በቀጥታ ለእናቱ ማስረከቡም ልዩ የሚያደርገው የልጅነት መለያው ነው።

መጠሪያ ስሙን ያወጡለት አባቱ ሲሆኑ፤ደመወዛቸው ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ሀብታሙ ተብሏል። በልጅነቱ በጣም ከሚያስደስተው ጨዋታዎች መካከል የመጀመሪያውን ሰርግ ቤት ሄዶ መዝፈንና መደነስ ነው። ሀኪም መሆን የመጀመሪያ ፍላጎቱ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ነጋዴ መሆን ምርጫው ነበር። ሆኖም የነበረበት ጫና በትምህርት የተሻለ አቅም ኖሮት ህክምናውን መቀላቀል እንዳይችል አድርጎታል።

የእነ ሀብታሙ ቤተሰብ 10 ብቻ አልነበረም እናትም የሌሎች ችግረኛ ልጆችን በመሰብሰብ ይደግፋሉ። በዚህም እናት አረቄ እያወጡ የቤቱን ቀዳዳ ለመድፈን ቢጥሩ፤ አባት የሚያገኟትን የወር ደመወዝ ቢደጉሙ፤ እርሱም በየአቅጣጫው ባልጠነከረው የልጅነት ጉልበት የተለያዩ ሥራዎችን ቢሰራ ቀዳዳው መደፈን አልተቻለም ነበር። ስለዚህ የቤተሰቦቼን ስቃይ ከማይ ብሎ ስደትን ምርጫው አደረገ።

ትምህርት

ሀብታሙ ነገሮችን ቶሎ የመቀበል አቅም ያለው ልጅ በመሆኑ በትምህርቱ ጎበዝ ከሚባሉት ተርታ ይሰለፋል። ግን ይህንን ሁኔታ በሚገባ የሚያስቀጥለው ምቹ ሁኔታ አልነበረውም። የአባቱ የሥራ ሁኔታ፤ የእናቱ የሥራ ጫናና እርሱም ቤተሰቡን ለማገዝ የሚያደርገው ጥረት ጉብዝናውና ውጤታማነቱ እንዳይስማሙ አደረጋቸው። የልጅነት ህልሙ ላይም እንዲደርስ እድል አልሰጥ አለው። በተለይም አባቱ አንድ ቦታ ላይ ተቀምጠው አይሰሩምና እርሳቸው በሚያስፈልጉበት ቦታ መዘዋወሩ ደግሞ ይበልጥ ጫናውን አበዛበት።

ሀብታሙ ትምህርቱን በጣም የሚወድ ልጅ ነው። ስለዚህም በሄደበት ሁሉ ካቋረጠበት ይቀጥላል። ይህ ደግሞ በተለያየ ቦታ ትምህርቱን እንዲከታተል አድርጎታል። ትምህርቱን ጭሮ፣ ቦኬ፣ በዴሳ እያለ ነው እስከ12ኛ ክፍል የተከታተለው። ከዚያም ስደት ላይ በመሆኑ ትምህርቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ሆኗል። ካናዳ ከገባ በኋላ ግን የትምህርት ጥማቱን ለማርካት ማታ ላይ የሚሰራውን ሥራ በመተው ጆርጅ ብራውን ኮሌጅ ገብቶ የአይቲ ትምህርት መማር ችሏል።

ከአገር ውስጥ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሱማሊኛ፣ አፋርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ የሚናገረውና የሚሰማው ሀብታሙ፤ ከውጪም እንግሊዝኛና ጣሊያንኛ ቋንቋም ይችላል። ይህ ደግሞ ለስራው የሚያግዘውን የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲወስድ እንዳስቻለው ይናገራል።

ስደትና ፈተናው

በ1976 ዓ.ም ነበር የቤተሰቡን ችግር መቋቋም ቢያቅተው ጭሮ ከተማን ለቆ የዘጠኝ ሰዓት የእግር ጉዞን ለመጋፈጥ የተነሳው። «እንደማይመቸኝ፤ እንደምሞትና እንደማያልፍልኝ አውቃለሁ። ግን ቤተሰብ ከዚህ የበለጠ ችግር ውስጥ ወድቆ ማየት ለእኔ ከአቅሜ በላይ ነው።» ይላል። እናም ያጋጠመው ችግር ካሰበው በላይ እንደሆነበት አይዘነጋውም። በተለይ ብዙ አሰቃቂ ድርጊቶች ሲከወኑ ሲያይ ለወጣት ትግስትን የሚያላብስ አልነበረም። ሆኖም ግን ከቤቱ የወጣ ስደተኛ አርፈህ ተኛ ነውና የመጣውን ከመቀበል በቀር ምንም ማድረግ አይችልም ። ስለዚህ ተጋፈጠው።

የአካባቢው ሰዎችን ለመመሳሰል ሲል መጠሪያ ስሙን በ«አብዲ» ተክቷል። ያም ሆኖ ከስቃይ አላመለጠም። ሊገድሏቸው ሲጋበዙ የነበሩ ሽፍቶች የነበራቸውን ንብረት ውሃ እንኳን ሳያስቀሩ ወስደውባቸዋል። በዚህም በሞትና ህይወት አፋፍ ላይ ደርሰው ነበር። ውሃ ጥሙ ስለበረታባቸው እራስን ለማትረፍ መንፈራገጥ አልቀረምና በሹል ድንጋይ አሸዋውን በመቆፈር ለጠብታ ያህል ውሃ አግኝተው ተቃመሱ፤ከዚያም ህይወታቸውን የሚያተርፍላቸውን ሲያማትሩ መጀመሪያ ከሽፍቶቹ የታደጋቸው ሰው አሁንም ደርሶ አዳናቸው። የዚህ ሰው ውለታ ቀላል እንዳልነበር የሚያነሳው ሀብታሙ፤ ከሰባት ቀን የእግር ጉዞ በኋላ ጅቡቲ የስደተኞች ካምፕን እንዲቀላቀሉ የረዳቸው እርሱ እንደነበር ይገልጻል። ካምፑ ጥቁሮች የሚኖሩበት ቢሆንም ምንም የሚበላና የሚጠጣ የለበትም። በተለይ እንዲህ በእግር ጉዞ ለተንገላታ የሚሆን ነገር አይገኝም። እዚህም ቢሆን የተለየ እድል እንዳልገጠማቸው ይናገራል።

በካምፑ የሚተኙበትና የሚለብሱት እንዳልነበራቸው የሚያወሳው ባለታሪኩ፤ ከላይ ዝናብ ብቻ ሳይነካቸው ለቀናት ያህል እንደቆዩ፤ ሙቀትና በሽታ ግን እንደተፈራረቀባቸው ይገልጻል። ምክንያቱ ደግሞ እርስ በእርስ ተጠጋግቶ ስለሚኖሩ እንደሆነ ያነሳል። አንድ ቀን ሌሊት ግን ለህይወቱ እፎይታን የሚሰጥ አዲስ ተዓምር እንደተፈጠረለት የሚገልጸው ሀብታሙ፤ብቻውን ከካምፑ ወጥቶ ብርድ እንዳይነካው የለበሳትን ቲሸርት ወጥሮ በአንድ ቋጥኝ ላይ ተቀምጦ ሳለ ሁለት ሰዎች በስሩ አለፉ። እርሱም ይህ ይደረግልኛል ባይልም ለሰላምታ ትንንሽ እጆቹን ዘርግቶ አውለበለበላቸው። እነርሱም አጸፋውን መለሱለት። ግን የሰውነቱ ሁኔታ በጣም ስላስደነገጣቸው ቀርበው ምን እንደሚፈልግ ጠየቁት። በወቅቱ የሚፈልገው በልቶ ማደር ስለነበር የቻለውን ያህል ችግሩን አስረዳቸው። ወዲያው ያላቸውን በማዋጣት ወደ ሰባት ሺ ብር በጥሬው ቆጥረው ሰጡት።

ይህንን ማመን ያልቻለው እንግዳችን፤ አይቶት የማያውቀውን ብር በማግኘቱ እጅግ ተደሰተ። ግን ምን ሊያደርግበት እንደሚችል ግንዛቤው አልነበረውም። እናም በቀጥታ በአገሪኛው «ለአርዙ ቃር» የሚባል ምግብ ለመመገብ ከጓደኛው ጋር ተጓዘ። እስከሚበቃቸውም በልተው የተረፈውን ገንዘብ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ተወያዩ። ዋና አላማቸው ከአገር መውጣት አደረጉና ብሩን ሳያባክኑ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ እየበሉ ትራሳቸው ሥር ቀበሩት። ግን «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» ሆነና ያስቀመጡት ብር በጎርፍ አደጋ ተወሰደ። ከዚያም ሌላ ስቃይ ውስጥ ገቡ።

ለሌላ ሌላ ቀን አለው እንደሚባለው የመረረ የችግር ህይወቱን እየገፋ ሳለ ዳግም ሌላ ተስፋ የሚሰጥ ነገር አገኘ። አንድ የሙስሊም ድርጅት እነርሱን ለማገዝ በካምፑ ዙሪያ አንዣበበ። በወቅቱ ደግሞ እርሱ ሌሊት መተኛትን አይወድምና እንደተለመደው በጃኬት ራሱን ሸፍኖ በር ላይ ተቀምጦ ነበር። እርዳታ ሰጭዎቹም በቅርብ ስላገኙት ሃላፊያቸው መሆኑን አምነው 24 ድስት፣ 200 ሰሌን ሰጡት። በዚህ በጣም ተናደደ። ምክንያቱ ም ረሃብ እንጂ እቃ አልቸገራቸውም።

ግን «ማን አየበት» አለ መለስ ብሎ በሌላ መልኩ መጠቀም እንደሚችል ሲታሰበው። እናም በቀጥታ 24ቱን ድስትና 100ውን ሰሌን ከጓደኛው ጋር ይዞ ለመሸጥ ወጣ። ሸጦ ሲመለስም ዳቦ ገዝተው እስኪጠግቡ ድረስ በሉና የተረፈውን ገንዘብ በጥንቃቄ አስቀመጡ። 100ውን ሰሌን ደግሞ ለካንፑ ነዋሪዎች አከፋፈሉ። ካምፑ ከከተማው ራቅ ያለ በመሆኑ ያገኟት ገንዘብ ከተማ ታስገባቸዋለችና ተጠቀሙበት። ግን «ዋና ከተማው ለመግባት ገንዘብ ያስፈልግ ስለነበር በጓደኞቼ ላይ ግፍ ሰራሁ። ለመኖር ግን ይህንን ማድረግ ነበረብኝ። ይህ ገንዘብ ባይኖር ኖሮ እሞት ነበር። ያኔ ይህንን ማድረጌ ቢጸጽተኝም አሁን እየመለስኩ ስለሆነ እደሰታለሁ» ይላል።

ሀብታሙ፤ጅቡቲ ከተማ ቢገባም የተለየ ነገር አልገጠመውም።በረንዳ ላይ ማደር እጅግ ስቃይ መሆኑን ይናገራል። አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፈው በቀን ሥራ ሲሆን፤ ያልሞከረው የሥራ አይነት እንዳልነበረም ያነሳል። ይህ ደግሞ ብዙ ገንዘብ እንዲይዝ እንዳስቻለውና በጅቡቲ እስከ 1981ዓ.ም እንዲቆይ እንዳደረገው ይገልጻል። ለመውጣቱ መንስኤው የሆነችውም በአትክልት ተራ በሸክም ሥራ ያወቃት ሱማሊያዊት መሆኑን ያስታውሳል።

በወቅቱ ከሲታ ከመሆኑም በላይ ትርፍራፊ ምግብ የሚመገብና ጎዳና አዳሪ ነበር። ከቦዘኔዎች ጋር ቢያድርና ቢውልም እርሱ ግን ለየት ያለ ባህሪ ያለው፣ ታማኝና ለሰዎችም ታዛዥ ነው። በተለይ በጸባዩ ብዙዎች ይወዱትና ያቀርቡት ነበር። በዚህ ባህሪው ሱማሊያዊቷ የማይረሳ ውለታ ዋለችለት። ከባለቤቷ ጋር ተመካክራ ጣሊያን አገር የሚገባበትን ፓስፖርትና ቪዛ አዘጋጁለት። የሀብታሙ ፍላጎት ከዚያ ስቃይ መላቀቅ ብቻ ሳይሆን ጣሊያን አገር መግባትም ነበር። ስለዚህ ፍላጎቱን ስላሳኩለት እጅግ ተደስቶ ከወራት በኋላ ወደ ጣሊያን ማምራቱን ይናገራል።

ቆይታ በጣሊያን

“መከራ ከአገር አገር ደረጃው ቢለያይም ሁሉም ጋር ይኖራል” የሚለው ሀብታሙ፤ ጣሊያንም እንደጠበቃት እንዳላገኛት ይናገራል። አገራችን ብቻ ናት የሚገባንን ልትሰጠን የምትችለው። ሁሉም አገር ለራሱ ዜጋ እንጂ ለሌላው ምንም አይበጅም፤ ፈግተሽ አገሩን እንድትለውጪለት ይፈልጋል። እኔም በዚሁ መንገድ ከጽዳት ስራ ጀምሬ እብድ እስከ መጠበቅ ያለውን ሰርቻለሁ ይላል።

«የስደተኛ ቪዛ ሳይሆን የሥራ ቪዛ ይሰጠኝ» ብሎ በየዓመቱ የሚታደስ ፓስፖርት ተሰጥቶት መስራት እንደጀመረ የሚናገረው ባለታሪኩ፤ በስደት ህይወቱ በተለያየ የትምህርት መስኮች ከተመረቁና እውቀቱ ካላቸው ሰዎች ጋር በመገናኘቱ ብዙ የተማራቸውና ለህይወቱ መሰረት የሆኑ ነገሮች እንደነበሩ ያነሳል። ለአብነትም ባልተማረበት መስክ እንዲታጭ ያደረገው ይሄ ያገኘው የእውቀት ሽግግር መሆኑን ያስረዳል። “በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሜንታል ሄልዝ“ተምሬያለሁ በማለት በልምድ ብቻ የአዕምሮ ህመምተኛ ጠባቂ ተደርጎ ተቀጥሯል።

በጣሊያን አገር ሳለ «ጆርጆ» እየተባለ የሚጠራው ሀብታሙ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን የበሰለ አዕምሮ ባለቤት መሆናችንን የተገነዘብኩት በአቅምም ሆነ በግዝፈት መጠኑ ከእኔ የበለጠ የአዕምሮ ህመምተኛ ሲሰጠኝና እርሱን ማሸነፍ ስችል ነው ይላል። በተለይ በምክር አገልግሎትና የሚፈልጉትን በማጥናት በኩል ብዙ አቅም እንዳለን በዚህ ሥራ ተምሬያለው። ብዙ አስቸጋሪ ህመምተኞች ከእርሱ ውጪ የሚረዳቸው የለም ተብሎ እስከመጠራት ደርሷል፤ይህም በቀን 100 ዶላር እንዲከፈለው አድርጎታል።

«የአእምሮ ህመም ባለሙያ ነኝ ብሎ ዋሽቶ መግባቱ ትክክል ባይሆንም የምፈልገውን ገንዘብ ካገኘሁና ብዙዎችን ማገዝ እንደምችል ስረዳ አገሬንም ሆነ ራሴን ማዋረድ እንደሌለብኝ አምኜ በቀጥታ ወደ ካናዳ ገባሁ። ይህ ደግሞ ለሙያውም ሆነ ለአገሬ እንዲሁም ለአሰራኝ አካል ክብር ስላለኝ ያደረኩት በመሆኑ አልጸጸትም» ይላል።

የፈተናው መደምደሚያ

አቶ ሀብታሙ ካናዳ ሲገባ ጣሊያን አገር ያጠራቀመውን 30ሺ ዶላር ይዞ እንደነበር ይናገራል። ከዚያ የጽዳት ሥራዎችን ኮንትራት እየወሰደና ፓርኪንግ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ከቤተሰቡ ጋር መኖሩን ቀጠለ። ዋና ወደዚህ ውጥንቅጥ የበዛበት ህይወት ውስጥ የገባው በቤተሰቡ ችግር ምክንያት በመሆኑ ህይወት የተደላደለች እየሆነች በመምጣቷ በችግር ውስጥ የነበረውን ቤተሰብ አንድ በአንድ ማውጣቱን ቀጠለ። አምስቱን ወንድምና እህቶቹን ካናዳና ሌሎች አገሮች በመውሰድ ተምረው ራሳቸውን እንዲችሉ ሲያደርግ እናትና አባቱን ደግሞ ባሉበት የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ አድርጓል።

ካናዳ 16 ሰዓት በሥራ ላይ እንደሚያሳልፍ የሚናገረው አቶ ሀብታሙ፤ለ17 ዓመታት በዚህ ሁኔታ ቆይቷል። የሚፈልገው ደረጃ ላይ መድረሱን ሲያረጋግጥ እውቀትና ገንዘቡን ይዞ በአገሩ ላይ ሰርቶ ለሌሎችም የስራ ዕድል ፈጥሮ በደስታ ለመኖር ወደ አገሩ ገብቷል ማን እንደ አገር ብሎ።

ሥራ በአገር ቤት

አገር ቤት የገባው የተለያዩ ተሽከርካሪ ማሽኖችን ይዞ ነበር። ማሽኖቹን በማከራየት ስራ ጀመረ። ሆኖም ፍላጎቱ አልረካም። ምክንያቱም ገልባጭ፣ ኤክስካቫተር፣ ዶዘር የመሳሰሉት መሳሪያዎች ለብዙዎች የስራ ዕድል አይከፍቱም። እርሱ ደግሞ የአገሩን ልጆች በብዛት ማሰራት ይፈልጋል። እናም ለዚህ ምቹ የሚሆን የሥራ ዘርፍ ሲያማርጥ ሆቴል ላይ ቢሰራ የተሻለ መሆኑን አምኖ ወደ ሥራ ገባ። ወደ ትውልድ ቀዬው አመራና ብቸኛ የሆነውና የአካባቢውን ሰዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ሎጂ በእናቱ ስም « ከቡሽ ኢንተርናሽናል ሎጂ» በማለት ከፈተ።

የመጀመሪያ ሥራውን ጎን ለጎን እየሰራ ዛሬ ከ100 በላይ ሰራተኞችን በስሩ አሰማርቷል። ሎጂውን እያስፋፋ የሄደው አቶ ሀብታሙ፤ባለቤት ቢሆንም ከሰራተኛው እኩል ይሰራል፤ችግራቸውን ተካፍሎ መፍትሄ ይሰጣቸዋል። የሰራተኞቹን ቤተሰቦች ጭምር ያግዛል። ልጆቻቸው በእርሱ ረዳትነት ይማራሉ፤የሚያስፈልጋቸውም ቁሳቁስ ይሟላላቸዋል። ማረፊያ ቤትም በሎጂው ቅጥር ግቢ ውስጥ ተሰርቶላቸዋል።

ሀብታሙ ሌላ የገቢ ምንጭ ለማግኘት በአዲስ አበባ ቤት ሰርቶ አከራይቷል። ድሬዳዋ መግቢያ ላይም ይህንኑ ሥራ ለማስፋት ባህላዊነቱን የተላበሰ ዘመናዊ ሎጂ ጀምሯል። ጥሩ የቱሪስት ማረፊያ ሎጂ ሰርቶ ለብዙዎችም የሥራ እድል እንደሚፈጥር አጫውቶናል። አሁን በጭሮ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሎጂም ቢሆን በዘመናዊ መንገድ እያሰፋው ይገኛል። በተለይም ችግረኞችን መርዳትና የሥራ እድል መፍጠሩ ላይ ይበልጥ እንደሚሰራ ይናገራል።

የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ከባድ ፈተና እንደሆነበት ይናገራል፤የሚጠበቅበትን ግብር ቢከፍልም የማስፋፊያ ሥራ ሊያሰሩት እንዳልቻሉ፤ የገዛውን ቦታ እንኳን ለማስረከብ ዓመታትን በመፍጀቱ ብሩን መልሶ እንደተቀበለና መስራት እንደተቸገረ ይገልጻል። ይሄ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እንዳለበት ይጠቁሟል።

ማህበራዊ ተሳትፎ

«ከሀገር ያሰደደኝ ችግር ነው። ችግርን ያላየ ማንም ሰው የሰው ፊት እንዲገርፈው አይፈልግም። ስለዚህ ቸግሮት የመጣን በገንዘብ ሳይሆን ስራ ሰርቶ እንዲለወጥ ማገዝ እፈልጋለሁ።» የሚለው እንግዳችን፤ልቀጠር ብሎ የመጣን ሰው እንደማይመልስ ይናገራል። አካል ጉዳት ብቻ ችግርን አያሳይም፤በቤት ውስጥ ብዙ የሚደፈኑ ቀዳዳዎች ያሉበት ብዙ ሰው አለ። እናም ለልመና የመጣን ወደ ሥራ እንዲገባ አደርጋለሁ። በዚህ ብዙ ሰራተኞች ዘመድ እንደሆኑት ይገልጻል።

«ያንን ሁሉ ችግር እንድጋፈጥ ያደረገኝ አንድም ሰው ይህችን አብረን እንቋደስ ስላላለኝ ነው። ሌሎችም መሰደድን ምርጫ የሚያደርጉት ገንዘብ ያለን ሰዎች ማካፈልን ስላለመድን በመሆኑ ይህንን ለማድረግ ተነስቻለሁ» ይላል። አሁን ያለው ሀብት ለቀጣይ ህይወቱ አንደላቆ የሚያኖረው መሆኑን ቢያውቅም ለብቻ መኖር መኖር እንዳልሆነ ያምናል። ይልቁኑም ኖርኩ የሚለው ታሪክ ሰሪ መሆን ሲችል ብቻ እንደሆነ ይናገራል።

«ከሰራተኞቼ ጋር አብሬያቸው ስመገብና ስሰራ ውስጤ ይረካል» የሚለው እንግዳችን፤ በግቢው ውስጥ 15 ልጆችን እያስተማረ ይገኛል። በሰራተኝነት ተቀጥረው መማር ለሚፈልጉት ሁሉ በሩ ክፍት ነው። የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያሟላላቸዋል። ይህም ተምረው እንዲመረቁና አሁንም የሚማሩ ሰራተኞች እንዲበራከቱ አድርጓል።

ሎጂው በሚቦርቁ ህጻናት የተሞላው አቶ ሀብታሙ፤ለሚያሳድጋቸው ልጆች የሚጫወቱበት፤ የሚመገቡበትና የሚተኙበት የራሳቸው ክፍል አዘጋጅቷል። ከዚያም አልፎ ለነፍሰጡር ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያቸው እንዳይቋረጥ ያደርጋል። የሚያረግዙት ግን ከትዳር ውጪ ከሆነ አይደግፍም። ምክንያቱም ራሳቸውን መለወጥና መማር አይችሉም የሚል ሀሳብ አለው። “ትዳር ኖሯቸው እኔ ጋር ለመስራት መጥተው ቢያረግዙ እስኪወልዱና መልሰው ወደ ሥራ እስኪገቡ ድረስ ግን የመንከባከብ ግዴታ እንዳለብኝ አምናለሁ። ስለዚህም የሚያስፈልጋቸውን አደርጋለሁ” ይላል።

ሰው በርትቶ ከሰራ የሚያጣው ነገር አይኖርም። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ብዙ እድል አለ። ስለሆነም ሁሉም ሰው እንጀራ አፉ ላይ እንዲደረግለት መጠበቅ የለበትም። ሁልጊዜ ለለውጥ መስራት አለበት። ገንዘብ አገኛለሁ ብሎ ሳይሆን ሥራ ይለውጠኛል ብሎ መስራት ያስፈልጋል። ከገንዘብ ይልቅ ሥራን ወዶ መስራት ለውጤት ያበቃል መልዕክቱ ነው።

ምስክርነት

የወጥ ቤት ሰራተኛ ናት። በሎጂው የገባችው ከስምንት ዓመት በፊት ነበር። በዚህ ቤት ዘላለሟን ብታገለግል እንደማይሰለቻት ትናገራለች። ምክንያቱም ወልዳ ደመወዟ አልተቆረጠም፤ ለልጇም ቢሆን የሚያስፈልገው ነገር ይሟላለታል። እርሷም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ስለሆነች የስራ ሰዓት ከመቀነሱም በላይ ሙሉ ወጪዋ ይሸፈንላታል። «ይህ ደግሞ የእርሱ በጎነት ያመጣው ነውና ዘላለሜን ላገለግለው ቃል እንድገባ አድርጎኛል» ትላለች።

ሥራዋን ትታ ከሄደች በኋላ ተመልሳ በአስተናጋጅነት መቀጠሯን የምትናገረው ሌላዋ ሠራተኛ ደግሞ ስለ አቶ ሀብታሙ እንዲህ ትላለች፡፡ «ለሰዎች ያለው ክብር ስቦኝ ነው የተመለስኩት የምትለው አስተናጋጇ፤ አሁንም ከእርሱ ጎን በመቆም መስራት እፈልጋለሁ። ከእኛ እኩል እየሰራ ሥራን ያለማመደን፤ የሚቸግረንን የሚፈታልን አባታችን፣ ወንድማችንና ቤተሰባችን በመሆኑ ከእርሱ ጋር መራቅን አልመኝም» ስትል በጎነቱን ትናገራለች።

ገና አገርቤት ሲገባ ጀምሮ እንደሚያውቁት የሚናገሩት ደግሞ የግምጃ ቤት ሰራተኛው አቶ ነጋሽ ከበደ ናቸው። እርሱ ሰራተኞቹን ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ሰው ጭምር በችግሮቹ የሚደርስ ሰው መሆኑን ይናገራሉ። በተለይም በከባድ በሽታ የተያዙትን ከማሳከም አኳያ ይኑርልን የሚያስብለውን ስራ እየሰራ ነው። ብዙዎች የተፈወሱት በአካባቢው ላይ ሥራ ያገኙትም በእርሱ ነው። ሀሳባቸውን ሲቋጩም «ስለ እሱ ብናገር ቃላት አይበቁኝም» አሉ።

ትዳርም በከንቱ

ጅቡቲ በስደት ላይ ሳለ ነበር ከመጀመሪያዋ ሚስቱ በፍቅር የተቆራኙት። ከዚያ በትዳር ታሰረና ጣሊያን፣ ካናዳ እያሉ ተሳስበው በመኖር ሁለት ልጆችን አፈሩ። ካናዳ ከገቡ በኋላ ግን መስማማት ስለተቸገሩ ተለያዩ። ከእርሷ ሌላ ለምኔ ብሎ ቆየና አገሩ ከተመለሰ በኋላ ግን የአንድ ልጁን እናት አገባ። ይህም ቢሆን አልበረከተም በፍቺ ተቋጨ። ልጁንም ለብቻው ለማሳደግ ተገደደ። ይሄም ልጅም ጓደኛም አስገኘ። «ሁለቱም ሴቶች የልጆቼ እናቶች ናቸው። ምንም እንኳን ተስማምተን መኖር ቢያቅተንም ልጆቼን ስላበረከቱልኝ አመሰግናቸዋለሁ። » ይላል።

አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011

ጽጌረዳ ጫንያለው