አሉባልታን ከእውነታ የነጠሉ የስኬት ተምሳሌቶች

30

በያዝነው የክረምት ወቅት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ሲሆን ይህም ሀገሪቱ በትምህርት ዘርፉ እያከናወነች ላለው ተግባር ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል። በዓመቱ ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ 152 ሺ 463 ተማሪዎች የሚመረቁ ሲሆን ከግል ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ይመረቃሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

ምሩቃኑ ሚዛናዊና ምክንያታዊ በሆነ አስተሳሰብ በመመራት አገራችንን አሁን ካለችበት ፈታኝ ሁኔታ ለመታደግ የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት ያለባቸው ሲሆን መማር ማለት እውቀት መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የተማረ ሰው በሚያጋጥመው ነገር ላይ ጠለቅ ያለ እይታ ያለውና ለሁሉም ነገር በቂ ምርምር በማድረግ ሚዛናዊና ምክንያታዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ለሀገርና ለወገናቸው መለወጥ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ተብሎም ይታመናል።

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ትምህር ታቸውን በአግባቡ በመከታተል ሀገርና ህዝብ የጣለባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት እና ሳይማሩ ያስተማሯቸውን ወላጆቻቸውን ለማስደሰት ከጥላቻና ብሄር ተኮር ግጭት ርቀው ለውጤት እንዲበቁ ይፈለጋል። አሁን በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች የነገ ተስፋን የሰነቁ ወጣት ተማሪዎችን ህይወት ሲቀጥፉና አካላቸውን ሲያጎድሉ እየተስተዋለ ሲሆን ይህም ለሀገርና ህዝብ ትልቅ ጉዳትም ክስረትም ተደርጎ ይቆጠራል።

ባሳለፍነው ሳምንት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ስነስርአት ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው ወላጆችና ተመራቂ ተማሪዎችም ያጋሩን ይህንኑ ነው። የልጃቸውን ምረቃ ስነስርአት ለመታደም ከአዲስ አበባ የመጡት አቶ ወንድሙ ታሪኩ እንደሚሉት በትምህርት ተቋማት በተማሪዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች አላማና ራዕይ አንግበው ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን ብሎም ሀገራቸውን ለመጥቀም ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የሚሄዱ ተማሪዎችን መንገድ በአጭር የሚያስቀር፣ የወላጅን ተስፋ የሚያከስም እና ሀገርም እንቁ የሆነውን ወጣት የሰው ሀይል እንድታጣ የሚያደርግ ነው።

ሰላም በመኖሩና ልጃቸው ቃልዓብ በትምህርቱ ላይ ብቻ በማተኮር ከግጭቶችና ሁከቶች ራሱን በማራቁ ለዚህ ቀን መብቃቱን የሚናገሩት አቶ ወንድሙ “ወጣቶች ነገሮችን በሰከነ መንፈስ በመከታተል፣ ከአሉባልታና ከውሸት ወሬ ራሳቸውን በማራቅ የሰነቁትን አላማ ከግብ ማድረስ ሲችሉ ቤተሰብ ደስታው እጥፍ ድርብ ይሆናል፤ በተቃራኒው ግን አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ገብተው ህይወታቸውን ሲያጡና አካላቸው ሲጎድል ለቤተሰብም ለሀገርም ትልቅ ጉዳት በመሆኑ ቆም ብሎ ማሰብና መንገድን ማስተካከል ይገባል“ ብለዋል።

ወይዘሮ ፋይቱ እሸቱ ነዋሪነታቸው በአርባምንጭ ከተማ ሲሆን፣ የተመራቂ ዘሀራ ያሲን ወላጅ እናት ናቸው። ወይዘሮ ፋይቱ ልጃቸው በከፍተኛ ማዕረግ በመመረቋ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልፁ እንባ እየተናነቃቸው ነበር። ዘሀራ ከልጅነቷ ጊዜ ጀምሮ ሰላም ወዳድ እና ትሁት እንደሆነች የተናገሩት ወይዘሮ ፋይቱ ከምንም በፊት ሰላም ወሳኝ ነውና ተማሪዎች ለሰላም መከበር ድርሻቸውን እንዲወጡ መክረዋል።

“ደስታም፣ ሀዘንም የሚያምረው ሀገር ሰላም ስትሆን ነው፤ ሰላም ያለው ደግሞ በሁላችንም እጅ ነው” ያሉት እኒህ እናት “ወላጅ ከልጅ ብዙ ነገር ይጠብቃልና ለፍቶ መና ሆነን ልናዝን አይገባንም፤ የወላጅ ትልቁ ስጦታ የልጆች ስኬት ነው” ብለዋል።

ተመራቂዎቹ በበኩላቸው ለዚህ ውጤት ለመብቃታቸው የፈጣሪ፣ የቤተሰቦቻቸው፣ የመምህራንና የእነሱ ጥረት ትልቁን ድርሻ ቢወስድም በዩኒቨርሲቲው የነበረው አንፃራዊ መረጋጋትም አስተዋፅኦ እንደነበረው ገልፀዋል።

በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አልፎ አልፎ ግጭቶች ተከስተው የነበረ ቢሆንም የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርሱ እልባት እንደተገኘና ይህም የሆነው በዩኒቨርሲቲው ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ ጥረት እንደነበር ተመራቂዎች ነግረውናል።

ለዚህም ይመስላል የጋሞ አባቶች በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እርጥብ ሳር ይዘው በመንበርከክ ጉዳት እንዳይደርስ ላደረጉት ሀገራዊ ተምሳሌትነት ሰኔ 29/2011 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው እውቅና የተሰጣቸው።

የዋንጫ ተሸላሚው ቃልዓብ ወንድሙ በአምስት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ቆይታው ሰላምን ከሚያውኩና ግጭትን ከሚቀሰቅሱ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ተቆጥቦ መቆየቱን ገልፆ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ አሉባልታዎችና የሀሰት መረጃዎች አለመታለሉን አጫውቶናል።

“ምንጫቸው እንኳን በውል የማይታወቁ ወሬዎች በሚናፈሱበት በዚህ ወቅት ተማሪዎች ክፉውን ከደጉ ለይተው መራመድ አለባቸው” ያለው ቃልዓብ “አላማን ለሚያስቱና አገርን ለሚያተራምሱ ሀይሎች መጠቀሚያ መሆን የለብንም፤ ለዚህም ነገሮችን በጥሞና ማየትና ቆም ብሎ ማሰላሰል ያስፈልጋል” ሲልም ተናግሯል።

‘’የእኛ ስኬት የቤተሰቦቻችን የደስታ ምንጭ በመሆኑ ለፍተው ለዚህ ደረጃ ያደረሱንን ወላጆቻችንን መካስ ካለብን ራሳችንን ከግጭትና ብሄር ተኮር መቃቃር አርቀን በወንድማማችነትና እህትማማችነት ስሜት በምንወዳት ሀገራችን ለመጨረሻዋ የምረቃ ቀናችን መድረስ ተቀዳሚና ልንደራደርበት የማይገባው ጉዳይ ነውም’’ ብሏል።

በቀጣይ በትምህርቱ የመግፋት አላማ እንዳለው የነገረን ቃልዓብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለዋንጫ ተሸላሚ ተመራቂዎች በገቡት ቃል መሰረት የውጭ ሀገር የትምህርት እድል ተመቻችቶለት ትምህርቱን መቀጠል እንደሚፈልግ ይናገራል።

ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2011 ዓ.ም ሴት ተመራቂዎች መካከል 3.92 በማስመዝገብ አንደኛ የወጣችውና የወርቅ ሀብል ሽልማቱን የወሰደችው የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ተመራቂዋ ዘሀራ ያሲን በበኩሏ አስተዳደጓ በስነምግባር የታነፀ እና በትምህርቷም የደረጃ ተማሪ እንደነበረች አስታውሳ ለዚህ ስኬት መብቃቷ እንዳስደሰታት ትናግራለች።

ዘሀራ የተመጠነ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ልምድ እንዳላት የተናገረች ሲሆን ለአሉባልታና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ቦታ እንደማትሰጥም ትናገራለች። የምትፅፋቸው እና የምትጋራቸው መልዕክቶች ቁምነገር ያዘሉ መሆናቸውን የምትናገረው ዘሀራ ጊዜዋን በማህበራዊ ሚዲያ ሳታባክን ትምህርቷ ላይ ትኩረት በማድረጓ ለዚህ ስኬት መብቃቷን አጫውታናለች።

ሁለቱም የማዕረግ ተመራቂዎች ለዚህ ስኬት ያበቋቸውን ወላጆች፣ መምህራን፣ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብና ጓደኞቻቸውን አመስግነው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ አንድነት እና ሰላም መጠበቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

አዲስ ዘመን ሀምሌ 8/2011

 ድልነሳ ምንውየለት