‹‹ውድ ተመራቂዎች፣ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ከሆንን ኢትዮጵያችን አረንጓዴ መሆን አለባት›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

28

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትናንት 9ሺህ 637 ተማሪዎችን አስመርቋል። በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተገኙ ሲሆን ለሁለት አንጋፋ ሰዎችም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥተዋል። በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

በኑሮ ቀንበር ሳትጎብጡ፣ በውጣውረድ ሳት ደናቀፉ፣ የመጨረሻውን ጣፋጭ ጣዕም ቀምሳችሁና አጣጥማችሁ ለትውልድ መጨረስ እንደሚቻል በተግባር ያስተማራችሁ የእለቱ እንግዶች በድጋሚ እንኳን ደስ ያላችሁ። ደስታችሁ እንዲያድግ፣ ደስታችሁ እንዲተርፍ፣ እንዲሁም ደስታችሁ ለሌሎች ሁሉ እንዲበዛ ያለኝን ታላቅ ምኞት ልገልፅላችሁ እፈልጋለሁ።

ትልቁ የእውቀት መሸመቻ ምዕራፍ ዩኒቨርሲቲ ቢሆንም የሰው ልጅ ሁሌም እንደአዲስ በየዕለቱ ከበላይና ከበታቾቹ እንዲሁም ከተፈጥሮ እንደተማረ የትምህርትን መጨረሻ ሳያይ ይዘልቃል። ነገር ግን በዩኒቨርሲቲ፣ ያውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መመረቅ ያለውን ክብር ከጥቂት ዓመታት በፊት እኔም ቀምሸው ስለማውቀው ከእናንተ ፊት ቆሜ በዚህ የምረቃ ሥነሥርዓት ከእናንተ ፊት ንግግር ለማድረግ በመቻሌና የደስታችሁ ተጋሪ በመሆኔ የተሰማኝን ልዩ ክብር ልገልፅላችሁ እፈልጋለሁ።

ውድ ተመራቂዎች በተለይም ወጣቶች፤ ከፊታችሁ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ይጠብቋችኋል፤ የትዳር ዩኒቨርሲቲ ከፊታችሁ ይጠብቃችኋል። ይህ የትዳር ዩኒቨርሲቲ ኮርሱ በ101 የሚጀምር አይደለም፤ የፈተና ስርዓቱም እዚህ የለመዳችሁት አይደለም። ነገር ግን እሱም መውደቅና መመረቅ አለው። ከትዳር ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ የሥራ ዩኒቨርሲቲ አለ። በሥራ ዓለም ውስጥ ከታላላቆች፣ ከሴቶች ከወንዶች፣ ልምድ ካላቸውና ከሌላቸው ሰዎች ጋር ገብቶ ውሎ የመግባት አዲስ ልምምድ የሚጠይቅ እሱም እንዲሁ መመረቅና መውደቅ በውስጡ ያለ ሌላ ዩኒቨርሲቲ ከፊታችሁ አለ። እንዲሁም የሕይወት ፈተናን ተጋፍጣችሁ በጥሞና በማስተዋል ከአካባቢያችሁ የምትማሩበት የፈተና ሂደቱም በውጤት የሚለካበት ሌላ ዩኒቨርሲቲ ከፊታችሁ አለ።

እስከዛሬ የሚሰጣችሁን ኮርስ የላቀ ውጤት በማምጣት የማንበብ ልማዳችሁ ተቀይሮ ከምትማሩት ትምህርት ውጪ አዳዲስ ጽሁፎች፣ አዳዲስ ሀሳቦች ለማንበብ ለማወቅ የምትለማመዱበት ሌላ ዩኒቨርሲቲ ከፊታችሁ አለ። ሌሎች ያልጠቀስኳቸው በርካታ የሕይወት ልምድና ትምህርት የሚወሰድባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከፊታችን ያሉ ቢሆንም፤ የመመረቂያ ሥነሥርዓቱ ግን ዛሬ ከምናየው የተለየ ነው። የም ትለብሱት ገዋን፣ አቀማመጣችሁ፣ የዲፓርትመንቶች ፉክክር፣ እንዲሁም የላቀ ጥረትና ውጤት ያመጡ ሰዎች የመጨረሻውን የደስታ ጽዋ የሚቀምሱበት ይህ የምረቃ ሥነሥርዓት ከሁሉም የተለየ የሚያደርገው፤ በዩኒቨርሲቲ በመሆኑና በአንድ ጊዜ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሰዎች የሚመረቁበት መሆኑም ጭምር ነው።

ይህ ምርቃት የተለየ የሚያደርገው በዩኒቨርሲቲ መማራችሁ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ማንሳት ጠቃሚ ይሆናል። ዩኒቨርሲቲ ማለት በላቲን ቋንቋ “የተሟላ” ማለት ነው። አንድ ሰው ወደ ሙላት የሚያድግበት ተቋም ማለት ነው። ወደ ሙላት ለማደግ መወዳደር የግድ ነው። ወደ ሙላት ለማደግ ማነጻጸር ይጠይቃል። ወደ ሙላት ለማደግ ማስተያየት፣ ማገናዘብ፣ አመዛዝኖ፣ የጎደለ ለይቶ፣ አክሎ መሙላት ይጠይቃል።

በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አንድ የምትወዱትን ሰው ትምህርት ተምሮ መመረቅ አይቻልም፤ የአንድ ሰው መጽሐፍ አምጥቶ ፕሮጀክት መጻፍ አይቻልም። ነገሮችን በተለያየ ዕይታ ማየትና ማገላበጥ፣ መሞገት፣ ማመዛዘንና የላቀውንና የተሻለውን አስበልጦ መውሰድ ይጠይቃል። ለዚህ ነው ወደሙላት የሚታደግበት የተሟላ ተቋም ያሉት-የያኔው የላቲን ምሑራን።

እንዲሁም “ግራጁዬሽን” ማለት በመካከለኛው የሥራ ዘመን ቋንቋ የተለመደ መሆኑና ስርወ ቃሉ ከየት እንደመጣ እየተዘነጋ ያለ ቢሆንም፤ “ግራጁዬት” ማድረግ ወይም “ግራጁዬሽን” ማለት ወደላይ መውጣት ማለት ነው። መላቅ ማለት ነው፤ መሻል ማለት ነው። ከነበረው ዩኒቨርሲቲ ከናንተ ጋር ከገባው ሁሉ ልቃችሁ ተሽላችሁ መመረቃችሁን በኩራት ልትቀበሉ ይገባል። ነገር ግን የአማርኛው “ግራጅዌሽን” ከላቲኑ ወይም ከመካከለኛው አውሮፓ ከሚጠቀሙበት “ግራጅዌሽን” በእጅጉ የላቀ ነው። ለጭንቅላት ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ለውስጥ ማንነትም ትምህርት አለው። መመረቅ ማለት መባረክ ማለት ነው። መመረቅ ማለት ባዩት፣ በቀመሱት ሰዎች ታምኖብህ ተሸልመሀል እና ይፅደቅልህ ማለት ነው። ይሄንን ምርቃት ለማግኘት ገፊ ኃይል ሆኖ እንድንማር ያደረገንን ነገር በተወሰነ ደረጃ ማንሳት እፈልጋለሁ።

አንድ ሰው ለማወቅ ለዘመናት ወደ ተቋም ገብቶ አዳዲስ እውቀት ሲገበይ ዋናው ለመማር ገፊ ኃይል የነበረው ምንድነው የሚለውን ማወቅ የግድ ያስፈልጋል። ሰዎች ለመማርና ለማወቅ ለዘመናት የሚያደርጉትን ጥረት የተለያየ ምሁራን በተለያየ መንገድ ገልፀውታል። ሁሉም ምሁራን ለመማር የሚደረገውን ጥረት ተመሳሳይ የሆነ ትርጓሜና ስያሜ አልሰጡትም። ለምሳሌ ፍሬድሪክ ኒቼን ብንወስድ ሰው ለመማር ለመጣር የሚያደርገው ገፊ ኃይል ለመግዛት መሻት ነው ይለዋል። ሌላውን ለመግዛት ሌላውን ለማሸነፍ ከሌላው ለመላቅ ነው ሰው የማያቋርጥ መማር የሚፈልገው ብሎ ያስባል። ኮፊያማ ደግሞ ይህን የግለሰቦች ቡድን ሲወስደው “ሜጋ ጎፎሚያ” ይለዋል። በበላይነት በገዥነት የመኖር መሻት ነው ለመማር ገፊ ኃይል የሚሆነው ይላል። ነገር ግን የሰው ልጅ ዘላለማዊ አይደለም፤ ለዘላለም አይኖርም፤ ለዘላለምም መግዛት አይችልም። በመሆኑም የሁሉም ሰው ፍላጎት መግዛት ነው የሚለውን ትርጓሜ ትክክል አይደለም ብለው የሚሞግቱ ሌሎች ምሁራን አሉ። ከነዚህ መካከል ጀርሚ ሜርካም ተጠቃሽ ነው። ጀርሚ ሰው ለመማር ገፊ ኃይሉ የሀብት ጥማት ነው ይላል። የመግዛት ፍላጎት ሳይሆን የሀብት ፍላጎት ነው የሚል እምነት አለው። የራስን ገፅታ ለመሸፈን ሰው መማር እንደሚፈልግ የሚገልፀው – ጀርሚ ። የሰው ልጅ ደስታውን ለማግኘት የማይከፍለው ነገር አይኖርምም ይላል።

የራስን ደስታ ለመሸመት ሰው መማርን እንደ ሚፈልግ የሚገልጸው ጀርሚ የሰው ልጅ ደስታውን ለማግኘት የማይከፍለው ዋጋ የለውም ይለዋል። ለመደሰት ይሰርቃል። ለመደሰት ይገላል። ለመደሰት ይቀማል። ደስታውን ለማግኘት ማንኛውንም ዋጋ ይከፍላል። ይሄ የወንጀል ድርጊት መሰረቱ ምን እንደሆነ ለማጥናት የሚሰሩ ምሁራን እንደሚገልጹት ወንጀለኛው ወንጀል በመስራት ከሚያገኘው ደስታ ይልቅ ቅጣቱን በማክበድ የቅጣቱን ሕመም የቅጣቱን ጣሪያ ማግዘፍ ወንጀልን ለመቀነስ ፋይዳ እንዳለው ይገልጻሉ። ወንጀልን የምንቀንስበት የቅጣቱ ሕመም ጠንክር ያለ ካልሆነ ሰው ደስታውን ለማግኘት ሲል የማያደርገው ነገር እንደሌለ የጀርሚን እሳቤ በመደገፍ ሀሳብ ይሰነዝራሉ። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ይህን ይቃወማሉ። የተለየ ሀሳብ ያራምዳሉ።

ቻርልስ ዳርዊን ሰው ለመኖር ሰው እያበላ አሊያም እየበላ የራሱን መኖር ብቻ ለማረጋገጥ የሚጥር ነው ይለዋል። ለሰርቫይቫል ሲባል መብላት ለሰርቫይቫል ሲባል ማባላት እስከ መቼ? ሰው ዘለአለማዊ ሕይወት እንደሌለው እያወቀ ለመብላት የሚያባላ- ለመብላት የሚበላ ከሆነ በዘላቂነት ሰርቫይቫልን እውን ማድረግ ስለማይቻል ይህም ትክክል አይደለም ብሎ የሚሞግተው ቲሶር የተሰኘው ምሁር‹‹ ሰው ለመማር የሚገፋው ዋናው ኃይል ትርጉም ላለው ነገር ለመኖር ሲል ነው›› ብሎ ይተረጉመዋል። ይህ ትርጉም ያለው የመኖር ዘዬ ማለት መስጠት ነው። ማፍቀር ነው ። መውደድ ነው። ማገልገል ነው። ሰዎች በመንፈስ የሚያገኙትን ደስታ በመግዛት ሊያገኙት አይችሉም። የመጨረሻው የደስታ ምንጭ ከራስ አልፎ ለወገን ማድረግ መቻል በመሆኑ የዚህ ሰው እሳቤ ለእኛ ጠቃሚ ቢሆንም መልካምነትን ደግነትን ፍቅርን በምን መለካት ይቻላል ?

አንድ ሰው አንድ ኪሎ ስኳር መግዛት ቢፈልግ ሌላ አንድ ኪሎ ክብደት ያለው መዳብ ብረት ነሀስ ወይም ድንጋይ በአንድ ጎን አስቀምጦ በሌላ ወገን ስኳሩን እያስቀመጠ አንድ ኪሎ መሆኑን መለካት ይችላል። አንድ ኪሎ ስኳር ለመለካት አንድ ኪሎ ክብደት ያለው ሌላ ነገር ከሌለው አቅጣጫ ይፈልጋል። ወይንም አንድ ሊትር ውሃ ዘይት ለመለካት የፈለገ እንደሆነ ያንን መለካት የሚያስችል እቃ መያዝ ይኖርበታል።መልካምነትን ደግነትን ፍቅርን መስጠትን በምን መለኪያ ልንለካው እንችላለን ? መልካምነትንና ደግነትን የሚሰጡ ሰዎች በአብዛኛው ወገን የሰጣችሁት ካልተለካ ችግሩ እናንተጋ አይደለም። ሰውየው ጋ መለኪያው የለም ማለት ነው። መሰላቸት ተስፋ መቁረጥ ማኩረፍ ሳይሆን የመልካምነት መመዘኛን መጎናጸፍ እንድትችሉ አበክራችሁ መስ ራት ይኖርባችኋል። መልካምነት ያላችሁ ሰዎች መልካምነት በሚዛን የማይለካ ስለሆነ ሁሌ ለመስጠት ሁሌ ለማፍቀር ሁሌ ለመተግበር ብቻ እውን እንዲሆን ብዙ ጊዜ ካለፋችሁ በኋላ የሚነገር መሆኑን አውቃችሁ ዛሬም ነገም መልካም መሆንን በተለይ በዚህች ድንቅ ሀገር መልካም መሆንን መውደድ ይኖርባችኋል።

መጥረቢያው ብቻውን ዛፍ እንዲመታ የሚሰበር ቁመቱ አጭር ውፍረቱም መካከለኛ የሆነ ዛቢያ ያስፈልገዋል። ከዛቢያ የተዋደደ መጥረቢያ ትልልቅ ዛፍ መቁረጥ ይችላል። እናንተ የተማራችሁ፣ ያወቃችሁ ራሳችሁን አሸንፋችሁ የተሰጣችሁን ፈተና ያለፋችሁ ድንቅ ምሩቃን፣ ካልተማረው ሕዝብ ጋር ካልተዋደዳችሁ በስተቀር ፍላጎታችሁን ማሳካት አትችሉም። የእናንተ መጠረብ፣ የእናንተ መዘጋጀት ብቻውን ምንም የሚመስለውን ዛቢያ መርጦ መዋደድ ይሻልና በየሄዳችሁበት ባይማርም ካስተማራችሁ፤ ባይኖረውም ቆርሶ ከሰጣችሁ ማኅበረሰብ ጋር ተዋዳችሁ ኢትዮጵያን ማስቀጠል የሁላችሁም የነገ ተልዕኮ እንደሆነ በዚሁ አጋጣሚ ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ።

በቅርቡ አራት ቢሊዮን ዛፍ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጥረት ለመትከል ሥራ ጀምረን ነበር፡፡ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ስንወስን የተሳለው የተጠረበው መጥረቢያ ዛቢያው ከሌለ ብቻውን እንደማያሳካው ስለሚያውቅ ይህንን ቅዱስ ሃሳብ ለመላው ሕዝብ በቀረበው ጥያቄ መሰረት እስከዛሬ ድረስ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን በላይ ዛፍ ተክለናል፡፡

ኃያል ከሚባሉ የአውሮፓ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መካከል አንዱ ከትናንት ወዲያ ደውሎልኝ ‹‹በእኔ አገር አራት ቢሊዮን ዛፍ የለም፡፡ አንተ በአንድ ክረምት አራት ቢሊዮን ዛፍ እተክላለሁ ብለህ ማሰብህ ትልቅ ነገር እንደምታስብ ያሳያልና ምን ላድርግልህ›› ብሎኝ ‹‹ፕሮግራሙን ለማስፈፀም አንዳንድ ነገር ያስፈልጋል›› ብየው 130 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ ሰጠን፡፡

ትልቅ ሃሳብ ትልቅ ሆኖ ትልልቆቹን የሚያሳምነው ሲተገበር ነው፡፡ አራት ቢሊዮን ብለን አራት ቢሊዮን ማድረግ የምንችል ሕዝቦች መሆናችንን ትላልቅ ማሰብ ትላልቅ መከወን የምንችል መሆናችንን ለዓለም ስናሳይ ድህነትንም እንደዚሁ አሸንፈን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ መሆናችንን ዳግም እናረጋግጣለን፡፡

ውድ ተመራቂዎች፣ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ከሆንን ኢትዮጵያችን አረንጓዴ መሆን አለባት፡፡ ስንሞት ኢትዮጵያ ከሆንን ቢያንስ መቃብራችን በዛፍ ጥላ ስር መሆን አለበት፡፡ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ከሆንን ቢያንስ ልጆቻችን ድህነትን ዳግም የማያስተናግዱ፤ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ወጥቶ ‹‹በጀት አንሶኛል›› የሚልበት ዘመን ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ይህ እንዲሆን የተሳላችሁ፣ የተጠረባችሁ የተዘጋጃችሁ ምሁራን ዛቢያውን ሳትዘነጉ ከዛቢያው ጋር ተዋዳችሁ ካልተማረው፣ ካልተዘጋጀው፣ ብዙዎች ከሚንቁት ግን ታሪክ ከሚሰራው የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነን ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከማንም በላይ ከእናንተ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ላይ በዚህ ክረምት 448 ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ሥራ ተጀምሯል፡፡ ይህንን ሥራ በመንግሥት በጀት ቢሆን ኖሮ አምስት ዓመት አሥር ዓመት ይፈጅብን ነበር፡፡ ምክንያቱም የጨረታ ሕግ ስላለ፤ ምክንያቱም የበጀት ስርዓቱ ውስንነት ስላለበት፡፡ ነገር ግን ብዙ ባለሀብቶችና የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ወጣቶች ተባብረው 448 ት/ቤቶች ክረምቱን አድሰን፣ ብላክ ቦርድ ቀይረን፣ ወንበር ጠግነን፣ አጥር ጠግነን፣ ዛፍ ተክለን በንፅፅር ሻል ያለ ት/ቤት ለልጆቻችን ለማዘጋጀት የምናደርገው ጥረት ሌሎች ትልልቅ ጉዳዮችን ከተባበርን ማሳካት እንደምንችል ምስክር መሆን ይችላል፡፡ በዚህ ክረምት በመንግሥት ት/ቤት ለሚማሩ 600ሺ ታዳጊዎች ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ደብተር በዚሁ መንገድ እያዘጋጀንላቸው ሲሆን ተማሪዎች መስከረም ላይ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ለእያንዳንዳቸው ደብተር ሰጥተን ለ600ሺ ተማሪ ዩኒፎርም አሰፍተን፣ ትምህርት ቤት አድሰን፣ አምና ጥለውት የሄዱትን አስውበን ብናስገባቸው ከ600ሺው 60ሺው ቢሳካልን፤ከ60ሺው ስድስት ሺ ቢሳካልን፤ ከስድስት ሺው 600 ቢሳካልን፤ከዚያም 60 ቢሳካልን ቢያንስ ቢያንስ ስድስት ቢሳካልን ስድስቱ ለኢትዮጵያ ብርሃን መሆን ይችላሉ፡፡ በዛሬው እለት እያንዳንዱ ኢንቨስትመንት የራሱን አባዝቶ ሀብት ላተረፉ ጉልበት ላተረፉ መልስ መሆኑ ስለማይቀር የምንሰራው እያንዳንዱ ሥራ ቢጠናቀቅ ሄዶ ሄዶ ኢትዮጵያን ከለማኝነት የሚያወጣ መሆኑን መገንዘብና መርዳት ከሁላችን ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪ በከተማ ውስጥ የሚገኙ ከአስር በላይ የመንግሥት ሆስፒታሎች በእድሳት ላይ ይገኛሉ። ብዙ ማህበረሰብ ለህክምና ሄዶ የሚቸገርባቸውን የህክምና ጣቢያዎች በማደስ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ በመንግሥትም ቢሆን አሁንም አድካሚና በረጅም ጊዜ የማይከወን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከአንድ ሺ በላይ አቅመ ደካማ እናቶችና አባቶች የሚኖሩበትን ቤት አድሰን ክረምቱን ዝናብ መጣ ብለው ሳይሳቀቁ፤ ዝናብ ሳይሆን የልጆቻቸው ጉልበትና ሀብት ደስታ የሚሰጥ መሆኑን አምነው ለናንተም ተጨማሪ ምርቃት የሚመርቁ እናቶችን ለማስደሰት በተጀመረው ሥራ ከ450 ቤት በላይ እድሳት ተጀምሯል ፡፡ አንድ ሺውም በክረምት ይጠናቀቃል።

ውድ ተመራቂዎች አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ችግር ይነገራል፡፡ ነጋ ጠባ መርዶ አለ፡፡ የሚያስፈራ ነገር አለ። ዛሬ የተመረቁ 9ሺህ637 ተማሪዎች በእኔነት ከወሰናችሁ እና በልባችሁ አምናችሁ ካረጋገጣችሁ በእርግጠኝነት የምገልጽላችሁ ኢትዮጵያ አንድ ሆና ወደ ብርሃን የምትሻገርበት እንጂ ወደ ኋላ የምንልበት ነገር አይኖርም። ይሄ ውሳኔ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ይሆናል። ኢትዮጵያን ማፍረስ፤ ኢትዮጵያን ማሳዘን፤ ኢትዮጵያን መዝረፍ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም። ኢትዮጵያን ቆፍራችሁ ብትጠይቋት ትነግራችኋለች። በዘመናት መካከል ብዙዎች ሞክረዋል፤ ሰዎች ገለዋል፤ ኢትዮጵያን ማፍረስ ግን አይቻልም ።

ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን ውድና መከታ እንድንሆን ዛሬ በዚህ ታላቅ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምረቃ ወቅት ቀላሉን ሳይሆን ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ ግድ ነው። ትርጉም መስጠት ለሚችሉ ነገሮች መኖር ስትችሉ ስትመራመሩ ስትጠይቁ የመኖር ትርጉሙ ሲገባችሁ የምላችሁን ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን።

በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከኬንያ ይበልጣል በአስር ቢሊዮን ገደማ የኢትዮጵያ ጂዲፒ ከኬንያ ይበልጣል ። ነገር ግን የኬንያ የዓመት በጀት ከኢትዮጵያ በጀት በእጥፍ ይበልጣል። እኛ 13 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በጀት ስንይዝ ኬንያ 27 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በጀት ይዘዋል። ከጂዲፒያቸው ከአንድ ሶስተኛ የሚበልጠውን የመንግሥት ወጪ አድርገው ይዘውታል። ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት ኢትዮጵያውያን በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ጉልበቱን ጊዜውን አልፎ አልፎም ምላሱን የሚጠቀም ዳያስፖራ በብዛት አለ።

በተንደላቀቀው ቪላ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ብዙ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ብዙዎቹ ለፍተው ጥረው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያግዙ መሆናቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ በዓመት እያንዳንዱ ዳያስፖራ አምስት ሺ፤ በስድስት ወር ሁለት ሺ አምስት መቶ፤ በሶስት ወር ሰባት መቶ ብር ( ሂሳቡን ለእናንተ ትቼ) ማዋጣትና የጋራ ኩባንያ መፍጠር ቢችል አምስት ሺ ዶላር አንድ ሰው ካወጣ አንድ ሚሊዮኑ አምስት ቢሊዮኑ፤ ሁለት ሚሊዮኑ አስር ቢሊዮን ዶላር በዓመት ማምጣት ይችላሉ ማለት ነው። ይህ ስጦታ አይደለም ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በየዓመቱ 10 ቢሊዮን ዶላር ዲያስፖራ ወደእኛ ቢልክ በየዓመቱ ምን ያክል ዕድገት እንደምናመጣና በአጭር ጊዜ ከአፍሪካ ትላልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንደምንመደብ ሂሳቡን ኢኮኖሚስቶች ከእኔ የተሻለ ማስላት ይችላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ጉልበታችንን ፣እውቀታችንን፣ ጊዜያችንን ሳንሰጥ የምንመኛትን ኢትዮጵያ መፍጠር አንችልም፡፡ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የወሰነ በየትኛውም ስፍራ ያለ ዜጋ ገንዘቡን ዱባይ ከሚያስቀምጥ ፣ ገንዘቡን ለንደን ከሚያስቀምጥ ፣ ገንዘቡን ቻይና ከሚያስቀምጥ እነርሱ የእኛን ተቀማጭ ገንዘብ መልሰው ኢንቨስት ከሚያደርጉ ኢትዮጵያዉያን በተባበረ መንገድ በህጋዊና ስርዓት ባለው መንገድ ኢንቨስት ብናደርግ ባጠረ ጊዜ ኢኮኖሚያችንን ማስቻልና ተመርቀው ሥራ የሚያጡ ልጆቻችንን ሥራ ለማስያዝ ሰፊ ዕድል ይሰጠናል፡፡ ነገር ግን የዛሬ ሰባ አምስት ዓመት ገደማ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንጉሰ ነገስቱ ቤት ሥራ ሲጀምር የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በሁለት በሬና በሞፈር ያርሱ ነበር፡፡ ዛሬም ከሰባ አምስት ዓመት በኋላ አባትና እናቱን ከሞፈርና ቀንበር መገላገል ያልቻለ ትውልድ ቢማርም ባይማርም ምን ትርጉም አለው? ሌላ ሰባ አምስት ዓመት እንዳንቆይ ንስር ሆኖ የተፈጠረ አሞራ ጅግራ ሆኖ መሞት ስለሌለበት የተማረ ኢትዮጵያዊ እንዲሁ በከንቱ መጥቶ በከንቱ ዲግሪ ቆጥሮ መመለስ ስለሌለበት በተባበረ ክንድ አርሶ አደሩን ከሞፈር፣ ከቀንበር፣ ከበሬ ተላቆ በዘመነ መንገድ አርሶ በልቶ የሚያበላን እንዲሆንና ለማኝነት ከኢትዮጵያ እንዲወገድ በተባበረ ክንድና “በዩኒቨርሳል ቫሊዩ/እሴት/” በጋራ እንድንሰራ በታላቅ ትህትና ጥሪዬን ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ፡፡

ከእናንተ የሚፈለገው ነገር ሰርቶ ገቢ ማግኘት ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ የተማራችሁትን ዩኒቨርሳል እሴት የማህበረሰቡ እሴት ማድረግ ነው፡፡ ዩኒቨርሳል እሴት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በስፋት መኖር ያለበት መሆኑ ይታመናል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ እሴቶቻችሁ አንደኛው ክብር ነው፣ የሁሉንም አበርክቶ የሁሉንም በዕውቀት የሁሉንም ችሎታ ማክበርና በጸጋ መቀበል አንድ ዩኒቨርሳል እሴት ተብሎ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ሁሉንም ማክበር ማለት ከመሳደብ መቆጠብ ማለት ነው፡፡ ሁሉንም ማክበር ማለት ሌላው ወገን ጋር እሴት እንዳለ ማመን ማለት ነው፡፡ ይህን ማስተማር ከእናንተ ይጠበቃል፡፡

ሁለተኛው ልህቀት ነው፡፡ በምንሰራው ሥራ በጥናት በምርምር በመድከም የተሻለ ነገር ማምጣት መቻል ነው፡፡ ይህንን ከእናንተ አሳልፋችሁ ማህበረሰቡን ማስተማር ይጠበቅባችኋል፡፡ ሶስተኛው እሴት ትህትና ነው፡፡ ሰዎች ትህትናን መላበስ አለባቸው፡፡ ሰው ትሁት ሆኖ ደካሞችን ማክበርና ማገልገል ቢችል ማዘንና ማሰብ ቢችል ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም ፡፡ ሚዛኑ ተመልሶ እራሱ በጎነት ስለሆነ በጎነትን በኪሎ፣ በጎነትን በሜትር፤ በጎነትን በሊትር ሳንለካ ሁሌም በመስጠትና ትሁት በመሆን ማህበረሰባችንን መስጠትና ማስተማር ከእናንተ ይጠበቃል፡፡ አራተኛው ዩኒቨርሳል ቫሊው አገልግሎት ነው፡፡ ዛሬ ከ9 ሺ በላይ ምሩቃን ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ቢያንስ 100 ሺ ችግኝ እንጠብቃለን፡፡ ቤት ስትገቡ በእናንተ ግቢ ውስጥ ፣ በእናንተ ሰፈር ወይም በእናንተው ትምህርት ቤት ውስጥ አምስት አምስት፣ አስር አስር ችግኝ ብትተክሉ ትልቅ የማገልገል ልምምድ ዛሬ መጀመራችሁ ለነገውም ፈር ቀዳጅ ስለሚሆን እንደ አንድ ማስተማሪያ መንገድ ሀገርና ህዝብን በማገልገል ለትውልድ እራሳችሁን በመስጠት እንደማሳያ ተጠቀሙበት፡፡

አምስተኛው እንግዳ መቀበል ነው፡፡ በርካታ ቱሪስቶች ኢንቨስተሮች እየጋበዝን ነው፡፡ ኢንቨስተርና ቱሪስት መቀበሉ ቆይቶ፣ ኦሮሞዎች ሳይቸገሩ በባህር ዳር፣ አማራዎች ሳይቸገሩ በመቀሌ፣ ትግራዮች ሳይቸገሩ በቦረና በጉጂ፣ ሲዳማዎች ሳይቸገሩ በሶዶ፣ ጉራጌዎች ሳይቸገሩ በወራቤ የሚንቀሳቀሱባትን ኢትዮጵያ እንፍጠር፡፡ ኢትዮጵያ ለ100 ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን በቂ ናት፡፡ ኢትዮጵያን 100 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን ከተባበርንና ከተደመርን አንቀባራ ማኖር ትችላለች፡፡ ንፉግነት ኖሮ አንተ የኔ አይደለህም የሚል ሀሳብ ግን ኢትዮጵያን ትንሽ ስለሚያደርግና ኢትዮጵያ ካነሰች ለዛሬ ኢትዮጵያውያን የነገ ኢትዮጵያ ስለምታንሱ ለራሳችሁ ክብር ብላችሁ የኢትዮጵያን ክብር ለመጠበቅ ሁላችሁም መጓዝ ይኖርባችኋል፡፡

ስድተኛው ጽናት ነው፡፡በዚህ መከራ፣ በዚህ ችግር፣ በዚህ ክፉ ጊዜ ጽናት ያስፈልጋል፡፡እናንተ እድለኞች ናችሁ፡፡ ከብዙ ሚሊዮን መመረጥ ችላችኋል፡፡ ሳይመረቁ ሳይማሩ ያለፉ ብዙ አሉ፡፡ ለኢትዮጵያ በጽናት መታገልና ብርሃን ለማምጣት መስዋእት መሆንም ቢሆን ክቡር መሆኑን አውቃችሁ በጽናት ለኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና እንድትሰሩ በከፍተኛ ትህትና ልጠይቃችሁ እፈልጋለሁ፡፡

ሰባተኛው መጠን ነው፡፡ በዚህ መልኩ ዛሬ 2ሺ ሴት ተማሪዎች ባይመረቁ፣ አካል ጉዳተኞች ባይመረቁ ወንዶች እድሜያቸው ከ25 እስከ 30 ብቻ ቢሆን ምን ያህል ጎዶሎ እንደሆነ አስቡት፡፡ ሴቶች ፣ አካል ጉዳተኞች የ80ውም ብሄር ብሄረሰቦች ተቀላቅሎ መመረቅ ከዚያም አልፎ ከጎረቤት አገራት አገራችንን እናተን አምነውና ወደው ከእናንተ ጋር ተምረው የተመረቁ መኖራቸውን ማየት እጅግ በጣም የሚያኮራ መሆኑን አውቃችሁ ለህብረትና ለመሰባሰብ ልባችሁን ክፍት አድርጉ፡፡

ዶክተር ሀይሌ ፊዳ በፈረንሳይ በነበረው ቆይታ ከፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ጋር በጋራ ይማሩ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የመጀመሪያ ጥያቄው አፍሪካ ያጣችውን እንቁ ሰዎችን ያስባል፡፡ ዛሬ ከእናንተ ጋር የተማሩት ነገ ቻይና፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ ሄደው የሚመሩ ሰዎች መድረሻቸው አይታወቅም፡፡ የናንተም እንዲሁ፡፡ ከእናንተ ውስጥ ሳይንቲስቶች አሉ፤ የአገር መሪዎች አሉ፤ ከእናንተ ውስጥ ችግር የሚፈቱ ትላልቅ ጭንቅላቶች አሉ፡፡ ሌላውን ሰው ስታገኙት እናንተ ሳይንቲፊክ ሆናችሁ እርሱ የአገር መሪ እንደሆነ አስባችሁ አክብራችሁ ተቀበሉት፡፡

የመጨረሻውና ስምንተኛው ትምህርት ለህይወት ነው፡፡ ትምህርት መነሻ እንጂ መድረሻ የለውም፡፡ ትምህርት አያበቃም፡፡ ሁሌ ተማሪ መሆን ሁሌ ለመማር መዘጋጀት ከተፈጥሮ መማር እንዳለብን አስበን መዘጋጀት ይጠበቃል፡፡ ዛሬ ከየቤታችሁ ስትመጡ የሆነ አርሶ አደር መሬቱን ለቅቆ የሆነ አርክቴክት ዲዛይን አድርጎ የሆነ ሲቪል ኢንጂነር አስፓልቱን ገንብቶት የሆነ ኢኖቬተር መኪናውን ሰርቶ ይታያል፡፡ በብዙ ሰዎች መሰረት ላይ እንደተገነባችሁ አስባችሁ እናንተም ለትውልድ አዲስ መሠረት ለመጣል መነሳትና መዘጋጀት ይኖርባችኋል፡፡ ብቻውን ያለቀ ነገር የለም በአንደኛው መሠረት ላይ ሌላ መሠረት እየጣልን ትውልድ በቅብብሎሽ የሚቀጥልበት አገር እንድትሆን አዲስ መሰረት አዲስ ማንነት በመገንባት ከልብ እንድትነሱና ያንን ማድረግ እንድትችሉም ምኞቴን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ፡፡

ውድ ተመራቂዎች በአንድ መርከብ የተሳፈሩ ሰዎች በተለያየ ክፍል ቢቀመጡ ያቺ መርከብ በአንድ አቅጣጫ መቅዘፏን ማረጋገጥ አለባቸው ።ግማሹ ከላይ ግማሹ ከታች ፣ ግማሹ ከፊት ግማሹ ከኋላ ከተቀመጠ በተለያየ አቅጣጫ ቢቀጠል መርከቧ መድረስ የሚገባት ቦታ አትደርስም ። እያንዳንዳችን የጋራ ታሪክ መፍጠር ካልቻልን ምሁራን፣ተነጋግራችሁ፣ ተወያይታችሁ ፣ የማያስፈልገውን ትታችሁ፣ የሚያስፈልገውን የሚጠቅመንን የጋራ ታሪክ ማውጣት ትችላላችሁ። የሚጠቅመንን የጋራ ራዕይ ማስቀመጥ ትችላላችሁ ። ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መዳረሻ ብልጽግና መሆኑን አምነን በአንድ አቅጣጫ መጓዝ ካልቻልን ያኮረፈ ሁሉ ወደ ቀበሌ ካለ፤ ኢትዮጵያ ትንሽ ትሆናለች። ይሄ እንዳይሆን መብራቱ ጨለማውን ገፎ መንገድ ማሳየት ሲገባው ራሱ ብርሃኑ በጨለማ ተውጦ ብርሃን ማሳየት ከተሳነው ጉዞው ይደናቀፋል።

የተማረው፣ ያወቀው፣ መንገድ ማሳየት የሚገባው ተምሬያለሁ አውቄያለሁ ብሎ መንገድ የሚያጠፋና የሚያደናብር እንዳይሆን ማስተዋል፣ መነጋገር፣መደማመጥ እና ለሁሉም ህዝቦች የሚመቸውን መንገድ መፍጠር ከእናንተ የሚጠበቅ ይሆናል።

የዛሬ ምሩቃን ውለታ አለባችሁ። የመጀመሪያው ውለታ ሳይማሩ፣ ጠግበው ሳይበሉ መቀነታቸውን ፈተው ያስተማሩ ወላጅ ቤተሰቦች ናቸው። ወላጆቻችሁ ከእናንተ የሚፈልጉት የመጀመሪያው ነገር የእናንተን ስኬት ማየት ነው። ከስኬታችሁ በኋላ እንደ ኢትዮጵያ ባህል እነሱን መጦር ፣ እንዳስተማሩዋችሁ የመጨረሻ ጊዜያቸውን በደስታ እንዲያሳልፉ ማድረግ ከእናንተ ይጠበቃል። ወላጆቹን የዘነጋ ሀገሩን ማስታወስ አይችልም።

ሁለተኛው ውለተኛው መምህራኖቻችሁ ናቸው። መምህራኖቻችሁ በትምህርት ስፍራችሁ በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ያስተማሩዋችሁ ሰዎች እናንተ ዛሬ የምታገኙትን ዲግሪ እና ከዛም በላይ ያለውን ያላገኘ ህዝብ አለ ።እነሱ ቀልጠው እናንተን አሻግረዋችኋል። ዛሬ ከዩኒቨርሲቲ የተማሩ ሰዎችም እናንተ ከምትደርሱበት ለመድረስ ብዙ ይቸገራሉ። የእነሱ ጊዜ እያለቀ የእናንተ ጊዜ እየጀመረ ስለሆነ ባለፋችሁበት መንገድ ሁሉ ወደኋላ መለስ ብላችሁ ረግጣችሁ ያለፋችሁትን ድልድይ ማስታወስና ማመስገን ያስፈልጋል ። ለምሳሌ በክረምት የገጠር ልጆች በአካባቢያችሁ ያሉትን ተማሪዎች አስተባብራችሁ ብታስተምሩ፣ ችግኝ ብትተክሉ፣ በጥገና ሥራው ብትሳተፉ ለመምህራኖቻችሁ ውለታ እንደዋላችሁ ይቆጠራል ።

ሶስተኛው የቀደምቶቻችሁ ውለታ ነው። ለእኛ መሰረት የጣሉ፣ ያቆዩ ሀገር ማስቀጠልና ለትውልድ ማስተላለፍ ከእናንት ይጠበቃል። በማንኛውም ጉዳይ ተነጋገሩ፣ በማንኛውም ጉዳይ ተወያዩ፣ተመካከሩ ነገር ግን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት ጉዳይ ለአፍታም ቢሆን ለድርድር አታቅርቡ።

በመጨረሻም የሀገር ውለታ አለባችሁ። እናንተን ለማስተማር ኢትዮጵያ ትልቁን በጀት ያስቀመጠችው ለትምህርት ነው። ይሄንን ሁሉ ሀብት የምታፈሰው ተምረው ድህነትን፣ ችግርን፣ ረሀብን፣ እርዛትንና አለመደማመጥን አለመሰልጠንን አስቀርተው ስልጡን ኢትዮጵያን ይፈጥሩልኛል የሚል እምነት ስላላት ነው።እስካሁን ላስተማረች ኢንቨስት ላደረገች አገር በመስራት ውለታዋን እንድትከፍሉ በዚህ አጋጣሚ በትህትና ልጠይቃችሁ እፈልጋለሁ።

ሀገር በፈተና ወቅት፣ በመከራ ጊዜ በስቃይ ጊዜ ችግሯን የሚያበዛና ስቃይዋን የሚያገዝፈው የማያውቁ ሰዎች ጩኸት ሳይሆን የሚያውቁ ሰዎች ዝምታ ነው። የምናውቅ ሰዎች ዝም ካልን፣ የምናውቅ ሰዎች አይተን እንዳላየን ከሆንን ዮፍታሄ ንጉሴ እንዳሉት “ሀገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ“ ብለዋል ። አመሰግናለሁ፡፡!

አዲስ ዘመን ሀምሌ 8/2011

በጋዜጣው ሪፖርተሮች