ትዕግስት በተሞላበት ውይይትና ድርድር ለሁሉም የሚጠቅም ሠላማዊ አስተዳደር መመስረት ይገባል

48

ኢትዮጵያ፣ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን የያዘች እንደመሆኗ ይሄን ብዝሃነቷን ያቅፍላታል በሚል የፌዴራል ስርዓትን ዕውን አድርጋ እየተዳደረችበት ትገኛለች፡፡ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀሩ ላይ ምሑራንን በአንድ የሚያስማማ ነገር ባይኖርም በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47/1 የፌዴራሉ መንግሥት አካል የሆኑ ዘጠኝ ክልሎች (ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የጋምቤላ ሕዝቦች እና የሐረሪ ሕዝብ ክልል) በሚል ተዘርዝረዋል፡፡

በንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ እነዚህ ክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ ሆኖም በንዑስ አንቀፅ ቁጥር ሦስት ስር ይሄን የክልል ምስረታ እውን ማድረግ የሚቻልባቸው አምስት ያክል መለኪያዎችን አስቀምጧል፡፡ይሄን ሕገ መንግሥታዊ መብት መሰረት በማድረግም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ሲነሱ የቆዩ ቢሆንም፤ እስካሁን አንድም ጥያቄ ምላሽ ማግኘትና ክልል መመስረት አልተቻለም፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢቀመጡም፤ ዛሬ ላይ የተገኘውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ ጥያቄዎች እንደ አዲስ ገንፍለው የወጡበትን ሂደት ማየት ተችሏል፡፡

ከእነዚህ መካከል የሲዳማ ብሔር የክልል ጥያቄ ጎልቶ የሚገለጽ ሲሆን፤ ጥያቄውም ገፍቶና ሕጋዊ መስመሩን ተከትሎ ከክልሉ ምክር ቤት ወደ ምርጫ ቦርድ ስለመድረሱ ይነገራል፡፡ ላለፉት 11 ወራት በዚህ መልኩ የተጓዘው ይህ ጥያቄም ምላሽ ዘግይቷልና በራስ መፍትሄ እንሰጠዋለን የሚል እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱ በስፋት ይነገራል፡፡ ለመሆኑ ይህ እንቅስቃሴና የሕግ መስመሩ እንዴት ይደጋገፋሉ? ይሄን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችስ ምን ይሆኑ? ችግሮቹ እንዳይከሰቱስ ምን መሰራት አለበት? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሕግ ምሑራንን ሀሳብና አስተያየት እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡

ክልሎች እንዴት ተመሰረቱ

ዶክተር ጌታቸው አሰፋ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የክልሎች አወሳሰን በሽግግሩ ዘመን በ14 ክልል ተደራጅቶ የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ 64 ብሔር ብሔረሰቦችን በመዘርዘርም እንደ አመቺነቱ አጎራባቾች/ኩታ ገጠም የሆኑ እንደ ፍላጎታቸው ሰፋ ያለ ክልል በመመስረት ወደ አንድ ክልልነት መጠቃለል እንደሚችሉ ተደንግጎ ነበር፡፡ ከዚህም ባለፈ በወረዳና ከዛ በላይ የራስ አስተዳደር ማስተዳደር የሚችሉ ብሎ የለያቸውም ነበሩ፡፡ ከሽግግሩ በኋላ ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ ደግሞ ዘጠኝ ክልላዊ መንግሥታት እንዲኖሩ ተደርጎ፤ በክልሎቹ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦችም በማንኛውም ጊዜ ክልል መመስረት እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡

ክልሎቹ በዚህ መልኩ ሲዋቀሩ ግን የራሱ ክፍተት ነበረበት፡፡ ለምሳሌ፣ የክልሎቹ ባለቤት የተባሉ ብሔረሰቦች የህዝብ ቁጥር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይለያያል፡፡ በዚህም ከአንድ ሚሊዬን በታች የህዝብ ቁጥር ያላቸው ክልል የተሰጣቸው ወደ ሦስት ክልሎች አሉ፡፡ በአንጻሩ ሁለትና ሦስት ሚሊዬን ያላቸው ከሦስት ያላነሱ ብሔሮች በደቡብ ክልል ውስጥ ተጠቃልለው ይገኛሉ፡፡ ይህ ሂደትም አሁን ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ጉልህ አስተዋጽዖ ያለውና እንደ ምክንያት ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡

በዚህ መልኩ ክልሎች መካለላቸውና ጥያቄዎች አሁን ላይ በርክተው መነሳታቸው ደግሞ በወቅቱ ክልሎቹ ሲዋቀሩ በምን መልኩ መቋቋም አለባቸው የሚለው በሰፊ ውይይት ላይ ተመስርቶ ያለመከናወኑ ውጤት ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሰው የሚሰጠው ሀሳብ ይጠቅማል በሚል ህዝቡ ውይይት አድርጎበት፣ ሀሳቦች ተፋጭተው አሸናፊ የሆነውና ህዝቡም የተቀበለው ተካትቶበት የጸደቀና የተተገበረ ቢሆን ኖሮ ለሰላሙ ዋስትና ይሆናል፤ ምናልባትም አሁን የሚነሱ ጥያቄዎች በዚህ መልኩ ላይነሱ ይችላሉ፤ ወይም የተለየ መልክ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እናም በወቅቱ የነበረው ሂደት በዘርፉ ምርምር ለሚያደርጉ ባለሙያዎች እንኳን መልስ የማይገኝላቸው በመሆናቸው በወቅቱ የተሰራው ሥራ የፈጠረው ችግር አለ፡፡

የሕግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ ውብሸት ሙላት በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ የክልሎች አወቃቀርን በአራት አካሄዶች መድቦ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ሰፋ ያለ ቦታ ይዘው በአንድ አካባቢ ተከማችተው የሚገኙ ቁጥራቸው ከሌሎቹ በዛ ያሉ ብሔሮች በስማቸው ክልል የመሰረቱበት ሲሆን፤ በውስጣቸው ሌላ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ቢኖሩም የክልሎቹ ስም አወጣጡ ቁጥሩ በበዛው ብሔር መጠሪያ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሁለተኛው ከ56 ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በላይ የያዘው የአሁኑ የደቡብ ክልል (በሽግግሩ ወቅት በአምስት ክልሎች ተዋቅሮ የነበረው) ነው፡፡ ይሄን አወቃቀር ደግሞ እንዳንድ የክልሉ ተወላጆች ደቡብ የሚለው ሥያሜ አቅጣጫን ከመጠቆም በስተቀር ማንነትን አያመለክትም በማለት ይተቹታል፡፡ ሦስተኛው ምደባ ደግሞ አምስት አምስት ነባር ብሔረሰቦች ኑሯቸው የተዋቀሩበት የጋምቤላ ሕዝቦች እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ናቸው፡፡ አራተኛው የሐረሬ ክልል የተመሠረተበት ሁኔታ ነው፡፡

ይህን አይነት የክልል አወቃቀር ደግሞ ትችት ሲቀርብበት ይታያል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር በሰፊው ከሚወቀስብት አንዱ ለክልልነት የተወሰዱት መስፈርቶች ናቸው፡፡ በዓለም ላይ አንድ ወጥ መስፈርት ባይኖርም፤ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ጀርመንን በመሳሰሉት በዋናነት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን ከግምት ያስገባ ነው፡፡ ናይጀሪያ፣ ስፔን፣ ቤልጅየም፣ ህንድ፣ በተወሰነ መልኩ ካናዳ ደግሞ ከመልክዓ ምድር በተጨማሪም ብሔርን ከግምት አስገብተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደግሞ ቅይጥ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 46(2) መሠረት በኢትዮጵያ ክልል አመሠራረት ሂደት የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ከግምት መግባት አለባቸው፡፡ ቀደም ሲል ከተጠቀሱት መሥፈርቶች አንጻር ደግሞ አንድ ብሔር በዛ ብሎ የሚገኝባቸው (ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ) ክልሎች ማንነትና ቋንቋ ገነን ብለው ይታያሉ፡፡ በደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ኢኮኖሚና የመሳሰሉት መሥፈርቶች ቢኖሩም መልክዓ ምድር ጎልቶ ይታያል፡፡

በእነዚህ ክልሎች የተካተቱ ህዝቦች ደግሞ በአንድ አካባቢ በመገኘታቸው እንጂ ቋንቋቸው ወይም ማንነታቸው ስለተመሳሰለ አይደለም፡ ፡ በዚህ መልኩ የሚጠቀሰው በሽግግሩ ወቅት አሥራ አራት የነበሩትና ከሽግግሩ በኋላ ዘጠኝ የሆኑት የኢትዮጵያ ክልሎች፤ በሂደት በኋላ የተለያዩ ብሔሮች ክልል ለመመሥረት ፈልገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፤ወይንም ትተውታል፡፡ በዚህ መልኩ በየጊዜው የሚነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎችም የዚሁ ማሳያ እንደሆኑ ምሁራኑ ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሲዳማ፣ ከፋ፣ ጋሞ፣ ጉሙዝ፣ በርታ እና ጉራጌ በተለያዩ ወቅቶች የራሳቸውን ክልል ለመመሥረት ጥያቄ አንስተው የነበሩ መሆኑ ሲታይ ወደውና ፈቅደው ክልሎቹን የመሰረቱ ስለመሆናቸው ሊያጠራጥር ይችላል፡፡

አዳዲስ የክልል ጥያቄዎችና ጉዟቸው

እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለጻ፤ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶችም ሆነ በሌላ ምክንያት አሁን ላይ እየተነሱ ያሉ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ሕገ መንግስታዊ መሰረት አላቸው፡ ፡ ሕገ መንግስቱም በተቋቋሙት ክልሎች ውስጥ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች በፈለጉት ጊዜ ክልል መመስረት ይችላሉ በሚል በአንቀጽ 47 አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄዎቹ ቀደም ሲልም ይነሱ የነበሩ እንደመሆናቸው በዛን ወቅት ዝምታን ከመምረጥ ይልቅ በአዎንታዊ መልኩ ቢስተናገዱ ኖሮ ይሄን ያህል ችግር ያለው አልነበረም፡፡ ሆኖም በወቅቱ የሚነሱ የክልል ጥያቄዎችን በቀናነት አለመቀበል መኖሩ ጥያቄዎቹ ተከማችተው እንዲቆዩና አሁን ላይ ተበራክተውና ገፍተው እንዲነሱ አድርጓል፡፡

አሁንም ቢሆን የእነዚህ ጥያቄዎች መነሳት ችግር የለውም፤ ሕጋዊ መሰረት ያለውም ነው፡፡ ነገር ግን ሊታሰብና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ጥያቄውን የሚያነሱትም ሆነ ጥያቄውን የሚመልሱ ወገኖች ዘላቂ መፍትሄ በሚያመጣ መልኩ እንዲፈጸም ለማስቻል የድርሻቸውን ማበርከት የሚገባቸው መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ አይነት ጥያቄዎች መፍትሄ ሲያገኙ ተከትሏቸው የሚመጣ ችግር መኖር የለበትም፡፡ እናም ጥያቄዎቹ ሲመለሱ ሁሉንም በጋራ ተጠቃሚና ተሳታፊ በሚያደርጉ፤ ክልል ጠያቂውም ሆነ ቀደም ሲል በዛ ክልል ውስጥ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ብሎም ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘላቂ ሰላማቸውን በሚያረጋግጡበት አግባብ ጥያቄው ሊስተናገድ ይገባዋል፡፡

በዚህ መልኩ ለጋራ ሰላምና ጥቅም አስቦ መንቀሳቀስ ካልተቻለና ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠው ብቻ ይተርጎም ከተባለ ግን ሕገ መንግሥቱ ብዙ የማይፈታቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ህዝብ ክልል ሆኖ ሲወጣ እሱ ከሚወጣበት ክልል ጋር ምን አይነት ግንኙነት ይኖረዋል፤ በሚወጣው ክልል ውስጥ ለሚቀሩ ሌሎች ብሔረሰብ አባላት ተወላጆችስ ምን ግዴታ አለበት፤ የሀብትና ንብረት ክፍፍል ጉዳዮችስ እንዴት ይፈጸማሉ፤ የሚሉና በርካታ ተያያዥ ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽና በዝርዝር አልሰፈሩም፡፡

እነዚህ ጉዳዮች በዝርዝር አልሰፈሩም ማለት ግን ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ማለት ሳይሆን፤ ጠያቂው ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ምላሹም ምላሽ ሲሰጥ እነዚህን ከግንዛቤ ባስገባና እልባት በሚሰጥ መልኩ መሆን እንደሚጠበቅበት መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ባልተፈቱበትና በተደበላለቁበት ሁኔታ ክልል ሆኜ ልውጣ ማለት ለጠያቂውም አይጠቅምም፤ ለሌላውም አይጠቅምም፡፡

ስለዚህ ይሄንን በሰከነ ሁኔታ መመልከት ያስፈልጋል፤ በተለያየ ደረጃ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችንም ማሳተፍና ሀሳባቸውንም በማድመጥ ከጥድፊያ ወጥቶ ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን በሚያመጣ መፍትሄ ላይ ተመርኩዞ መራመድና መስራት ያስፈልጋል፡፡ መብቱን የጠየቀ መብቱ እንደሚመለስለት የሚያውቀውን ያክል፤ መብት በመጠየቅ ሂደት ግዴታዎች መኖራቸውን በመገንዘብ ለድርድርና ውይይት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል፡፡

እንደ አቶ ውብሸት አገላለጽ ደግሞ፤ እስካሁን ዘልቆ የመጣው የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ ቀደም ሲል ምላሽ የተነፈገው ሲሆን፤ ባለው ሁኔታም የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሕገ መንግሥቱን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ ክልል የመመሥረት መብት አላቸው፡፡ ሆኖም ሂደቱ የራሱ የሆኑ ደረጃዎችና አካሄዶች ያሉት ሲሆን፤ የብሔሩን ጥያቄ በብሔሩ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ድጋፍ ከማግኘት ጀምሮ ለክልሉ ምክር ቤት በደብዳቤ የማሳወቅንና የህዝበ ውሳኔን እስከማካሄድ ቅደም ተከተሎችን ያከበረ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሰረት ድምጸ ውሳኔ የማዘጋጀት ኃላፊነት የተጣለበት የክልሉ ምክር ቤት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ለሲዳማ ጉዳይ ድምጸ ውሳኔ የሚያዘጋጀው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ነው፡፡ በምርጫ ሕጉ ደግሞ፣ ሕዝበ ውሳኔ የሚያዘጋው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ከዳር ለማድረስ ምርጫ ቦርድ ከክልሉ ምክር ቤት የቀረበውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ህዝበ ውሳኔ ማካሄድ ይኖርበታል፡፡

እዚህ ላይ ግን መነሳት ያለበት አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ይኸውም፣ የክልሉ ምክር ቤት በአንድ ዓመት ጊዜ ድምጸ ውሳኔ ማዘጋጀት ካልቻለ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ሲሆን፤ ሕገ መንግሥቱም ይሄን በዝምታ አልፎታል፡፡ በመሆኑም የክልሉ ምክር ቤት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ድምጸ ውሳኔ ካላዘጋጀ፤ ድምጸ ውሳኔ እንዲዘጋጅ አስተዳደራዊ መፍትሔ ወይም በሕጋዊ መንገድ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ድምጸ ውሳኔ እንዲዘጋጅ መጠየቅ እንደመፍትሔ የሚወሰድ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ተጠያቂነት ያለበት ይህ ግዴታ የተጣለበት አካል ነው፡፡

ይሁን እንጂ፣ በተናጠል ማለትም ጥያቄውን ያቀረበው ብሔር፣ ድምጸ ውሳኔም ሳይከናወን ክልል መመሥረትና ክልል መሥርተናል ብሎ ማወጅ የሚቻልበት አካሄድ የለም፤ ተገቢነትም የለውም፤ ይሄን አይነት አካሄድም ሕጋዊ የሚያደርግ ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ ላይ አልተቀመጠም፡፡ በመሆኑም ጥያቄን ከማቅረብና ምላሽ እንዲገኝ ከመሻት ባለፈ፤ ምላሽ ዘገየ ብሎ ወዳልተገባና በሕግ ወደማይደገፍ አካሄድ መግባት ስለማይገባ በእርጋታ መንፈስ መራመድ ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ ምን ይሠራ

እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለጻ፤ የክልል ጥያቄና ምላሹ በዚህ መልኩ በጥድፊያ ይሁን ከተባለና ከተደረገ ችግር ነው የሚወልደው እንጂ መፍትሄ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ልሂቃኑም ሆነ ህዝቡ ለውይይት ዝግጁ በመሆን በጊዜ የተወሰነ መርሐ ግብር በማውጣት መከናወን ያለባቸውን ሥራዎች ደረጃ በደረጃ በማከናወን የጥያቄው ምላሽ ውጤታማ የሚሆንበትን ሂደት ለማጠናቀቅ ሁሉም የድርሻቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል፡፡

አሁን ያለውን ጥያቄ ደግሞ ህዝበ ውሳኔ በማካሄድ ብቻ ዘላቂ መፍትሄ ይገኝለታል ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ከላይ የተጠቀሱና ሌሎችም በሕገ መንግሥቱ በዝርዝር ያልተቀመጡ ነገር ግን በአግባቡ ተፈትሸው መመለስ የሚገባቸው ነገሮች ባሉበት ሕዝበ ውሳኔው ቢካሄድና ክልል ሆነ ቢባል እንኳን በርካታ ችግሮች ተከትለውት ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የሐዋሳ ዜጎች የኑሮ ሁኔታ፤ የንብረትና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ቀድመው እልባት ማግኘት ካልቻሉ፤ ከእነዚህና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡

በመሆኑም ከህዝበ ውሳኔው በፊት እነዚህን እንዴት እንፍታ ብሎ መምከርና የጋራ መፍትሄ ማስቀመጥን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ደረጃ መነጋገር ከተቻለና በመሠረታዊ ነገሮች ላይ ተግባብቶ ወደ ህዝበ ውሳኔው ተሄዶ የክልል ጥያቄው እውን ከሆነ፤ ለሌሎች ጉዳዮች እንደየባህሪያቸው በሂደት እየተለዩ መፍትሄ መስጠት ይቻላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በተጀመረው መልኩ ክልል የመሆን ጉዞው አንድም አይጠቅምም፤ ቢሆንም ደግሞ የጭቅጭቅ ምንጭ ነው የሚሆነው፡፡

ለጥያቄው መፍትሄ የመስጠትና የማድረግ ሃላፊነቱም ሆነ ስራው ደግሞ የምርጫ ቦርድ ብቻም ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ ሕገ መንግሥቱም ላይ ስለ ምርጫ ቦርድ የሚያወራው ነገር የለም፡፡ የምርጫ ቦርድ ኃላፊነት የመጣው በኋላ በወጣው የምርጫ ሕግ መሰረት ነው፡፡ በዚህም ቢሆን ሕዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ የሚወስነው አካል ከወሰነ በኋላ የማስፈጸም ኃላፊነት ነው ያለበት፡፡ ስለዚህ ውሳኔው ከሌላ ቦታ ነው የሚመጣው፡፡ እናም ሥራው የቦርዱ ብቸኛ ሥራ ነው ተብሎ መወሰድ የለበትም፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን ባለው ሁኔታ የቦርዱ በተገቢው መልኩ ያለመዋቀርና ያሉት የለውጥ ሂደቶች የጥያቄው ምላሽ ለመዘግየቱ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ አሁን ግን ጥያቄው ለቦርዱ የደረሰ እንደመሆኑ ቦርዱ ስራውን መስራት ያለበት ሲሆን፤ ይሄንንም ብቻውን ሳይሆን ቀድመው መሰራት ያለባቸው ስራዎችን ሰርቶ ለክልል ምስረታው ውጤታማነት እንዴት ጀምረን እንጨርሰው የሚለውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዳዮች ቦርዱን ሊያስጨንቁት፤ ሌሎቹም የድርሻቸውን ሊያበረክቱባቸው የሚገቡ ናቸው፡፡

በዚህ ጉዞ ውስጥ ደግሞ ዋናው ትዕግስት ነው፡፡ ለውጤታማነቱ በትዕግስት መራመድ፣ በመደማመጥ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ የምወስደው ውሳኔ ምን ጉዳት አለው፤ ውሳኔውም ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአገርስ ይጠቅማል ወይ፤ በእኔ ላይስ በዘላቂነት ምን ተጽዕኖ ያመጣል፤ የሚሉና መሰል ጉዳዮችን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጠያቂም ሆነ ምላሽ ሰጪ አካላት በመጀመሪያው መስመር ላይ ያሉ ወገኖች የማይተካ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ተረድተው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሂደቱም ሁሉም በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ህዝቦች መሆናቸውን መዘንጋት የለበትም፤ የሚወሰኑ ውሳኔዎችም ዘላቂ ችግር የሚፈጥሩ ስለመሆን አለመሆናቸው ቆም ብሎ ማስተዋል ይፈልጋል፡፡ በተቀመጠው ስርዓት ያልተካሄደ ሕዝበ ውሳኔም በሕግም የማይደገፍና ተጠያቂነት ያለበት ነው፡፡ ወደፊት ብዙ ዘመን በክልልነት እንኖራለን፤ እንመራለን፤ ተብሎ ሲታሰብ፤ ትንሽ ጊዜ ታግሶ በስርዓት በማስኬድ ጨርሶ ሰላማዊ የሆነ አስተዳደር መመስረት ለሁሉም ይጠቅማል፡፡ በዚሁ አግባብ አስቦም ነው መራመድና መስራት የሚገባው፡፡

እንደ አቶ ውብሸት አባባል ደግሞ፤ እስካሁን ዘልቆ የመጣው የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ ቀደም ሲል ምላሽ የተነፈገው ሲሆን፤ ባለው ሁኔታም የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሕገ መንግሥቱን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን ህዝቡ ሊረዳው የሚገባውና ቀድመው ሊታሰቡ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በክልል ምሥረታ ሂደት ሕገ-መንግሥቱ ስለንብረትና ዕዳ ክፍፍል የሚያነሳው ነገር አለመኖር ነው፡፡ ለአብነት፣ ሲዳማ ዞን ክልል ሲሆን ሀዋሳን ይዞ ሊዋቀር ይችላል፡፡ የደቡብ ክልል ደግሞ ሀዋሳ ላይ ብዙ የመሠረተ-ልማትና የቢሮ ግንባታዎችን አከናውኗል፡፡

እነዚህ ደግሞ በደቡብ ክልል ውስጥ ለሚኖሩት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሲባል የተገነቡና ወጪ የተደረገባቸው ናቸው፡፡ ሲዳማ እነዚህን መሠረተ-ልማትና ቢሮዎች ይዞ ከደቡብ ሲወጣ፤ ደቡብ ክልል እንደገና በሚመሠረተው ዋና ከተማ ላይ ከዓመታዊ በጀቱ እየቆነጠረ ለሌሎች የልማት ሥራዎች ማዋል የሚችለውን ለቢሮና ለመሳሰሉት ግንባታዎች ሊያውለው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ደቡብ ሲጎዳ ሲዳማ ይጠቀማል ማለት ነው፡፡

በተጨማሪም ክልሉ የተበደረው ገንዘብ ቢኖርበት እና በተለይም ብድሩ የዋለው የሲዳማ ዞንን የሚጠቅም ተግባር ላይ ከሆነ፤ ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ ይህንን ብድር የመክፈል ወይም የመጋራት ግዴታ ይኑርበት ወይም አይኑርበት የሚገልጽ ሕግ የለም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሕገ- መንግሥቱ ክልሉ ሥልጣኑን እንደሚያስረክብ እንጂ ሌሎች ንብረትና ገንዘብን በተመለከተም የገለጸው ነገር የለም፡፡

እነዚህ ጉዳዮች በዘላቂነት እልባት ሳያገኙ ወደ ክልልነት መገባቱ ደግሞ ምላሹን ዘላቂ መፍትሄ ከማሰጠት ይልቅ ችግሮችን አስከትሎ የሚመጣ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሕገ- መንግሥቱን ማሻሻል ወይንም በሌላ ሕግ እልባት መስጠት ከሚፈጠር ግጭት ያድናል፡፡ በቀጣይ ለሚከሰቱ ጥያቄዎችም ምላሽ መስጫ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም፤ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ተቀራርቦ መስራትና ጥያቄው ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚቻልበትን እድል በጋራ መክሮ መፍጠር ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን በመወጣት ካልተገባ ኪሳራ መዳን ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን ሀምሌ 8/2011

 ወንድወሰን ሽመልስ