በአጭሩ ያየነውን ስኬት ተስፋፍቶ እንድናይ ተስፋን እንሰንቅ!

24

 አዲስ አበባ 31ኛውን ከንቲባዋን ሾማ መተዳደሯን ከጀመረች እነሆ ዛሬ አንድ ዓመት ሞላት፡፡ ለሚሰራ ዕድሉ ካልተሰጠ መስራቱና አለመስራቱ አይታወቅምና ለከተማዋ ሁለገብ ሥራ ፈፃሚነት የምክትል ከንቲባው የቆይታ ጊዜ ገና አንድ ዓመት መሆኑ ለግምገማ በቂ ባይሆንም ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራትን ማሳካታቸው ግን ያስመሰግናቸዋል፡፡ ተግባራዊ ውጤቱም እንዲህ ይመዘናል፡፡

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሐምሌ 10/2010 ዓ.ም ቃለ መሃላ ፈፅመው ሥራቸውን ሲጀምሩ ከ6 እስከ 20 ዓመት በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ የማስመለስ ሥራ ላይ ተጠመዱ፡፡ በዚህም ያለ ልማት ተቀምጦ የነበረን ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ውስን የሕዝብ ሀብት (መሬት) ወደ መንግሥት እንዲመለስ አድርገዋል፡፡

ወደ መንግሥት የመሬት ማኔጅመንት ገቢ የተደረጉት መሬቶች በጊዜያዊነት ለመኪና ፓርኪንግ አገልግሎት እንዲውሉ በማድረግ 38 የመኪና ማቆሚያዎችን በሁሉም ክፍለከተሞች በማስገንባት ለከተማዋ ወጣት ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ሊጠቀሱ ከሚችሉ ተግባራት መካከል ይገኙበታል፡፡

«ጥቂት ግለሰቦች በአርሶ አደሩ መሬት ላይ ባለጸጋ ሆነው አርሶ አደሩንና የአርሶ አደሩን ልጅ ጥበቃና የጉልበት ሠራተኛ ሆኖ ማየት አልፈልግም። ይህ ደግሞ ኦሮሞን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን በከተማዋና በዙሪያዋ የሚኖሩትን ሁሉ የሚመለከት ነው» ያሉት ከንቲባው፤ በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ከዚህ ቀደም ነዋሪዎችን አፈናቅሎና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን አናግቶ ይከናወን የነበረውን የግንባታ አካሄድ ቀይረዋል።

ከንቲባው በሥራ ዘመናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ዋነኛ ችግር የሆነውን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ጨምሮ፣ የውሃ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ለሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለማዳረስ ሃሳብ መሰነቃቸውን ገልጸው ነበር፡፡ በዚህ ሃሳባቸውም በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ የከተማ አስተዳደሩ ቤቶችን ከሕገወጦቹ በመንጠቅ አቅም ሌላቸውና ለደሃ ነዋሪዎች የማስተላለፍ ሥራ ሰርተዋል።

የከተማዋን የውሃ አቅርቦት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀርፋል የተባለው የለገዳዲ ቁጥር 2 የከርሰ ምድር ውሃ ልማት ፕሮጀክትን በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅና በቀን 86ሺ ሜ.ኩብ የውሃ አቅርቦት እንዲሰጥ የለገዳዲን ቁጥር 2 የውሃ ፕሮጀክት አስጀምረዋል፡፡

ከከተማዋ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት፣ የዓድዋ ማዕከል፣ የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት፣ ከፑሽኪን አደባባይ – ጎተራ ማሳለጫ የሚገነባው መንገድና የቤተ-መንግሥት ቅርስ ጎብኚዎች የመኪና ማቆሚያ፣ የአዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ በተያዘው እቅድ መሠረት በለገሃር የተቀናጀ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ተጠቃሽና ባለፈው አንድ ዓመት የታቀዱ ናቸው፡፡

ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ የተለያየ የአቅም ደረጃ ያላቸውን አመራሮች የመቀየር፣ በከተማ አስተዳደሩ ተደራራቢ ሥራዎችን የሚያከናውኑ በርካታ መሥሪያ ቤቶች እንዲታጠፉ መደረጉ፣ በከተማዋ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን ነዋሪዎች ለማቋቋም የተጀመረው ፕሮግራም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳትና መልሶ የማቋቋሙ ሥራ፣ የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ሥራ፣56 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውና 29 ቢሊዮን ብር የሚፈጀው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት፣ በከተማዋ የገቢ አሰባሰብ መስክ በበጀት ዓመቱ ከ32 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ከንቲባውና የሚመሯቸው ተቋማት የቱን ያህል ውጤታማ ሥራ እንዳከናወኑ ያሳያል፡፡

የሚሰራ ሰው ያሰበው ሁሉ ይሳካለታል ባይባልም፤ በአጭር ጊዜ የተገኘውን ውጤት በመመዘን ለረጅሙ መጪው ጊዜያችን ከዚህ የተሻለ ሰርተው እንደምናይ ተስፋን መሰነቅ ይገባናል፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2011