በማስተዋል መጓዝ ረዥም መንገድ ያስኬዳል

14

አርቆ አስተዋይ ረጅም ርቀት እንደሚጓዝ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም አርቆ አስተዋይ መነሻውን ብቻ ሳይሆን መድረሻውን፣ ጎን ለጎንም የሚያስከትለውን ጥቅምና ጉዳት በቅጡ ለመገንዘብ የሚችልበት የተረጋጋ መንፈስና ቅን ልቦናም አለውና! በመሆኑም አርቆ እያየ በማስተዋል የሚጓዝ እርምጃው ሁሉ በስኬት የታጀበች ትሆናለች።

ሀገራችን የብሔር ብሔረሰቦች ሀገር ነች፡፡ ሁሉም በየደረጃው ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ መሆኑም መብቱ ነው፡፡ ሌሎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም አሉት፡፡ ነገር ግን መብቶችን ሲጠይቅና ለመጠቀም ሲንቀሳቀስ በማስተዋልና በሕግ አክባሪነት መሆን አለበት፤ ይገባዋልም፡፡ ይህ ሲሆን መዳረሻውን ሩቅ፣ ውጤቱም ያማረ ይሆናል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሲጸድቅ ዘጠኝ ክልሎች እንዳሉና በሂደት ግን ክልል የመሆን ጥያቄ የሚያነሳ ብሔር ብሔረሰብ ክልል መሆን እንደሚችል በአንቀጽ 47 ደንግጓል፡፡ ስለሆነም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባሉ የዞን አስተዳደሮች የሚነሱ የክልል እንሁን ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን በማስተዋል፣ በሕገ መንግሥቱና በሕጉ መሠረት ሂደታቸውን ጠብቀው ሰላማዊ ሆነው መቅረብም መፈጸምም አለባቸው፡፡

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ካሉ 56 ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የሲዳማ ብሔር እራሱን ችሎ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄ ማቅረቡ መብትም ተገቢም ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊም ነው፡፡ ተቀባይነትም አለው፡፡ ነገር ግን ጥያቄውን ለማስፈጸም የሚኬድበት አግባብ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረርና የጥፋት አካሄድ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል።

«ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ…» እንደሚባለው በችኮላና በጥድፊያ የሆነ ነገር ሁሉ መጨረሻው የማያምር መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆንም ማስተዋል ይገባል፡፡ ያስፈልጋልም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄን አስመልክቶ ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ መደረግ ያለባቸው ቅድመ-ዝግጅቶችን በሚገባ ያስቀመጠ ነው። በማስተዋልና በሰከነ መንገድ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚቻል መሆኑንም አመላካች ነው፡፡

ለክልል እንሁን ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ ለማደራጀት ግንባር ቀደሙ ተግባር ሕዝበ ውሳኔውን የሚመራው ተቋም አቅም ነው፡፡ ሕዝበ ውሳኔ የሚመራበት መመሪያና ሌሎች ተግባራት መሰራት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም መሆኑ ቦርዱ አስታውቋል፡፡ ስለሆነም የአንድ ዓመት የጊዜ ገደቡ ገና አምስት ወራት ይቀሩታል፡፡ በእነዚህ ወራት የሚሰሩ ሥራዎችንም ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡

ሕዝበ ውሳኔ የሚከናወነው የሕዝብን ፍላጐትና ውሳኔ ሕጋዊ እና ነፃ በሆነ አግባብ መሰጠቱን ለማረጋገጥ ስለሆነ ቦርዱ ተገቢና በቂ ዝግጅት አድርጐ ሕዝበ ውሳኔውን ማካሄድ ይችል ዘንድ የሕዝበ ውሳኔ አካሄድ የሚመራበት የሥነሥርዓት መመሪያ እንዲሁም የሕዝበ ውሳኔ አጠቃላይ ጊዜ ሰሌዳና በጀት ማዘጋጀት፣ በሕዝበ ውሳኔ ዝግጅትና ድምፅ መስጠት ሂደት ስለሚኖረው የፀጥታ አጠባበቅ ሁኔታ ግብረ ኃይል ማደራጀትና ዕቅድ ማፅደቅ፣ ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚዎች መመልመል፣ ማሰልጠንና ማሰማራት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረክ ማዘጋጀት፣ የድርጊት መርሃ ግብር ማውጣት፣ በሕዝበ ውሳኔ አፈፃፀም ሂደቱ ላይ የጋራ ምክክር መርሃ ግብሮችን አውጥቶ መተግበር፣ የሰነድና ቁሳቁስ ዝግጅትና ህትመት ሥራዎች ማከናወን፣ ድምፅ መስጫ ወረቀቶችና ፖስተሮች ማዘጋጀት፣ ማሳተም፣ ማሰራጨት፣ ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ማሰጠት፣ ቆጠራና ውጤት ማሳወቅ ተግባራት በቅደም ተከተልና በእርጋታ ማከናወን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ ጠያቂው አካል በማስተዋልና በትዕግስት መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡ ቦርዱንም ማገዝ አለበት፡፡

ቦርዱ ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ለሚያደርገው ዝግጅት የደቡብ ክልል ምክር ቤት መስራት ያለበትን የቤት ሥራም ሰጥቷል፡፡ የሃዋሳ ከተማ ጉዳይ፣ የጋራ ጸጥታ አጠባበቅ፣ በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሔር ብሔረሰብ አባላት ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ሕጋዊ የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ግልጽ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲያዘጋጅና ለቦርዱ እንዲያሳውቁም አስታውቋል፡፡ ይህም የሕዝበ ውሳኔ ሂደት አካል መሆኑን ተገንዝቦ ሥራዎቹን በወቅቱ መስራት አለበት፡፡

በአጠቃላይ የሲዳማ ሕዝብ የክልል እንሁን ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሊያገኝ የሚችለው በሰከነ ውይይት እና ሕጋዊ መንገድ ብቻ ማወቅ ይገባል። ዛሬ ላይ የሚደረገው እንቅስቃሴ የወደፊቱን ዕጣ ፈንታ ይወስናል። ስለዚህ ማንኛውም እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጥንቃቄ እና ማስተዋል ሊሆን ይገባል!  

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011