«የክልል እንሁን መብታችንን በሰላማዊ መንገድ እየጠበቅን ነው» – የሀዋሳ ከተማ ወጣቶች

14

ለውጡ በሁለት እግሩ እንዳይቆም የሚያደርጉ በርካታ ተግዳሮቶች በዚህ በአንድ ዓመት ውስጥ አጋጥመዋል፡፡ አንዱ ችግር ሲታለፍ ሌላ እየተወለደ መንግሥት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት በፍጥነት እንዳያረጋግጥ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በየጊዜው የሚፈጠሩት ችግሮች የለውጥ ኃይሉን ወጥሮ ለመያ ዝና ትኩረቱን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ተራማጅ እንቅስቃሴውን ለመግታት ያለሙ የሚ መስሉ ናቸው፡፡

በቅርቡም ሕገ መንግሥታዊ መብትን መሠረት አድርገው የተጠየቁ ጥያቄዎች በዚያው መሠረት መመለስ ሲገባቸው ከሕግ አግባብ ውጪ የሚንቀ ሳቀሱ አካላት መኖራቸውን ማህበራዊ ሚዲያዎች ያሳብቃሉ፡፡ በዚህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ውስጥ ከሚጠለፉ የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ዋነኞቹ ደግሞ ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቶች ያሉበት የዕድሜ ክልል ለስሜታዊነት የሚያጋልጣቸው በመሆኑ በሌሎች ተገፋፍተው ጥፋትን ለመፈጸም የሚፈጥኑ ናቸው፡፡

በሕገ ወጥ መንገድ የክልልነት መብታቸውን ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ወጣቱም የዚህ ተልዕኮ አስፈጻሚ በመሆን ቀውስ እንዳይፈጠር እራሱን መቆጣጠር እንደማይገባው በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች ይመክራሉ፡፡

አዲስ ዘመን አስተያየት እንዲሰጡ ከጋበዛቸው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ወጣት ውብሸት ዘርፉ አንዱ ነው፡፡ ውብሸት ተፈጥሯዊ የመሬት ስበት ሕግ ለሁላችንም ተመሳሳይ እንደሆነ ሁሉ ሕገ መንግሥቱም ለሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች እኩል ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆን ይገባዋል ይላል። ስለዚህ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለሌሎች ያጎናጸፈውን መብት ለደቡብ ክልል የሚከለክልበት ምክንያት እንደሌለ ያምናል፡፡

ወጣቱ እንደሚለው ሕገመንግሥታዊ መብትን ተጠቅሞ ጥያቄ ማቅረብ እንደተቻለ ሁሉ ሕገ መንግሥታዊ መልስ መጠበቅብም አስፈላጊ ነው ይላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ ክልል የሚገኙ አንዳንድ ዞኖች ክልል የመሆን ጥያቄያቸው ጎልቶ እየተሰማ ያለው መልስ የሚሰጥና ሕገ መንግሥቱን የሚያስፈጽም የለውጥ አመራር በመፈጠሩ ነው ብሏል፡፡

በተለይም ሰሞኑን በደቡብ ክልል «ጥያቄያችን አፋጣኝ ምላሽ ካላገኘ እራሳችን ክልል መሆናችንን እናውጃለን» በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙት አሉባልታዎች ሕገወጥ መሆናቸውን በመጥቀስ በተለይ ወጣቱ ከእንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ እንዲቆጠብ መክሯል፡፡ ጥያቄ ሲቀርብ እንደ ሀሳብ ሆኖ እንጂ እንደ አቋም ሆኖ መቅረብ የለበትም የሚለው ወጣቱ የቀረበው ጥያቄም ሕጋዊ አግባብን ተከትሎ እስኪመለስ በትዕግስት መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል፡፡

አብዛኛው ወጣት የዶክተር አብይ አስተዳደር ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ እየሰጠ መሄዱንና በቀጣይም በክልሉ እየቀረቡ ያሉ ጥያቄዎች እንደሚመለሱ የሚያምን ቢሆንም የተወሰነው ደግሞ ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ባለማገናዘብ የራሱን አቋም ብቻ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ይገልፃል፡፡

ዛሬ በችኮላ ምላሽ ይሰጥ መባሉ ነገ ተያያዥ ችግሮች ተፈጥረው ሀገራችን ያለችበትን ያለመረጋጋት የሚያባብሱ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ወጣቱ ስሜታዊ እይታውን አስወግዶ ምክንያታዊ እይታውን በማስፋት የትኛ ውንም ዓይነት ጥያቄ ለመመለስ ከሁሉ በፊት የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በሚደረጉ ሥራዎች ከመንግሥት ጎን መቆም ይኖርበታል ብሏል ወጣት ውብሸት፡፡

ወጣቱ የክልሉ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገሩም ጉዳይ የራሱ እንደሆነ ተረድቶ በትዕግስት የመንግሥትን ምላሽ ቢጠብቅ መልካም እንደሆነ የሚገልጸው ወጣት ውብሸት ለአካባቢው ሰላም ባለቤቱ ወጣቱ እንደሆነና የሰላም ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ያለመሆኑን ተናግሯል፡፡ ሰላም ማለት የምንተነፍሰው አየር እንደማለት ስለሆነ አየር ካጣን መተንፈስ እንደማንችል ሁሉ ሰላምም ካጣን ችግሩ በዚያው ልክ መሆኑን ተገንዝቦ ወጣቱ እራሱን ከጥፋት መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡

ሌላዋ አስተያየት የሰጠችን የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰላማዊት ባልቻ ናት፡፡ እርሷም እንደቀደመው ወጣት ሁሉ የክልልነት ጥያቄ ማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ እንደሆነ ገልጻ በክልሉ የሲዳማም ሆነ ሌሎች ዞኖች ክልል የመሆን ጥያቄ ማቅረባቸው ተገቢነው ትላለች፡፡ ከሰሞኑም «የክልል የመሆን ጥያቄያችን እስከ ሐምሌ 11 ምላሽ ካልተሰጠው ራሳችን ክልል መሆናችንን እናውጃለን» በሚል በማህበራዊ ሚዲያ እየተለቀቀ ያለው ሕገወጥ ቅስቀሳ የአካባቢውን ማህበረሰብ እያወከ እንዳለ አስረድታለች፡፡

ሰላማዊት እንደምትገልጸው መንግሥት ሕዝብ የሚያቀርብለትን ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ምላሽ መስጠት እንዳለበትና ሕዝብም የመንግሥትን ምላሽ በትዕግስት መጠበቅ እንደሚገባው ትመክ ራለች፡፡ በዚህ ሂደት ግን አንዳንድ ግለሰቦች ለፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ወጣቱን ወዳልተፈለገ አቅ ጣጫ በመንዳት ለጥፋት እንዲነሳሳ የሚያደርጉ ቅስቀሳዎችን ማድረጋቸውን ትተቻለች፡፡

ወጣቱ ከስሜት ነፃ ሆኖ የአካባቢውን ደህንነት በማስጠበቅ በከተማው ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችንን እና ቱሪስቶችን ስጋት ውስጥ ከሚከቱ ጉዳዮች መቆጠብ እንደሚገባው ትመክራለች። «የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ እንደመሆኑ የአካባቢው ሰላም መደፍረስ የወጣቱን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል» ብላለች፡፡

አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶችም ኃላፊነት በጎደለው መልክ በተለያየ ወገን ቆመው ጉዳዩን ማራገባቸው በአካባቢው ነዋሪ ላይ ስጋት ጥሏል ትላለች፡፡ በአካባቢው የነበረው ጥሩ የሰላም መንፈስ እንዲቀጥል ወጣቱ የአካባቢውን ደህንነት መጠበቅ እንዳለበትና ኅብረተሰቡን ለስጋት የሚዳርጉ ጉዳዮች እንዳይፈጠሩም ከሰላም ኃይሎች ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግ ትመክራለች፡፡ ወጣት የዘመናዊ አስተሳሰብ ባለቤትና የሥልጣኔ ፋና ወጊ መሆን አለበት የምትለው ሰላማዊት ችግሮችን በውይይት መፍታት አንዱ የሥልጣኔ መገለጫ ነው።

ወጣት ታሪኩ ሾና በበኩሉ እንደሚገልጸው አንድ ዞን ክልል ለመሆን የሚያስችለውን ሕገመንግሥታዊ መመዘኛ እስካሟላ ድረስ ጥያቄውን ባቀረበ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከፌዴራል መንግሥት ምላሽ እንደሚሰጠው ይጠቅሳል፡፡ በዚህም መሠረት በደቡብ ክልል በርካታ ዞኖች ክልል የመሆን ጥያቄ ጠይቀው መልስ እየጠበቁ ናቸው፡፡ የሲዳማ ዞንም በ2011 ዓ.ም ያቀረበውን ክልል የመሆን ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተፈጻሚ እንደሚሆንለት በመተማመን ሕዝቡ በጉጉት የፌዴራል መንግሥቱን ውሳኔ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

ጥያቄው ሀገሪቱ በፌዴራል ሥርዓት መተዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲጠየቅ የኖረ ቢሆንም የሕዝብን ጥያቄ የሚሰማ አካል ባለመኖሩ እዚህ ደርሷል፡፡ ዛሬ ግን አዲስ የለውጥ ኃይል ከመጣ ወዲህ በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች እየተመለሱ በመሆናቸው የሲዳማ ሕዝብም ሌሎች ክልሎች ያገኙትን መብት እንዲሰጠው ጥያቄውን አቅርቦ በሰላማዊ መንገድ ውጤቱን እየተጠባበቀ ይገኛል ብሏል፡፡

ይህ የኅብረተሰቡ ጥያቄ ያልተፈለገ አቅጣጫን እንዲይዝ የሚያደርጉ አንዳንድ ውዥንብሮች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲሰራጩ ይታያል፡፡ ነገር ግን የሲዳማ ሕዝብ እስከዛሬ ድረስ በትዕግስት ሲጠባበቅ እንደነበር ሁሉ አሁንም የፌዴራሉን መንግሥት ውሳኔ በትዕግስት ይጠባበቃል የሚል እምነት እንዳለው ወጣት ታሪኩ ይገልጻል፡፡

የአካባቢው ወጣቶች ሰላማቸውን ለማስጠበቅም ከመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር የሚሰሩ እንጂ ለምን ጥያቄያችን አልተመለሰም ብለው ግርግር ለመፍጠር የሚዘጋጁ ያለመሆናቸውንም ይናገራል፡፡ እርሱን ጨምሮ ሌሎች ወጣቶችም ትግሉን እስከመጨረሻ ድረስ በሰላማዊ መንገድ ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደማይኖራቸው ይናገራል፡፡

የሀዋሳና አካባቢው ወጣቶች ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ እንግዶችን ወደ ሀዋሳ ከተማ ይዘው ሲመጡም የከተማውን ፀጥታ በማስከበርና የለውጡ ደጋፊ መሆናቸውን ያሳዩ ናቸው፡፡ ወጣቱ ጥያቄውን ጨዋነት በተመላው መንገድ እያቀረበ መልስ ይጠብቃል እንጂ አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ ይገባል የሚል እምነት እንደሌለው ይገልጻል፡፡ መንግሥት ግን በአጭር ጊዜ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚፈቱ ጥያቄዎችን እየለየ መልስ መስጠት ቢችል እንዲህ ዓይነት ስጋቶችን ማስወገድ ይቻላል ይላል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ሙከራዎች በመንግሥት ላይ ጫና እንዳሳደሩ የሚናገረው ወጣት ታሪኩ የታየው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ለሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ተስፋ የሚሰጥ በመሆኑ ወጣቱ የሚንከባከበው መሆኑን ተናግሯል፡፡

ያም ሆነ ይህ በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚባለው ሳይሆን ምንም ዓይነት ኮሽታ ሳይኖር የተባለውን ቀን አልፎ ሕገመንግሥታዊ ውሳኔውን ብቻ የሚጠብቅ እንጂ የሚረብሽ ወጣት እንደማይኖር ያለውን እምነት አስቀምጧል፡፡ ወጣት ታሪኩ እንዳለው ወጣቱ በሲዳማ ሥርዓትና ባህል መሠረት ያደገ የአባቶቹን ምክር የሚሰማ በመሆኑ በስሜት ተገፋፍቶ ወዳልተፈለገ ነገር ይገባል ተብሎ አይታሰብም ፡፡ ነገር ግን መንግሥት ለሲዳማ ጥያቄ ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሌሎች ክልሎች ያገኙትን መብት ማጎናጸፍ ይኖርበታል፡፡

የሀዋሳ ወጣቶች እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ ቅድሚያ የአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ የሚፈልጉ ናቸው የሚለው ደግሞ ወጣት ድርሻዬ ገብረሚካኤል ነው፡፡ ዶክተር አብይ ሀዋሳ መጥተው ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት የሀገሪቱ ሰላም ከተረጋገጠ በኋላ ማንኛውንም ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ እንደሆኑና የሲዳማ የክልልነት ጥያቄም በሕገ መንግሥቱ መሠረት መመለስ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ የሀገር ጥያቄ መልስ ሳያገኝ የክልል ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት በማለት ሕገወጥ ድርጊት ለመፈጸም የተዘጋጀ ወጣት ይኖራል ብሎ እንደማያምን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ በሀገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት ተጠቅሞ በመንግሥት ላይ ጫና በማሳደር ጥያቄው እንዲመለስለትም እንዲህ ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ የሚል ማስፈራሪያ ይሠነዝራል ብሎ እንደማይገምት ወጣት ድርሻዬ ያስረዳል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙትና ወጣቱ ሕገወጥ እርምጃ ለመውስድ እንደተዘጋጀ ተደርጎ የሚነገሩ ውዥንብሮች የአካባቢውን ወጣቶች የሚገልጹ አይደሉም ባይ ነው፡፡ ለውጡ ቀጣይነቱ ሲረጋገጥም ወጣቱም ሆነ ሕዝቡ ተጠቃሚ መሆኑን ተረድቶ የጥፋት ኃይሎችን መተባበር እንደሌለበት ወጣት ድርሻዬ ምክረ ሀሳቡን ሰንዝሯል፡፡

በአጠቃላይ ወጣቶች በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ የቀረበው ጥያቄ በዚያው መሠረት ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ እንደሚገባቸው አስተያየት ሰጪዎቹ አስገንዝበዋል፡፡ ወጣትነት ስሜታዊነት የሚንጸባረቅበት የዕድሜ ክልል በመሆኑ ወደ ጥፋት የሚገፉ ማናቸውንም እቅስቃሴዎች ወጣቱ ተረድቶ እራሱን ከሕገ ወጥ ድርጊቶች እንዲጠብቅ አስተያየት ሰጪዎቹ መክረዋል፡፡

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011

ኢያሱ መሰለ