የባሕልና የራስ ማንነት

11

አፈወርቅ በዘመናቸው ድንቅ የቆሎ ተማሪ ነበሩ፡፡ መሪጌታ ዘሚካኤል የደብሩ መምህርና አለቃ ብዙ ሊቃውንቶችን ያፈሩ፤ በጥበባቸው የተደነቁ ነበሩ፡፡ በያኔው ተማሪያቸው አፈወርቅ (ወርቅ አፍ እንደማለት) ትምህርት የመቀበል ችሎታ ፍጥነት ይደመሙና ይመሰጡ ነበር ዋናው መሪጌታ፡፡

ዛዲያ ይህ ኮበሌ ከፍ እያለ ሲሄድ ይገዳደረኛል ብለው አብዝተው ይጨነ ቃሉ። የያኔው ወጣት አፈወርቅ ግእዙን ቅዳሴ ውዳሴውን ተምረዋል። ዝማ ሜውን ደግሞ ረዥሙን መቋሚያ ይዞ ንፋስ እንዳወዛወዘው የባሕር ዛፍ ከወዲያና ወዲህ እየተዘወረ በዥርጋዳ ቁመቱ ይወዛወዝበት ገባ፡፡ ቁጭ ብድግ ፤እጥፍ ዘርጋ ሄድ መጣ እያለ በከበሮው እየታገዘ ሲውረገረግ በአርምሞ የሚያስተውሉት መሪጌታ ዘሚካኤል እንዲህ ነው እንጂ ልጅ መልካም፤ መልካም፤ ድንቅ ፤ድንቅ እያሉ ይመሰጡበት ነበር፡፡

የሚያስተምሩትን ሁሉ ከስር ከስሩ እየለቀመ እየቀደመ አፈወርቅ የቀለም ቀንድ ሆነ፡፡ የኋላው መሪጌታ፡፡ የመሪጌታ ዘሚካኤል ደብር ልጆች አልፎ ከሌላ ደብር ተማሪዎች ጋር ይወዳደራሉ። ዩንቨርሲቲ ከዩንቨርሲቲ እንደሚወዳደረው፡፡ አፈ ወርቅ የቤተ ክህነት አለማዊ ስማቸው ደግሞ ሙሉጌታ።

ጎንደር ጋይንት አውራጃ ነፋስ መውጫ ትንሽ ከፍ ብሎ ደምበጣ ሚካኤል ተብላ የምትጠራ ደብር ነው የተወለዱት፡፡ ዘመኑ ከኢጣሊያ ወረራ በፊት ነው፡፡ ቤተሰቡ ኑሮና አዳሩ ግብርና ነው፡ ፡ በገጠር ዋናው የሕዝብ መተዳደሪያ፡፡ የአራሽ የወታደር ወይንም የቀዳሽ ልጅ መሆን ክብር ነበር ያኔ፡፡ አፈወርቅ በወጣትነት የቆሎና በኋላም ትንታግ ተማሪ ሁነው እያለ መሪጌታ ዘሚካኤል ጠልቀው አስተውለው ኖሮ፤

ታይቶም አይታወቅ የልጅ መሪጌታ

በቅኔው የሚዋኝ ምስጢር የሚፈታ

ኑሮው ከሩቅ ቦታ፤

ብለው ለአፈወርቅ ገጠሙ ይባላል፡፡

ግብርና ቤተክህነት ቤተመንግስት ጥብቅ ቁርኝት ነበራቸው ድሮ፡፡ በቤተክህነትና በመንግስት መካከል ፍቺ ሳይፈጸም በፊት፡፡

ዘመን ሳይዘባርቅ ሳይቃዥ አስቀድሞ፡፡ ረዥም ዘመናት የጸና፤ በፍቅር የተንሰላሰለ፤ በአብሮነት የተደጋገፈ ዘመናትን የተሻገረና የዘለቀ ቁርኝት ነበር፡፡ ብርቱ ገበሬ አሊያም ብርቱ ካህን ብር ወታደር መሆን የዘመኑ ታላቅ የአንቱነት ምርጫ ነበር፡፡ የዘመናይቱ ኢትዮጵያ ታላላቅ የሚባሉት ምሁራን ሁሉም ምንጫቸው የሚቀዳው ከእነዚሁ አራሽ ገበሬዎች ካህናትና ወታደሮች ነው፡፡

አሊያም የቤተ ክህነት አገልጋይ፤ የቆሎ ተማሪ ሁኖ የትም ተንከራቶና ዞሮ በየገዳማቱ በየዝክሩ መሀራ እየበሉ ለማይነጥፍ እውቀት መታተር የግዜው እውቀት ፈላጊ ፈተና ነበር፡፡ አይ ግዜ ደጉ ስንቱ ተለወጠ፡፡ በየሀገሩ በየቤተክህነቱ በታዋቂ መሪጌታዎች፤ ሊቆች፤ ሊቃውንቶች፤ ደጀሰላሞች ደርሶ ዞሮ ዞሮ ነው እውቀትና ጥበብ የሚሰበስበው፡፡

እየዞረ ተምሮ ተመርቆ መውጣት። እንዲያ ነው መሪጌታነት፡፡ ከዚያ በኋላ የተወለደበትን መንደርና ሰፈር ለቆ ራቅ ወዳለ ሀገር ለአገልግሎት መውጣት ነው። ብዙዎቹ አንዴ ከወጡ ወደ ሀገራቸው አይመለሱም። አይመለሱም ብቻ ሳይሆን ጭርሱንም ወደ ተወለዱበት ደብር አይመ ጡም።

ርቀው ሄደው ኖረው ያልፋሉ፡፡ ከጋይንት ተነስቶ ቤተልሄምን ርብና ጉማራ ወንዞችን እያቋረጡ መቄትን፤ ሸደሆን ፤ ላስታ ላልይባላን ፤ዳውንትን፤ዋድላ ደላንታን እየ ዞረ በየሊቃውንቱ ዘንድ አገልግሎት እየገባ እያገለገሉ መማር ግዴታ ነው፡፡ መሪጌትነት ማዕረግ ለመውሰድ ለመድረስ ፈተናው ፈታኝ ነው፡፡ እንደዛሬ ምሁራን በተመቸ ቤትና ሁሉም በተሟላበት እየኖሩ በሶስትና አራት አመታት ግዜ የሚገኝ ማዕረግ አይደለም፡፡

መቼም የሰው ሀገር ምሁራንን ማድነቅ ማወደስ የእከሌ ሀገር ፕሮፌሰር ፤ዶክተር፤ ምናምን ማለት እንወዳለን፡፡ የእኛን ሊቃውንት ማን አውቋቸው? ማንስ ተናግሮ ላቸው? መሪጌታነት የዶክተር ማዕረግ ነው አቻው፡፡ ሊቃውንት፤ ሊቀ ሊቃውንት ደግሞ ያውም የእኛ ይበልጣል በውጭ ምንዛሪው አይን ከወሰድነው ፕሮፌሰር ማዕረግ ነው፡፡

አበሻ ሲጃጃል የራሱን እውቀትና ቅርስ እየጣለ የባሕርማዶ ሰውና እውቀት ሲያወድስ ሲክብ ሲያደንቅ ውሎ ያድራል። ሀገርና ታሪክ የገደለው ይሀው ነው። ባሕርማዶ የተሻገረ እንደሁ የራሱን ትቶና ረስቶ ፈረንጅ መሆን ይዳዳዋል፡፡ ይጃጃላል፡፡ ራሱን ትቶ እነሱን ለመሆን ሲሞክር ከራሱ ከባህሉ ከማንነቱ ይፋለሳል። መመጻደቅ መኩራራት ከእኔ በላይ አዋቂ የለም ከማለት አልፎ ግብዝነት ውስጥ ይመሽጋል፡፡

የእኛን ሊቆች እነ መሪጌታን ሊቃውንቱን ሊቀ ሊቃውንቱን ማንአያቸው ማንስ ሰማቸው ? ያንን ጥልቅና ታላቅ ምስጢር ማን አግኝቶት? ማንስ ደርሶበት? የእኛ ሊቃውንቶች እውቀት ለሀገር በሚበጅ መልኩ ቢጠቀሙበት በእጅጉ የሚጠቅም፤ የላቀ ሀገራዊ ውጤትን ሊያስገኝ የሚችል የእውቀት አምባና ውቅያኖስ ነው። የራስን አክብሮ መያዝ ሲገባ በውጭ ባሕልና እምነት መመጻደቅ እጅግ አደገኛ ብሔራዊና ትውልዳዊ የዘመን ኪሳራን ይፈጥራል፡፡ ዛሬ የሆነውም እየሆነ ያለውም ይኸው ነው። ከባሕልና ከትውልድ ከራስ ማንነት ጋር የሚጋጭ ተግባር መከላት ነው የሚገባው። ሀገርና ትውልድን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በዚህም አያበቃም፡፡

ማንነቱን የተሰረቀ ታሪክ አልባ፤ አሻራ አልባ ትውልድ ይሆናል፡፡ የአባቶቹን ታሪክ ስራ ድካም ልፋትና ውጣ ውረድ ማክበር ያልቻለ ትውልድ እንደምን የአባቶቹ ልጅ ይሆናል ? ከታሪክ መቀራቅር ሌላ የትውልድ ዝቅጠት ውስጥ ይዘፈቃል። መሪጌታ እውቀትና ጥበብ ፍለጋ ሱዳን ድረስ ተሻግረው አራት አመት ኖረዋል፡፡ ለሀገሩ ባዳ ለሰው እንግዳ ሆነው፡፡

ከሱዳን ሊቃውንት በተለይ ባሕላዊ ሕክምናን በተመለከተ ሰፊ እውቀት ወስደዋል። ሱዳኖች በባሕላዊ እውቀት ከእኛ ይበልጣሉ እንዴ ስል ጠየኳቸው መሪጌታውን ፡፡ ተደመሙና አይ የልጅ ነገር አሁን ምኑን ምን ልበልህ አሉኝ፡፡ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች በትውልድ ውስጥ የዳበረ እውቀት አላቸው፡፡

እኛም በየፈርጁ ብዙ አለን፡፡ የእኛን ማን ተጠቀመበትና ጭርሱንም የነበረው እንዲጠፋ የሚታገል እኮ ነው የበዛው። የእኛም የእነሱም ወደዘመናዊነት አላደገም። የሚዳበስ የሚጨበጥ የማይጨበጥም እውቀት ባለቤቶች ነን። ወፍ እንደሀገሯ ትጮሀለች ይላሉ ልጄ። በየሀገራችን የየራሳችን ነው የምንለው ብዙ ነገር አለን። እውቀት ጥበብ ባህል ፍልስፍና። ያንን አስፍቶ ማሳደግ ከዘመኑ ጋር አስተሳስሮ መጠቀም ለተተኪው ትውልድ በሚበጅና በሚጠቅም መልኩ ማስተማር ስራም ላይ ማዋል የባለድርሻው ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡

ለምን መሰለህ ወፍ የምትጮሀው እንደ ሀገሯ። ከሰማሀት መልእክቷ ከገባህ ብዙ ትነግርሀለች፡፡ ትምህርትና ጥበብ በየሀገሩ ሞልቶ ተርፏል ፡፡ ከጥበብም በላይ ዘመን ከዘመን የሚዋረሳቸው ዳግም አምጦ የሚወልዳቸውም ጥበቦች አሉ፡፡ የአለም ምስጢራት የትየለሌ ናቸው፡፡ የሰውን ልጅ ሁልግዜም ለምርምር ይገፋዋል፡፡ እውቀት በቃኝ፤ ጠገብኩ አይባልም፡፡

በባሕላዊው እውቀት ውስጥ እጅግ ብዙ ተደብቀው ያሉ ያልወጡ ለአደባባይ ያልበቁ እውቀቶችና ጥበባት አሉ፡፡ ይሄ ጥበብና ምስጢር የሚገለጥላቸው ብዙ ሊቃው ንቶች ነበሩን የዛሬን አያደርገውና። እንዲህ አምባው ሳይሳሳና ሳይመናመን። የዛሬ ዘመን ልጆች ቢነግሯችሁ አታምኑም። ቧልትና ስላቅ ይቀናችኋል፡፡ ጥልቅ እውቀት ጥበብ ተአምራትና ድንቅ ስራዎች የነበሯቸው ሊቃውንቶች ነበሩን፡፡ በቅጡ ያደመጣቸው እውቀታቸውን ለማስቀረት የሞከረ የለም አሉና ‹‹ኤድያልኝ ኤድያ›› ብለው መሪጌታ በቁጭት ስሜት ወደኋላ በሀሳብ ሸመጠጡ። ጋለቡ ማለት ይቀላል።

መሪጌታ… መሪጌታ ብዬ ዝምታቸውን ለመስበር ዳዳኝ። ‹‹ምኑን ላስረዳህ በል›› አሉኝ እንደመባተት ብለው፡፡ የቱን አንስቼ የቱን ልተወው የሰማይ ከዋክብት ይቆጠራል ፤ የባህር ውቅያኖስ ታፍሶ ይዘለቃል ወይ ልጄ አሉ? የሊቃውንቶቻችን እውቀት ማለት እንዲህ ነው አሉኝ፡፡ ከመሪጌታነት—- መሪጌታነት ይበልጣል ወጉስ ማዕረጉስ? ሁኑበት መሪጌታ፤ ሁኑበት አልኩ አይን አይናቸውን እያየሁ፡፡

ይህ አይነቱ የጥንታዊ እውቀት ምጥቀት በቃልና በቋንቋ አይገለጽም፡፡ ምን ልበልህ ምኑ ተነክቶ ምኑ ይቀራል፤ ምኑስ ተወርቶ ምኑስ ይተዋል አሉና አንገታቸውን ወደ ሰማይ አሰገጉ።ያን ካባቸውን በተቀመጡበት ሁነው ግራና ቀኝ አዛንፈው ደረቡት፡፡ መሪ፤ መሪ፡፡ እጅግም የከተማው ሕይወት አይዋጥላቸውም፡፡ ወስላታ ፤ ወመቴ ፤ ቀጣፊ፤ ሰላውዲ የሚሏቸው ወካይ ቃላቶች አላቸው፡፡ ከተሜውን ይሄን ስልጡን ነኝ ባይ ሁሉ ሲወርፉት፡፡ እነዚህን አጥረግርጎ ወዲያ ማለት እንጂ ምን ረቡን፤ አሉ በቁጣ ስሜት ተውጠው ጭራቸውን ግራና ቀኝ እየነሰነሱ፡፡

ስር ማሽ፤ ቅጠል በጣሽ እያለ አበሻ የሚያጣጥለው አዋቂውን እኮ ነው። ለመድ ሀኒትነት የሚፈለገው ስር ያውም በብቸኝነት በሚያውቀው ሰው ተቆፍሮ ካልወጣ፤ ፈልጎ ካልቆረጠው መድሀኒቱም ሆነ ፈውሱ ከወዴት ይገኛል ሲሉ ጠየቁ። ፈረንጅ የእኛን የአባቶቻችንን ጥንታዊ የእፅዋት መጽ ሀፍ እየዘረፈ እያስተረጎመ አይደለም ወይ የሚጠቀመው ለመሆኑ ይሄ ትውልድ ይህን ያውቃል? ሲሉ መሪጌታ ጠየቁ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011

ወንድወሰን መኮንን