የፓራ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል

8

የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ከሐምሌ 8 ቀን/2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሂድ የቆየው አገር አቀፍ የፓራ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል። በቻምፒዮናው በመላ አፍሪካ ጨዋታና በኦሊምፒክ ፓራ አትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች እንደሚመረጡ ታውቋል።

በቻምፒዮናው አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ተሳታፊ ሲሆኑ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችም ተካፋይ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚም ተወዳዳሪ ሆነዋል።

ቻምፒዮናው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ በተለያዩ ፉክክሮች የፍፃሜ ውድድሮችን እያስተናገደ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል ሙሉ በሙሉ አይነስውራን በሆኑ ወንዶች መካከል የተካሄደው የመቶ ሜትር የሩጫ ውድድር አንዱ ነው። በዚህ ውድድር ታደሰ በቀለ 00፡11፡40 በሆነ ሰዓት በመግባት ከኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሆኗል። በተመሳሳይ ከኦሮሚያ ክልል መሐመድ ከድር 00፡11፡74 ሰዓት በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሆኗል።

እዮብ ሌንዳሞ ከደቡብ ክልል 00፡12፡16 በመግባት ሦስተኛ ሆኖ ውድድሩን ፈፅሟል። ሙሉ በሙሉ አይነስውራን ባልሆኑ ሴቶች መካከል የተካሄደው የመቶ ሜትር የሩጫ ውድድር ሞሚና አቡ ከኦሮሚያ ክልል 00፡13፡34 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ አበቡ ሞስየ ከአማራ ክልል 00፡ 14፡23 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ያምሮት ካሳ 00፡14፡ 90 በመግባት ከአማራ ክልል ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች።

የእጅ ጉዳት ባለባቸው ሴቶች መካከል በተካሄደው የመቶ ሜትር የሩጫ ውድድር 00፡13፡54 በመግባት ጥሩነሽ ደሳለኝ ከአማራ ክልል ቀዳሚ መሆን ችላለች። ሳባ ተራማጅ ከደቡብ ክልል 00፡14፡02 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ስትፈፅም በተመሳሳይ ከደቡብ ክልል መሰረት ዮሐንስ 00፡14፡36 ገብታ በሦስተኛነት ውድድሩን ጨርሳለች።

በወንዶች መካከል በተካሄደው ተመሳሳይ ውድድር ኤከር መቻል ከደቡብ ክልል በ00፡11፡29 ሰዓት አሸናፊ ሆኗል። ሮባ ደበሌ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ 00፡11፡ 52 በመግባት ሁለተኛ ሲሆን ቤዛ አለሙ ከአማራ ክልል 00፡11፡ 80 አስመዝግቦ በሦስተኛነት ጨርሷል። በወንድ ዊልቸር ተጠቃሚ 1ሺ500 ሜትር ውድድር ደምስ አበረ ከአዲስ አበባ 1ኛ ፣ ዮሴፍ ዓለሙ ከኦሮሚያ 2ኛ እንዲሁም ታከለ ፈለገህይወት ከአማራ 3ኛ በመሆን ጨርሰዋል።

ቻምፒዮናው ዛሬ ሲጠናቀቅ በስምንት መቶ ሜትር በሁሉም የጉዳት ዓይነቶች ውድድሮች የሚከናወኑ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ በርዝመት ዝላይ ሙሉ በሙሉ አይነስውራንና ጭላንጭል አይነስውራን እንዲሁም በእጅ ጉዳተኞች መካከል እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ የውድድር ክፍል ኃላፊ አቶ ዮናስ ገብረማርያም በውድድሩ ወቅት ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ስፖርት ውጤታማ ቢሆንም ካለው አካል ጉዳተኛ ቁጥር አኳያ በቂ አይደለም። ለዚህም ብዙ ምክንያቶችን ያስቀመጡ ሲሆን፣ በዋናነት የውድድሮች ማነስ፣ወጥ የሆነ የሥልጠና ሥርዓት አለመኖር፣የማዘውተሪያ ስፍራና ቁሳቁሶች አለመሟላት ስፖርቱን እንዳያድግ አድርገውታል።

ያም ሆኖ ባለፉት ሁለት የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በተለያየ ጊዜ አራት የነሐስ ሜዳሊያና አልጄርስ ላይ ሁለት ብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ ተመዝግቧል። ከነችግሮቻቸውም ቢሆን የፓራሊምፒክ አትሌቶች ውጤታማ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ዮናስ፤ ከዚህ በላይ ውጤታማ መሆን እየተቻለ በውድድርና በቁሳቁሶች እጥረት በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ አብራርተዋል።

የውድድሩን ዓላማ አስመልክተው የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ስጦታው እንደገለፁት፤ የፓራሊምክ ስፖርት በርካታ ስፖርቶችን ያቀፈ መሆኑ እና ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ፓራ አትሌቲክስ መሆኑን ጠቁመው፣ በፓራ አትሌቲክስ ኢትዮጵያ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ውጤታማ እየሆነች መምጣቷን ተናግረዋል።

በመሆኑም የዚህ ውድድር ዓላማ በቀጣይ በሚካሄዱ የፓራሊምፒክ መላ አፍሪካ ጨዋታ፣ የዓለም ቻምፒዮና እና የቶኪዮ ፓራሊምፒክ ለመሳተፍ የማጣሪያ ውድድሮች ስለሚካሄዱ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የመጀመሪያ ዙር ዕጩ የብሔራዊ ቡድን ለመምረጥ ታስቦ እንደተዘጋጀ አብራርተዋል። የብሔራዊ ቡድን ምርጫው በዚህ የሚያበቃ ሳይሆን በቀጣይ በሚካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ጥሩ ብቃት ያላቸው አትሌቶች እንደሚመረጡም አክለዋል ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011

ቦጋለ አበበ