ዋልያዎቹ ጅቡቲን ለመግጠም ልምምድ ጀምረዋል

8

የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) በመጪው ዓመት ጥር ወር መጀመሪያ ላይ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ካሜሩን አስተናጋጅነት ይከናወናል። የአስተናጋጅነቱን ክብር ያጣችው ኢትዮጵያ የቅድመ ማጣሪያ ድልድል ውስጥ መካተት ግድ ብሏታል።

በቅድመ ማጣሪያ ድልድሉ መሠረት ከጅቡቲ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጅቡቲን በሜዳዋ ትገጥማለች። ከሳምንት ቆይታ በኋላ የመልሱን ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ የምታደርግ ይሆናል። በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ዋልያዎቹ ከቀናት በኋላ ጅቡቲን ለመግጠም ዝግጅታቸውን ትናንት ጀም ረዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከትናንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ ልምምዱን ማድረግ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል። አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና ረዳቶቹ በቅርቡ 23 ተጫዋቾች ያሳወቁ ሲሆን፣ ግብ ጠባቂዎች መሳይ አያኖ ከሲዳማ ቡና፣ ተክለማርያም ሻንቆ ከሐዋሳ ከተማ፣ ምንተስኖት አሎ ከባህርዳር ከተማ ሲሆኑ፤ ተከላካዮች አስቻለው ታመነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ደስታ ደሙ ከወልዋሎ አዲግራት፣ ያሬድ ባየ ፋሲል ከተማ፣ ወንድሜነህ ደረጀ ከባህርዳር ከተማ፣ አህመድ ረሺድ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ጌቱ ኃይለማርያም ከሰበታ ከተማ፣ አምሳሉ ጥላሁን ፋሲል ከተማ፣ ረመዳን የሱፍ ስሁል ሽረ ናቸው።

አማካዮች አማኑኤል ዮሐንስ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ሙሉዓለም መስፍን ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀይደር ሸረፋ ከመቐለ 70 እንደርታ፣ አፈወርቅ ኃይሉ ከወልዋሎ አዲግራት፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፋሲል ከተማ፣ ታፈሰ ሰለሞንና ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ሐዋሳ ከተማ ሆነዋል። አጥቂዎች አቤል ያለው ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝና አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመቐለ 70 እንደርታ፣ አቡበክር ነስሩ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ሙጅብ ቃሲም ከፋሲል ከተማ እና ፍቃዱ ተክለማርያም ከመከላከያ መሆናቸው ታውቋል።

የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) በአገር ውስጥ ሊግ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን የሚያሳትፍ የውድድር መድረክ ሲሆን፤ በሁለት ዓመት አንዴ ይደረጋል። እኤአ 2009 የተጀመረው ቻን የመጀመሪያዋ ዋንጫ ኮትዲቯር ስታዘጋጅ፤ 2ኛውና እኤአ በ2011 የተካሄደውን ደግሞ ሱዳን አዘጋጅታለች። እኤአ በ2014 ደቡብ አፍሪካ ሦስተኛውን ስታስተናግድ፤ እኤአ በ2016 ሩዋንዳ 4ኛውን አዘጋጅታለች። በ2018 በሞሮኮ አዘጋጅነት ለ5ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ 6ኛውና እኤአ በ2020 የሚካሄደው የቻን ዋንጫ ደግሞ ወደ ምዕራብ አፍሪካ በመጓዝ ካሜሩን ቤት መግባቱ ተረጋግጧል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2011

ዳንኤል ዘነበ