የሀገራችንን ችግሮች ለመፍታት ምሁራን ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን ያፍልቁ!

11

አገር ከመሬት ተነስታ በምኞት ብቻ አታድግም የሚያስብላት፣ የሚቆረቁርላት እና ሊያሳድጋት የሚፈልግ፤ ፍላጎቱንም ለማሳካት የሚታትርላት ሰው ያስፈልጋታል። ይህ ታታሪ ሰው የተማረ ምሁር ከሆነ ደግሞ ያለምንም ጥያቄ አገር ማደጓ የማይቀር ነው። ምሁር ከሰው ሁሉ በላይ የሚያውቅ በመሆኑ የማያውቁትን መንገድ ያመላክታል።

ከማያውቁት ቀድሞ በመንቃት የወደፊቱን በመተንበይ መፍትሔዎችን ያስቀምጣል። ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ሲጓዙ ታዝቦ አያልፍም። መንገዱ የተሳሳተ መሆኑን በመጠቆም የመመለሻ መንገዱን ያሳያል። ያደጉት አገራት ምሁራኖች ይህንን ማድረግ በመቻላቸው ዛሬ ላይ ዜጎቻቸው ተንደላቀው መኖር እንዲችሉ ሌሎችን እንዲረዱ እና ለቀጣዩ ትውልድ ሀብት እንዲያስቀምጡ ማድረግ ችለዋል።

እርግጥ ነው፤ በኢትዮጵያ ብዙ ምሁራኖች ለአገር ብዙ ማድረግ የሚችሉ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ስልጣናቸውን ለማቆየት በሚንገበገቡ መንግሥታት በጅምላ እና በነጠላ በግፍ ተገድለዋል፤ በተለያየ መልኩ እንዲንገላቱ ራሳቸውን እንዲያጠፉ ከአገር ተሰደው ብን ብለው እንዲጠፉ ተደርገዋል።

በሌላ መልኩ ያሉት መንግሥታት የሚሠሩት ጥፋት ቢያበሳጫቸውም የባሰ ጥፋት እንዳይስፋፋ የጣሩ ምሁራንም አይጠፉም። አሁን ደግሞ ለውጥ አለ። በለውጡ ከዩኒቨርሲቲው እና ከየምርምር ተቋማት፤ ከተለያዩ አገራትም ኢትዮጵያውያን ምሁራኖች ብቅ በማለት አስተያየቶቻቸውን ሲሰጡ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች እየታዩ ነው። ከታዩትም በላይ ደግሞ ያልታዩና በተለያየ ቦታዎች ላይ እራሳቸውን ቀብረው አውቀው እንደማያውቁ ሆነው የሚኖሩም አይጠፉም። እነዚህ ምሁራን ዛሬ ቀና ብለው የሚያምኑበትን ሃሳብ ማስተላለፍ አለባቸው።

የሚያምኑበትን ሃሳብ ሲባል ደግሞ ‹‹የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መላልሶ›› እንደሚባለው ያለፈውን ስህተት ደጋግሞ መናገር አይደለም። ከፋም ለማ ባለፉት መንግሥታት ብዙ ስህተቶች ቢሠሩም የተሠሩ ጥሩ ነገሮችም ነበሩ። ያን ለታሪክ በመተው በቀጣይ ምን ይደረግ ለሚለው ምሁራን እየታዘቡ መንግሥትን ከመውቀስ ይልቅ በየጉዳዮች ላይ ጥናት በማድረግ ሃሳብ በማመንጨት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች የሚፈቱባቸውን መንገዶች ማመላከትና መንግሥትን መደገፍ ይጠበቅባቸዋል።

መንግሥት የሚሄድባቸው መንገዶች የተሳሳቱ ከሆኑም በድፍረት በመጠቆም አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረብ አለባቸው። ዛሬ ላይ እንደፈለጋችሁ ተሳተፉ በሚል ዕድል ተሰጥቷል። አጉል ተጠራጣሪ ከመሆን ተላቆ ተደራጅቶ ሳይንሳዊ መንገዶችን በመከተል አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት አገሪቷን ከመታደግ ባሻገር፤ ህዝቡንም ከከፋ ድህነት መታደግ ይገባል።

ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩ በተደጋጋሚ ቢገለጽም ዛሬም አርሶ አደሩ የሚያርሰው በበሬ ነው። ኢትዮጵያውያን የሚመገቡትን ምግብ ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ማምረት አልቻሉም። ስንዴ፣ ስኳር፣ ፍራፍሬ እና ሌሎች ምግቦች የሚመጡት ከውጭ አገራት ነው። በእርግጥ ያደጉት አገራትም ከውጭ አገር የሚመገቡትን ያስገባሉ።

ነገር ግን ሌሎች ብዛት ያላቸው ምርቶችን ደግሞ ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ። ወደ ውጭ የሚልኩት ወደ አገር ውስጥ ከሚያስገቡት ምርት ጋር የተመጣጠነ ነው ወይም ከሚያስገቡት በላይ ወደ ውጭ ይልካሉ። ኢትዮጵያ ግን ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ወደ ውጭ ከምትልከው ጋር የተመጣጠነ አይደለም።

ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው እጅግ የበዛ ነው። ይህንን ገንዘብ የምታገኘው ደግሞ በዕርዳታ ወይም በብድር ነው።

ብድር ተፀናውቶናል፤ ልመና መለያችን ሆኗል። ወደድንም ጠላንም ድህነት ዛሬም መገለጫችን ነው። በዚህ ላይ እዚህና እዚያ የሚጫሩት እሳቶች ልማቱን እየገቱ ተጨማሪ ፈተና ሆነዋል። መንግሥት ይህን ችግር መፍታት እንዳለበት ጥያቄ የለውም። ነገር ግን ችግሩ የሁሉም በመሆኑ ለመንግሥት ብቻ ሊተው አይገባም።

ምሁራኖች ሚናቸውን መወጣት አለባቸው። የማያውቀውን መመለስ፤ ከዚያም ባሻገር ጥናት በማካሄድ ላጋጠሙ ችግሮች መፍትሔ እንካችሁ ማለት ይገባል። ወቀሳ ክስና ስህተት ፈላጊነት አዋቂነት አይደለም። ማወቅ የተሳሳቱትን ማረም ነው። የተሳሳቱ መንገዶችን ማቅናትና ትክክለኛውን መንገድ ማስያዝም ነው።

ቁጥሩ ከፍተኛ ለሆነው ወጣት የሥራ ዕድል እንዴት ይፈጠር? እየተከሰቱ ያሉ የሰላም መደፍረሶች እንዴት ይስተካከሉ? የአርሶ አደሩ ህይወት እንዴት ይለወጥ? የወጣቶች ስነምግባር እንዲሻሻል ምን ይደረግ? የትምህርት ስርዓታችን በምን መልኩ ይስተካከል? ኢኮኖሚው በምን መልኩ ይደግ? ዝንት ዓመት ሲወራለት የኖረው የንግድ ስርዓት እንዴት ፈር ይያዝ? በአጠቃላይ የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በምን መልኩ ይቃኝና ድህነቱ ይብቃ? ለእነዚህና ሌሎችም ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ምሁራኖች በጥናት ላይ የተመሰረተ ሳይንሳዊ መልሶችን ማዘጋጀት አለባቸው። በየሙያ ማህበሩ ተደራጅተው ከመሥራት ባሻገር የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ግኝታቸውን ለመንግሥት ኃላፊዎች ማሳወቅና ሚናቸውን በመወጣት የነገዋን የበለፀገችዋን ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት ግድ ይላቸዋል!

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2011