ዓለምን ያነጋገረው የጋዜጠኛዋ ህልፈትና የአልሸባብ ዛቻ

15

የአፍሪካ ቅኝ ገዢዎች በአገሮች መካከል በዘፈቀደ ያሰመሯቸው ድንበሮች አንድ አገርን ከሌላ አገር ሲያጋጩ መቆየታቸው ይታወቃል። እነዚህ ድንበሮችም እስካሁን ድረስ የግጭት መንስኤ ሆነው የዘለቁ ሲሆን፤ የተለያዩ ጎሳዎችን ያቀፉ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ቅኝ ገዢዎቹ በሚከተሉት የአስተዳደር ዘይቤ በመከፋፈላቸውና ርዕስ በርዕስ እንዳይተማመኑ በመደረጋቸው በብዙ የአፍሪካ አገሮች በድኅረ ነፃነት ጦሱ አብሯቸው መዝለቁ አልቀረም።

በቅኝ ግዛት ዘመን ቅኝ ገዢዎች በአንድ አገር የጎሳ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ ፣ የሃይማኖትና አጠቃላይ የአስተዳደር ዘይቤ ልዩነት ብሎም መቃቃርን የሚያበረታቱ ስለነበር አለመተማመኑን በቀላሉ ማጥበብ ሳይቻል ቆይቷል።

በድኅረ ነፃነት ዘመንም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ትርጉም ያለው ዕርምት መውሰድ ባለመቻላቸው እና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ችግሮቹ ውስብስብ በመሆናቸው በተለያዩ ሰበቦች አፍሪካ በርዕስ በርዕስ ጦርነቶች እየተናጠች ትገኛለች። የአፍሪካን ጉዳይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፤ እነዚህ የርዕስ በርዕስ ጦርነቶች የወለዷቸው የሽብር ኃይሎች በአህጉሪቱ አያሌ ግፍና ሰቆቃን ከመፈፀም ባሻገር የዓለም ሠላም ሥጋት መሆን ከጀመሩ ቆይተዋል።

ለአብነትም የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የነበረው የዚያድባሬ የቀድሞውን መሪ ሰይድ መሐመድ ሐሰንን የዘመናት ህልም ለማሳካት፤ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት አካሄዶ ለተወሰነ ጊዜ የኢትዮጵያን ግዛት መቆጣጠር ችሎ ነበር። በኋላ በጦርነቱ ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ግዛት ከወጣ በኋላ በአገሪቱ በተፈጠረ የውስጥ ችግር ምክንያት የዚያድባሬ መንግሥት መንኮታኮቱን ተከትሎ አገሪቱ ወደ ለየለት የርዕስ በርዕስ ጦርነትና መከፋፈል ልትገባ ችላለች።

ይህ የርዕስ በርዕስ ጦርነት የወለደው የሽብር ቡድን ከወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሶማሊያ ብቅ ያለ ሲሆን፤ ‹‹ሀረካት ሸባብ አል ሙጅሃዲን›› ወይም ‹‹አልሸባብ›› ተብሎ የሚጠራው የሶማሊያ አሸባሪ ቡድን እ.ኤ.አ የካቲት 29 ቀን 2008 በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በአሸባሪ ቡድንነት ለመመዝገብ በቅቷል።

ቡድኑ እ.ኤ.አ በጥቅምት 2008 በአንድ ጊዜ በሁለት የሶማሊያ ከተሞች አምስት የአጥፍቶ ጠፊ መኪና ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎችን ተጠቅሞ በማፈንዳት 26 ሰዎች እንዲገደሉና ሌሎች 29 ሰዎች እንዲጎዱ አድርጓል። ቡድኑ እ.ኤ.አ በ2010 በኡጋንዳ ካምፓላ በአጥፍቶ ጠፊዎች 70 ሰዎችን እንዲገደሉ ከማድረጉም በላይ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሶማሊያ፣ በታንዛኒያና በኬንያ ለተካሄዱ አሰቃቂ የሽብር ጥቃቶች እጁ እንዳለበት ይታወቃል።

አገሪቷም ከፕሬዚዳንት ሞሐመድ ዚያድባሬ ውድቀት በኋላ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በላይ በጦር አበጋዞች ማን አለብኝነት ስትታመስ ዜጎቿም ለስደት፤ ለችግርና በሽታ ተዳርገው መክረማቸው ዓለም የሚያውቀው ሐቅ ነው። አገሪቷም ሕግ አልባና መንግሥት አልባ ሆና አንዱ ወገን የሽብርተኞች ምሽግ ሌላኛው ወገን ደግሞ ሽብርተኞችን አሳዳጅ ሆኖ በአገሪቱ ሠላም ከራቀ ሰነባብቷል።

በአገሪቷ የሠላም አየር እንዲነፍስ የተባበሩት መንግሥታት ባደረገው ጥረት አገሪቷ የራሷን መንግሥት ከረጅም ዓመታት በኋላ ያቋቋመች ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2017 የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ በበዓለ ሲመታቸው ሥነሥርዓት ባሰሙት ንግግር ሶማሊያን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቃል በመግባት፤የሶማሊያን መንግሥት ለሚወጋው ለአክራሪው የአልሸባብ ቡድን አባላት የሠላም ጥሪም አስተላልፈው ነበር።

ፕሬዚዳንቱ በሥልጣን ዘመናቸው የአገሪቱን ፀጥታ ለማስከበር፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፤ ሙስናን ለመዋጋት እና እርቀ ሠላም ለማውረድ እንደሚጥሩ ቃል በመግባት፤ በተለይ ተታለው አልሸባብን የተቀላቀሉ ወጣቶች ወደ መንግሥታቸው የሚመለሱ ከሆነ እጃችንን ዘርግተን እንቀበ ላችኋለን ብለው ነበር።

በወቅቱ ፕሬዚዳንቱ ይሄንን የሠላም ጥሪ ቢያስተላልፉም፤ ‹‹የሶማሊያ መንግሥት በሽብር እና አሸባሪዎች ላይ የያዘው አቋም አልተቀየረም በሚል ሰበብ የፕሬዚዳንቱን የሠላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው ፕሬዚዳንቱ በሚቆዩበት የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው እንዋጋቸዋልን›› ሲል የሽብር ቡድኑ ጦርነት አውጆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የአገሪቱ ህዝብም ከትናንት ዛሬ የተሻለ ቀን ይመጣል በሚል ተስፋ በአገሪቱ ሠላም እንዲመጣ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፤ ከአልቃ ይዳ ጋር ግንኙነት ያለው ይህ የሽብር ቡድን በሚያደርሰው የአጥፍቶ ማጥፋት ጥቃት የሶማ ሊያውያን ኑሮ ከድጡ ወደማጡ እያደረገው ነው።

በዚህም በአብዛኛዎቹ መገናኛ ብዙኃንና የዓለም አገራት ሶማሊያ የጦርነት ቀጣና፣ ድርቅ እና ረሃብ የማይለያት፤ የእርዛትና ጥማት ተመሳሌት እንዲሁም የርዕስ በርዕስ እልቂት ምሳሌ ሆና በዓለም ህዝብ ዘንድ ታውቃለች። አንዲት ሴት ግን ይህን አስቀያሚ የአገሪቱን መጥፎ ገጽታ ለመቀልበስ ተነሳች።

ይቺ ሴት ሆዳን ናላዬህ ትባላለች። ሆዳን በሰሜን ሶማሊያ ላስ አኖድ በምትባል ከተማ ብትወለድም ከ6 ዓመቷ ጀምሮ ያደገችው ካናዳ ውስጥ ነው። እርሷም ካናዳ በቆየችበት ጊዚያት ትምህርቷን በመከታተል በብሮድካስት ጋዜጠኝነት ሁለተኛ ዲግሪዋን በያዘች ማግስት፤ የራሷን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መሥራት ጀመረች።

ይህቺ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ አካሏ ካናዳ ቢሆንም ሁሌም ሐሳቧ ሶማሊያ በመሆኑ፤ አገሯን ዓለም ከሚያውቀው የተመሰቃቀለ ታሪኳ ባሻገር ያለውን የሶማሊያን ውበት፣ መልካም ገጽታና የሕዝቧን ትስስር ለተቀረው ዓለም ለማሳየት ቆርጣ የተነሳች ሴት በመሆኗ ከዓመት በፊት ከካናዳ ወደ ሶማሊያ ተመለሰች። እርሷም ዓላማ ያደረገችው በዓለም ላይ እንደ አሸዋ የተበተኑ የአገሪቷን ሕዝቦች በተለይም ውጭ አገር ያደጉ የሶማሊያ ወጣቶችን ማነቃቃትና አገራቸውን እንዲወዱ ማድረግ ነበር።

‹‹ሶማሊያ ጦርነት ብቻ አይደለም ያለው…፣ ሕይወት አለ፣ ፍቅር አለ…›› እያለች በጦርነትና በድርቅ የተደበቀውን የአገሯን ውበት ለዓለም ህዝብ በማስተዋወቅ የአገሯን ገጽታ ለመቀየር ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዘችው። ብዙዎች ትውልደ ሶማሊያዊያን በእርሷ አነቃቂ የጋዜጠኝነት ሥራዎች ምክንያት ወደ አገራቸው መትመም ጀመሩ። ዓለምም አድናቆቱን እያደር ይቸራት ጀመር። እርሷም ሶማሊያ ከጎሰቆለው ታሪኳ በስተጀርባ ያለውን ውበቷን ለዓለም ህዝብ በብሮድካስት እና በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ማስተዋወቁን እያደር አጧጧፈችው።

በዚህም ናላዬህ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ከኪስማዮ ከተማ ወጣ ብሎ ወደ ሚገኝ ስፍራ በማቅናት አሳ እያጠመዱ ለገብያ ስለሚያቀርቡ የሶማሊያ ወጣቶች እና ስለአካባቢው ውብ ተፍጥሮ በትዊተር ገጿ ለዓለም ህዝብ በማስተዋወቅ ከፍተኛ አድንቆትን አግኝታ ነበር።

ይቺ በመላው ዓለም የሶማሊያ አምባሳደር ሆና ትታይ የነበረችው ናላዬህ ይህን ባደረገች ማግስት በደቡባዊ ሶማሊያ ኪስማዮ ከተማ ባረፈችበት አንድ ሆቴል ውስጥ በታጣቂዎች በደረሰ ድንገተኛ ጥቃት መገደሏ ታውቋል። ጥቃቱ የተፈፀመው በአሳሰይ ሆቴል የአገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎችና ፖለቲከኞች መጪውን የአካባቢ ምርጫ ተአማኒና ዲሞክራሲያዊ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተወያዩ በነበረበት ወቅት ሲሆን፤ በዚህ ጥቃት እርሷና ባለቤቷን ጨምሮ 26 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

ይህ ጥቃት የበርካታ ሶማሊያዊያንና በተለይም የእርሷን ሥራዎች የሚከታተሉ፤ የእርሷን ተስፋ የሚመገቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በዓለም ዙሪያ ያሉ አድናቂዎቿን ቅስም ሰብሯል። ናላዬህ በጥቃቱ ሰለባ ስትሆን 43 ዓመቷ እንደሆነና የሁለት ልጅችም እናት መሆኗ ተገልጿል። ቤተሰቦቿ በፌስቡክ ገፃቸው እንዳሳወቁት ‹‹በተገደለችበት ወቅትም ነፍሰ ጡር ነበረች›› ብለዋል።

በአንድ ወቅት ሟቿ ናላዬህ ወደ ፊት በምን እንድትታወስ እንደምትፈልግ ተጠይቃ፤ ‹‹እኔ ገንዘብም ዝናም ብዙም አይማርከኝም፤ ለኔ ትልቁ ህልም የሶማሊያን አንድነት ማየት ነው… የምኖረው ያን ለማሳካት ነው›› ስትል ተናግራ ነበር።

«ብሩህ አዕምሮና ውብ ነፍስ የታደለች» ስትል ቢቢሲ የምትሠራዋ ጓደኛዋ ፋርሃን ናላዬህን የገለፀቻት ሲሆን፤ የእርሷ መገደል ይበልጥ ሶማሊያዊያን እንዲቀራረቡና የቆመችለትን ዓለማ ወደ ፊት እንዲገፉ የሚያደርጋቸው ነው ስትል ተናግራለች።

የአገሪቱ ባለስልጣናት በበኩላቸው ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ነገሩን በማየት የደረሰውን አደጋ እንደሚያስረዱት፤ ጥቃቱ የደረሰው ቦንብ የጫነ የአጥፍቶ ጠፊ መኪና ወደ አሳሴይ ሆቴል ጥሶ ከገባ በኋላ በመፈንዳቱ ነው። ከፍንዳታው በኋላ መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ ወደ ሆቴሉ በመግባት በሆቴሉ በነበሩ ሰዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ግድያና ጉዳት ማድረሱን ገልፀዋል።

የደህንነት አባል የሆነው አብዲ ዱሁል ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገረው፤ በጥቃቱ 26 ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ገልፆ፤ ከሞቱት መካከል የቀድሞው የአካባቢው አስተዳዳሪ የነበሩት ሰው እንደሚገኙበት ጠቁሟል። በተጨማሪም ከሟቾቹ መካከል ሦስት ኬኒያውያን ሦስት ታንዛኒያውያን እንዲሁም ሁለት አሜሪካውያንና አንድ የእንግሊዝ ዜጎች እንደሚገኙበት ባለሥልጣኑ አረጋግጠዋል።

የአካባቢው መገናኛ ብዙኀን እና የሶማሊያ ጋዜጠኞች ማኅበር ደግሞ የ43 ዓመቷ በትውልድ ሶማሊያዊቷ በዜግነት ካናዳዊቷ የሆነችው ታዋቂዋ የቴለቪዥን ጋዜጠኛ ናላዬህ እና ባለቤቷ ከሞቱት መካከል መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የሶማሊያው ታጣቂ እስላማዊ ቡድን አልሸባብ በበኩሉ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን በመውሰድ፤ የፓርላማ አባል የሚሆኑ እጩዎችን አቅርበዋል ያላቸውን የጎሳ መሪዎች ‹‹ከሃዲዎች›› በማለት ከጥቃቱ በኋላ መግለጫ አውጥቷል። ቡድኑም በመግለጫው ‹‹ለከሃዲው የሶማሊያ ምክር ቤት አባልነት እጩዎችን የሰየሙ የጎሳ መሪ የተባሉት ግለሰቦች ኢአማኒ መሆናቸውን በግልጽ አስመስክረዋል፤ የእስልምና እምነታቸውን ዋጋ አሳጥተውታል›› ሲል ቡድኑ በድረገፁ ባወጣው መግለጫ ዘልፏቸዋል።

አልሸባብ በመግለጫው አክሎም የጎሳ መሪዎቹ ፈፀሙት ላለው ሐጢያት በ45 ቀናት ውስጥ ‹‹ንስሐ›› እንዲገቡ ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ ካልሆነ ግን የጂሃዳዊ ቡድኑ ኢላማ በመሆን እንደሚገደሉ አሳውቋል። አልሻባብ ጨምሮም የጎሳ ሽማግሌዎች ክልላዊ አስተዳደርን በመመስረቱ ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፉም አሳስቧል።

ይህ የማስጠንቀቂያ መግለጫ በእስላማዊ ቡድኑ የወጣው ጁባላንድና ጋልሙዱግ በተባሉት የሶማሊያ ግዛቶች ውስጥ ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅት ሲሆን፤ ቡድኑም ይህ ምርጫ እንዳይካሄድ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ እንደሚያስቀር በመግለጫው ጠቁሟል።

ከአልቃኢዳ ጋር ትስስር እንዳለው የሚነገርለት አልሸባብ ቀደም ሲል ሲቆጣጠራቸው ከነበሩ አብዛኞቹ ዋነኛ የሶማሊያ ከተሞች ተገፍቶ የወጣ ቢሆንም አሁንም የአገሪቱ ከፍተኛ የደህንነት ሥጋት እንደሆነ ይገኛል። በተጨማሪም ይህ ታጣቂ እስላማዊ ቡድን በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈውን የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥትን ለመጣል እየተፋለመ ሲሆን፤ በተለያዩ ቦታዎች ተከታታይ ጥቃቶችን ሲፈፅም ቆይቷል። ቀደም ሲል በተካሄዱ የሶማሊያ ክልላዊ ምርጫዎች ላይ የቀረቡ በርካታ ዕጩዎችን መግደሉም ይታወሳል።

አዲስ ዘመን ሀምሌ 12/2011

 ሶሎሞን በየነ