ኢትዮ ቴሌኮምን ከመሸጥ ይልቅ ተወዳዳሪዎችን ማስገባት የተሻለ መሆኑ ተገለፀ

122

አዲስ አበባ፡- የኢትዮ ቴለኮምን ድርሻ መሸጥ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ተጨማሪ ተወዳዳሪ ድርጅቶችን ማስገባት ላይ በዋናነት ሊተኮር እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በዓለም አቀፉ ቴሌኮሙኒኬሽን ማህበር እና በተለያዩ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ድርጅቶች በከፍተኛ ኃላፊነት ደረጃ ለ50 ዓመታት የሰሩት ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ እንደገለጹት፤ የቴሌ ኮምዩኒኬሽን ዘርፍ ቁልፍ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መንገድ በመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮምን መሸጥ አግባብ አይደለም። ከዚያ ይልቅም ተወዳዳሪዎችን ማስገባት በመንግስት ስር ያለውን ኢትዮ ቴሌኮምን ተወዳዳሪ ለማድረግ ይረዳል።

እንደ ኢንጂነር ተረፈ ገለጻ፤ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ለአንድ አገር የደህንነት ስራ፣ ከሚዲያ እና ከግብርና እና ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። የውጭ ድርጅት ሲገባ ግን ቁጥጥር ቢደረግበት እንኳን ይህን ሁሉ የአገር ጥቅም ሊያስከብር አይችልም። በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮምን 49 በመቶ መሸጥ የሚለው ጉዳይ ላይ ጠንቀቅ ማለት ያስፈልጋል።

ድርጅቱን ብቁ ማድረግ እና አገልግሎቱን ተወዳዳሪ ማድረግ ካስፈለገ እንኳን ማኔጅመንቱ ቢዝነስ ላይ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ ማሻሻል ይቻላል። ለዚህ ደግሞ በመንግስት ስር ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥሩ ምሳሌ ስለሚሆን ቴሌን ከመሸጥ ተጨማሪ ኦፕሬተር ድርጅቶችን ማስገባት ላይ ሊተኮር ይገባል።

«ቴሌኮም ድርጅታቸውን የሚሸጡት በአብዛኛው የአፍሪካ አገራት ናቸው» የሚሉት ኢንጂነር ተረፈ፤ ከእነዚህም መካከል ዩጋንዳና የታንዛኒያ መንግስት ከዘርፉ ጥቅም አልባ መሆናቸው ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል። እንደ ሲንጋፖር፣ ቻይና፣ ህንድ እና ሌሎችም የእስያ አገራት ግን ቴሌኮሙዩኒኬሽናቸውን በመንግስት ይዞታ ስር በማድረጋቸው ከገቢም ሆነ ከደህንነት ስራ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር ፖሊሲዎቻቸውን ለማስፈጸም የሚጠቀሙበት መሆኑን አብራርተዋል።በተለይም ህንድ ሁለት የመንግስት እጅ ያለባቸው ትላልቅ ኦፕሬተሮችን በመያዝ ለ78 ተወዳዳሪ ድርጅቶች ፍቃድ ተሰጥቶ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ኢንጂነር ተረፈ ገለፃ፤ በኢትዮጵያም የኢትዮ ቴሌኮምን አቅም ለማሳደግ 49 በመቶውን ይሸጥ የሚለውን ሃሳብ በመተው እራሳቸውን ችለው የሚሰሩ ተወዳዳሪ ድርጅቶች ብቻ ማስገባት ያስፈልጋል። ከውሳኔው በፊት ግን በጉዳዩ ላይም ከሙያተኞች ጋር ሰፊ ክርክር እና ውይይት በማድረግ ለአገር የሚበጀውን ለመምረጥ መድረክ መክፈት ወሳኝ ነው፡፡

በተለያዩ አገራት በቴሌኮም ዘርፈ የሰሩት አቶ ታከለ መኮንን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ቴሌን መሸጥ ሳይሆን ብቃት ያላቸው ሁለትና ሶስት ተፎካካሪ ድርጅቶችን መርጦ ማስገባት ይገባል። ቴሌን መሸጥ ግን የአገርን ጥቅም ለማስከበር አያመችም። በተለይ የግል ተቋማት ሲገዙ መንግስት ተገቢውን ቁጥጥር ቢያደርግ እንኳን ካላቸው ቴክኖሎጂ እና አሰራር ዘመናዊነት አንጻር ሊቆጣጠራቸው ይቸገራል።

በዓለም የሚታየው ዕውነታ የቴሌኮም ድርጅታቸውን የሸጡ ሀገራት ሳይሆኑ ተወዳዳሪ ያስገቡ አገራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ተፎካካሪ ሲገባ ኢትዮ ቴሌኮምም አገልግሎቱን ሆነ ቴክኖሎጂውን የበለጠ ለማሻሻል የሚያነሳሳ መሆኑን አስረድተዋል። የንግድ ሂደቱ የግድ መቆየት ስላለበት ኢትዮ ቴሌኮም እራሱን እያደራጀ ሊቀጥል የሚችለው ተወዳዳሪዎች ቢገቡለት መሆኑን ጠቅሰው፤ መሸጡ ግን የመንግስትን አቅም የሚያዳከም መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ደግሞ፤ መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ 49 በመቶ ለመሸጥ መዘጋጀቱ ጥቅም እና ጉዳቱ ላይ ሰፊ ጥናት ተደርጎበት ነው። የበርካታ አገራት ተሞክሮም ተወስዷል። የቴሌኮሙኒኬሽን ገበያ ለግሉ ዘርፍ መከፈቱ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በተጨማሪም በዲጂታል መሠረተ ልማት የነበረውን ክፍተት በማሻሻል በኢኮኖሚው መስክ ኢትዮጵያን ወደፊት ያራምዳል፡፡

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና በማስፋፋት ረገድም ትልቅ ድርሻ የሚኖረው መሆኑን አስገንዝበው፤ በተጨማሪም እጅግ ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎት መኖር በቴክኖሎጂ የመጠቁ የኢንዱስትሪ ምርቶች በሀገሪቱ እንዲመረቱ የሚያመቻች መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሀገሪቱ የዲጂታል መሠረተ ልማትን ማሳደጓም አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦች እንዲታዩ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮምን ለኢንቨስተሮች ከፍሎ መሸጡ እና ተጨማሪ ተወዳዳሪዎችን ለማስገባት መታቀዱ ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13/2011

 ጌትነት ተስፋማርያም