በጉን ማን አውሬ አደረገው?

12

ዓለማችን በታሪኳ ካየቻቸው ታላላቅ ሰዎች አንዷ የናዚ ጭካኔ ሰለባ የነበረችው እንቦቆቅላዋ አና ፍራንክ ተፈጥሯዊ በሆነ ዕይታ የይቅርታን መሰረት በሚጥል መልኩ የሰው ልጆችን መሰረት በጎነት የመዘነው ህሊናዋ ነበር። አና ከአስከፊው የግፍ ግድያና ጭፍጨፋ በህይወት ተርፋ ገጠመኞቿን ለመተረክ ባትበቃም ቅሉ ከእጇ በማትለያት ትንሽዬ የዕለት ማስታወሻዋ ያሰፈረቻቸው ዕይታዎቿ ድንቅ ነበሩና በህይወት ከነበሩት የናዚ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ጄነራሎች በላይ ዓለም የሚያወድሳት፣ በክብር የሚያወሳትና በምሳሌነት ህያው አደረጓት እንጂ ስሟም እንደ ስጋዋ ትቢያ ለብሶ እንዲቀር ማድረግ አልተቻላቸውም።

በተለይም በቤተሰቧና በዘሯ ላይ ሲደርስ ያየችው አሰቃቂ ግፍ ያሳደረባት ስነ-ልቦናዊ ስብራት ሳያንስ በጨቅላነቷ መራሩን ስቃይ ግተው የሞት ፅዋ ያስጎነጯት ናዚዎች ድርጊት ሊበርዘው ካልቻለ ጠንካራ መንፈሷ የፈለቀው “ማንም ሰው ከመሰረቱ መጥፎ አይደለም ሁኔታዎች መጥፎ እንዲሆን ያደርጉታል እንጂ..” የሚል ንግግሯ ዛሬም ድረስ ዓለምን እንዳስደመመ ስሟም ከስሞች ሁሉ በላይ እንዲነሳ ያደረገ የታላቅነቷ አብይ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የምትክ የለሽ ዕንቁ ሰብዕና ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ይህ ንግግር የአና ታላቅነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን ዛሬ አይሁዳውያን ጥቁር ጠባሳቸውን በይቅርታ ሽረው ከጀርመኖችም ሆነ ሌላ ህዝብና መንግስታት ጋር ስለ ሰላምና ትብብር ጉዳይ በአንድ ጠረጴዛ እንዲያወሩ መሰረት የጣለ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። በዛች ትንሽ የ15 ዓመት ልጅ የተተየበችው ትንሽዬ ማስታወሻ (ዲያሪ) ምናልባትም በጀርመንና አይሁዳውያን ቁርሾ መናጥ አይቀሬ የነበረባትን ግዙፍ ዓለም መፃኢ የታሪክ አቅጣጫ ቀይሮ ህዝቦችን በይቅርታ የዋጀ ጠበል ነበረ ቢባልም ማጋነን አይሆንም።

ለማንም ምንም የነበሩት፤ እረኛ እንደሌለው በግ መንግስት እንኳ ያልነበራቸው ህዝቦች፣ ሀገር፣ ርስት አፈር አጥተው በየአገኙበት የተበተኑት ቤት አልባዎች ዓለምን የሚዘውር ጡንቻ ባፈረጠሙበት፣ የምድሪቱ ባንክ፣ ንግድና ቴክኖሎጂ ቋት ያዥ ለመሆን በበቁበት በዛሬው ሁኔታ የአና ፍራንክ አስተሳሰብ ባይኖር ምን ሊከሰት እንደሚችል አያዳግትም። ምናልባትም ጥቃት እንደጀመሩባቸው ከሚወሱት የሮማ ግዛት ነዋሪዎች አንስቶ ጀርመናውያንም ሆኑ ግብራበሮቻቸው ትንሽም ቢሆን ገፈቱን እንዲቀምሱ መፈለጋቸው ባልቀረ ነበር። ነገር ግን የአና ፍራንክም ሆነ ያሉበት ዘመን አስተሳሰብ ይህንን እንዳልፈቀደ ለተገነዘቡት መሪዎቻቸው ምስጋና ይግባና ዛሬ እስራዔል በሚል የመሰረቷት ሀገርና አይሁዳውያን ድምፃቸውን አጥፍተው የዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ሚሊተሪ ሳይንስ ቁንጮ ለመሆን በቅተዋል። እዚህ ላይ ደግሞ ከፍልስጤምና ሌሎችም አረብ ሀገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በወንድማማችነት መንፈስ መፍታት ችለው መልካም ግንኙነት ቢመስርቱ ሁለቱም ህዝቦች ከግጭቱ በላይ የበለጠ ከሰላም ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። ይህ የመላው ኢትዮጵያውያንም ሆነ ዓለም ህዝቦች ምኞት ነው።

እንደ አና ፍራንክ ካሰብን ማንም ይሁን ማን የተገደለው፣ የቆሰለው የታሰረው ሰው መሆኑን መዘንጋት የለብንም ምክንያቱም ሟች ሲወለድ በሰው እጅ ለመሞት እንዳልተወለደ ሁሉ ገዳይም ለመግደል ታስቦ ክላሽ ወይም የገዳይነት ስነ-ልቦና ይዞ አልተወለደም። ይህች ዓለም ያስታጠቀችውን የክፋት ጦር ዕቃ ታጥቆ፣ በዚች ዓለም መጥፎ እሳቤ ተጠምቆ ጨካኝ በሆነ ሰው ማንም ሲጎዳ ያማል፣ ማንም ሲታኮስ ይረብሻል፣ ማንም ሲሞት ሀዘኑ ጥልቅ ይሰብራል። ሰው ለሆነ ሰው ማለቴ ነው።

ታዲያ ማንኛውም የሰው ልጅ ከመሰረቱ መጥፎ ካልሆነ፤ ሁሉም ሰው በተፈጥሮው መልካም ከሆነ ማን ማንን መጥፎ አደረገው? ምንስ ዓለምን እንዲህ የጭካኔ ገበታ አደረጋት? ብለን እናስብ ይሆናል። የስነ-ህዝብ፣ ማህበረሰብና ኢኮኖሚያዊ ሳይንስ ሊሂቃን ተብዬዎች ቻርለስ ዳርዊንን ጨምሮ ለዚህ የሚሰጡን ምላሽ በህዝብ ቁጥር መጨመር፣ በተፈጥሮ በብዛት ጥቅም ላይ መዋልና መዛባት ምክንያት የሚፈጠር የምርታማነት መቀነስ፣ የሀብት እጥረት እንዲሁም የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣምን ተከትሎ የሚከሰት እሽቅድምድም የህዝቦችና ሀገራት ግጭት በኋላም የሰው ልጆች እልቂት መነሻ ነው ብለው ያምናሉ። ይህም ኢቮሉሽን ቲዎሪ በሚል በሀገራችን ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካቶ ስንማረው እናድግና እኛም የአብሮነትና መቻቻልን ከውስጣችን አሽቀንጥረን በመጣል “ተቋቁሞ ያሸነፈ በህይወት ይቆያል… ተሸናፊው ደግሞ ቦታውን ላሸናፊ ይለቃል” `The fittest will survive` በሚለው ሰይጣናዊ ዕሳቤ እንጠመቃለን።

እናም አምላኩ ሰላም አውሎ ሰላም ስላሳደረው ብቻ የሚያመሰግን፤ የህሊና እረፍት፣ የፍላጎት ገደብ፣ ባለው ልክ መብቃቃት ከምንም በላይ የሚበልጥበት፤ ከፈጣሪው ሰማያዊ ጥበብ፣ በረከትና ቸርነት ውጪ ሌላ ሌላው ምኑም ያይደለ ሰው የቤተክርስቲያንና መስጅድን ደጅ በጠና ለመዝረፍ የቋመጠለትን ምድራዊ ወርቅና ገንዘብ እንደሚጋራው አልያም ቀድሞት እንደሚወስድ በማሰብ ምስኪኑ ሃይማኖተኛ ሰው ባላወቀውና ባላሰበው ነገር ሲያሳድደው የሚኖር፣ መቆሚያ መቀመጫ፣ መግቢያ መውጫ የሚያሳጣ፣ ባስ ሲልም በሀሰት ኮንኖ የማይችለውን መከራ የሚግተው ዕድሜ የጠገበ የእንጨት ሽበት ከትንሽዬዋ አና ፍራንክ ቢማር ባይ ነኝ።

ለዚህ ደግሞ እንደኛ ሀገር የኛ ያልሆነውን “ያሸነፈ በህይወት ይቆያል…ተሸናፊው ደግሞ ቦታውን ላሸናፊ ይለቃል” `The fittest will survive` የሚለውን ዝግመተ ለውጥ /የኢቮሉሽን ቲዎሪ/ዕሳቤና አስተምህሮ ለባለቤቶቹ ትቶ “አሁንም ሆነ ወደፊት የሰው ልጅ የሚያስፈልገው ሁሉ ሳይጎድለው ተፋቅሮ፣ ተሳስቦና ተዋዶ በህብረት እንዲኖር ሁሉም ነገር በጥንቃቄ ተሰልቶ፣ ታስቦና ታልሞ የተፈጠረ ማህበራዊ እንስሳ ነው። ያንዱ መብላት ሌላውን አያስርበውም፣ ያንዱ ማግኘት ሌላውን አያሳጣውም፣ ያንዱ ምልዓት ሌላውን አያጎድለውም” በሚለው ህያው የግበረ-ገብና ሰብዓዊ ለዛ ያሸበረቁ ሊቅ አባቶቻችን ሃይማኖታዊና ፍልስፍና ነክ ዕይታዎች እንመራ። ሁላችንም ዓለማችንንም ሆነ የሰውን ልጅ የትኛው ወደ ጥፋት ይመራል የትኛውስ ከጥፋት ይታደጋል የሚለውን እንለይ።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 13/2011

 አንድአርጋቸው ምንዳ