‹‹እንዲያው መላ ሰውነቴን ይዞ …››

13

በመሠረቱ በዚህች በሰፈርንባት ምድር ‹‹ይህን ያህል ያልታመሙ በሽተኞች ይገኛሉ›› ብሎ አኃዛዊ መግለጫ ለማውጣት፣ ግራና ቀኝ በሠንጠረዥ አድርጎ ማረጋገጫ ለመስጠት የሚቻል አይደለም። ይህን መረዳት ይገባናል። ስለምን? ‹‹ጤና ይስጥልኝ! ዶክተር!! ያልታመምኩ በሽተኛ መጥቼአለሁና አክመኝ›› በማለት ረድኤት የለመነ ሰው መኖሩን ከማለዳው ያመነ እስካሁን አልተገኘመና!! እንዲህ በመሆኑ ያን ‹‹ ታምሜአለሁ›› እያለ ጠዋት ማታ በብርቱ የሚወተውተውን ሰው መርምሮ ‹‹የደዌውን ›› ምሥጢር ተመራምሮ ኋላም የታመመውን ካልታመመው ሠንጥሮ ለማወቅ፣ ለማስታወቅ ባለሙያ ሲለፋ ጊዜ ሲጠፋ ይገኛልና! ይህ ‹‹ዓቢይ›› የሚባለው ችግር ነው።

በአንድ በኩል ችግሩ ይህ ሆኖ ሳለ በሌላ በኩል ደግሞ ትኩረት የመንፈጉ ነገር ነው። በሰነዶች እንደ ተመለከተው በሌላ ቁጥር ሥፍር ለሌለው፣ ብዛቱም ለማይዘረዘር አካላዊ፣ ልቦናዊ ጉስቁልና ማዕምራዊ ትድግና ይደረግ ዘንድ በዚህ በዛሬው ዘመን በርካታ ምርምሮች ተካሂደዋል። ግና እልፍ አእላፍ የሰው ልጆች ተይዘው መከራ የሚቆጥሩበትን ‹‹ሕመም አልባ ሕመም›› ከሥርወ መሠረቱ ሲፈትሹ፣ መፍትሔ ሲሹ የተስተዋሉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እጅግም አልነበሩ።

‹‹ዘጠኝ ዓመት ሙሉ በአምስት መቶ አሥራ ሁለት ሕሙማን ላይ ጥልቅ ምርምር ተደረገ። ሥፍራው በብሪታንያ መናገሻ በሎንዶን ነው። ባለፋት ዓመታት ውስጥ የተደረገው እርሱ ብቻ ነው›› ይላሉ ሰነዱ።

ሆኖም ፈረንጆች ‹‹ሀይፖንድሪያሲስ›› የሚባለውን ‹‹ሕመም አልባ ሕመም›› የሚቆልለውንም ክቡድ ጫና ያልናቁ መዘዙን ጠንቀቅው ያወቁ ለሰው ልጅ ሕላዌ አጥብቀው የተጨነቁ ሙሁራን ምስጋና ይድረሳቸውና ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያካሄዱት ጥልቅ ምርምር ምን እንኳ ‹‹መጨረሻ›› ሊባል ባይችል ወደ ፊት ለሚጠናቀሩት መዛግብተ ጥናት ‹‹መነሻ›› ሊሰኝ መብቃቱን የተጠራጠሩ የሉም።

እንዲህም ሲሆን በዚህ ጹሑፍ ወደተጠቀሰው በተጓዳኝ አልባነት ሕይወታቸውን የሚመሩ ሚስት ወይም ባል ሳያገቡ ብቻቸውን የሚኖሩ ለ‹‹ሀፖይኮንድሪያሲስ›› እጅግም ያልተጋለጡ መሆናቸውን ወደሚገልፀው መዝገበ ጥናት እንዝለቅ።

በፈታሾች እገማገም በአሁን ወቅት ያልታመሙ በሽተኞች ሆነው የተገኙት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ናቸው። ከሰፈረው አኃዛዊ መዘርዝር መረዳት እንደተቻለው ወንዶች በሠላሣውና በሠላሳ ዘጠነኛው መሐከል ባለው ዕድሜ፣ ሴቶች ደግሞ በዐርባና ዐርባ ዘጠኝ መሐከል ባለው ዕድሜ ነው ያልታመሙ በሽተኞች ሆነው በብርቱ የሚማቅቁት። በ‹‹ሀይፖኮንድሪያሲስ›› ከተያዙት ውስጥ ስድሣ ስድስት በመቶ ያህሉ ሴቶችና ወንዶች በጋብቻ የተጣመሩ፣ ወይም በወዳጅነት የተሳሰሩ፣ አብረውም የሚኖሩ መሆናቸው ሳይረጋገጥ አልቀረም። ያልታመሙ በሽተኞች ስለሚመርጡት እና እንዲያ ሲልም ‹‹የደዌ አቤቱታ››፣ ክፍለ አካል ወዘተ እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹…ራሴ የእኔ አይደለም። ጉሮሮዬን ደግሞ ምን እንደነካኝ አላውቅም። እንደ መከርከር እንደ መጠዝጠዝም ይለኛል›› ይህ ባልታመሙ በሽተኞች ነጋ ጠባ የሚደመጥ ነው። በአንድ ፈታሽ አገላለጽም ‹‹ለራስና ለጉሮሮ ቅድሚያ ይሰጣል።›› በአመዛኙ ያልታመሙ በሽተኞች የሚደመጠው ይኸው ነው።

ከዚያስ በኋላ ምን ይቀጥላል? ምላሹን አሁንም ከጥናታዊው ሰነድ፡-

‹‹…ከዚያ ወዲያማ ምኑ ቅጡ!! ውጋት የእጅና የእግር መገትገት፣ የሰውነት መከትከት፣ የወገብ ቁርጥ ማለት፣ ከየት መጣ የማይባል የጆሮ ደወል መስማት፣ እንዲያው መላ ሰውቴን…›› ይመጣል። ሁልጊዜ ይህን መሰል ጩኸት ይደመጣል።

በሎንዶን ተሠይመው ምርመራቸውን ያካሄዱ ሊቃውንት እንደሚያስረዱት ቆየትየት ባለው ዘመን ያልታመሙ በሽተኞች ከባድ ሥጋት የሳምባ ነቀርሳና የቂጥኝ በሽታ መሆኑ የሚያጠራጥር አልመሰለም። ስለምን? ለዓመታት እርጅና በምስክርነት ሊቆም በበቃ በዚያ ዘመን ሳያሰልሱ ከሐኪም ወደ ሐኪም እየዞሩ ‹‹መርምሩን ታመናል በበሽታው ተለክፈናል ›› በማለት ያስቸገሩን ሰዎች በቁጥር ጥቂት እንዳልነበሩ የሚያረጋግጡ ወረቀቶች በአስረጅነት ተጠቅሰዋልና።

ይህን በዚህ አቆይተን ‹‹ተጓደኝ አልባ የሆኑቱ በሀይፓኮንድሪያሲስ እጅግም የማይጠቁ አግብተው ወይም እንደነገሩ ተወዳጅተው አብረው የሚኖሩ ደግሞ በአመዛኙ በሕመም አልባ ሕመም ተይዘው የሚማቅቁ ናቸው›› በሚል መደምደሚያ መደረሱን አንብበናል።

የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ መዝገበ ጥናቱን ተመርኩዞ ምጥን ትንታኔ ለማቅረብ ከሞከረበት ጊዜ አንሥቶ በተለይ ለዚህ ነጥብ ልዩ ትኩረት ከመስጠት አልቦዘነም።

ነገር ግን በቅድሚያ ለአንባቢ ግልፅ መሆን ያለበት ‹‹ያገባ ይታመማል፣ ያላገባ በጤነኝነቱ ይዘልቃል›› ለማለት ያልተደፈረ ይህን መሰልም የይሁንታ ብያኔ ለመስጠት ፍጹም ያልተሞከረ መሆኑን ነው። ይህን ልብ ማለት ያሻል።

ወደ ጉዳዩ እንመለስና ብዙውን ጊዜ እዚህ በሀገራችን እንደሚታየው ባል ወይም ሚስት ቀን በየተግባራቸው ውለው ማታ ሲገናኙ በነገር የማይጣጣሙ በሐሳብ የማይስማሙ ከሆነ በቅድሚያ ስለማጀቱና ስለቤቱ ጉድለት ስለመኖው እጥረት ስለማገዶው እጦት፣ ስለመብራት፣ ውሃ መቁረጫ መድረስ በእነዚህም ምክንያት ንትርክ መቀስቀስ ቅራኔ ማባባስ ይወዳሉ። በዚህን ጊዜም ተጨቃጫቂው ‹‹አሞኛልን›› ይመርጣል። ይህ ግን ለጊዜው ‹‹ማስታገሻ›› ይምሰል እንጂ እስከ መጨረሻው ይዘልቅና ለሕመም አልባ ሕመም ይዳረጋል። ምክንያትም አለው። ተከታዩን አጭር ሐሳብ ወለድ ጭውውት እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

-‹‹ምነው አቶ እገሌ የት ሄደ?››

– ‹‹እንጃ አሞኛል ብሎ ተኝቷል››

‹‹እስቲ ልጠይቀው …… ምን ሆንክ እባክህ?››

‹‹እንዲያው ራሴን በጣም ይዞኛል እባክህ !!››

-‹‹አዎን ሰሞኑን እኮ እኔም ልጠይቅህ ነበር››

-‹‹ምነው ምን አየህብኝ?››

-‹‹አይ … ብቻ … ፊትህ ትንሽ ጠቆርቆር ማለት ከጀመረ ሰንብቷል››

እንግዲህ ከሚስት ጭቅጭቅ ለመሸሽ ‹‹አሞኛል›› በማለት የተኛው ባል ጠያቂው ጠቆም ያደረገውን ካደመጠ ወዲህ ክፉኛ መስጋት ይጀምራል። ‹‹… እንዲያው በራሴ ስቀልድ ኖሯል ለካ!›› ይልና ክሊኒኮችን ማሰስ ላቦራቶሪዎችን ማዳረስ ይቀጥላል። ጉንጩን ማጅራቱንም ሳይቀር በመስተዋት ማየቱ፣ ጥቁረቱን መመልከቱን፣ ፈለጠኝ ቆረጠኝ፣ ማለቱን መጨነቁን፣ ይያያዘዋል። ሰው በጠየቀው ቁጥር ‹‹እንዲህ መላ ሰውነቴን ይዞ…›› ይለዋል። በሌላ መልኩ ደግሞ ጥቂት የሚግባቡ ከሞላ ጎደልም ቢሆን የሚተሳሰቡ ወይም እንዲያው ለመምሰል የሚጥሩ አንዳንድ ተጓዳኞች ፍቅራቸውን ለመግለጽ በሚሞክሩበት ወቅት የሚጠቀሙበት ስንኩል ብልጽግና።

-‹‹ምነው ዛሬ ደግሞ ምን ሆነሀል አንተ?

-‹‹ምን ሆንኩ››

-‹‹ኦ!ኦ! በጣም ፊትህ ሁሉ ልክ አይደለም››

-ምነው ከሳሁብሽ››

-‹‹አትቀልድ እባክህ! እኔ እኮ ያለአንተ ሌላ ማንም የለኝም!!››

-‹‹እሺ ምን ሆንኩ››

-‹‹ ክብደትህ በጣም ቀንሷል እኮ !! አሁን ደግሞ ዛሬ ዓይንህ ሁሉ ድብልቅልቅ ያለ ይመስላል››

ወይዘሮዋ ወይም ወይዘሪቷ ይህን ባለች ‹‹አዛኝነቷን አሳቢነቷን ስጋቷን ጭንቀቷን …›› ገለጸችና ጥቂት ተወደደች። እርሱ ግን ከዚያ ቀን ጀምሮ ጉበትን፣ ሀሞትን፣ ልብን፣ አንጀትን ሲያሰላስል በሐሳብ ሲሰለሰል ይከርማል። በኋላም ሕመሜን ንገሩኝ ‹‹በሽታ ስጡኝ›› እያለ ሐኪሞችን እያዞረ መለመኑን ሥራዬ ብሎ ይይዘዋል። ለደዌ ምፅዋት መዋተት! ባሏ በየቀኑ ለሕላዌዋ እያሰጋ በነገር ፍላጻ እየወጋ ቢያስቸግራት ‹‹አሞኛል››ን መርጣ በሽተኛነቷን አረጋግጣ የተቀመጠች እንዲህ ያለች ሴት ደግሞ በሴቶች ላይ ከሚከሰተው ‹‹ከመንፈቀ ሕይወት ጭንቀት›› አንስቶ ስድሳኛውን እስካገባደደችበት ወቅት ድረስ ‹‹ሕመምተኝት›› እየተባለች ብቻ ሐኪም በሽታዋን ሳይረዳ እርሷም አውቃው ሳታስረዳ ትኖራለች።›› እንዲያው መላ ሰውነቴን›› እያለች!!

‹‹አንቺ ይህን አትችይም ብዙ መንገድ ለመጓዝ ልብሽ ይደክማል›› እያለ የጤነኛ ሚስቱን ሕይወት ያገረጣ ያልታመመ በሽተኛ (ሀይፓኮንድሪያክ) ያደረገም አልታጣ።

ይህንኑ በሚመለከት አንድ ወዳጄ ያጫወተኝም አለ። ይኸውም ሴትየዋ (ዛሬ በሰማንያኛው ዘመነ ሕይወት ላይ ይገኛሉ።) ‹‹አመመኝ›› ሲሉ ‹‹መላ ሰውነቴን›› ሲሉ የተደመጡ ዛሬ ሳይሆን ምናልባት ከዐርባ አመት በፊት ይሆናል። ይሁንና በቂ ሕክምና ሳያገኙ ተመርምረው የታወቀ ነገር ሳይሆን እነሆ ለአረጋዊትነት በቅተዋል።

እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ? በተአምር አይደለም። ከታሪካቸው እንደተረዳነው በዚያው አመመኝ በሚሉበት ዘመን አንድ ባል ነበራቸው። ነጋ ጠባ የሚነዘንዙ፣ በነገር የሚገዘግዙ ባል!! ፈቅደው ያገቧቸው ወደው የተጎዳኙዋቸው ቢሆኑም ‹‹በቃኝ›› ብሎ ለመውጣት፣ ለፍቺ መሰናዳት በእምነት ተጽዕኖ ሳቢያ የሚቻላቸው አልሆነም። በኋላ ግን ሞት አይቀርምና የጨቅጫቃው ባል ሕልፈት ለሚስትየዋ ሕይወት ሆነ። ከዚያ ወዲህ ያ ‹‹መላ ሰውነቴን›› በመጠኑ ቀረ። የባልና ሚስትን ጉዳይ በዚህ እንግታውና ሰዎችን ‹‹ሀይፓኮንድሪክ›› የሚያደርጉ ሌሎችስ እንዴት ያሉ ምን የሚሉ ናቸው?

-‹‹አይ ጋሼ እንዲያው አሁን ይህን ላንተ ይስጥህ››

-‹‹አዎን ምን ይደረግ ሰጠኝ!!››

-‹‹መቼም የዓይን ነገር እንዲህ በቀላሉ የሚታይ እንኳ አልነበረም እንዲያው የእርሱን ምስጢር ለእሱው ብቻ መተው እንጂ ….››

-‹‹ምን ይደረግ አዎን እንደው መቼስ ….›

-‹‹ደግሞ እኮ ጠቆርቆር ብለሃል።

-‹‹ሌላስ የሚያምህ አለ››

-‹‹አይ … እኔስ አይመስለኝም።

-‹‹እንዲህ ከሰውነት ወጥተህ››

ይህ ከፍ ሲል የሠፈረው ምልልስ ሰዎችን ‹‹ሀይፓኮንድሪያክ›› የሚያደርጉ ሌሎችስ እንዴት ያሉ ምን የሚሉ ናቸው? ለተሰኙት ጥያቄዎች በከፊል ምላሹን ይቸራል።

የሠፈረውን ቃለ ምልልስ በቅርቡ ብናጤነው እጅግ አሳዛኝ ሊሆን የሚበቃ መሆኑን ከመገንዘብ አንታቀብም። ስለምን? ይህ ጥያቄ የተሰነዘረው ይህ ገጽታን የሚመለከት አጉል አስተያየት የተወረወረው ለዓይነ ሥውር ነውና!! ለመሆኑ ከጊዜ በኋላ የዓይኑን ብርሃን አጥቶ ፍዳ የሚቆጥረው፣ አበሳ የሚዘረዝረው መከረኛን እንዲህ ሲባል ምን ይሰማዋል?

መቼም ይህን መሰል ‹‹የገጽታ መርዶ›› ሲሰማ ማንም ሰው ቢሆን በደስታ ፈንድቆ፣ በሐሴት ቦርቆ እንደማይገኝ ሳይታለም የተፈታ ነውና በዚህ አንጠያየቅበትም። ልዩ የሚያደርገው ይበልጡን የሚያሳዝነው ግን መስተዋት አይቶ በራሱ ላይ የዓይን ምስክርነት ሲሰጥ፣ የገጹን የቅርጹን ሁኔታ ሊያረጋግጥ የማይችል ዕይታን የተከለከለ፣ ለብሌን ፀጋ ያልታደለ የመሆኑ ነገር ነው። ‹‹እውነት ምን እመስል ይሆን?›› እያለ በጭንቀት ማዕበል ይመታል።

ከዚያስ ምን ያደረጋል? ምላሹ አሁንም አጭር ነው። ከሐኪም ወደ ሐኪም እየዞረ ከላቦራቷሪ ወደ ላቦራቷሪ እየተዘዋወረ በሽታ ፍለጋ ይገባል። ‹‹እንዲያው መላ ሰውነቴን ይዞ ….›› ማለቱን ይቀጥላል። ‹‹ምንም የለብህም›› ቢባልም ‹‹አለብኝ›› እያለ ይሟገታል። ለደዌ ምፅዋት ይወተውታል። በመጨረሻም ‹‹ሀይፖኮንድሪያክ›› ተብሎ ያልታመመ በሽተኛ ሆኖ ‹‹ጠዘጠዘኝ ገተገተኝ›› ን ይዞ ይቀራል።

አንዳንድ አዛኝ መሳይ ‹‹የገጽታ ገምጋሚዎች በሚሰጡት አስተያየት በቁጥር ያላነሱ፣ በአኃዝ ያልኮሰሱ ጤነኞች ‹‹ያልታመሙ በሽተኞች›› ሆነው በሐሳብ ሲያልቁ፣ ሲማቅቁ ተገኝተዋል። ምንም እንኳ ቃለ ምልልሱም ሆነ ዝርዝር ታሩኩ ‹‹ሐሳብ ወለድ›› ቢመስል ቁም ነገሩ ግን እንዳለ መዘንጋት የለበትም።

በሕመም አልባ ምርምር ላይ ተመርኩዘው ለገጸ ንባብ ከበቁ ሰነዶች መረዳት እንደተቻለው እንዲያው ‹‹ከአንገት በላይ›› ብቻ ተገድቦ የቀረበ አልመሰለም። ራሱ ‹‹አንገት›› ልዩ ትርጓሜ ያለው ሆኗልና!! ‹‹አንገቴ የተጣመመ ይመስለኛል›› በማለት እጅግ የተጨነቀ፣ ጠቢባዊ ረድኤት የጠየቀ አንድ ‹‹በሽተኛ›› ለሐካምያኑ ብርቱ ችግር ፈጥሮ እንደነበረ ተጠቅሷል። ‹‹ራሴ አንገቴ ላይ በትክክል የተቀመጠ አለመሆኑ ተሰምቶኛልና መፍትሔ ፈልጉልኝ›› በማለት ወደ አንድ የቀዶ አካሚ ጠቢብ ሄዶ የኦፕራሲዮን ተማፅኖ ያቀረበ መኖሩም ተወስቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ሆዴን ቆረጠኝ፣ ራሴን ፈለጠኝ፣ ደረቴን ወጋኝ —›› የሚባለው አንድ ራሱን የቻለ ‹‹የመላ ሰውነት ሕመም›› ዘርፍ መሆኑን ተገንዝበናል። በእጅጉ ግሩም ሊባል የሚበቃው ግን ‹‹ጨጓራ ያለኝ አልመሰለኝም፣ ሳምባዬ ተጎርዶ የወደቀ፣ ጉበቴ ተቀዶ ያለቀ መሆኑ ይሰማኛል። ወዘተ —›› የተሰኘው በሙያው ለተሰማሩት የሚቀርበው አቤቱታ ነው።

አዲስ ዘመን ሀምሌ 13/2011

 አሸናፊ ዘደቡብ